Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቀድሞው የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት የጎህ ቤቶች ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰየሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጎህ ቤቶች ባንክን በፕሬዚዳንትነት የሚመራ ባለሙያ ሲያፈላልግ የቆየው የጎህ ቤቶች ዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የቀድሞውን የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም ፀጋዬን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርጎ መሰየሙ ታወቀ፡፡

ከጎህ ቤቶች ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አቶ ግሩም ከጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የጎህ ቤቶች ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው ሥራ ጀምረዋል፡፡ 

አቶ ግሩም የጎህ ቤቶች ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት ባንኩ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩትን አቶ ሙሉጌታ አስማረ በመተካት ነው፡፡ 

አቶ ሙሉጌታ ኃላፊነታቸውን በሕመም ምክንያት ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረቡ ረዘም ያለ ወራትን አስቆጥረው እንደነበር የሚያመለክተው መረጃ፣ የጎህ ቤቶች ባንክ ቦርድ የአቶ ሙሉጌታን መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ፣ ነገር ግን አዲስ ፕሬዚዳንት እስኪሰየም ድረስ ግን ኃላፊነታቸውን ይዘው እንዲቆዩ በተደረሰ መግባባት ቆይተዋል፡፡ ከ23 ቀን 22016 ዓ.ም. ጀምሮም ቦታውን ለተጠባባቂው ፕሬዚዳንት አስረክበዋል፡፡ 

የጎህ ቤቶች ባንክ ቦርድ በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት የሰየማቸውን አቶ ግሩም ቋሚ የባንኩ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ የሚቀርብ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

አቶ ግሩም ከሦስት ወራት በፊት ከብርሃን ባንክ በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በባንኩ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ የቆዩት አቶ ግሩም፣ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ደረጃ ከሠሩባቸው ተቋማት ውስጥ የኅብረት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ከኅብረት ባንክ እስከሚለቁ ድረስ የመጨረሻዎቹን ስድስት ወራት የባንኩ ሲኒየር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን መሥራታቸውን የሥራ ልምዳቸውን የሚያመለክተው መረጃ ያሳያል፡፡ የኢትዮ የሊዝ ፋይናንሲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው መሥራታቸው ይጠቀሳል፡፡ 

ለ11 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ የትምህርታቸውን በተመለከተም፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በኤምቢኤ (MBA) የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ታውቋል፡፡    

አቶ ግሩም ከብርሃን ባንክ ከለቀቁ በኋላ የብርሃን ባንክ ቦርድ አቶ ሰለሞን አሰፋን በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት ከሰየመ በኋላ፣ ቋሚ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የቀድሞ በባንኩ ውስጥ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲሠሩ የቆዩትን አቶ ኤርሚያስ ተፈራን በማጨት ሹመቱ እንዲፀድቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

ጎህ ቤቶች ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው የሞርጌጅ ባንክ በመሆን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት 1.3 ቢሊዮን ብር ማበደር የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶው የሞርጌጅ ብድር መሆኑንም መግለጹ ይታወሳል፡፡ 

ባንኩ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 1.3 ቢሊዮን ሲሆን፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑንም 2.63 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች