Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዩኔስኮን ደጃፍ ለማንኳኳት የታሰበለት የአገው ፈረሰኞች በዓል

የዩኔስኮን ደጃፍ ለማንኳኳት የታሰበለት የአገው ፈረሰኞች በዓል

ቀን:

‹‹በመካከለኛው እስያ ቱርክሜኒስታን ግዛት ውስጥ የሚገኝ የፈረስ ዝርያ ነው- ‹አክሃል-ቴክ››› የዚህ ዝርያ ፈረሶች በትልቅ መጠናቸው፣ ብልህነታቸው፣ ቅልጥፍናቸው፣ ጥንካሬያቸውና አንፀባራቂ ኮቴአቸው ተለይተው የሚታወቁ፣ ጠንካራና ለረጅም ጊዜ ያለ ምግብና ውኃ መቆየት የሚችሉ ናቸው። በአክሃል-ቴክ ፈረሶች ዙሪያ ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች አንፃር ብዙ ልማዶችና ወጎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የስም አወጣጥ ሥርዓቶች፣ የፈረስ የውበት ውድድር፣ የእሽቅድምድምና የግልቢያ ጨዋታዎች ይገኙበታል። በተጨማሪም ከሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ጋር በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሽራው ሙሽሪትን የሚወስዳት ባሸበረቀው የአክሃል-ቴክ ፈረስ ላይ በመቆናጠጥ ነው፡፡››

ይህ ሐተታ የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ፣ ባለፈው ኅዳር የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታት ኮሚቴው በቦስትዋና ባካሄደው ስብሰባው፣ በዓለም ቅርስነት ስለመዘገበው የቱርክሜኒስታን የአሃል-ተኬ የፈረስ ማራቢያ ጥበብና የፈረስ ማስጌጥ ወጎች በተመለከተ ያስተጋባው ነው፡፡

የቱርክሜኒስታን የፈረስ ትውፊት ለሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ሊመዘገብ የቻለው፣ የአገሪቱ የዩኔስኮ ብሔራዊ ኮሚሽን የአካዴሚ ተመራማሪዎችን፣ የፈረስ አርቢዎችን፣ የፈረስ ጌጣጌጥ ሠሪዎችን፣ እንዲሁም ታዋቂ ባለሙያዎችና የፈረስ ጥበብ ባለሙያዎችን ሰፊ ተሳትፎን ያካተተ ሰነድ በማዘጋጀቱ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢትዮጵያም ከፈረስ ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች ብሂልን ከባህል ያዛመዱ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በክብረ በዓል ደረጃም ገዝፈው የሚታዩም ጭምር፡፡ ከነዚህም አንዱ በወርኃ ጥር በአዊ ማኅበረሰብ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የፈረስ በዓል ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡

‹‹የአዊ ማኅበረሰብ የፈረስ ትርዒት›› በሚለው መጣጥፋቸው አቶ አሥራት በጋሻው እንደሚገልጹት፣ ፈረስ ከአዊ ማኅበረሰብ ሕይወት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አዊዎች ፈረስን ለእርሻ አገልግሎት የሚጠቀሙት ፈረስን ከፈረስ ጋር ወይም ፈረስን ከበቅሎ እንዲሁም ከመሰነች ላም ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ሕይወታቸውንም በየፈርጁ ከሚመሩባቸው መካከልም ለሰረገላና ጋሪ መጎተቻ፣ ዕቃና ሰው ማጓጓዣ፣ አስከሬን፣ ሙሽራና ታቦት ማጀቢያ በማድረግም ፈረስን ይዘውታል፡፡ ፈረስን ከዚህም ባሻገር አበው ‹‹ቼ ፈረሴ›› ብለው በጦር አውድማ ተሳትፈውበታል፡፡

በጣሊያን ሁለተኛው ወረራ (1928-1933) ኢትዮጵያ ድል ስታደርግ ከዘመቱት አርበኞች የሚገኙት አዊዎች ፈረሳቸውን እየጋለቡ በመዝመት በድል ሰንደቅ ተመልሰዋል:: አዊዎቹ ይህን ድል በየወሩ፣ በየዓመቱ በተለየ መልኩ እየዘከሩት ከስምንት አሠርታት በላይ ዘልቀዋል::

በ1933 ዓ.ም. በጣልያን ወረራ ወቅት በጦርነቱ ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሠላሳ ፈረስ ባላቸው ወንዶች ብቻ የተቋቋመው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማኅበር ዛሬ ግን ሴቶችን አካቶ ከ62 ሺሕ በላይ አልፏል፡፡

ዘንድሮ በዓሉ ለ84ኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ በሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ 444 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው በአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና ከተማ እንጅባራ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹የሰላም አርበኝነት ለወንድማማችነት›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

በዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ዘገባ መሠረት በበዓሉ ከብሔረሰቡ ባህላዊ ጭፈራ በተጨማሪ የፈረስ ዝላይ፣ የስግሪያ ጨዋታ፣ ድንግል አንሳ፣ ጉግስና ሽርጥ የተሰኙ ትርኢቶች ቀርበውበታል፡፡

በዓሉ የሕዝቡን ባህላዊ እሴቶች አጉልቶ ከማሳየት ባለፈ የፈረስን ዘርፈ ብዙ ባለውለታነት በሚያጎላ አግባብ መከበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ክብረ በዓሉ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደሚሠራ ኃላፊው አቶ ጣሂር መሀመድ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ክብረ በዓሉን በማስመልከት በዋዜማው በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ፣ በዓሉ በዩኔስኮ ተመዝግቦ ማኅበራዊና ኢከኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ባህልና ታሪክ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍም ሁሉም ማኅበረሰቦች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

የፈረስ ክብረ በዓሉ ሲገለጽ

ከፈረሰኞች ልዩ ልዩ ትርዒቶች ባሻገር ከዚህ ቀደም በነበረው አሁንም ባለው ትውፊት መሠረት ባህላዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓት፣ ባህላዊ የእርቅ አፈታትና የአገው (የአዊ) ባህላዊ ምግቦችም የክብረ በዓሉ መገለጫዎች ናቸው፡፡

በቀደመው አጠራሩ ስለ ሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር ከዓመታት በፊት ጥናታቸውን ያባቀረቡት ሰው አገኝ አሥራት (ዶ/ር) ገለጻ፣ የፈረስ ማኅበሩ በራሳቸው የሚተዳደሩ ከጎጥ፣ ከቀጣናና ከቀበሌ እስከ ወረዳ ድረስ በነፃነት የተደራጁ ሲሆን፤ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር ስያሜውን ያገኘው አንካሻ፣ ባንጃ፣ ኳኩራ፣ ጫራ፣ መተከል፣ ዚጊምና አዘና በተባሉ ወንድማማቾች ነው፡፡ የዛሬው አንከሻ፣ ባንጃ፣ አዘና እና ዘጊም ወረዳዎች እንዲሁም ኳኩራ፣ ጫራና መተከል ከተሞች ወንድማማቾችን በመወከል የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የማኅበሩ አባል የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑና በጾታ ረገድም ወንድም ሴትም መሆን ይችላሉ፡፡

ፈረሶች በልዩ ልዩ ጌጣ ጌጦችና አልባሳት ይደምቃሉ፡፡ መጣምር/ከቆርቆሮና ከቆዳ የተሠራ ብርቅርቅ ጌጥ/ፋርኔሳ የፈረስ የአንገትና የጆሮ ጌጥ ውዴላ /ኮርቻውን ከሃላ ደግፎ የሚይዝ/፣ እምቢያ ጉስምና እርካብ ይጠቀሳሉ፡፡ ፈረሰኛው ሎፊሳ የተሰኘ ለምድ ይለብሳል፡፡ ገንባሌ፣ የቡሽ ባርኔጣና እንዲሁም ዘንግ፣ አለንጋና የመመከቻ ጋሻ ይይዛል፡፡

አዊዎች የፈረሱ ባለቤት ማኅበራዊ አስተዋጽኦና ሰብዕና እንዲሁም ዳኝነት፣ ቻይነትና ደፋርነት ለመግለጽና ለማሞገስ የሚጠሩት የፈረስ ስምን በመጠቀም ነው፡፡ ለዚህም አባ መስጠት፣ አባ ባህር፣ አባ ዳኘው፣ አባ መቻል፣ አባ ደፋር፣ አባ መርዞ በማለት ይጠራሉ፡፡

የፈረስ በዓሉን ለማድመቅ አስተባባሪ አለቆች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ሥነ ሥርዓቱን ከፊት ሆነው ይመራሉ፡፡ አይሞሎ፣ የዳማ ጌታ፣ የቦራ ጌታ፣ የጥርኝ ጌታ እያሉ ፈረሱን በማሞገስ ያቀነቅናሉ፡፡ በየቀጣናው፣ ወር በገባ በ23 ሲከበር ቀጥሎ በዓመት ደግሞ ከጥር 23  በኋላ ባለው እሑድ ይከበራል፡፡

ከመብላት፣ ከመጠጣት ባለፈ የልማት ሥራ ይሠራበታል፡፡ ተጣልተው የነበሩ ይታረቁባል፡፡ የተበደለ ይካሳል፣ እርቅ ስምምነት እንዲደረግ ይመክራሉ፡፡ ድንበር የገፋ የሰረቀ ይቀጣል፡፡ ለወረቀት እስክሪብቶ ለጸሐፊ ወጪና የሚያባክን ጊዜ ይቆጥባሉ፡፡ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ላይ ይወያያሉ፡፡ የተቀማ ያስመልሳሉ ብለዋል ዶ/ር ሰውአገኝ በጥናት ወረቀታቸው፡፡

ጥፋተኞች ከምክር ግሳጼ በተጨማሪ ከማኅበር እስከመገለል የሚደርስ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል፡፡ ከማኅበሩ የተገለሉት ደግሞ ችግር ላይ ይወድቃሉ ልቅሶና ማኅበራዊ መገለል ይደርስባቸዋል፡፡ ፈረሰኛው ችግር በደረሰበት ጊዜ ዕርዳታ ይደርግለታል፡፡ ቢታመም ያሳክሙታል፣ ቤቱ ቢፈርስ ከገንዘብ እስከ ጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ ይሠራሉ፡፡ የማኅበሩ፣ አባል ፈረስ በግልቢያ ወቅት ቢሞት ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ፈረስ ገዝተው ይተካሉ፡፡ አቅመ ደካሞች አባል ባይሆንም ይታገዛሉ፡፡ ለሠርግ ከእንጨት ፈለጣ ጀምረው ሾመው  ይድራሉ፡፡

ለአቅመ አዳም የደረሰ ልጅ ለሌለው ቤተሰብ መረዳዳት መተጋገዝ መተሳስብ ባህላቸው ነው፡፡ ለቅሶ በማጀብ ከቀብር እስከ ቁርባን ያስፈጽማሉ፡፡ ጉግስ ጋላቢ ቢጎዳ ቂም የለም፣ ፈረስ ጋር ቢጋጭ ዘንግ ያየዘው ጉዳት አድራሽ በሕግ አይጠየቅም፡፡

ቦታ አያያዝ፣ ጌጣጌጥ፣ አለንጋ፣ ዘንግ፣ ጋሻ መክት የፈረሰኞቹ ትዕይንት ማድመቂያ ነው፡፡ በጨዋታ ወቅት የሚደረገው ሁሉ ለነፍስና ለሥጋ ዋጋ የሚያስገኝ ተደርጎ ይታመናል፡፡ በርካታ ግጥሞች ይገጠማሉ፡፡ ‹‹አይሞሎ›› ከሚለው ጭፈራ ቃላዊ ግጥሞች መካከል ለምሳሌም

‹‹ቆርበጥ ቆርበጥ ባይል እንደሚደቋ

ስንቱ ያውቀዋል የሠንጋን ቋንቋ››

ይህንንም የግጥም መልዕክት ሲያብራሩ፣ እንስሳት ከባለቤቶቻቸው ጋር የሚግባቡበት ደመ ነፍሳዊ ቋንቋ እንዳላቸው ከግጥሙ ፈረስ ለግልቢያ ከመነሳቱ በፊት የፊት እግሮቹን ብድግ ብድግ ሲያደርግ የሚረዳው ጋላቢ ብቻ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡  ሳብ ረገብ አደርጎ የፈረሱን ፍላጎት መረዳት የባለቤቱ ችሎታ ነው፡፡

የፈረስ ትርዒቱም በየተረኛ ወረዳና ለፈረስ ግልቢያ በተከለለ ስፍራ ይከናወናል፡፡ አሰላለፉም ከቀበሌ እስከ ዞን በአለቃ አማካይነት ጥሩንባ ፊሽካ በመንፋት ይሆናል፡፡ ለታዳሚው የፈረስ ጉግስና ሽርጥ ውድድር በማሳየት ታዳሚውን ያዝናናሉ፡፡ ይፎክራሉ በፈረሶቻቸው ይንጎራደዳሉ፡፡

የአዊ ብሔረሰብ የፈረስ ትውፊትን፣ ከነጓዙ ከነ አበጋዙ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ፣ እንደ ቱርክሜኒስታን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የዩኔስኮ ብሔራዊ ኮሚሽንን፣ የቅርስ ባለሥልጣንን፣ የአካዴሚ ተመራማሪዎችን፣ የፈረስ አርቢዎችን፣ የፈረስ ጌጣጌጥ ሠሪዎችን፣ እንዲሁም ታዋቂ ባለሙያዎችና የፈረስ ጥበብ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ሰነድ ማዘጋጀት የግድ ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...