Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎች ሚኒስቴር በጥር ወር ተግባራዊ ይደረጋል ያለው የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት ተጨማሪ ጊዜ ይወስዳል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓመታት ዝግጅት በኋላ በተያዘው የጥር ወር ተግባራዊ እንደሚሆን ሲጠበቅ የነበረው የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ (electronic invoicing) ሥርዓት ትግበራ ለማስጀመር ተጨማሪ ወራት እንደሚወስድ ተገለጸ፡፡

ከሽያጭና ከአገልግሎት በኋላ የደረሰኝ አሳጣጥ ሥርዓቱን ሙሉ ለሙሉ በማዘመን ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ (Cash Register Machine) ወደ ሙሉ ኤሌክትሮኒክ (e-invoicing) ሥርዓት ለመዘዋወር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ለዓመታት ሲሠራ ቆይቶ፣ ትግበራውንም ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በተያዘው ወር ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች በመጀመሪያ የሙከራ ሥራውን ሊያከናውን ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ተጨማሪ የማጠናቀቂያና የውስጥ ሙከራ ሥራዎችን ለማከናወን በማሰብ ‹‹ለጥቂት ጊዜያት››  ቆይቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የገቢዎች ማኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ረታ አሰፋ የገለጹት፡፡

በጥቅምት 2016 ዓ.ም. የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም ንጉሤ፣ መሥሪያ ቤታቸው ሁሉንም ዝግጅት አጠናቆ ‹‹በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ›› የኤሌክትሮኒክክ ደረሰኝን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተናግረው፣ በጊዜው በማኑዋልና በደረሰኝ መመዝገቢያ መሣሪያ ላይ ተመርኩዞ ገቢን መሰብሰብ አስቸጋሪ እንደሆነ፣ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝን በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የጀርመን የልማት ትብብር ተቋም ጂአይዜድ (GIZ) ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው የሰባት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ያካሄደውን የኤሌክትሮኒክ አስተዳደር (e-governance) ጨምሮ፣ በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ከባቢ ላይ የሚሠራውን ፕሮጀክት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ባካሄደው ሴሚናር ላይ የተገኙት አቶ ረታ ስለኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር መቼ ተግባራዊ እንደሚደረግ ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ረታ በሰጡት ምላሽ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያቀደው በጥር ወር (እ.ኤ.አ. ጥር 2024) መሆኑን ገልጸው፣ ሥርዓቱ ለምቶ ሲጠናቀቅ ጠንካራ የሆነ የፕሮጀክት አስተዳደርና የሙከራ ሥራ እየተከናወነበት ስለሆነ በታሰበው ጊዜ ተግባራዊ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹የመጀመሪያ ከመሆኑም አንፃርና ሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ ትልቅ ስለሆነ፣ ወደኋላ ላለመመለስና የሚያጋጥሙ አንዳንድ ህፀፆችን ነቅሶ ከማውጣት አኳያ ነው እንጂ በጥቂት ወራት ውስጥ ይተገበራል፤›› ብለዋል፡፡

ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ጋር በመሆን የገቢዎች ሚኒስቴር እያለማ ያለው የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲደረግ፣ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ላይ ያለውን ጥገኝነት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀርፈውና በከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ተግባራዊ ሲደረግ ሽያጭን በሚመለከት የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንዲኖረው መደረጉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ‹‹ማን አጭበረበረና ማን ምን አደረገ የሚለውን ማወቅ ያስቸግር›› እንደነበር አቶ ረታ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የበለጠ ገቢ እንዲሰበስብ የደረሰኝ አጠቃቀማችን መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይገባል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ (e-invoicing) የገቢዎች ሚኒስቴር እያካሄዳቸው ካሉ የዲጂታል ለውጥ ክንውኖች አንደኛው ሲሆን፣ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት መሥሪያ ቤታቸው በርካታ የዲጂታል ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበር ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሕጎችን መሠረት በማድረግ ተቋማችን ስትራቴጂ ነድፏል፤›› ብለዋል፡፡

በተያዘው ዓመት የገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ገቢና ታክስን ጨምሮ 529 ቢሊዮን ብር ከግብር ከፋዮች ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው አፈጻጸም ከ70 በመቶ በላይ ያለውን ገቢ እየሰበሰበ ያለው በኤሌክትሮኒክ ነው ተብሏል፡፡ በቴሌ ብር የሚሰበሰበውን ጨምሮ ከ20 በላይ ባንኮች መሰማራታቸው ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች