Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የመንግሥት ሠራተኞችን የሜዳይና የኒሻን ተሸላሚ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ቀረበ

የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የመንግሥት ሠራተኞችን የሜዳይና የኒሻን ተሸላሚ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ቀረበ

ቀን:

በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ለአገር የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሜዳይና የኒሻን ተሸላሚ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ የሲቪል አገልግሎት ሜዳይ ድንጋጌም ተካቶበታል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በታኅሳስ 2016 ዓ.ም. ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላከው ረቂቅ ውስጥ እንደተብራራው፣ የመንግሥት ሠራተኞች ለረጅም ጊዜ አርዓያነት ያለው አገልግሎት ሰጥተውም ሆነ በሥራ ላይ እያሉ የሚታወሱበት የዕውቅናና የክብር ሽልማት ተካቷል፡፡

‹‹ብሔራዊ የላቀ የሲቪል አገልግሎት ሜዳይ አሰጣጥ›› ተብሎ በረቂቁ የቀረበ ድንጋጌ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ሥርዓት ያልነበረ መሆኑንና በመንግሥት ሠራተኞች ዘንድ ተነሳሽነት እንዲፈጠር፣ ዲሲፕሊን ኖሯቸው በታታሪነት እንዲሠሩ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ሜዳሊያውም በታማኝነት አገራቸውን ላገለገሉ ሠራተኞች የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሜዳሊያው ከወታደራዊና ከፖሊስ አገልግሎት ውጪ መሆኑና ለሽልማት የሚያበቃ ተግባር ለፈጸሙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወይም የውጭ አገር ዜጎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን በረቂቁ ውስጥ ተገልጿል፡፡

በረቂቁ ሦስት ሜዳሊያዎች ማለትም ብሔራዊ የላቀ የፈጠራ ሥራ ሜዳይ፣ ብሔራዊ የህዳሴ ሜዴይ፣ እንዲሁም ብሔራዊ የላቀ ሲቪል ክልሎች ሜዳይ እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ የሚሰጡት ኒሻኖች የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻንና የአፍሪካ ታላቅ የክብር ኒሻን ናቸው፡፡

በረቂቁ መሠረት የሜዳይና የኒሻን ተሸላሚ የሆነ ግለሰብ የሚኖረው መብት ከደመወዙ መጠን 25 በመቶ፣ ጡረተኛ ከሆነ ደግሞ ከጡረታ አበሉ 40 በመቶ ይጨመርለታል፡፡ ደመወዝ ወይም ጡረታ ከሌለው ደግሞ አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጣ መመርያ የሚወሰን የገንዘብ መጠን በስጦታነት እንደሚሰጠው በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

በተጨማሪም በመንግሥት የትምህርት ተቋማት ቅድሚያ የትምህርት ዕድል፣ በመንግሥት የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኝ የተደነገገ ሲሆን፣ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተፈረመ መታወቂያና ሰርተፊኬት እንደሚሰጠውም ተገልጿል፡፡

ተሸላሚው የብሔራዊ በዓላት አከባበር ሥነ ሥርዓት በሚከናወንበት ቀንና ሥፍራ በሚዘጋጅለት ቦታ ይቀመጣል፣ መንገድ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ ሕንፃ ወይም ተመሳሳይ ተቋም እንደሚሰየምለት ተደንግጓል፡፡

ከሁለት ጊዜ በላይ ሜዳይ ወይም ኒሻን የተሸለመ ግለሰብ በማንኛውም የአገሪቱ አካባቢ አግባብነት ባለው ሥፍራ ሐውልት ሊቆምለት እንደሚችል የተጠቀሰ ሲሆን፣ የሚቆመው ሐውልት ይዘት፣ ዓይነትና መጠን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚወጣ መመርያ እንደሚወሰን የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል፡፡

የብሔራዊ የሜዳይና የኒሻን ሽልማት ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ የተቋቋመ ሲሆን፣ የኮሚቴውን ሰብሳቢ ጨምሮ የኮሚቴው አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሾማሉ ተብሏል፡፡ ኮሚቴው የሜዳይና የኒሻን ሽልማት የሚገባቸውን ዕጩዎች የመመልመል፣ የመመርመርና ተገቢ የሆነ ውሳኔ እንደሚሰጥ በረቂቁ ውስጥ ሰፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...