Monday, February 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ፈር ቀዳጁ የሥነ ልቦና ሊቅ፡ ዩሱፍ ዑመር ዓብዲ

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ (ሥነ ልቦና) ትምህርት ክፍል ለአራት አሠርታት መምህር የነበሩት ዩሱፍ ዑመር ዓብዲ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የማሰተማር ጉዞአቸው ዛሬ በአገሪቱ አሉ ለተባሉ የሳይኮሎጂ ምሁራን የዕውቀት አባት ለመሆን በቅተዋል። ዕውቀታቸውን ለሁሉም ለማካፈል የሚተጉ፣ የግል ጥቅም ወይም የግል ጉዳይ የማያስጨንቃቸው፣ ደሞዛቸው በከፊል ለቤተሰባቸው፣ ከፊሉን ደግሞ በገንዘብ ችግር ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ለመደገፍ የሚያውሉ እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሁሉ መስክረውላቸዋል። ማኅበረሰባዊ ክፋትን የሚጋፈጡ፣ እውነትን ደግፈው የመቆም መርህ እንደነበራቸው በቅርብ በሚያውቋቸው  ወዳጆቻቸው ተመስክሮላቸዋል፡፡

ፈር ቀዳጁ የሥነ ልቦና ሊቅ፡ ዩሱፍ ዑመር ዓብዲ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሳይኮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ዩሱፍ ዑመር ዓብዲ (ዶ/ር)

እኚህ የሥነ ልቦና ምሁር በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን (በከፊል የታተሙ) አበርክተዋል፡፡ ሁሉም ሥራዎች ለአካዴሚው ዓለም በጣም ጠቃሚ በመሆናቸው  ተሰባስበው በጥሩ አዘጋጅ ተቀናጅተው ለኅትመት መብቃት እንዳለባቸው ታምኖበታል፡፡ 

ዩሱፍ ዑመር አብዲ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አቅራቢያ በምትገኘው ደኢህባ መንደር እ.ኤ.አ. በ1940 ተወለዱ። የትምህርት ጉዞው የተጀመረው በአካባቢው በሚገኘው የቁርዓን ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በኋላም ሀረር ይኖሩ ወደነበሩት ወንድማቸው በመሄድ በወቅቱ ታዋቂ በነበረው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አዳሪ ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱም በሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታለዋል። በ1959 በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በመቀሌ አፄ ዮሐንስ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ትምህርት አስተማሪ ሆነው ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል።

የዕውቀት ጥማታቸው ከፍተኛ ስለነበር በወቅቱ ይሰጥ የነበረውን የመግቢያ ፈተና በማለፍ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በ1966 በታሪክ በመጀመርያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም ወደ አሜሪካ በመጓዝ ከዩታ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሥነ ልቦና ካገኙ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ጊዜ መምህር በመሆን ሠርተዋል፡፡ ዩሱፍ ትምህርታቸውን በመቀጠል ከሳውዘርን ኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1974 አጠናቀዋል፡፡

 በሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ዩሱፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአራት አሠርታት ቆይታቸው ከነበራቸው ኃላፊነቶች መካከል በተለይም የትምህርት ምርምር ኢንስቲትዩት የመጀመርያ ዳይሬክተር ሆነው ለ12 ዓመታት መሥራታቸው ሲጠቀስ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽንም የትምህርትና የሰው ኃይል መምርያ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። የካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ በኢትዮጵያ ከፍ እንዲል መሠረት መጣላቸው፣ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል አማካሪ በመሆን ዕውቅና ማግኘታቸው ይወሳል፡፡

ዩሱፍ (ዶ/ር) ከአካዴሚክ  ባሻገር እ.ኤ.አ. ከ1992 እስከ 1994 የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሶዴን) ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ (ኢሶዴሊ) መሥራች አባል በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ለሥነ ልቦና ተባባሪ ፕሮፌሰር ለነበሩት ዩሱፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዕውቅና ለመስጠት በኢትዮጵያ ካውንስሊንግ ማኅበር በተዘጋጀውና በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም በጥር የመጀመርያ ሳምንት በተካሄደው ስብሰባ የተገኙት ዳርጌ ወሌ (ፕሮፌሰር)፣ የዩሱፍን (ዶ/ር) ቅን አገልግሎት ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹በዩኒቨርሲቲው ለሚሰጠው የካውንስሊግ ትምህርት ዋልታው ነበሩ›› ሲሉ አወድሰዋቸዋል። በእርሳቸው ሌት ተቀን ጥረት እግር የተከለው የሥነ ባህርይ ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የካውንስሊንግ ማኅበሩ በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚገባው የበኩላቸው አስተያየት ሰንዝረዋል። 

ሌላው ተናጋሪ ለረጅም ጊዜ እንደሚያውቋቸው የተናገሩት፣ ሀብታሙ ወንድሙ (ፕሮፌሰር)፣ ከዩሱፍ ጋር በተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ የምርምር ሥራዎችን እንደሠሩ፣ ከሌሎችና ብቻቸውን በጥናት መጽሔቶች እንደታተሙ አስረድተዋል።

‹‹ዩሱፍ ለሰው እንጂ ለራሳቸው አልኖሩም›› በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ከተማሪዎቻቸው አንዱ የሆኑትና የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የነበሩት አብዱናስር አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ወደር የማይገኝላቸው ተማሪዎቻቻውን አፍቃሪ በትምህርት እንዲገፉ የሚያበረታተቱ፣ ለማስተማር አንድ ክፍለ ጊዜ የማይበቃቸው፣ ታታሪ መምህር እንደነበሩ አስታውሰዋል።  አያይዘውም ‹‹ደሞዛቸውን ለሁለት ከፍለው ግማሹን ለቤተሰብ ግማሹን ደግሞ ለችግረኛ ተማሪዎች የሚሰጡ የተለዩ ሰው ነበሩ፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል።

የኢትዮጵያ ካውንስሊንግ ማኅበር ፕሬዚደንት ትዕግሥት ውሂብ ጸጋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩሱፍ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሥነ ባህርይ  ተቋም ከመጀመርያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለመድረስና በርካታ ባለሙያዎችን ለማስገኘት፣ እነዚህም ባለሙያዎች በልዩ ልዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተመድበው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል፣ በተለይም በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሠማርተው የካውንስሊንግ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማደረግ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበረ አብራርተዋል። በተጨማሪም ያልታተሙ ሥራዎች እንዳሏቸውና እነዚህም ሥራዎች መታተም እንደሚገባቸው በአጽንኦት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ካውንስሊግ ማኅበር ህልውና እንዲያገኝ ስለተደረገው ጥረት፣ ህልውናውን ካገኘ በኋላም ስላበረከተው ተቋማዊና አገራዊ አስተዋጽኦ፣ እንዲሁም የወደፊት አቅጣጫም አስረድተዋል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ባቀረቡት ጽሑፍ መሠረት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ዩሱፍ ከ1968 እስከ 2008 ድረስ ለ40 ዓመታት በሥነ ልቦና እና በተዛማጅ መስኮች ሲያገለግሉ ከታተሙላቸው ጽሑፎች መካከል በአፍሪካ ዓውድ ውስጥ በሳይኮሎጂ መስክ ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶችና እምቅ እድሎችን የሚዳስሰውና በኢንተርናሽናል ጆርናል ኦፍ ሳይኮሎጂ በ1975 የታተመው ‹‹The Problems and Prospects of Psychology in Africa››  አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ‹‹The Personnel and Guidance›› በሚል ርዕስ በ1983 በጆርናል ላይ በታተመ ሥራቸው ልዩ በሆነው በኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያለውን የመመርያና የምክር እንቅስቃሴ በጥልቀት ፈትሸዋል። ይህ እትም በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ በለውጥ ወቅት የምክር ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የትምህርት ጥናት በሶሻሊስት ኢትዮጵያ የሚለው ጥናታቸው፣ በዘመኑ የነበረውን የትምህርት አተገባበርና ፖሊሲዎችን ለመረዳት አስተዋፅዖ ያደርጋል። በአማርኛ በ1986 የታተመው መሠረታዊ የማኅበራዊ ሳይኮሎጂ፣  ማኅበራዊ ሥነ ልቦናን ለሚማሩ ተማሪዎች እንደ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው።

በባዕድ አገር ጥገኝነት የመጠየቅን ውስብስብ ሁኔታ በመዳሰስ የአንድ የተወሰነ ማኅበረሰብ ልምድ ግንዛቤዎች የሰጡበት የምርምር ፕሮጀክታቸው ‹‹በፊንላንድ የሶማሊያ ጥገኝነት ጠያቂዎች ችግር›› በሚል ርዕስ የሠሩት ነው፡፡

ካልታተሙ ሥራዎች መካከልም በኢትዮጵያ ከአእምሮ ሕመም ጋር ተያይዘው የሚታለፉ ተግዳሮቶችን በመዳሰስ ግንዛቤን ለማሳደግና በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን ሁኔታ ለመረዳት የሚጠቅመው ‹‹የአእምሮ ሕመም፡ በኢትዮጵያ በጣም የሚታወቁ ችግሮች፣ ቀዳሚው ነው፡፡ ‹‹የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተፈጥሮና ፍላጎት በኢትዮጵያ›› የተሰኘው የምርምር ፕሮጀክት አካል ጉዳተኛ ሕፃናት የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችን ለመረዳት ይረዳል፡፡

‹‹የተማሪዎች የአካዴሚክ አፈጻጸም ግምገማ፡- የደረጃ አሰጣጡ ጨዋታ እንዴት ነው›› በሚል ርዕስ በ1985 ባቀረቡት ጽሑፍ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዴሚክ ምዘና ተለዋዋጭነትን በትችት ተንትነዋል፡፡ ስለ ውጤት አሰጣጥ ሥርዓቶችና በተማሪዎች ላይ ስላለው ተጽዕኖ ግንዛቤዎችን አቅርበዋል፡፡

የአካዴሚክ ስኬት ምስጢር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመርያና ምክር፣ የአካል ጉዳተኞች ሳይኮሎጂ የሚሉ በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጇቸው የምርምር ሥራዎችም አሏቸው፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ውቤ ካሣዬ (ዶ/ር)፣ረዳት ፕሮፌሰሮቹ አህመድ ዘከርያና አበራ ጌታቸው የራሳቸውን ምልከታና የኢትዮጵያ ካውንስሊንግ ማኅበር ምን ማድረግ እንደሚገባው የበኩላቸውን ገንቢ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሌላው ተናጋሪ ሐጅ ዒሳ ሸኽ ዑመር በሰነዘሩት አስተያየት፣ በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ በወቅቱ የነበረውን የተማረ የሰው እጥረት ለመቅረፍ በሶማሌ ክልል ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲደረግ መጣራቸውን አውስተዋል፡፡

ዩሱፍ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ንግድ ባንክ ባሉ ታላላቅ ድርጅቶች አማካሪ በመሆን ዕውቀታቸውንና ግንዛቤያቸውን አካፍለዋል።

ባለትዳርና አራት ልጆች ያሉት የቤተሰብ መሪ የነበሩት  ዩሱፍ ዑመር ዓብዲ (ዶ/ር) ያረፉት በ2008 ነበር፡፡ ትውልዶችን በማነሳሳት የቀጠለ፣ በአካዴሚክ መስክ ብቻ ሳይሆን በሰፊው የማኅበረሰብና የአመራር ዓውድ ውስጥ ስለነበሩ ሥራዎቻቸው ለመጭው ትውልድ የዕውቀት ቀንዲል በመሆን ያበራሉ።

ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles