Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቤቶች ኮርፖሬሽን ያወጣው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሽያጭ ጨረታ እንዲታገድላቸው የ97 ቆጣቢዎች ጥያቄ አቀረቡ

ቤቶች ኮርፖሬሽን ያወጣው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሽያጭ ጨረታ እንዲታገድላቸው የ97 ቆጣቢዎች ጥያቄ አቀረቡ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ለሚገነባቸው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) በ1997 ዓ.ም. ተመዝግበው በመቆጠብ ላይ ያሉና እስካሁን ድረስ በተደረጉ 14 ዙር ዕጣ ማውጣትና ቤት የማስተላለፍ ሒደቶች፣ የቤት ባለቤት መሆን ያልቻሉ 959 ቆጣቢዎች፣ ኮርፖሬሽኑ ያስገነባቸውን 3,452 ቤቶች ከከተማዋ የዲዛይንና ግንባታ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በጨረታ ለመሸጥ የጀመረው ሒደት እንዲታገድላቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጥያቄ አቀረቡ። 

ላለፉት 19 ዓመታት የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ እንዲደርሳቸው ሲጠባበቁ መቆየታቸውን የገለጹት ከስቱዲዮ እስከ ባለሦስት መኝታ ቤት ድረስ ቤቶች ለማግኘት እየቆጠቡ ያሉ ተመዝጋቢዎች፣ እስከ 2015 ዓ.ም. የካቲት ወር ድረስ ያለውን ቁጠባቸውን ከባንክ ደብተር መለያ ቁጥራቸውና እያንዳንዳቸው ምን ያህል እንደቆጠቡ ከሚያመላክት ሙሉ ስማቸውን ከፊርማቸው ጋር ያረፈበትና በአጠቃላይ 144,820,85.43 ብር መቆጠባቸውን ከሚያሳይ ሰነድ ጋር አያይዘው አቅርበዋል። 

የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የከንቲባ ልዩ ጽሕፈት ቤት ገቢ ባደረጉት የጥያቄ ደብዳቤ ላይ፣ 8000 ሰዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች፣ በተለያዩ ጊዜያት የቤት ጥያቄያቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት የከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ እንደሆነና ተጠቃሚነታቸውንም ያረጋገጡ ንግግሮቹን በሙሉ ተስፋ ሲጠብቋቸው እንደነበሩ ገልጸዋል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በከተማ አስተዳደሩ ተነሳሽነት በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ያላግባብ በሕገወጥ መንገድ የተላለፉ ቤቶችን እንዲያጠና ተደርጎ ተገኙ የተባሉትን ከ21 ሺሕ በላይ ቤቶችንና በተጨማሪም እየተገነቡ በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን በማካተት፣ በቅድሚያ ለ1997 ዓ.ም. በአስተዳደሩ ‹‹ብቁና ንቁ›› የተባሉ ቆጣቢ ነዋሪዎች ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በወጣው የ14ኛ ዙር ዕጣ ሙሉ በሙሉ እንደሚካተቱ ቢገለጽም፣ ዕድሉን ባለማግኘታቸው እስካሁን የከተማ አስተዳደሩን ይሁንታና ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ለከተማ አስተዳደሩ በኅብረት ሆነው ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ያሉት ተመዝጋቢዎች በ14ኛው ዙር ዕጣ ሳይደርሳቸው ሲቀር ፍትሕ ለመጠየቅ የተሰባሰቡና ጉዳያቸውን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለማቅረብ እንዲያመቻቸው 16 አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋማቸውን፣ የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ ተሰማ ለሪፖርተር አስረድተዋል። 

ባለፈው ዓመት የካቲት ለከንቲባ ልዩ ጽሕፈት ቤት ባስገቡት በዚህ ደብዳቤ፣ ‹‹አቅምና ፍላጎት ያለን ተመዝጋቢዎች ሁኔታዎች ተመቻችተውልን በማኅበር ተደራጅተን ቤቶች እንድንሠራ አማራጭ ሐሳብ የቀረበልን ቢሆንም፣ በዚህ ኮሚቴ አቅም ልናገኝ የቻልናቸውን ተመዝጋቢዎች አነጋግረን አዎንታዊ ምላሽ አላገኘንም፤›› ብለዋል። 

‹‹የከተማ አስተዳደሩ እያደረሰብንና እያለፍንበት ያለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ምስቅልቅልና ተስፋ አስቆራጭ ቤት የማግኘት ችግር ተቋቁመን እስካሁን ይሁንታ እየተጠባበቅን በመሆኑ የከንቲባ ልዩ ጽሕፈት ቤቱ የመፍትሔ ምላሽ ይስጠን፤›› ሲሉ ጠይቀዋል። 

ደብዳቤውን ለከተማው የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ፣ ለከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት፣ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገቢ ያደረጉ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ውይይቶች ማድረግ የተቻለው ከዕንባ ጠባቂ ተቋም ጋር ብቻ እንደሆነ የኮሚቴው አባል አቶ ቴዎድሮስ ማኅተመ ሥላሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል። 

አቶ ቴዎድሮስ የአቤቱታ ጥያቄዎቻቸውን ለተቋማቱ ለማስገባት፣ ‹‹ተቋም ስላልሆናችሁና ማኅተም ስለሌላችሁ ደብዳቤያችሁን ለመቀበል ይቸግረናል›› የሚል ምላሽ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖባቸው ቢቆይም፣ በብዙ ትግል ጥያቄዎቻቸውን ለማቅረብ መቻላቸውንም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተመዝጋቢዎች ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ምርመራ ማድረጉን በመግለጽ፣ ተመርምሮ የተሰጠውን ውሳኔ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ምላሹን አሳውቋቸዋል። 

የምርመራ ውሳኔው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ገልጿል። 

በመጀመሪያ ኮርፖሬሽኑ የጋራ መኖሪያ ቤት ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ሥራ ላይ ባለው መመርያ ቁጥር 3/2011 መሠረት፣ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ዕጣ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፣ በ2005 ዓ.ም. ከባለአንድና ሁለት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በፊት ቅድሚያ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ከተላለፉ 18,630 ቤቶች፣ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ብቻ እንዲስተናገዱ መደረጉን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ በሁለተኛነት በ14ኛው ዙር ዕጣ ያልደረሳቸው ነባር የቤት ተመዝጋቢዎች በቀጣይ የቤት ማስተላለፍ ሒደቶች ቅድሚያ በመስጠት ቅድሚያ እንዲገቡ ይደረጋል ብሏል። 

በመጨረሻም በ14ኛ ዙር ዕጣ የ1997 ዓ.ም. ብቁ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ ይስተናገዳሉ የሚል ገለጻ በኮርፖሬሽኑ በኩል አልተሰጠም በማለት፣ ለነባሮች ቅድሚያ ሰጥተናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ቤት ደርሷቸው ሳይጠናቀቁ የ2005 ዓ.ም. በዕጣው የሚካተቱ ከሆነ ምርመራው እንደሚቀጥል ገልጿል። 

የተመዝጋቢዎቹ ሁኔታ በዚህ ደረጃ በተያዘበት ወቅት ኮርፖሬሽኑ ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ፣ አጋጠመኝ ያለውን የፋይናንስ አቅም ችግር ለመፍታትና ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት በማለት፣ 3,452 ቤቶች (3,146 የመኖሪያ ቤቶች እና 306 የንግድ ሱቆችን) በጨረታ ለመሸጥ ከከተማዋ ዲዛይንናና ግንባታ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን እየሠራ መሆኑን በመግለጽ የጨረታ ሰነዶችን ሽያጭ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 20 ቀናት እንደሚያካሂድ ይፋ አድርጓል። 

በኮሚቴ የተወከሉት ተመዝጋቢዎችም ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዩን በመጥቀስ፣ ‹‹ላለፉት 19 ዓመታት ቤት በመጠባበቅ ላይ እያለን እንዲህ ዓይነት በሽያጭ የማስተላለፍ የጨረታ ሒደት እኛን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ስለሆነ፣ በእናንተ በኩል ይህንን እንድታስቆሙልንና ቤቶቹ ለእኛ ለሕጋዊ ተመዝጋቢ ጠባቂዎች እንዲተላለፍ እንዲወሰንልን፤›› በማለት ጥያቄያቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ከሪፖርተር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢደረግላቸውም፣ ‹‹መልሼ እደውላለሁ›› የሚል የስልክ ጽሑፍ ምላሽ በመስጠት ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...