Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው›› ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ አስተምረዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሶማሌን አካባቢ በጥልቀት ካጠኑ ምሁራን አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮ ሶማሊያን ጦርነት ለማጥናት ነበር ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ያዞሩት፡፡ ይሁን እንጂ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍል በአካዴሚ ማኅበረሰቡ በደንብ ያልተጠናና ያልተገለጸ ሆኖ ስላገኘሁት፣ በጥልቀት ስለአካባቢው ማጥናቴን ቀጠልኩ ይላሉ፡፡ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ኦጋዴን አስተዳደር ተብሎ የቆየውን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክፍል እስከ ዘመነ ደርግ መገባደጃ አስተዳደራዊ ሁኔታውን፣ እንዲሁም አካባቢው ያጋጠመውን ጦርነት ጨምሮ ማጥናታቸውን ይናገራሉ፡፡ ወደ ፒኤችዲ ዲግሪ ጥናት ሲገቡም በዚሁ አካባቢ ማኅበረሰብ በተለይ አርብቶ አደርነትና አሠፋፈርን የተመለከቱ ጉዳዮችን በሰፊው የዳሰሰ ጥናት ላይ ሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ የተለያዩ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ላይ በማተኮር የሁለቱን አገሮች ጉርብትናና የሕዝቡን አኗኗር የተመለከቱ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ አሁን የኢትዮጵያና የሶማሌላንድን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን የወቅቱን ፍጥጫ በቅጡ ለመረዳት ይረዳ ዘንድ፣ የዚህን ቀጣና ታሪክ መለስ ብለው ያወጉበትን ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተለይም የሶማሌ አካባቢ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር የጋራ ታሪክ እንደሌለው ተደርጎ ይቀርባል፡፡ በቅርብ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተጠቃለለና ከኢትዮጵያ ጋር ቁርኝት የሌለው ነው የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- የተዛቡ ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዴ እነዚህ ዳር አገር የሚባሉ አካባቢዎች በእርግጥ ዳር አገር አይደሉም፡፡ ከውጭ አገሮች ጋር የሚያገናኙ ወሳኝ ድልድዮች ናቸው፡፡ ከማዕከላዊው መንግሥት ራቅ ያሉ ስለሆኑ ለአመፅም ቀረብ ያሉ ናቸው፡፡ ማዕከሉ እየደከመ ሲሄድ አመፅ በእነዚህ አካባቢዎች መፈጠር ይጀምራል፡፡ ኢትዮጵያን ሲፈትኑ የኖሩት ብዙ ጊዜ በእነዚህ አካባቢዎች የሚነሱ አመፆች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ መሀል ላለው አካባቢም ሆነ መንግሥት በእጅጉ የሚያስፈልጉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ የሌላው ኢትዮጵያ ክፍል አያስፈልግም ለማለት ሳይሆን፣ የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ለባህር በር መንገድ ስለሆነ ጭምር፡፡ የባህር በር ደግሞ ለአንድ አገር እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያም ለባህር በር ጉዳይ ለ500 ዓመታት ስትታገል ቆይታለች፡፡ አዶሊስን የሚያክል ወደብ የነበረን፣ ከቀይ ባህር አልፈን የመን ድረስ እንቆጣጠር የነበርን ሰዎች በባዶ መቅረታችን የሚያስቆጭና ስንታገልለት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ  ሶማሌ (ኦጋዴን) የሚባለው የኢትዮጵያ ክፍል የዓድዋ ጦርነት ከመካሄዱ በፊት እኮ ነው ወደ ኢትዮጵያ የተጠቃለለው፡፡ እንደሚታወቀው ከዓድዋ ጦርነት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የገቡ አካባቢዎች አሉ፡፡ ምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ግን ከዚያ ይቀድማል፡፡ ሐረር በተያዘ ወዲያው ነበር ልዑል ራስ መኮንን ኦጋዴንን ወደ ኢትዮጵያ ያስመለሱት፡፡ ‹‹ምን ያህል ተቆጣጥረው አስተዳድረውታል?›› የሚል ጥያቄ ካልተነሳ በስተቀር፣ ኦጋዴን ከዓድዋ ቀድሞ የኢትዮጵያ ሆኖ ነበር፡፡

በዘመናዊት ኢትዮጵያ ይታይ ከተባለ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከአንዳንድ አካባቢዎች ቀድሞ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት አካል የነበረ ነው፡፡ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ጥንታዊ የንግድ መስመር ነው፡፡ የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ማንነትና ቋንቋ ያላቸው ሕዝቦች ሲነግዱ ኖረዋል፡፡ ከውጭም፣ ከውስጥም፣ ከመሀልም፣ ከዳርም ያሉ ሕዝቦች ሲነጋገዱበት የቆየ ጥንታዊ የንግድ መስመር ነው፡፡ በዚህ ንግድ ምክንያት ብዙ መስተጋብር የተፈጠረበት መስመር ነው፡፡ ጦርነትና ግጭትም ኖሮ እንኳን ይህ የንግድ መስመር አይዘጋም ነበር፡፡ ለሁሉም ወገን የሸቀጣ ሸቀጥ ምንጭ ስለሆነ መንግሥታቱ ቢጋጩም ንግዱን አያግዱትም ነበር፡፡ በዚህ ቀጣና ማለትም በምሥራቅ ኢትዮጵያ ካበቡ የንግድ መስመሮች አንዱ ደግሞ የዘይላ ንግድ መስመር ይገኝበታል፡፡ የበርበራ ወደብ ንግድም ቢሆን ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ ነው፡፡ ወደ ታች ወደ ሶማሊያ ሲወረድም ቢሆን ብዙ ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ወደቦች አሉ፡፡ ጂቡቲ ታጁራና ሌሎች ወደቦች ነበሩ፡፡ በምሥራቁ ኢትዮጵያ በንግድ የተነሳ ብዙ መስተጋብር ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ ንግድ ለሕዝቦች መስተጋብር ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ እስልምናም ሆነ ሌሎች እምነቶች በሰፊው በኢትዮጵያ የተስፋፉት በንግድ ነው፡፡ ሲራራ ንግድ የሚባለው ረዥም መንገድ ተሻጋሪ (ካራቫን ትሬድ) ንግድ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አስተሳስረው የያዙ የንግድ መስመሮችን ፈጥረዋል፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ሸቀጥ ከሚገኝበት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከከፋ ጀምሮ ወደ ሰሜን የሚሄድ አንድ ትልቅ የንግድ መስመር ሲኖር፣ ወደ ምሥራቅ ደግም የሚዘረጋ ሌላ መስመር አለ፡፡ ምሥራቁ ኢትዮጵያ ደግሞ የበለጠ ወሳኝ የንግድ በር እንደሆነ ነው የሚገመተው፡፡

አንዳንዴ የቅርብ ጊዜው ሁኔታ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረውን ጦርነት ወይም እንግሊዞች የጀመሩትና የሶማሊያ መንግሥት ተቀብሎ ያስቀጠለውን የኢትዮጵያን ግዛት የመንጠቅ ፖሊሲ በማየት ብቻ፣ ይህ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍል የኢትዮጵያ አይደለም የሚል ግምት የተሳሳተ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ያሉ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ጥያቄያቸውን በቅጡ የተረዳነው አልመሰለኝም፡፡ እኔም በጥናቶቼ ይህንን ነው ለማስረዳት የሞከርኩት፡፡ በተለይ ከደርግ  በፊት የነበሩ መንግሥታት ይህንን ለመመለስ ይቸገሩ ነበር፡፡ በተለይ ጥያቄው የብሔር ጥያቄም ሆኖ ስለሚቀርብ አንዱ ጋ ከተነሳ ሌሎች ዘንድም ይገነፍላል በሚል ሥጋት ጥያቄውን ይጫኑት ነበር፡፡ እዚህ ላይ የመገንጠል ሐሳብ አልነበረም እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን መገንጠልን ምን ያህሉ ነው የሚደግፈው የሚለውን ጥያቄ ያጭራል፡፡ መገንጠሉ ለእነሱ ምን ይጠቅማል የሚለው ብዙ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ኤርትራ ተገንጥላ ለብቻዋ ቆማለች፡፡ ነገር ግን የሶማሌ ክልል ልገንጠል ቢል የሚጠብቀው ትልቅ ሶማሊያ ውስጥ ገብቶ አንድ ትንሽ ግዛት መሆን ነው፡፡ የሶማሌ ክልል ማኅበረሰብ በእኔ ዕይታ ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ሕዝቦች ጋር በሃይማኖትም ሆነ በባህል ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይህንን የሕዝቦች ትስስር የበለጠ ለማጠናከር የተሠራው ሥራ ጥያቄ የሚነሳበት ካልሆነ በስተቀር፣ ሕዝቡ ለረዥም ዘመን የራሱን መስተጋብር ፈጥሮ ነው የቆየው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመቼ ጊዜ ጀምሮ ነው የባህር በር ለማስመለስ ኢትዮጵያውያን ትግል ማድረግ የጀመሩት?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- ኦቶማን ቱርኮች ወደ ቀይ ባህር ከመጡ በኋላ ነው የወደብ ጉዳያችን እየተወሳሰበ የመጣው፡፡ ወደብ አልባ መሆን የጀመርነው ኃያላኑ ወደ ቀይ ባህር መስፋፋት ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ በፖርቹጋል ጀስዊትሶች ምክንያት በሕዝቡ መካከል በገባው የሃይማኖት ልዩነት ሳቢያ ብዙ ቀውስ ተፈጥሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት የውጭ ኃይሎችን በማባረር ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ዝግ አድርገው የቆዩበት ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ ከውጭ የሚመጡ ኃይሎች ሁሌም ችግር ይዘው ነው የሚመጡት የሚል ዕሳቤ ሰርፆ ቆይቷል፡፡ ያም ቢሆን ከዘመነ መሣፍንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት የባህር በር ለማስመለስ ብዙ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ በዘመነ መሣፍንት ባህር በር ለማስመለስ ፍላጎት ቢኖርም አቅም ግን አልነበረም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከመጡ በኋላ ግን በተደጋጋሚ ጥያቄው ሲነሳ ነበር፡፡ ቢቻል በስምምነት ካልሆነም በጉልበት ጭምር ኢትዮጵያ የባህር በር ለማስመለስ መታገል የጀመረችው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያን ቅርፅና ማንነት የለወጠ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድ ነበር፡፡ ይህንን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው ደግሞ በቀይ ባህር ቀጣና የንግድ የበላይነት ለመቆጣጠር ሲፎካከሩ ፖርቹጋሎችና ቱርኮች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ ግጭት እጃቸውን ማስገባታቸው ይታወቃል፡፡ በስተመጨረሻ ግን ጦርነቱ አትዮጵያን ያዳከመ ውጤት ያመጣ ሲሆን፣ ወደቦቿንም በውጭ ኃይሎች ለመነጠቅ እንዳበቃት በጥናትዎ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ውጤት ይዞ በመጣ ጦርነት ዛሬ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ፡፡ ሆኖም የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በታከለበት በዚያ ጦርነት ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ አልከፈለችም?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ የውስጥ  ችግሮችን ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቀደም ሲል ጀምሮ ከግብፆቹ በኩል ይህንን መሰል ፈተና ሲገጥመን ነው የቆየው፡፡ ግብፆችም በኋላ በኦቶማን ቱርኮች ተያዙ፡፡ በዚህ የተነሳ የግብፆቹ ላይ የኦቶማን ቱርኮች ሐሳብ ታከለበት፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በቀይ ባህር ቀጣና የኦቶማን ቱርኮች ተፅዕኖ የገዘፈ ነበር፡፡ ኦቶማኖች ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እያደጉ መጥተው 16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደግሞ እጅግ ኃያል መንግሥት የፈጠሩ ናቸው፡፡ ቱርኮቹ ኤዢያ ማይነር የሚባለውን የንግድ መተላለፊያ ሲቆጣጠሩ ንግዱንም ዘግተውታል፡፡ አውሮፓ በአብዛኛው የሚፈልጋቸውን የቅንጦት ዕቃዎች የሚያገኘው ከሩቅ ምሥራቅ ነበር፡፡ እነዚህ ዕቃዎች በሁለት መስመር ነው ወደ አውሮፓ የሚገቡት፡፡ አንድም በቀይ ባህር ሌላም በፋርስ ባህረ ሰላጤ አድርጎ የተወሰነውን ደግሞ በየብስ ተጉዞ ነው ሜዲትራኒያን የሚራገፈው፡፡ ሌላው ደግሞ ሲልክ ሮድ የሚባለው ከቻይና መካከለኛው እስያን አቆራርጦ ወደ አውሮፓ የሚዘልቀው የሃር ንግድ (ሲልክ ሮድ) የሚባለው የንግድ መስመር ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን በኦቶማን ቱርኮች ተቋርጦ ነበር፡፡ ኦቶማኖች የዘጉትን የንግድ መስመር ለመክፈት ደግሞ በዘመኑ እንደ ፖርቹጋል ያሉ ኃያላን የአውሮፓ አገሮች ትግል ጀምረው ነበር፡፡ አኅጉር አሳሽነት የተስፋፋው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ፖርቹጋሎች ይህንን ችግር ለመፍታት አትላንቲክን አቆራርጠው በደቡባዊ አፍሪካ ዞረውና በህንድ ውቅያኖስ አድርገው ህንድ ለመገናኘት ቻሉ፡፡ ስፓኞች ደግሞ አትላንቲክን ተሻግረው አሜሪካንን አገኙ፡፡ ሁለቱም ግን በወቅቱ ሩቅ ምሥራቅ ሄዶ የአውሮፓ ገበያ የሚፈልጋቸው ሸቀጦችን ጭኖ መምጣትና ማትረፍ ነበር ግባቸው፡፡ ስፓኞች መሬት ይዞ አዲስ ግዛት መሥርቶ ማምረትና መጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ ፖርቹጋሎች ግን ማረፊያ ቦታም ይዘው ንግዱን መቆጣጠር ነበር ዕቅዳቸው፡፡ ይህ የፖርቹጋሎች ፍላጎት ደግሞ ወደ ቀይ ባህር አመጣቸው፡፡ ወደ ቀይ ባህር ሲመጡ ደግሞ አንድ ፕሪስተንጆን የተባለ ክርስቲያን መሪ አለ የሚል የቆየ ታሪክ ሰምተው ነበር የመጡት፡፡ ሆኖም በቀይ ባህር ቀጣና ኦቶማኖች ባላንጣ ነበር የሆኑባቸው፡፡

ለወትሮም ከኦቶማኖች ጋር እየሩሳሌምን ነፃ በማውጣት ግብግብ ውስጥ የነበሩት አውሮፖዎቹ፣ አሁን ደግሞ በቀይ ባህር ቀጣናም ሌላ ግብግብ ፈጠሩ፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በኢትዮጵያ (በምሥራቅ አፍሪካ) ፕሪስተንጆን የተባለውን በቀደመ ትርክት የሰሙትን ንጉሥ አግኝተው ወዳጅነት ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ መጥተውም ከክርስቲያን ነገሥታት ጋር ወዳጅነት ፈጠሩ፡፡ ከዚህ ቀድሞ ግን ኦቶማኖቹ በኢትዮጵያ ከነበሩ ሡልጣኖች ጋር ግንኙነት ጀምረው ነበር፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር በዚህ ቀጣና ደጋፊ ለማፍራት አስበው ነበር የመጡት፡፡ እኛ ግን እርስ በእርስ የበላይነትን ለመቀዳጀት ግጭት ውስጥ ገብተን ነበር የጠበቅናቸው፡፡ አንዳንዴ በረድ ይበል እንጂ በንግድና በሥልጣን የበላይነት የተነሳ ከ200 ዓመታት በላይ የዘለቀ ግጭት በሰሜን ኢትዮጵያ ነገሥታትና በሡልጣኖች መካከል ሲደረግ ነበር፡፡ ሐረር ላይ የተመሠረተው የአዳል ሡልጣንነት ግን ጠንካራ አቅም ፈጠረ፡፡ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመን በኦቶማኖች የሚደገፈው በኢማም አህመድ (አህመድ ግራኝ) የሚመራው የአዳል ሡልጣን ከፍተኛ ድል አስመዘገበ፡፡ በዚህ ጊዜ የሰሜኖቹም መሪዎች የፖርቹጋሎቹን ዕርዳታ ጠይቀው ተዋጉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከውጭ የምንጋብዛቸው ኃይሎች የሚመጡብን ጦሶች ብዙ ናቸው፡፡ ውስጣችን እንደፈለገ ቢሆን አንዱ ሌላውን አሸንፎም ቢሆን በስተመጨረሻ መርገቡ አይቀርም፡፡ የውጭ ኃይሎችን ስንጋብዝ ግን ይዞብን የሚመጣው ጣጣ ብዙ ነው፡፡ ኢማም አህመድ በጊዜው የተሻለ መሣሪያ የሚታጠቁትን መስኬተርስ የሚባሉትን የደቡብ የመንና የቱርክ ተዋጊዎችን ከተጠቀመ በኋላ፣ ሥጋት የለብኝም ብሎ ባሰበ ጊዜ ወዲያውኑ መልሷቸዋል፡፡ ክርስቲያን ነገሥታት ለዕርዳታ የተጠጓቸውም ፖርቹጋሎች ቢሆኑ በስተመጨረሻ ሥጋት ነው የሆኑት፡፡ ነገሥታቱ ወደ ዝግ ፖሊሲ (ክሎዝድ ዶር ፖሊሲ) የገቡትም በዚሁ የተነሳ ነው፡፡ በአብዛኛው ኦርቶዶክስ የነበረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘዋቸው በመጡት በጀስዊትሶች በኩል መሪዎቹን በማጥመቅ ወደ ሕዝቡ ለማውረድ ነበር የሞከሩት፡፡ ንጉሥ ሱስኒዮስ ካቶሊክነትን ተቀብሎ የመንግሥት ሃይማኖት ሲያደርገው ወዲያው የእርስ በእርስ ጦርነት ተፈጠረ፡፡ ወደ 5,000 ሰው ያለቀበት ከባድ ግጭት ነው የነበረው፡፡ በዚህ የተነሳ አፄ ፋሲለደስ አባቱን ተክቶ ንጉሥ ሆነ፡፡ የውጭ ኃይሎች ሲመጡ ኢትዮጵያ ጤና ታጣለችና እንዳይገቡ ብሎ በር የመዝጋት ፖሊሲን አወጀ፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬስ የውጭ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- ያው ነው በተመሳሳይ ጦስ ይዘው ነው የሚመጡት፡፡

ሪፖርተር፡- ዘይላ ከዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በስም የሚጠቀስና ኢትዮጵያውያን ብዙ ሲጠቀሙበት የቆየ መሆኑን በጥናቶች ጠቅሰዋል፡፡ ዘይላ ወደብ የኢትዮጵያውያን ነው ሊባል ይችላል?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያሉት ወደቦች በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ ስንል ሰፊ ሕዝብ ስላለው አካባቢ ነው የምናወራው፡፡ በወቅቱ ግን ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ወዘተ. ተብለው የሚገለጹ አገሮች አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ የፑንት ምድር ስንል ስለኢትዮጵያ ነው ወይስ ስለሶማሊያ የቱን በተመለከተ ነው የምናወራው የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ላንድ ኦፍ ፑንት ሲባል ኢትዮጵያንም ሶማሊያንም አካባቢውንም የሚያያይዝ ነው፡፡ ምናልባት አፍሪካ ቀንድ ብለን ካላወራን በአሁኑ የአገሮች ማንነት ልንሰይመው በጣም ያስቸግራል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩት ስያሜዎችም ሆነ የሚያካልሉት ድንበርን አሁን ባለው ላይሠራ ይችላል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ትተን ዘይላን ከወሰድን አዱሊስ ከቀረ በኋላ በዛጉዌዎችና ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሙበት የነበረ ወደብ ነበር፡፡ ያን አካባቢ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አስቸጋሪ ነበር፡፡ የዳር አገሮች የሰሜን ኢትዮጵያ ነገሥታት ከሚያስተዳድሯቸው አካባቢዎች በባህል ለየት የማለት ጠባይ አላቸው፡፡ አብዛኛው የአካባቢው የኑሮ መሠረት አርብቶ አደርነት ነው፡፡ በመሀል አገር ከተለመደው ግብርና የተለየ ነው፡፡ ለደገኛው ቀርቶ እዚያም ለሚኖረው ማኅበረሰብ ቆላማነቱ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በቋሚነት ዘይላን ከማስተዳደር ይልቅ በየተወሰነ ጊዜ እየሄዱ ማስገበርን ነገሥታቱ ይመርጡ ነበር፡፡ በቋሚነት ባታስተዳድርም በየተወሰነ ጊዜ እየሄድክ ግን ግብር መቀበል አለበህ፡፡ ያ የንግድ መስመር በነፃነት እንደሚሠራ ማረጋገጥም አለብህ፡፡ ንጉሥ ይስሃቅ ለምሳሌ በቀጥታ ዘይላ ድረስ ሄዶ ተቆጣጥሮ ያውቃል፡፡ ሆኖም በቋሚነት ለመግዛት ሳይሆን አስገብሮ የመመለስ ነገር ነበረው፡፡ በዚያ አካባቢ ባሉ ሡልጣኖች መካከል የኃይል የበላይነት ለመጨበጥ የሚደረገው ፉክክር ከፍተኛ ነበር፡፡ የሐረር ሡልጣን አለ፣ የዘይላ ሡልጣን አለ፣ በዚያ አካባቢ ሌሎች ሡልጣኖች አሉ፡፡ ኢማም አህመድ ሲመጡ እኮ እነዚህን ሡልጣኖች የማተስተባበር ሥራ ነው የሠሩት፡፡

ሪፖርተር፡- ቅኝ ገዥዎቹ ከተተኩ በኋላም ኢትዮጵያ ወደቦቿን ለማስመለስ ብትታገልም አልተሳካም፡፡ ለምን?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- ቱርኮችን የተኩት ግብፆቹ ነበሩ፡፡ ግብፆቹ ደግሞ የቀይ ባህር ወደቦችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም መቆጣጠር የግድ ነው ብለው ከመሪያቸው ከመሐመድ ዓሊ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመያዝ ሲንቀሳቀሱ ነበረ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1820 ሥልጣን የያዘው የዘመናዊት ግብፅ መሠረት የሚባለው መሐመድ ዓሊ ሱዳንን ይዞ ነበር፡፡ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ለመስፋፋት ሙከራ ሲያደርግ ነው የቆየው፡፡ ልጁ ከዲቭ ኢስማኤል የሚባለው መሪ ደግሞ ይህንኑ ኢትዮጵያን የመውረር ፖሊሲ በተለያዩ መንገደች አስቀጥሎታል፡፡ ስዊዝቦይ ከተገነባበት እ.ኤ.አ. ከ1869 በኋላ ግብፅ እጅግ ሀብታም ሆናለች፡፡ አውሮፖዎቹ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳላት አውቀው ጠንካራ ግንኙነት መሥርተዋል፡፡ ከዲቭ ኢስማኤል አውሮፓዊያኑን ቀጥሮ ነው ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣው፡፡ በሦስት አቅጣጫ ለወረራ ተሰማራ፡፡ ወደ መረብ ምላሽ ወይም ወደ ኤርትራ፣ ወደ ሀውሳ ዛሬ አፋር ወደ ምንለው፣ እንዲሁም ወደ ሐረር መስመር ነበር ለወረራ የመጣው፡፡ ከአንዱ በስተቀር በሁሉም ተሸንፏል፡፡ ግብፆቹ በአፄ ዮሐንስ ተሸንፈዋል፣ እንዲሁም በታላቁ የጦር መሪ በራስ አሉላ ተሸንፈዋል፡፡ በሀውሳ ሕዝብ ታላቅ ተጋድሎም በአፋር በኩል ያደረጉት መስፋፋት ከሽፎባቸዋል፡፡ በሐረር በኩል ግን ከዘይላ ዘልቀው ሐረር ከተማ ድረስ ገብተው ቢያንስ ለአሥር ዓመታት አስተዳድረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት በኢትዮጵያ ላይ ለመስፋፋት የውጭ ጠላቶች ያለ ማቋረጥ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው፡፡

ዘመነ መሣፍንት አክትሞ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ጠንካራ አገር የመፍጠር ጥረት የጀመሩት አፄ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይሎች መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤል ድረስ ዘምተው እየሩሳሌምን ከቱርኮች ነፃ የማውጣት ፍላጎት ሁሉ ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ እሳቸው ወደ ጀመሩት አንድነት የመፍጠር ጥረት ለመቀላቀል ከማይፈልጉ የጦር መሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት ለማድረግ በመገደዳቸው መንግሥታቸውን አዳክሞታል፡፡ ቴዎድሮስ ይከተሉት የነበረው የአስተዳደር ሥልት ዕረፍት የለሽ ተቃውሞ ፈጥሮባቸዋል፡፡ መሣሪያ ለማግኘት ብለው ያሰሯቸው አውሮፓውያን ደግሞ ከእንግሊዝ ጋር ጦርነት ውስጥ የከተቷቸው ሲሆን፣ ረዥሙ ሕልማቸው በጄኔራል ናፒር ዘመቻ በአጭር ተደምድሟል፡፡ ቀጥሎ የመጡት አፄ ዮሐንስ ደግሞ እንደ ራስ አሉላ ያሉ ጠንካራ የጦር መሪዎች ነበሯቸው፡፡ ራስ አሉላ ቀይ ባህርን ነፃ ለማውጣት፣ በተለይም መረብ ምላሽ መመለስ አለበት በሚል የታገሉ ሰው ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን የገጠሟት ፈተናዎች እየተወሳሰቡ ነበር የሄዱት፡፡ ግብፆች በዓባይ ላይ ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ነበር ወደ ኢትዮጵያ መስፋፋት የጀመሩት እንጂ ቅኝ ገዥነትን አስበው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ በሒደት እነሱ ራሳቸው የእንግሊዝ ቅኝ ተገዥ ሆነዋል፡፡ አሁን ከግብፆቹ ጋር ያለው ጉዳይ በዚያ የሚያቆም ብቻ ሳይሆን፣ ከቅኝ ገዥዎቹ እንግሊዞች ጋር የሚያገናኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የግብፅ ብቻ ሳይሆን የሱዳንም ጉዳይ የእንግሊዞቹ ሆኗል፡፡ እንግሊዞቹ ከዚያ ቀድመው የመንን ይዘዋል፡፡ ከኤደን እየተነሱ ሶማሌላንድንም ወረዋል፡፡ ሶማሌላንድን የያዙት የመን ለሚገኘው ሰፊ ኃይላቸው የበግና የፍየል ወይም የሥጋ ከብት አቅርቦት እንደ ልብ ለማግኘት ነበር፡፡ ሆኖም በሒደት ብሪቲሽ ሶማሌላንድ ብለው ያዙት፡፡ በቀጣናው ፈረንሣዮች መጥተዋል፡፡ ጣሊያኖችም ማንዣበብ ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቱርክን ችግር ሳትቋጭ፣ የግብፆቹን ጦስ ሳትወጣ፣ በእነሱ እግር ደግሞ አውሮፓውያኑ ተተክተው ዙሪያዋን ከበቧት፡፡ በውስጥ ከዘመነ መሣፍንት ጀምሮ አንድ ለመሆን ኢትዮጵያ የምታደርገው ትግል በራሱ ፈታኝ ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስም በዚህ ተፈትነዋል፡፡ የሸዋውን አፄ ምኒልክንና የጎጃሙን ራስ ተክለ ሃይማኖትን በሥልጣን ተቀናቃኝነት ይጠራጠሯቸው ነበር፡፡ ከጣሊያንና ከሌሎች የውጭ ጠላቶች ጋር ጠረፍ ለማስለቀቅ ሲዘምቱ የእሳቸውን ንግሥና እንዳይነጥቁባቸው ይሠጉ ነበር፡፡ በዚያ ላይ በጎረቤት ሱዳን ደርቡሽ የሚባሉት መሃዲስት ኃይሎች ተነስተዋል፡፡ መሃዲስቶቹ ሱዳንን ከግብፅና ከእንግሊዝ ጭምር ቅኝ ተገዥነት ነፃ ለማውጣት ነበር የሚታገሉት፡፡ አፄ ዮሐንስ በዚህ ፈታኝ ወቅት ወደብ ለማስመለስ ብለው ከእንግሊዞቹ ጋር መስማማታቸው ደግሞ ሌላ ቀውስ ይዞ መጣ፡፡ በምፅዋ በኩል መተላለፊያ አገኛለሁ ብለው ነበር የተስማሙት፡፡ የሕይወት ስምምነት (ሕይወት ትሪቲ) የተባለውና እ.ኤ.አ. በ1884 ከእንግሊዞች ጋር የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ የወደብ ጥያቄ ለመመለስ የተሞከረበት መንገድ ነበር፡፡ በቀይ ባህር ወደቦች የሠፈሩትና ኢትዮጵያን ዙሪያዋን የከበቧት አውሮፓዊያን ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት እንዳትመሠርት ሲሉ የምትፈልጋቸውን ሸቀጦች እንዳታስገባ ይከለክሉ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ወደብ ከሌላት ራሷን ለመከላከያ የጦር መሣሪያ ማስገባት ስለማትችል፣ አፄ ዮሐንስ ይህንን ለመለወጠጥ ስምምነቱን ፈረሙ፡፡ እንግሊዞቹ አፄ ዮሐንስ በሱዳን በመሃዲስቶች ተከቦ የሚገኘውን የግብፅ ጦር በኢትዮጵያ ግዛት በኩል ካስወጡላቸው ቦገስ የተባለውን የመረብ ምላሽ መሬት መመለስን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያ በምፅዋ ወደብ በነፃነት እንድትጠቀም ለመፍቀድ ቃል ገብተው ነበር፡፡  ራስ አሉላ በስምምነቱ መሠረት ሱዳን ገብተው ኩፊት በሚባል ቦታ መሃዲስቶችን አሸንፈው፣ የእንግሊዝ ጄኔራል የሚመራውን የግብፅ ጦር ከእነ መሣሪያው በኢትዮጵያ በኩል እንዲያልፉ በማድረግ የኢትዮጵያን ውለታ ተወጡ፡፡ በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል ብትፈጽምም እንግሊዞቹ ግን አላከበሩም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ከፈጸሟቸው የመጀመሪያ ክህደት አንዱ ሊባል ይችላል፡፡ ቦገስን መልሰው ምፅዋን ግን እ.ኤ.አ. በ1885 ለጣሊያን በመስጠት ወጡ፡፡ ከዚያ ቀድመው አሰብን ይዘው የቆዩት ጣሊያኖች አሁን ደግሞ ምፅዋን ደገሙ፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ኢትዮጵያ መሬት መስፋፋትም ቀጠሉ፡፡ ኢትዮጵያ ወደቦቿን ማስመለስ ሳትችል ብዙ ጠላት አተረፈች፡፡ የውጭ ኃይሎች አንዱ ሌላውን እየተካ የኢትዮጵያ የወደብ ማስመለስ ጉዳይ እየተወሳሰበ ነው የሄደው፡፡ በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ጥያቄም ሥጋት ላይ ወደቀ፡፡ ከ1880ዎቹ በኋላ ኢትዮጵያ ወደቦቿን ለማስመለስ የምታደርገው ጥያቄ ቀርቶ በቦታው በቅኝ ገዥ ላለ መወረር የሚደረግ ትግል ተተካ፡፡ ጣሊያኖቹ ሶማሊያን ከያዙ፣ የቀይ ባህር ወደቦችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ኢትዮጵያ ቅኝ ትገዛለች/አትገዛም የሚለው ጥያቄ አፍጦ መጥቷል፡፡ ሊቢያን ለመቆጣጠር የሚጋደሉት ጣሊያኖች ሰፊ ግዛት የመውረር ረሃብ ይዘው ነው ወደ ኤርትራም የመጡት፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዘይላ ወደብን በሀውድ የግጦሽ መሬት ለመለወጥ የተደረገ ትግልም ነበር፡፡ ለምን አልተሳካም?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- ብዙ ምክንያቶች ናቸው ያሉት፡፡ የሀውድ ዘይላ ድርድር በዋናነት በእንግሊዞች ይፈለግ ነበር፡፡ እንግሊዞቹ የሶማሌላንድ አስተዳዳሪዎች እንደ መሆናቸው ለከብቶች ግጦሽ ለምለም የሆነውን ሀውድ የተባለውን የኢትዮጵያን መሬት ፈልገውት ነበር፡፡ ለስድስት ወራት ለም የሚሆንና ውኃ ሳያስፈልግ ከብቶች የሚቀልብ ነው፡፡ የሀውድ መሬትን ከኢትዮጵያ በመውሰድ የሶማሌላንድ በማድረግ በምትኩ ዘይላን ወደብን ለመስጠት ይፈልጉ ነበር፡፡ በሶማሌላንድ ሀበር አወልና ሀበርዩኒስ የሚባሉትን ጨምሮ አምስት የጎሳ መሠረቶች አላቸው፡፡ ሰሜናዊው የሶማሌላንድ ክፍል ትንሽ ግብርና የሚሠራበት ቢሆንም፣ አብዛኛው ማኅበረሰብ በአርብቶ አደርነት ነው የሚኖረው፡፡ በአብዛኛው መሬቱ የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ወደ የሚገኘው የሀውድ አካባቢ ለግጦሽ ከብቶቻቸውን ይዘው በመምጣት ለስድስት ወራት በዚያ አካባቢ ነው ብዙዎች የሚያሳልፉት፡፡ የሀውድ መሬት ወደ አንድ ሚሊዮን ከብቶችን የሚቀልብ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች በዚህ ድንበር መመላለስና ኢትዮጵያ ዘልቆ ለስድስት ወራት መቆየት በሁለቱ አገሮች መካከል የሉዓላዊነት ጥያቄ የሚፈጥር ነበር፡፡ መሬቱን ወደ ሶማሌላንድ ለመቀላቀል የተለያዩ አማራጮች ቀረቡ፡፡ አሜሪካ ከሩሲያ ላይ አላስካ ግዛትን በገንዘብ እንደገዛችው ሁሉ እንግሊዞቹ ሀውድን ለመግዛት ፈለጉ፡፡ በሊዝ መያዝንም ጨምሮ በልዋጭ ዘይላ ወደብን እንስጥ የሚል አማራጭ አቅርበዋል፡፡ ዘይላ ወደብን ብቻ ሳይሆን ኮሪዶርም ለመስጠት ዕቅድ አቀረቡ፡፡ ኢትዮጵያ ሀውድን በልዋጩ እንድትሰጣቻ ፈልገው ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ የወደብ አማራጭ ስትፈልግ የነበረችው ኢትዮጵያ በዚህ መሬት ልዋጭ ዘይላ ወደብን ለማግኘት የሚያስችለውን ዕቅድ ደግፋዋለች፡፡ ይሁን እንጂ ሐሳቡ ብዙ መሰናክልም ነበረበት፡፡ የአካባቢው ዒሳ ማኅበረሰብና ሌሎች ጎሳዎች የሚፈልጉት ነገርም በዕቅዱ መካተት ነበረበት፡፡ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በግጦሽ መሬትና በውኃ ጉድጓዶች መጋጨት፣ እንዲሁም ከብትና ሌላ ሀብት መነጣጠቅ ሥር የሰደደ ችግር ነው፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ከዘይላ ወደብ በቅርብ ርቀት ባለችው ጂቡቲ የሠፈረው የፈረንሣይ ኃይልም ፍላጎቱ መታወቅ ነበረበት፡፡ ጉዳዩ ከእንግሊዝና ከኢትዮጵያ ውጪ ሦስተኛ ወገን (ፈረንሣይም) ሊገባበት የሚችል ነበር፡፡

የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ እንደ ዘይላ ዓይነት ወደቦችን በልዋጭ ለማግኘት የፈለገች ቢሆንም፣ የእንግሊዞቹ ጥያቄ ደግሞ መወሳሰብ ጀመረ፡፡ እንግሊዞቹ ኦጋዴንን በሙሉ ስጡን አሉ፡፡ ከዚያ ደግሞ ሀውድን በሙሉ ስጡን ብለው መጡ፡፡ ፈረንሣዮችን የማሳመን ሥራ ኢትዮጵያ ብቻዋን ትሥራ ይሉም ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ስምምነቱ ሳይፈጸም ብዙ መጓተት ተፈጠረ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት በመጡት የ1950ዎቹ ዓመታት አፍሪካውያን መነቃቃትና መታገል ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1956 ሱዳን ከቅኝ ተገዥነት ነፃ ስትወጣ ጋና በ1957 ተከተለች፡፡ አፍሪካውያኑ ነፃ መውጣታቸው ግልጽ እየሆነ ሲመጣ ኤርትራም ነፃ ስትወጣ ወደ እናት አገሯ ኢትዮጵያ ትመለሳለች የሚለው ተስፋ እየጎላ መጣ፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች በዚህ የተነሳ የዘይላ ወደብን በሀውድ የመቀየሩ ፍላጎታቸው እየቀነሰ በመሄዱ ትኩረታቸውን ኤርትራን ማስመለስ ላይ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሶማሌላንድን ለቀው ለመውጣት የተቃረቡት እንግሊዞች ቢያንስ የሀውድ መሬትን የሶማሌላንድ አድርገው ለመውጣት ስምምነቱን በጣም እየፈለጉት መጥተው ነበር፡፡ የእንግሊዞቹ ፍላጎት ቢጨምርም ኢትዮጵያ ግን እሱን ቸል ብላ ወደ ኤርትራ ነበር የዞረችው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደ ታሪክ ባለሙያ ሀውድን ሰጥቶ ዘይላን ከማግኘት ይልቅ ኤርትራን ማስመለስ የተተኮረበትን አጋጣሚ እንዴት ያነፃፅሩታል?

ሳሙኤል (ዶ/ር)፡- በማንኛውም መንገድ የባህር በር ማግኘቱ በዚያን ጊዜ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ ሆኖም ሀውድን የመሰለ መሬት ለዘይላ ሲባል መስጠት ያዋጣ ነበር ወይ የሚለው ንፅፅራዊ ጥያቄ መቅረቡ ተገቢነት አለው፡፡ ዘይላ ወደብ በወደብነት ጠቀሜታው ሲታይ የሚበቅል አለት (ኮራል ሪፍ) ያለበትና ትልልቅ መርከቦችን ወደ ጠረፍ አስጠግቶ ማቆም የሚያስቸግርም ነበር፡፡ ሆኖም ዘይላን ማግኘታችን ቢያንስ መከራከሪያ የሚሆን ሕጋዊ የባህር በር ያስገኝልን ነበር የሚለውን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን የባህር በር ፍላጎታችንን በማስታገሱ ረገድ ዘይላ የተሻለ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት ይመስላል ወደ ኤርትራ ትኩረት የተደረገው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...