Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከማሳ እስከ ማዕድ የሚዘልቀው ሥርዓተ ምግብ

ከማሳ እስከ ማዕድ የሚዘልቀው ሥርዓተ ምግብ

ቀን:

በየማነ ብርሃኑ

የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን አገራዊ የጥናት መድረክን የግብርና ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በጋራ አዘጋጅተው ነበር፡፡

ከማሳ እስከ ማዕድ የሚዘልቀው ሥርዓተ ምግብ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ አስተባባሪ ጌታቸው ድሪባ
(ዶ/ር)

ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ሚኒስቴራቸው የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን እንዲሳካ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን እንዲያሳካቸው ከሚጠበቁት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ከባቢያዊ ውጤቶች ውስጥ አንዱ የሥርዓተ ምግብ ዋስትናና የዜጎችን የተሟላ ጤንነት ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ ተቋማቸው ከጤናና ከሥርዓተ ምግብ ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት ያላቸውን ተግባራት ከመተግበር  በተጨማሪ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲተገበር የቆየውንና ፕሮግራሙን ለማሳለጥ የተቀረፀውን የሰቆጣ ቃል ኪዳን በማስተባበር በኩል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ውስጥ በክላስተር ሁለት የተመለከቱትን የሕፃናት፣ ወጣቶችና የእናቶችን የሥርዓተ ምግብ ሁኔታ ከማሻሻል፣ በሰቆጣ ቃል ኪዳን የተዋወቁትን የፈጠራ ሥራዎች ከማስፋትና ኅብረተሰቡ በንጥረ ምግብ የበለፀጉና የተሰባጠሩ ምግቦች እንዲመገብ የሚያስችሉ የባህሪ ለውጥ ተግባቦት ሥራዎችን ከማከናወን አንፃር የተዘጋጀውን የአመጋገብ መመርያ ወደ ተግባር ከማስገባት አንፃር ቁልፍ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ፣ የምግብ እጥረትና ሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ችግሮች አሁንም በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለጤና ችግሮች ተጋላጭ እያደረገ ይገኛል፡፡

የሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ለደም ማነስ፣ ከክብደት በታች ለመሆንና ለመቀንጨር ከማጋለጡም ባሻገር፣ ሕፃናትን ለተደጋጋሚ በሽታ የሚዳርግ ነው፡፡

እስከ 50 በመቶ ለሚሆነው ያለ ዕድሜ ሞትም ምክንያት ነው፡፡ በተለይ መቀንጨር በአዕምሮአዊና አካላዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሲሆን፣ ለዝቅተኛ የትምህርት አቀባበል ያደርሳል፡፡ አዳዲስ ነገሮችን የማፍለቅ ችሎታ ውስንነትና በሚሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ብቁ፣ ውጤታማና አምራች ዜጋ እንዳይሆኑም ያደርጋል፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የመቀንጨር ምጣኔ ቅነሳ ያሳየ ቢሆንም፣ በቅርቡ በተደረገው ጥናት ወደ 39 በመቶ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የቀነጨሩ፣ 11 በመቶ ደግሞ የቀጨጩ መሆናቸው የተረጋገጠ መሆኑን ደረጀ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

አሁን የሚታዩት የሥርዓተ ምግብ ችግሮች ሥር ከሰደዱ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት መጠን እየጨመረ ከመምጣት ጋር ተዳምረው በአገሪቱ ላይ መንታ ገጽታ ያለው የሥርዓተ ምግብ መጓደል ጫናን እንደሚፈጥሩ አክለዋል፡፡

ጫናውም አጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ የሰው ኃይል ልማትንና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ ገልጸዋል፡፡

የምግብና ሥርዓተ ምግብ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድና ከሌሎች አገሮች ለየት ባለ መልኩ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ እየተተገበረ ስለመሆኑ ማሳያ የሚሆነው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ነው፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን ውጤታማነት ለማረጋገጥና ለመምራት ያስችል ዘንድ፣ በ2015 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በተደረገው ጥናት፣ በ2014 ዓ.ም. በተከናወነው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ በአንድ ዓመት ብቻ 59,717 ልጆችን ከመቀንጨር መታደግና 2,904 ልጆችን ከሞት መከላከል ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጥናት መሠረት፣ 99,080 ሕፃናትን ከመቀንጨር ለመታደግ የተቻለ ሲሆን፣ 3033 ጨቅላ ሕፃናትን ከሞት መከላከል ተችሏል፡፡

ውጤቱን በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል እንዲቻልም፣ የፕሮግራም ትግበራው ከ240 ወረዳዎች ወደ 700 ከፍ እንዲል አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር፣ የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪና የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ አስተባባሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሥርዓተ ምግብ ማለት ከማሳ ዝግጅት እስከ ማዕድ፣ ከምርት እስከ አመጋገብ ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የተቀመጡና አባል አገሮች የተስማሙበት ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት አንፃር፣ በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳና በታለመለት አቅጣጫ እየሄደ ባለመሆኑ፣ ይህን ግብ ለማሳካትና ለማፋጠን የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታው የተዘጋጀው ሃያ ሁለት ሕጎችና ስድስት መቶ አምስት ተግባራትን አካቶ መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪው፣ በሚፈለገው ደረጃ እየተተገበረ እንደሚገኝና ቅንጅታዊ አሠራሩም መልካም ውጤት እየታየበት ስለመሆኑም አክለዋል፡፡

የመድረኩ መዘጋጀት ዋና ዓላማም የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ በተሳካ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ለማረጋገጥና የጥናቱን ግኝቶች በመገምገም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና የትብብር ስልቶችንም እንዲያጎለብቱ ለማስቻል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን አገራዊ ዲያግኖስቲክስ ጥናት መድረክ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ እ.ኤ.አ በመስከረም 23 ቀን 2021 የተካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታለች፡፡

የተዘጋጀውን የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግና ትራንስፎርሜሽኑን የተሳካ እንዲሆን ለማስቻል፣ ከሚኒስቴሮች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከለጋሾችና ከሲቪል ማኅበረሰብ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ድህነትን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት አንፃር በሥርዓተ ምግብ በተለዩ 22 የመፍትሔ ሐሳቦች፣ ተቀናጅቶ በመተግበር፣ የመሬት አሠራርና አጠቃቀምን በማዘመን፣ በገጠር ፋይናንስ አቅርቦት፣ የገጠር ኤሌክትሪክ አገልግሎትና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና በመሳሰሉት አጀንዳዎች ዙሪያ ከተጠሪ ሚኒስቴሮች ከልማት አጋሮች፣ ከለጋሽ አገሮችና ከክልሎች ጋር በጥምረት በመሠራት ላይ ነው፡፡

እንደ አገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የገለጹት ግርማ (ዶ/ር)፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ከስንዴ ምርት ከአየር ንብረትና ከተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ጋር የተያያዙ ተግባራትን በማከናወን የምግብና ሥርዓተ ምግብ ተግዳሮቶችን በመፍታት ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...