Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ዘርፉን የሚመለከቱት የንግድ ሕግን መጽሐፍት የማሻሻል ሥራ ሊጠናቀቅ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ60 ዓመታት በላይ አገልግሎት ላይ የነበረው የንግድ ሕግ ሲሻሻል እንዲዘገይ የተደረገው የፋይናንስ ተቋማትን የሚመለከተው የንግድ ሕግ ረቂቅን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ 

የቀድሞው የንግድ ሕግ ሲሻሻል የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፎችን የሚመለከቱት ሕጎች ለብቻ ተነጥለው እንዲሻሻሉ መወሰኑና የማሻሻል ሒደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስም ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ መደረጉ ይታወሳል። 

እነዚህን ሕጎች የባንክና የኢንሹራንስ ንግድ ሕግ አድርጎ ለብቻ ለማሻሻልም ሁለት የሕግ አርቃቂ ቡድኖች ተቋቁመው ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የመጨረሻውን ረቂቅ የማሻሻያ ሕግ ለማውጣት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ታውቋል። የፋይናንስ ዘርፉን በሚመለከተው ረቂቅ ሕግ ላይ ግብዓቶችን በማሰባሰብ የረቂቁን የመጨረሻ ምዕራፍ ወደማውጣት እየተሸጋገረ ስለመሆኑም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍን የሚመለከተው የንግድ ሕግ ከሌላው የንግድ ዘርፍ ሕግ ተለይቶ ማሻሻያው እንዲዘገይ የተደረገበት ዋና ምክንያት፣ ከዘርፉ አሠራር ጋር የተያያዙና ቴክኒካል ለውጦችን የሚጠይቁ በርከት ያሉ ጉዳዮች ያሉበት በመሆኑ ነው፡፡

አሁን በሁለት ቡድን ተከፍሎ እየሠራ የሚገኘው አርቃቂ ቡድን፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና የዘርፉ ምሁራንን አሳትፎ በጥንቃቄ እንዲሠራ በመወሰኑ፣ በዚሁ አግባብ የረቂቅ ዝግጅቱ ከሌላው የንግድ ሕግ ሊዘገይ መቻሉን ያነጋገርናቸው አንድ የረቂቅ ሕጉ ዝግጅት ቡድን አባል ገልጸዋል፡፡ 

እኚሁ የረቂቅ ሕጉ ዝግጅት ቡድን አባል ጨምረው እንደገለጹት፣ ባንክና ኢንሹራንስ የሚመለከተው የንግድ ሕግ የመጀመሪያው ደረጃ ረቂቅ (ፈርስት ድራፍት) ቀርቦ የኤክስፐርቶች ውይይት እየተደረገበትና እየዳበረ ነው፡፡ ተጨማሪ ግብዓት የማሰባሰብ ሥራው አሁንም የቀጠለ ቢሆንም፣ የመጨረሻ ደረጃ ረቂቅ ሕግ ለማውጣት በፍጥነት እየተሠራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ አሁን በተደረሰበት ደረጃም የመጨረሻው ረቂቅ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት አንፀባርቀዋል፡፡  ከቀድሞው የንግድ ሕግ ውስጥ ተሻሻለው ተፈጻሚ መሆን የጀመሩት ሦስት መጻሕፍት መሆናቸውን ያስታወሱት እኚሁ የአርቃቂ ኮሚቴው አባል፣ እነዚህም መጽሐፍ አንድ፣ ሁለትና አምስት የሚባሉት የንግድ ሕጎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ 

መጽሐፍ አራትና አምስት የሚባሉትን፣ የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፎችን የሚመለከቱትን ሕጎች ለማሻሻል የፋይናንስ ዘርፉ አሁን የደረሰበትንና መፃዒ ሁኔታዎችን ማገናዘብና ለዚህም ከሕግ ሙያ ውጪ ጥልቅ የፋይናንስ ዘርፍ ቴክኒካዊ ዕውቀትን የሚጠይቁ በመሆናቸው ለብቻቸው እንዲዘጋጁ መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡

የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፉ የንግድ ሕግ ዘግይቶ ለብቻው እንዲሰናዳ የተደረገበት ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ በረቂቁ ዝግጅት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃም ዓለም አቀፍ ኮንሰልታንቶች እንዲገቡበት ጭምር በመፈለጉ ጭምር ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከተለያዩ የውጭ ተቋማት አማካሪዎች በረቂቅ ዝግጅቱ ሐሳቦችን አርቃቂ ቡድኑ መቀበሉ ታውቋል፡፡  

ለየብቻ ዝግጅት እየተደረገበት ያለው የባንኩም ሆነ የኢንሹራንስ ዘርፉ የንግድ ሕግ ረቂቅ መጨረሻ ላይ አንድ ላይ በመሆን የፋይናንስ ሕግ መድብል (ፋይናንሺያል ሰርቪስ ኮድ) በሚል እንደሚወጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡   

የኢንሹራንስ የንግድ ሕጉ ከ1961 ጀምሮ ምንም ሳይሻሻል በመቅረቱና በዓለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ ዘርፉን የሚመለከቱ በርካታ ለውጦች በመደረጋቸው አዲሱ የንግድ ሕግ ይህንን ግንዛቤ ባስገባ መልኩ ይሰናዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

አዲሱ በኢንሹራንስ ዘርፉ የሚደረገው ማሻሻያን በተመለከተ፣ ከኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ባገኘነው መረጃ ማኅበሩ የአርቃቂ ቡድኑ አባል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንና በረቂቁ ውስጥ መካተት አለባቸው የተባሉ ሐሳቦችንም በጽሑፍ ጭምር በማቅረብ ለኢንዱስትሪው ጠቃሚ የሆነ የንግድ ሕግ እንዲወጣ የበኩሉን እያደረገ ነው፡፡  

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የኢንሹራንስ ባለሙያ ደግሞ፣ የኢንሹራንስ ዘርፍን የሚመለከተው የንግድ ሕግ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎቹም ሆነ ከተገልጋዮች አንፃር ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት፣ የኢንሹራንስ ንግድን የተመለከቱ በርካታ አንቀጾችም ጊዜያቸው ያለፈባቸው በመሆኑ፣ ሕጉን ማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታና ለውጥ የሚያመጣ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ባንክን የተመለከተው የንግድ ሕግም በተመሳሳይ ጊዜውን የዋጀ ማሻሻያዎች የሚያስፈልጉት ስለሆነ፣ በረቂቅ ሕግ ዝግጅቱ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ተሳትፈውበት እየተሰናዳ ነው፡፡ ከ60 ዓመት ወዲህ የባንክ ዘርፉን የተመለከተ በርካታ አሠራሮች ተለውጠዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን የተመለከቱ ሕግጋት በረቂቁ እንዲካተት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ 

በተለይ ከዲጂታል የባንክ አገልግሎትና ከብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት አዋጅ ጋር በተያያዘ የንግድ ሕጉ የሚያካትታቸው አዳዲስ አንቀጾች ይኖሩታል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ክፍት ከመሆኑ አንፃርም የንግድ ሕጉ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ለማስተናገድ የሚያስችሉና አተገባበራቸውን የተመለከቱ አዳዲስ አንቀጾች ይኖሩታል፡፡ እንዲህ ያሉ አዲስ አንቀጾች የሚሰናዱት የውጭ ልምዶችን እንደመነሻ በመውሰድ ጭምር ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አሻሚ ትርጓሜ ይሰጣቸው የነበሩ አንዳንድ አንቀጾችና ቃላትን ጭምር እንዲሻሻሉ የሚደረጉ ስለመሆኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

እንዳነጋገርናቸው የባንክና የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ማብራሪያ፣ በሁለቱም ዘርፍ በንግድ ሕጉ የነበሩ ብዙዎቹ አንቀጾች ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ መሆኑን ነው፡፡

በአብዛኛው በቀድሞ የንግድ ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ፣ ነገር ግን የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከቱ አዳዲስ አገልግሎቶች የንግድ ሕጉ አካል በማድረግ ተጠባቂ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው እንደ ምሳሌም የጠለፋ መድን ኩባንያን ጠቅሰዋል፡፡ 

የክፍያ ሥርዓትን የተመለከተው የተለያዩ ሕጎች ያሉ ቢሆኑም፣ በንግድ ሕጉ መታቀፍ ስለሚኖርባቸው ረቂቁ እንዲህ ያሉትን ጉዳይ ሁሉ ይመለከታል፡፡ 

አጠቃላይ የክፍያ ሥርዓቱን የተመለከቱ አሠራሮችን የንግድ ሕጉ አካል ሲሆኑ፣ በዚህ የአገልግሎት አሰጣጥ ሊኖር የሚችለውን እንዴት መፍታት እንደሚገባ የሚያመለክት ጭምር እንደሚሆንም ከባለሙያው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ከክፍያ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችል አለመግባባት ቢኖር በሕግ ሊፈታ የሚችልበት የአሠራር ሒደቶች ሁሉ በረቂቁ ይካተታል፡፡  

የኢንሹራንስ ውሎች ትርጓሜን ጨምሮ አጠቃላይ የውሉ ተፈጻሚነትን የተመለከቱ አዳዲስ አንቀጾች እንደሚኖሩት ተጠቅሷል፡፡ የኢንሹራንስ ክፍያ ጥያቄ አተገባበርም ማሻሻያ ይደረግባቸው ተብለው ከሚጠበቁ አንቀጾች መካከል አንዱ ነው፡፡ 

በሁሉም ዘርፎች የአገልግሎት ክፍያንም ሆነ የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተ፣ በነባሩ የንግድ ሕግ በጥሬ ገንዘብ ብቻ የሚፈጸሙ ክፍያዎችን በተመለከተም ረቂቁ አዳዲስ አንቀጾች ይኖሩታል፡፡

ከዚህ ቀደም አከራከሪ የነበሩ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሕግ ነክ ጉዳዮችን በመፈተሽም አከራካሪ የተባሉ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሔ የሚሆን ማሻሻያ እንደሚደረግላቸው ከብዙ በጥቂቱ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንበዝ ተችሏል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን የሚመለከቱ አዳዲስ ሕጎች ረቂቁ ይካተታሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ ይገኙባቸዋል፡፡  

የቀደመው የንግድ ሕግ ካሉት ከአምስቱ መድብሎች አሁን ተሻሽለው ሥራ ላይ የዋሉ መድብሎች ውስጥ አንደኛው ‹‹ስለንግድ ምዝገባ ፈቃድ›› እና ‹‹ነጋዴ ማነው?›› የሚለውን የሚተነትንና የሚያሳይ ነው፡፡ 

ሁለተኛው ደግሞ ስለንግድ ማኅበራት የተመለከቱ ሕግጋቶችን የያዘ ሲሆን፣ ሦስተኛው የኪሳራ ጉዳዮችን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን የያዘ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ 

ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው የተባለውን የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከተው ረቂቅ ሕግ፣ ሌላ ማጓጓዣን የሚያመለክተው መድብል ወደፊት ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ በተሻሻለው ሦስቱ የንግድ መድብሎች በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉ ስለመሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች