Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የክፉ ቀን ረሀብ ትዝታ

ትኩስ ፅሁፎች

ከ1880 እስከ 1884 ድረስ ሀይለኛ ረሀብ ሆነ፡፡ ሰውን ሰው መብላት ጀምሮ ነበር፤ አንዲት ሴት ሰባት ሕፃን በላች፡፡ አራዊትም ሰውን በቁም ይበሉት ነበር፡፡ ሕዝቡም፤

እህል በፊትሽ ሲሸሽ በሬ ሲያባርር፤

ሁሉም ተከታትለው ጠፉ አሉ ካገር፡፡

እህል ታሟል አሉ ሄደን እንየው፣

የማይተርፍ እነደሆነ እኛ እንቅደመው፡፡

እኔ ከእህል ጋራ ይቅርታም የለኝ፣

ሲያልቁ ዘመዶቼ ይብላኝ ያላለኝ፡፡

እህል ኮበለለ ሄደ በነፋስ፣

ተከተለው በሬ እንዳይመለስ፡፡

      እያለ ያለቅስ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ከብቶች ሁሉ በሽታ ፈጅቷቸው ነበር፡፡ በዚሁ የረሀብ ዘመን ከብት አልቆ የሚታረስበት መጥፋቱን ያዩት አፄ ምኒልክ «… የከብት ነገር ተፈፅሞ አልቋልና እግዚአብሔር ፊቱን እስኪመልስን ድረስ እኔም አብነት ለመሆን ብዬ በጄ የምቆፍርበት ዶማ፣ የምቆርጥበት መጥረቢያ አስበጅቻለሁና እናንተም እንደኔ ሁኑ…» እያሉ ለየመኳንንቱ ደብዳቤ ጽፈው ለእያንዳንዱም አንዳንድ ትናንሽ ዶማና መጥረቢያ ላኩላቸው፡፡ መጀመርያ የተላከላቸው የጐጃሙ ንጉሥ ተክለኃይማኖት፤ የወሎው ራስ ሚካኤልና የጐንደሩ ራስ ወሌ ነበሩ፡፡

ምኒልክ ለአብነት እሆናለሁ ብዬ ባሉት ቃል መሠረት መሬት ለመቆፈር የወጡት ለመታየት ብቻ አልነበረም፡፡ ፕሮፌሰር አፈወርቅ እንደጻፉት አንድ ቀን የየካን ዱር ሲመነጥሩ ጋሬጣና እሾህ እግራቸውን እየቀደደ ደም ብቻ አደረገው፡፡ በዚያ የነበሩ መኳንንትም ከምኒልክ እግር ብዙ ደም ሲፈስ ዓይተው ተደናገጡ፡፡ ወዲያውኑም በየሸማቸው የምኒልክን ደም ለመጥረግ ሲሻሙ ምኒልክ ተቆጥተው «ተው፡፡ አትንኩኝ፡፡ ይልቅስ እኔ ለእናንተ እንዳሳየሁ እናንተም ከበታቻችሁ ላለው ሰው አሳዩ፡፡ አስተምሩ፡፡ ከዚያ ወዲያ ትርፉንና ጥቅሙን ታዩታላችሁ…» አሏቸው፡፡ ይህ ካሉዋቸው በኋላ መኳንንቱ ሁላ ማጭድና መጥረቢያውን እየያዙ ዱሩን መመንጠር ጀመሩ፡፡

… ከዚህ በኋላ የረሀቡ ዘመን ተፈፅሞ የተድላና የጥጋብ ዘመን ተጀመረ፡፡ ያ ቀን አልፎ ሰብል መታየት ሲጀምር ሕዝቡ፡-

እህል ዱር አደረ ብቻውንም ዋለ፣

ጠላት እንደሌለው ሰው እንዳልገደለ፡፡

እህል ዘምቶ ገባ እኛም ዓየነው፣

አያሌ ሰው ቀረ ሳይገናኘው፡፡

እያለ ዘፈነ፡፡

– ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› (1984)

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች