Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊውስብስብ ችግሮችን የፈታው የውኃ ፕሮጀክት

ውስብስብ ችግሮችን የፈታው የውኃ ፕሮጀክት

ቀን:

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በዶሞ ሴሬ ወረዳ በደጌ ሴሬ እንጮቼ ቀበሌ ደጌ እንጮቼ የሚባል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ በ1979 ዓ.ም. አንደተመሠረተ ይነገራል፡፡ እንደተቋቋመ ከ1,000 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን በየዓመቱ ይቀበል የነበረው ትምህርት ቤቱ፣ ዛሬ ላይ የቅበላ አቅሙ ቀንሷል፡፡

በትምህርት ቤቱ እንዲሁም በአካባቢው የንፁህ ውኃ አቅርቦት ባለመኖሩ በሚፈጠሩ ውኃ ወለድ በሽታዎች ምክንያትም፣ በየዓመቱ ከ50 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንደሚገደዱ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ወ/ሮ ድንቅነሽ እምሩ ይገልጻሉ፡፡

ሴቶችም የወር አበባቸው በመጣ ቁጥር የሚቸገሩ በመሆኑ፣ በዓመት ውስጥ ሁለት ወራት ያህል ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአካባቢው በብዛት በውኃ ወለድ ከሚከሰቱ በሽታዎች አንዱ የአንጀት ጥገኛ ትል ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ሽታ ያለው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ስለሚያስከትል፣ በሽታው የያዘው ተማሪ ከትምህርት ይቀራል፡፡ አንዴ የሚቀር ተማሪ ደግሞ፣ ተመልሶ ወደ ክፍሉ ለመግባት አይፈልግም፡፡ በዚያው ትምህርቱን ያቋርጣል፡፡

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የውኃ ችግር በመኖሩም፣ በርካታ ተማሪዎች ወንዝ በመሄድ ለቤተሰባቸውና ለትምህርት ቤቱ ውኃ መቅዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ልብሳቸውን ለማጠብና ገላቸውን ለመታጠብ ወንዝ መውረድም ግድ ነው፡፡ ይህም ለብልሃርዚያ በሽታ እያጋለጣቸው ይገኛል፡፡ እግራቸውም በበሽታ ስለሚጠቃና ታክሞ ለመዳን ጊዜ ስለሚጠይቅ፣ በዚያው ከትምህርት የመቅረት ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ  ወ/ሮ ድንቅነሽ ይገልጻሉ፡፡

በትምህርት ቤቱ የንፁህ ውኃ አቅርቦት እንዲሁም ለሴትና ለወንድ የተለየ መፀዳጃ ቤት ስለሌለ በርካታ ልጃገረዶች በወር አበባ ጊዜ በወር ቢያንስ ከአምስት እስከ ሰባት ቀናት ቤት መዋላቸውም ዝቅተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ብሎም ትምህርት እንዲያቋርጡ እያደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2010 ዓ.ም. ባጠናው ጥናት መሠረት፣ በሁሉም የወላይታ ወረዳዎች የአንጀት ጥገኛ ትላትል እንዲሁም የብልሃርዚያ በሽታ ያለ ሲሆን፣ በሶሬ ወረዳ ደግሞ ችግሩ ይልቃል፡፡

የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኤካ እንደሚሉትም፣ በወረዳዎቹ የብልሃርዚያ በሽታ 51 በመቶ ነበር፡፡

የአንጀት ጥገኛ ትላትል በሽታዎች በአብዛኛው ንፁህ የመጠጥ ውኃ ካለማግኘት፣ ከመፀዳጃ ቤት እጥረት፣ ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት፣ እጅን በአግባቡ ካለመታጠብና ያልበሰሉ  ምግቦችን ከመመገብ የሚከሰት ነው፡፡

ችግሩ እርጉዝ እናቶች የቀነጨረ ሕፃን እንዲወልዱ ሲያደርግ፣ ሕፃናትን ደግሞ ይበልጥ ይጎዳል፡፡ ከሰው ወደ እንስሳት ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍም ገልጸዋል፡፡

በወላይታ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አብዛኞቹ በተለይም ዳሞት ሶሬ፣ ዳሞት ጋሌ፣ ዳሞት ሁሉሳ እንዲሁም ዳሞት በችግር የሚጠቁ ናቸው፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች ከ275 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች አሉ፡፡

አብዛኛው ማኅበረሰብም ሆነ ተቋማት ከንፁህ ውኃ አቅርቦት የራቁ፣ የወንዝ ውኃ የሚጠቀሙና መፀዳጃቸው ሜዳ በመሆኑ ለበሽታው መስፋፋት አመቺ ሁኔታ እንደተፈጠረና ዋጋ ሲያስከፍል እንደቆየ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ጥሪ መሠረት ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ከበሽታው እንዲላቀቁ ለማስቻል የዛሬ አምስት ዓመት ነበር ወደ ሥፍራው የመጣው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ጌሺ ያሮ ያለውን ፕሮጀክትም ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ ፕሮጀክቱን ዕውን አድርጓል፡፡

አቶ እንድሪያስ ሸኮዬ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የጌሾ የሮ ፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው፡፡ ጠቅላላ ለፕሮጀክቱ የአምስት ዓመት ቆይታ 29 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ይናገራሉ፡፡ በአምስት ወረዳዎች ለ275 ሺሕ የማኅበረሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራትም ወደ ወረዳዎቹ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡

29 ጥልቅ ውኃ ጉድጓድ፣ 111 የቦኖ ውኃ፣ በ37 ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች፣ 64 የንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ በ36 ጤና ጣቢያዎች የንፁህ ውኃ አቅርቦት በድርጅቱ ከተሠሩት የንፁህ ውኃ አቅርቦት ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ፕሮጀክቱ አዳዲስ ፈጠራ የታከለበት ሲሆን፣ ውኃ ከጉድጓድ ከወጣ በኋላ ቁጥጥር እንዲደረግበትና የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ችግሮች እንዳይኖሩ ታስቦ የተሠራ ነው፡፡

መኮሰኒ ወልጌ ከሶዶ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ የሚገኝ የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ መንገዱ ከመኪና ይልቅ በጋማ ከብት መጓዝን ያስመርጣል፡፡ ቀበሌዋ ሞቃታማ ስትሆን፣ ሥራቸው የገጠጡ ዛፎችም ከመንገዱ ጀምሮ ይታያሉ፡፡ ተራሮች ተቦርቡረው፣ ቦይ መስለውና ሸንተረሮች ሠርተው ይታያሉ፡፡ እነዚህ ቦይ መሰል ሸንተረሮች በአካባቢው ካለው ወንዝ የሚዘልቁ ሲሆን፣ በክረምት አፈሩን እያጠቡ እንዲያቀብሉት የተሠሩ ይመስላሉ፡፡

በበረሃ መሀል የሚገኘው ይህ ወንዝ ኩሬ ይመስላል፡፡ ለቤት እንስሳት ሆነ ለነዋሪዎች ወንዙ የውኃ ምንጫቸው ነው፡፡

አቶ አሳምነው መኮሴ ጌኖ ይባላሉ፡፡ በዚች ቀበሌ ነው ያደጉት፡፡ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ ጉድጓድ አስቆፍሮ ተጠቃሚ ካደረጋቸው ነዋሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ ለ8,000 ሺሕ ነዋሪዎች የሚያገለግሉ ሁለት ጤና ጣቢያዎች፣ ሁለት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንም የውኃ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ የውኃ ጉድጓዱ ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት እንዲያገለግል ሆኖ የተሠራ ነው፡፡

አቶ አሳምነው ቁጭት ባደረበት አነጋገር፣ ከፊት ለፊት ካለው ወንዝ አተኩረው ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ጎረቤቶቻቸው ውኃ ለመቅዳት ያሳለፉትን ድካም አስታውሰዋል፡፡ በሕይወት ያጧቸውን ሰዎችንና እንስሳት፣ ክረምት ሲመጣ የነበረው ጭንቀት ዛሬ እንዲህ ቀሎ በማየታቸው ‹‹ምነው ቀድሞ በሆነ›› እንዲሉም አድርጓቸዋል፡፡

በሥፍራው በተገነቡት መፀዳጃና ውኃ በተሟላላቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች መማር ጀምረዋል፡፡

በውኃ ዕጦት ችግር ውስጥ የነበረው የደጌ እንጮቼ ትምህርት ቤት ታሪክ ዛሬ እንደተቀየረ ተማሪ ትንሳዔ መንግሥት ትገልጻለች፡፡ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በሠራላቸው ሴቶች የወር አበባ ሲመጣባቸው ታጥበው አረፍ ከሚሉበት ክፍል አረፍ ብላ ነበር ያገኘናት፡፡ በወር እስከ አምስት ቀናት ከትምህርት እቀር ነበር ትላለች፡፡ አሁን ግን በየወሩ የንፅህና መጠበቂያ ሞዴስ ከትምህርት ቤት ስለሚወስዱና የውኃና የመፀዳጃ ቤት ችግራቸው ስለተቃለለ ለመማር ጥሩ ዕድል እንደፈጠረላቸው ታክላለች፡፡ በትምህርት ቤቱ የአካል ጉዳተኞች መፀዳጃና ገላቸውን መታጠቢያ የተገነባ መሆኑም ለተቸገሩት ዕፎይታን ሰጥቷል፡፡

የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎል፣ በወላይታ ዞን በከተማ ያለው የንፁህ ውኃ አቅርቦት 67 በመቶ፣ በገጠር ደግሞ 41 በመቶ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ፕሮጀክቱ በገጠር ያለውን ሽፋን ከፍ በማድረጉም በተለይ በገጠር ወረዳዎች ከፍተኛ ችግር ሆኖ የቆየውን የብልሃርዚያና የአንጀት ጥገና ትላትሎች በሽታ ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ትልቅ ሚና አበርክቷል ብለዋል፡፡

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ 50 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የድርጅቱ የፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ጥላሁን እንደሚሉት፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ለንፁህ ውኃ መጠጥ እንዲሁም ለሌሎች ፕሮግራሞች 14 ቢሊዮን ብር በመመደብ ከ15 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለመድረስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...