Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዩኤስኤአይዲ የ46 ሚሊዮን ዶላር የሕፃናት ቅድመ ትምህርት ፕሮጀክት ማጠናቀቁን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ከሰባት አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በ46 ሚሊዮን ዶላር በጀት ላለፈው አንድ ዓመት ሲያካሂደው የቆየውን በግጭትና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ከሦስት እስከ ስድስት ዓመታት ድረስ ያሉ ሕፃናት፣ ቅድመ ትምህርት ዝግጅትና አጠቃላይ ዕድገትን የማሻሻል ፕሮጀክት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ 

ዩኤስኤአይዲ ይህንን የገለጸው ትናንት ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የፕሮግራሙን አንደኛ ዓመት ክብረ በዓል በተመለከተ፣ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በነበረው ዝግጅት ላይ ነው። 

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪንግ ማሲንጋ፣ ፕሮጀክቱ ዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ ካሉት ፕሮጀክቶች ትልቁ ነው ብለዋል። 

ድርጅቱ በዋናነት በሴቭ ዘ ቺልድረን የሰብዓዊ ድጋፍ ተቋም አስፈጻሚነትና  ከአማራ፣ ከዋግ፣ ከኦሮሚያና ከአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማኅበራት፣ እንዲሁም ከሌሎች አስፈጻሚ አድርጎ ከመረጣቸው በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን በፕሮግራሙ 13,122 ለቅድመ ትምህርት የደረሱ ሕፃናት በአምስት የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ለትምህርት የማዘጋጀት ሥራ ማከናወኑን ገልጿል። 

ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የተደረገባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ፣ 239 የተፋጠነ የትምህርት ዝግጅት ማስተማሪያ ማዕከላት (Accelerated School Readiness Leaning Centers) በ26 አካባቢዎች ላይ ተገንብተው አገልግሎት ላይ መዋላቸው ተነግሯል።

የዩኤስኤአይዲ የአንድ ዓመት ፕሮጀክት ለማዳረስ አቅዶ የተነሳው በቀጥታ ግጭቶች ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱባቸው የተለዩ 22 የአማራ፣ የአፋርና የትግራይ አካባቢዎች፣ እንዲሁም ድርቅ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው በተባሉ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች 20 አካባቢዎች እንደነበር ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። 

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አደጋዎችና ችግሮች በተጠቁ አካባቢዎች የሚገኙ ለቅድመ ትምህርት ዕድሜያቸው የደረሱ 1.8 ሚሊዮን ሕፃናትን በሬዲዮ ፕሮግራም በኩል ማዳረስም የዕቅዱ አካል ነበር ተብሏል። 

ዩኤስኤአይዲ 2,520 ወላጆችና አሳዳጊዎችን የቋንቋና የሒሳብ ትምህርቶችን በቤት ውስጥ ማስተማር የሚያስችላቸውን ሥልጠና መስጠቱን የገለጸ ሲሆን፣ እንዲሁም 2,618 ሕፃናትን በቤት ውስጥ በፕሮጀክቱ ተደራሽ ማድረጉን ገልጿል። 

በዚህም መሠረት 660 ሕፃናትን በሶማሌ ክልል ቆራኸይና ሸበሌ ዞኖች፣ 1,529 ሕፃናትን በትግራይ ክልል በመካከለኛና ምሥራቅ ዞኖች፣ 180 ሕፃናትን በአማራ ክልል ዋግኸምራ ዞን፣ እንዲሁም 249 ሕፃናትን በአፋር ክልል በቀልበቲ ራሱና ፋንቲ ዞኖች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል። 

በዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያና አጋሮቹ የአንደኛ ዓመት ፕሮጀክት ክብረ በዓል ዝግጅት ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹በሕፃናት ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ወደፊታችን ስኬታማ እንዲሆን ማረጋገጥ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹በሕፃናት ቅድመ ትምህርት ዘርፍ አገሪቱ 50 በመቶ ሽፋን ላይ ደርሳለች፤›› ሲሉ አስረድተዋል። 

የዩኤስኤአይዲ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዩጵያ እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ 20 ሚሊዮን ሰዎች በግጭቶችና ከድርቅ ጋር በተያያዙ ችግሮች ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በአስከፊ ድርቅ የተጎዱት 13 ሚሊዮን መሆናቸው ተገልጿል።

በአገሪቱ ከትምህርት ውጪ የሆኑ 7.6 ሚሊዮን ሕፃናት እንደሚገኙ መረጃው ሲያመላክት፣ ስምንት በመቶው ዕድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሆነ ሕፃናት መሆናቸውን ያስረዳል። 

ሰብዓዊ ድጋፎች በሁሉም ዘርፎች ከመጠን በላይ በሚፈለግበት  በአሁኑ ወቅት፣ ትምህርት በተለይም የሕፃናት ዕድገትና ትምህርት ቅድሚያ እየተሰጠው እንዳልሆነም መረጃው ያብራራል።

ከግጭቶች በፊትም ቢሆን የበጀትና የአቅም ውስንነት የሕፃናት የቅድመ ትምህር ዝግጅት ፕሮግራሞችን ከማስፋፋት አግዷቸው መቆየቱም ተገልጿል። 

የትምህርት ሚኒስትሩ የሕፃናት ቅድመ ትምህርት ፕሮጀክቱ እንዲቀጥል እንዲያደርጉ አጋር የተራድኦ ድርጅቶችን አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ለጋዜጠኞች በሰጡት ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ አሁን ከተሰጠው በእጅጉ የበለጠና የተሻለ ድጋፍ ተደርጎለት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ምን ያህል የበለጠ በሚለው ግን ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች