Friday, March 1, 2024

እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የሙስና ተጋላጭነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም. ፓርላማ ቀርበው ሙስናን መዋጋት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የመንግሥት አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፣ በ2015 ዓ.ም ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡

እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የሙስና ተጋላጭነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የሙስና መገለጫ ባህሪያት በእጅጉ የተወሳሰቡና ሚስጥራዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ፣ ውስብስብ በሚባል ደረጃ የሚጠቀስ ሙስና በሥልጣኔ ተራምደዋል በሚባሉት አገሮችም ጭምር የሚስተዋል ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና በብዙ መለኪዎች የደከመ የቴክኖሎጂና ዴሞክራሲያዊ ቁመና በሌላቸው አገሮች ደግሞ፣ ከተወሳሰቡትና ሚሰጥራዊ ናቸው ከሚባሉት የሙስና ተግባራት በተጨማሪ በፖለቲካ አሻጥር የሚገለጹና የሕዝብ ሀብትን ተገቢና ጠንካራ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት ሳይከተሉ ባልተፈለገ መልኩ የሚውሉ መሆናቸው በእጅጉ ይነሳል፡፡

መቀመጫውን ጀርመን በርሊን ያደረገውና ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ በየዓመቱ የሙስና ቅኝት ጥናት በማካሄድ የአገሮችን የሙስና ሁኔታ የሚያሳይ ደረጃና ውጤት ይፋ የሚያደርግ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው። ድርጅቱ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው የአገሮች የ2023 የሙስና ተጋላጭነት ሪፖርት እንደሚሳየው፣ ኢትዮጵያ ከአገሮቹ መካከል በ37 ነጥብ 98ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ነጥቡ የሚሰጠው ከ100 ሲሆን፣ 100 ያገኘ አገር የሙስና ተጋላጭነቱ ንፁህ የሚባል ሲሆን ውጤት ያስመዘገበ አገር ደግሞ አስከፊ የሙስና ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ  በዚህ መለኪያ  መሠረት እ.ኤ.አ በ2023 በ37 ነጥብ 98ኛ ደረጃን፣ እ.ኤ.አ በ2022 38 ነጥብ በማግኘት 94ኛ፣ እ.ኤ.አ በ2021 በ39 ነጥብ በማግኘት 87ኛ፣ እ.ኤ.አ 2020 በ38 ነጥብ በማስመዝገብ 94ኛ ተቀምጣ ነበር፡፡ እየዋዠቀ የመጣው የኢትዮጵያ ተጋላጭነት በአገር ውስጥ በፖለቲከኞች ከሚነገረው ዲስኩር ጋር የሚስማማ አለመሆኑ ይነሳል፡፡

እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የሙስና ተጋላጭነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋምና በዓለም ባንክ የሚደገፈው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ሥጋት ጥናት ሲያካሂድ በመሠረታዊነት የሚጠቀማቸው ምንጮች የሲቪክ ማኅበረሰብና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰነዶችና መረጃዎችን እንዲሁም አገር ውስጥ ያሉ ከጉዳዩ ጋር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ይጠቀማል፡፡ የአገሮች ደረጃዎችን ለማውጣት ደግሞ 13 መለኪያዎችን ይጠቀማል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሙስና ከኢትዮጵያ የፀጥታ ሥጋቶች እኩል እንቅፋት መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ተገልጾ ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተመሠረተው የፀረ ሙስና ግብረ ኃይል ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ ግብረ ኃይሉ ሥራዎችን በጀመረ ጥቂት ወራት ውስጥ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና የተወሰኑትን ለፍርድ ማቅረቡንም ለተወሰነ ጊዜ በሚዲያ ሲያስተገባ ተደምጦ ነበር፡፡

ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ በአንድ በኩል መንግሥት ራሱን የቻለ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋቁሞ ባለበት ሌላ ግብረ ኃይል ማቋቋም መንግሥት ፖለቲካው ውስጥ ለማጥቃት የሚፈልጋቸውን አካላት ዘብጥያ ለማውረድ ነው የሚሉ አስተያየቶች የተደመጡ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ሙስና ለአገር ደኅንነት አደጋ በመደቀኑ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ትኩረት እንደሰጠው እንጂ ሙስናን አቅልሎ ማየቱን አያሳይም የሚሉ አስተያዮች ይደመጡ ነበር፡፡

መንግሥት  ከኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከአገር ውጭ እንደሸሸ በመግለጽ፣ ለማስመለስ ሥራ መጀመሩን ከጥቂት ዓመታት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ  ስለሸሸው ገንዘብ መመለስ ከመንግሥት አካላት መካከል ለዓመታት ምንም ዓይነት ፍንጭ አልተሰማም፡፡ በተመሳሳይ በአገር ውስጥም በበርካታ መንገድ ስለሚገለጸው የሙስና ተግባር ኮሚሽኑም ይሁን የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሲሠሩ አልተስተዋሉም፡፡

በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ የሙስና ግብረ ኃይሉ ከጅምሩ ሲቋቋም በግልጽ ተጠሪነቱ በሕግ ያልተደነገገና የማይታወቅ፣ ሥራውን ተከታትሎ የሚገምግም አካል የለውም ይላሉ፡፡ ይልቁንም ግብረ ኃይሉን ለኮሚሽኑ ተጠሪ ማድረግ ቢቻል ወይም ኮሚሽኑ ጠንካራ ቁመና እንዲኖረው ቢደረግ ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር ይላሉ፡፡ የአገር ሀብትን የዘረፉ አካላት ዝርዝር ለፍትህ ተቋማት ከተላከ በኋላ፣ በፍትሕ ተቋማት የሚሰጠው ውሳኔ አስተማሪ አለመሆኑና ሀብት የመዘበረ አካል ከመዘበረው ሀብት ውስጥ የፈለገውን ቢደብቅና ገንዘቡ ባይገኝ በሕግ አንዲመለስ እንደማይደረግ፣ ይልቁንም ለሆነ ዓመት ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጎ ሲለቀቅ የደበቀውን ሀብት ይጠቀማል ይላሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ አስተማሪ ባልሆነ የፍትህ ሥርዓት ሙስና የመቀነስ ሁኔታው ከባድ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃ ማሽቆልቆልና የሙስና ሥጋቱ ከፍ ማለት አበዳሪዎችና ለጋሾች እጃቸውን በኢትዮጵያ ላይ በሚያኖራቸው ሥጋት ከሚደርጉት ድጋፍ ይሰበስባሉ፣ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ ለመምጣት ይጠራጠራሉ ፍላጎት እንደሚያጡም አክለው ይናገራሉ፡፡

በቀጣይ ፖለቲካዊ ቀርጠንኝነት ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጠንካራ የሆነ መዋቅር እንዲኖረውና በጀት በመበጀት ሣይንሳዊ ምርመራ እንዲደርግ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አቶ መርሃጽድቅ መኮንን ጠበቃና የሕግ ባለሙያ ናቸው፣ ለሪፖተር ስለጉዳዩ ሲናገሩ፣ ከሰሞኑ የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ሀብት ማስመዝገብን በተመለከተ ለሚዲዎች በሰጡት መረጃ ከ41 የመንግሥት ኃላፊዎች የአንዱ ብቻ ትክክለኛ ሆኖ ተገኘ በሚል የቀረበው መረጃ፣ ዜና ሆኖ ባይቀርብ ጥሩ ነበር የሚል እምነት አለኝ ይላሉ፡፡

ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚካደሄው የሀብት ማስመዝገብ ሒደት ውስጥ ሀብታቸውን ባስመዘገቡ 41 የመንግሥት አመራሮች ላይ በተደረገው የትክክለኛነት ማጣራት አንድ አመራር ብቻ ትክክለኛ መረጃ አቅርቦ ነበር፡፡

‹‹ለአንድ የመንግሥት ኃላፊ፣ አሁን ከዚህ ያነሰ ኃላፊነት ምን አለ፣ ሀብት ማስመዝገብ ሲባል ትንሹ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው›› ይላሉ፡፡

በጊዜያዊነት የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ ዕርምጃ ሊወሰዱ ነው ተብለው በጉጉት ሲጠበቁ፣ በቅፅበት ምን እንደሠሩ ሳይታወቅ፣ ምን እንደፈየዱ፣ ምን ውጤት እንዳመጡ በውሉ እንኳ ሳይገመገምና ለሕዝቡ ሳይብራራ ወዲያውኑ ብን ብለው እንደሚጠፉ ተናግረዋል፡፡ የዚህ ግብረ ኃይል መልክም እንዲሁ ነው ብለዋል፡፡

አቶ መርሐጽድቅ አክለውም መሰል የዘመቻ ሥራዎች በቀደመው የኢሕአዴግ ዘመንም በተለይ በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬና የደኅንነት ዳይሬክተሩ ጌታቸው አሰፋ ወቅት 60 እና 70 ሰው በከፍተኛ ደረጃ ስመ ጥር የነበሩ ባለሀብቶችንና ባለሥልጣናት በአንድ ጊዜ መጠራረግ (Purge) ማድረግና በዜና በማጯጯህ ‹‹እስር ቤት አስገባናቸው፣ ዘብጥያ አወረዳቸው፤›› የሚል መረጃ መስጠት የተለመደ እንደነበር፣ ነገር ግን ወዲያውኑ ሕዝቡ ውጤቱን ሲጠብቅ ምንም ሳይፈጸም ጉዳዩ እንደሚረሳ አቶ መርሐጽድቅ ያብራራሉ፡፡ 

ይሁን እንጂ አንድ ነገር መታወቅ ያለበት የፀረ ሙስና እንቅስቃሴና ዘመቻ ውጤትና ዋናው ጉዳይ ከሶ ሰውን ማሰር ሳይሆን፣ በትክክል በማስረጃ ተደግፎ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ሲያደርጉና ፍትሕ ሲሠራ ማየት እንጂ ሰዎች ሲታሰሩ ማየት የማንም ፍላጎት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ከሰሞኑ ትራንስፓረንሲ ያወጣው ሪፖርትና ኢትዮጵያ በሙስና ሥጋት የተሰጣት ደራጃ በወረደ ቁጥር፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው እምነት በዚያው ልክ ድጋፋቸውንም የሚይዝበትና ትግሉን ሊያግዝና ሊረዳ የሚችል ፈንድ ለማግኘት ከባድ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለው ትልቁ መሰናክል በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃው የለም ሳይሆን ሰዎችን፣ ከማሰር ባለፈ ርቆ ሄዶ ወደ ምርመራ በሚገባበት ወቅት በአብዛኛው ሙስና በተቀነባበረ መንገድ የሚፈጸም በመሆኑና በዚህ ሒደት ውስጥ የሚዘፈቁትና የሚነካኩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለሚበዙ ጉዳዩ ብዙም ርቆ ሳሄድ ባለበት እንደሚቆም ይናገራሉ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ እምብዛም የተለመደውና እየሠራን ነው ለማለት ብቻ የቀበሌ ሊቀመንበር የሚጠየቅበት አካሄድ በአመዛኙ በትምህርትና ሥልጠና ሊስተካከል የሚችለው ላይ ትኩረት ይደረጋል እንጂ ግዙፍ (Grand) በሚባሉት ላይ ወሬው እንደተወራ ማጠፊያ ሲያጥረው ነው የሚታየው ብለዋል፡፡

‹‹የገዘፈ የሙስና ተግባር የለም የሚሉ አካላት እንድምታው መጥፎ ዝንባሌ ነው፤›› የሚሉት አቶ መርሐጽድቅ፣ ነገሩ የለም ሳይሆን ለመኖሩ በቂ ማስረጃ እንደሚኖር የሚታወቅ ጉዳይ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ችግሩ የዚህን ሒደትና ሙስና ሲገኝ ምርመራ ለማድረግና የፍትሕ ውሳኔ ለመስጠት ያለው አገራዊ ሥርዓት ደካማ መሆን፣ የረቀቀ ምርመራንና ከፍተኛ ቴክኖሎጂን የሚጠይቅ በመሆኑ የፀረ ሙስና ተቋሙም ይሁን ሌሎች አካላት ሚስጥራዊ የሙስና ተግባሩን ሊያገኙት ባለመቻላቸው መሆኑ ተናግረዋል፡፡

በውጭ አገሮች ተቋማቶቻቸው ጠንካራና ገለልተኛ ከመሆናቸው የተነሳ ባለሥልጣናትን በሙስና ቅሌት ለመርመርና ለማጣራት ብዙ አድካሚ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ላይ የፀረ ሙስና ትግል ከዚህ በመለስ ተብሎ  በሚል በምርጫ የሚሠራ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህ ተግባር በቀጣይ ማስተካከያ ካልተደረገበት አደጋው የከፋ የሥርዓትና የሕዝብ ጠንቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከሕዝብ እንደራሴ ውጭ መቼስ ለመንግሥት ሰማያት ወይም ለእግዚአብሔር ተጠሪ የሆነ ቋሚ የትም ማምጣት ስለማይቻል፣ ቢያንስ አስፈጻሚው ጣልቃ በማይገባበት መልኩ ለፓርላማው ተጠሪ ቢደረግ›› ለውጥ ማየት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ሙስና ምንም እንኳ በሌሎች አይከወንም ባይባልም በዋናነት ግን የሕዝብ ሀብትና ሥልጣን ያለው የአስፈጻሚው አካል ወሳኝ ተዋናኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ቢያንስ እንደ ዋና ኦዲተር፣ ዕንባ ጠባቂ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰብዓዊ መብቶችን የመሳሰሉ ተቋማት ተጠሪነቱ ለፓርላማው ማድረግ ቢቻል ጠንካራ ተቋማዊ ቁመና መፍጠር ይቻላል ይላሉ፡፡

የሥራ ኃላፊዎች ሀብት ያስመዝግቡ ሲባል ያን ያህል እስከ ታች ወርዶ የሾፌር ግብዓት ጭምር ማስመዝገቡ ፋይዳ የለውም የሚሉት አቶ መርሐጽድቅ፣ ሾፌር ንብረቱን እንዲያስመዘግብ ከማድረግ ይልቁንም የአገር ሀብት በእጃቸው ያሉ ታላላቅ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ትኩረት ቢደረግ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

 ይመዝገብ ከተባለ ደግሞ ከተመዘገበ በኋላ የተመዘገበውን ሀብት ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ተብሎ ቢቀመጥም ለሕዝብ በግልጽ ይፋ ካልተደረገ ለአንድ ተራ ሰው የአንድ ባለሥልጣን ሀብት ተመዘገበ አልተመዘገበ ምንም ለውጥ የሌለው በመሆኑ ይፋ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

መንግሥት በዘመቻ ሙስናን ልታገል ብሎ ሲጀምር ጅማሬው መልካም ቢሆንም፣ የአንድ ጊዜ የሕዝብ ስሜትን ለማብረድ ብቻ በከፍተኛ ሁኔታ በሚዲያ በማስተጋባት የሚቆም ሳይሆን ኃላፊነት ያለው አካል መድቦ ቁርጠኛ በሆነ መንገድ ካልተሠራ፣ ችግሩን የአጭር ጊዜ ሆይሆይታ አድርጎ መሄድ ውጤት እንደማያመጣ ጠቅሰው ውሳኔ የሚሰጥ ትልቅ ባለቤት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

ሙስናን የሚታገል ማኅበረሰብ መፈጠር አለበት የሚሉት አቶ መርሐጽድቅ፣ በየቤቱ የሚሰማው ዕሳቤ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚለው ጉዳይ በተለያየ መንገድ እንደሚስተጋባ ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ሙስና እንደ ማኅበረሰብ እንደ ቢዝነስ የሚቆጠር እንጂ አሳፈሪ ድርጊት መሆኑ እየቀረ በመምጣቱ ለሁሉም አካል ትልቅ ሚና መጫዎትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተሰጥተው የነበሩ የምርመራና ክስ ሥልጣኖች ወደ መደበኛ ፍትሕ ሥርዓት እንዲመለሱ ማድረጉ ጠቃሚ አልነበረም የሚሉት አቶ መርሐጽድቅ፣ ኮሚሽኑ እነዚህን ሥልጣኖች ሲሰጡት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ታስቦ የነበረ በመሆኑ አሁንም ሊመለሱለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው የሙስና ተግባር ማኅበረሰብንና ሥርዓትን የማፍረስ አቅም ያለው ወንጀል በመሆኑ ከትራንስፓረንሲ ሪፖርት ባሻገር አገርን ማዳን የእኛው የቤት ሥራ በመሆኑ የአገርን ሀብት ከምዝበራ ልንታደገው ይጋባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአኅጉር አቀፍም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የፀደቁ የፀረ ሙስና ስምምነቶችን የፈረመች በመሆኑ፣ በስምምነቱ መሠረት የሚጠበቅባትን ሚና መወጣት እንዳለባትና ኮሚሽኑንንም በተደነገገው መሠረት ገለልተኛ በማድረግ ሥራውን በነፃነት እንዲሠራና አስፈጻሚው አካል ላይ ያመዘነውን ሙስና እንዲጋፈጥ ማስቻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር የካቢኔ አባል በሆነበትና ፌዴራል ፖሊስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ በሆነበት እነዚህ አካላት አድርጉ የተባሉትን የሚሉ፣ በተለይም በዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብተው ይህን አቁሙ ይህን አታቁሙ የሚል ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ ምንም ሊያደርግ ቢሞክር በአስፈጻሚው አካል ጫና ውስጥ የመውደቅ ዕድሉ ሰፊ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ ትምህርት በማስተማር ጊዜውንና ገንዘቡን ሳያጠፋ ግዙፍ የሙስና ወንጀሎች ላይ የሚሳተፉ ባለሥልጣናትና ከእነሱ ጋር የሚተባበሩ ከፍተኛ ባለሀብቶች እንዲሁም የሕዝብ ድርጅቶች፣ አመራሮች የሚፈጽሙት ወንጀል ላይ አተኩሮ እንዲሠራና አስተማሪ ዕርምጃ ቢወስድ፣ ኮሚሽኑ በሥነ ምግባር ትምህርት ውስጥ ሳይገባ ሰው በሚወስደው ዕርምጃ በራሱ ጊዜ የሚማርበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ የሙስና ደረጃ ከዓመታት በፊት በተወሰነ መልኩ ይሻል የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን የባሰ እያሽቆለቆለ መሆኑን አስረድተው፣ ይህ ሁሉ የሚወጣው ከትኩረትና ቁርጠኝነት መጥፋት ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ካሳሁን በበኩላቸው፣ በአምነስቲ የደረጃ አወጣጥ እንዳልተገረሙ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ሲሰጥ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የነበሩትን ተስፋ ሰጭ የሕግ ማዕቀፎችና ለውጦች በማየት እንደነበር፣ ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታዩ ያሉት የሙስና ተግባራት ግን ተቋማት በቋንቋ፣ በብሔር፣ የተቀናጁበት መሆኑ፣ አገልግሎት ለማግኘት ቋንቋ፣ ብሔር፣ ገንዘብ የሚጠየቅበትና በጣም የከፋ የሚባሉ የሙስና ዓይነቶች በመታየታቸው ደረጃው አስገራሚ አይደለም ብለዋል፡፡

መንግሥት ፀረ ሙስና ላይ ሠራሁ እያለ፣ የትራንስፓረንሲ ውጤቱ ሲመጣ መሬት ላይ ያለው እውነት ጋር የማይገናኝ ለመሆኑ ሊገርመን የሚገባ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት ያቋቋመው የሙስና ኮሚቴ ባለሥልጣናትን ለማጋለጥና ለመያዝ የተደረገ እንጂ፣ በእውነቱ ዓላማ የሰነቀ ነው ወይ? ሲባል እስካሁን ምን ያህል ርቀት እንደሄደ መነጋር አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው አቶ ሳሙኤል ይገልጻሉ፡፡

ኮሚቴ በተቋቋመ ማግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ ሙስና የለም ብለው መናገራቸውን፣ በተመሳሳይ ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ ሲል እንደነበረው ፋብሪካ ሊመርቁ ሄደው በምርቃት ፕሮግራም ላይ ሙስና የአገር ጠላት ነው ልንዋጋው ይገባል ማለታቸውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተቃራኒው በሐዋሳ አንድ ፋብሪካ ምርቃት ላይ ተገኝነተው አውቃችሁም ይሁን ሳታውቁ የሰረቃችሁትን ገንዘብ ለልማት ካዋላችሁት እኛ አንጠይቅም የሚል ንግግር ማድረጋቸው፣ መንግሥት ዕርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑን እንደ ማያሳይና ለድርጊቱ ፈጻሚዎች የልብ ልብ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል አንደሚሉት የፀረ ሙስና ኮሚቴ ከመቋቋሙ በፊት የኮሚሽኑን አቅም መገንባት እንደሚቻልና ድሮ የነበረው የመመርመር፣ የመክሰስ ሥልጣኑን መሰጠት ቢቻል በጣም ለውጥ ማምጣት ይችላል ብለዋል፡፡

በአንድ አጋጣሚ ወደ ኢንዶኔዥያ ተጉዘው የአገሪቱን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋም ለመጎብኘት ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ኬፒኬ (KPK) እየተባለ የሚጠራው የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ተቋም ላይ ባደረጉት ጉብኝት፣ ይህ ኮሚሽን ሁሉንም ሥራ በነፃነት የሚሠራና የራሱ እስር ቤት፣ ፍርድ ቤት ያለው መሆኑን ተቋሙ ሙስናን መመርመር ሲጀምር ከግማሽ በላይ የፓርላማ አባላት በመታሰራቸው፣ ፖለቲከኞች ይህን ተቋም በዚህ መልኩ ማቋቋማችን ስህተት ነው በሚል መንግሥት ሊቀለብሰው መሆኑ ሲሰማ ሕዝቡ ጉዳዩን ሰምቶ ገንፍሎ ወጥቶ ተቋሙን እንዳዳነው ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥም ተቋሙን ከፖለቲካ ፓርቲ አባል ውጪ የሆኑ አካላት እንዲመሩት ለማድረግ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርኝነትና ተነሳሽነት እንደሚስፈልግና ‹‹መንግሥት የሰምና ወርቅ ኑሮውን ማቆም›› መቻል አለበት ብለዋል፡፡

በትራንስፓረንሲ የቀረበው ደረጃ ምንአልባት መንግሥት ትኩረት ላይሰጠው ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የተደማመሩ ውጤቶች መጨረሻቸው አገር ላይ የሚያመጣው ዳፋ ቀላል ስለማይሆን ቀና ብሎ መስማትና መደንገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -