Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

እየተነጋገሩ እንጂ እየተታኮሱ የሚፈታ ችግር የለም!

አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የሚበጀው ሰላማዊ መፍትሔ ነው፡፡ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጦርነት ሳይሆን ተቀምጦ መነጋገር ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሰላማዊ አማራጮችን ወደ ጎን ገፍቶ ጦርነት ወይም ግጭት ላይ ማተኮር ሲበዛ የሕዝባችን ሕይወት፣ ንብረትና መሠረታዊ መብቶች ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚስተዋሉ አደገኛ ሁኔታዎችን በሰላማዊ መፍትሔ መፍታት የግድ መሆን አለበት፡፡ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በአምስቱም በሮች በሰላም ወጥቶ መግባት እስኪያቅት ድረስ ሰላም ጠፍቷል፡፡ በየቀኑ የሞትና የጉዳት ዜናዎች በሰፊው ይሰማሉ፡፡ የሰዎች በነፃነት የመንቀሳቀስና የመሥራት መብት ተገድቧል፡፡ ኢንቨስተሮች ሥራቸውን ማከናወን ተስኗቸዋል፡፡ ምርቶችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ማንቀሳቀስ በማዳገቱ የአቅርቦት ችግር ለከፍተኛ የዋጋ ንረት እየዳረገ ነው፡፡ በየቦታው ዜጎችን መግደል፣ ማፈናቀል፣ ንብረታቸውን መዝረፍ፣ አግቶ የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅና የመሳሰሉት ወንጀሎች በስፋት እየተከናወኑ በአገር ላይ ከባድ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ግጭትም ሆነ ጦርነት በፍጥነት ካልቆመ መዘዙ የከፋ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በሰከነ መንገድ በመከባበር መነጋገር የሚቻልባቸው መድረኮች መፍጠር ነው፡፡ ለሰላም መጥፋት መባባስ የሆኑ ምክንያቶችን በግልጽና በድፍረት ፍርጥ አድርጎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ከአንድ ግጭት ወደ ሌላው ሰተት እየተባለ የሚገባባቸው ችግሮች መፈታት የሚችሉት፣ በእውነተኛ ንግግርና በመደማመጥ ብቻ ስለሆነ ቀልብን ሰብሰብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት የዜጎች ደኅንነት ለአደጋ ከመጋለጡም በላይ፣ የአገር ህልውና ጉዳይ አስፈሪ እየሆነ ነው፡፡ ለሰላም መጥፋት መንስዔ የሆኑ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው መርምሮ ግጭቶችን ማስቆም የግድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃኑ ብቻ ሳይሆኑ መላውን ሕዝብ ሊወክሉ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ በሕዝብ ውስጥ የሚብላሉ ጥያቄዎች ለውይይት ቀርበው መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል፡፡ መንግሥት በመደበኛው መንገድ ሕግ ማስከበር አቅቶኛል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየደጋገመ ሲያወጣ፣ በዚህ መንገድ ተጉዞ ዘለቄታዊና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደማይቻል መገንዘብ አለበት፡፡ ከዚህ በፊትም የወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ምንም እንዳልፈየዱ ማስታወስ ይኖርበታል፡፡ አዋጩ መፍትሔ ለሰላም መስፈን በጋራ መሥራት ብቻ ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ የትጥቅ ትግሎች ምክንያት በዜጎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት አመራሮች ላይ ጭምር ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በአገር ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት በጣም ያሳስባል፡፡ የሕዝብና የጭነት ተሸከርካሪዎች በፌዴራል መንግሥት አውራ ጎዳናዎች ላይ በታጣቂዎች እየጋዩ ነው፡፡ በባንክ ብድርና በዕቁብ ሥራቸውን ለማከናወን ደፋ ቀና የሚሉ ዜጎች ንብረታቸው በግላጭ እሳት እየበላው ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ ሲገቡ መመልከት ያስቆጫል፡፡ ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ለሌሎች ሥራ መፍጠር የሚችሉ ዜጎች፣ ንብረታቸው እየወደመ የሚይዙትና የሚጨብጡት ሲያጡ የአገር ተስፋ ይጨልማል፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ የሁለት ዓመት አውዳሚ ጦርነት መማር ሳይቻል ቀርቶ፣ አሁንም እዚያው አስደንጋጭ ጥፋት ውስጥ መገኘት ተያይዞ ከመጥፋት የዘለለ ዕርባና አይገኝበትም፡፡ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ ሥልጡን አማራጮች እያሉ፣ የትናንትና ስህተቶችን እንዳሉ በመደጋገም የሚገኝ መልካም ውጤት እንደሌለ የማንም ልቦና ይረዳዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ፀንቶ መቀጠል የሚችለው በመከባበር ተቀምጦ በመነጋገርና በመደራደር እንጂ በመፋጀት አይደለም፡፡

ሰሞኑን በአማራ ክልል 15 ከተሞች ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸው በስፋት ተዘግቧል፡፡ በየከተሞቹ በተደረጉ ውይይቶች ከኅብረተሰቡ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ የእነዚህ ጥያቄዎች ዋነኛው ማጠንጠኛ በክልሉ የተከተሰተው ጦርነትና ያስከተለው ፈተና ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በንግግርና በድርድር መፈታት የነበረባቸው ልዩነቶች ትኩረት ስላልተሰጣቸው፣ በአሁኑ ጊዜ የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን መላው ሕዝባችን ጭምር ከፍተኛ ጭንቅና ሥጋት ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጦስ አንዱ ቀማሽ የነበረው የአማራ ክልል፣ አሁን የለየለት ውጊያ ውስጥ ገብቶ በርካታ ምስቅልቅሎች ተፈጥረዋል፡፡ አሁን ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ መቀየር የሚቻለው ውጊያውን አጠናክሮ በመቀጠል ሳይሆን፣ ለሰላም መስፈን የሚረዱ መፍትሔዎችን በጋራ በማመንጨት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ትጥቅ ካነገቡ ኃይሎች ጋር ተቀምጦ ለመነጋገር ፈቃደኝነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ውጊያ ከዕልቂትና ከውድመት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ አካባቢ የሚፈጠር ችግር የጋራ አገራዊ ተግዳሮት መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረት መተማመን ሲኖር ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈን የሚያግዙ ሐሳቦችን በጋራ ማዋጣት አያቅትም፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ይሁን ስብስብ ከሥልጣንና ከጥቅም በፊት አገር እንደምትቀድም መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የአንድን ወገን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ አጉል ሩጫ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ስለሚሆን፣ ለጋራ አገራዊ ዓላማና ግብ ራዕይ አንድነት መፍጠር ይጠቅማል፡፡ ይህ አንድነት ለልዩነት ዕውቅና በመስጠት የመተባበርን አስፈላጊነት ማሳያ መሆን ይኖርበታል፡፡ ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ጠመንጃ ውልወላ ውስጥ ከመግባት በፊት ሌሎች ሰላማዊ አማራጮች የሚቃኙት፣ በመከባበርና በትብብር መንፈስ ለመሥራት ውስጣዊ ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ፈቃደኝነት በማይኖርበት የግትርነት ዓውድ ውስጥ እንኳንስ አንድነት መፍጠር ዓይን ለዓይን መተያየት አይቻልም፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ሕዝቡን ለማነጋገር የተጀመረው ሙከራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ከሕዝብ ጋር በሀቅና በአገራዊ ስሜት መነጋገር ሲቻል፣ መሣሪያ አንግበው ከሚገዳደሩ ጋርም ለመደራደር የሚያስችል ዕድል ይፈጠራል፡፡ ይህ ዕድል ባክኖ ዕልቂትና ውድመት እንዳይቀጥል የሚመለከታቸው ሁሉ ያስቡበት፡፡

በተደጋጋሚ ለማስታወስ እንደተሞከረው ልዩነት ሲፈጠር በሰከነ መንገድ በመነጋገር ማጥበብ ሥልጡንነት ነው፡፡ ልዩነት ማለት ጠላትነት አይደለም፡፡ ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› የሚለው ዕድሜ ጠገብ አባባል እዚህ ላይ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ፓርቲዎች እርስ በርስ በሚያደርጓቸው መስተጋብሮች በሁሉም ነገሮች ላይግባቡ ይችላሉ፡፡ በሁሉም ነገሮችም መስማማት አይጠበቅባቸውም፡፡ ልዩነት ሲኖር በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር ለተሻለ ሐሳብ ዕውቅና መስጠት እንዳለ ሁሉ፣ የሌላውን የልዩነት ሐሳብ ጤናማ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ተገቢ ነው፡፡ ክርክር የሚያስፈልገው ልዩነት ሲኖርም ተቀምጦ በጨዋነት መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚስተናገዱበት ገበያ እንደ መሆኑ መጠን፣ ልዩነት ሲፈጠር መነጋገር እንጂ ለመታኮስ መጣደፍ ፀረ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ ተብለው የሚታሰቡ ልዩነቶች ተቀምጦ በመነጋገር እንደሚፈቱ የታወቀ ቢሆንም፣ በሴራ ፖለቲካ ምክንያት አገር ቁምስቅሏን እያየች ሕዝብ አሳሩን እየበላ ነው፡፡ ይህንን መራራ እውነት በመገንዘብ አገርን መታደግ ይገባል፡፡ እየተነጋገሩ እንጂ እየተታኮሱ የሚፈታ ችግር እንደሌለ ግንዛቤ ይኑር!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...