Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዘንድሮም ሰዓቱ የጥፋት አፋፍ ላይ ናችሁ ይላል!!

ዘንድሮም ሰዓቱ የጥፋት አፋፍ ላይ ናችሁ ይላል!!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አንድ ሰዓት አለ፡፡ ዱምስደይ ክሎክ ይባላል፡፡ የምፅዓት ቀን፣ የዕለተ ደይን፣ ወይም የቂያማ ቀን ሰዓት እንደ ማለት ነው፡፡ የተፀነሰውም፣ የሚቆጥረውም ዓለማችን ታይቶ በማይታወቅ፣ አምሳያ በሌለው አደጋ ውስጥ መውደቁ ነው፡፡ ሰባ ሰባት ዓመት የሞላውን ይህንን ሰዓት አምጦ የወለደው የማንሃተን ፕሮጀክት የተባለው የኑክሌር መሣሪያን የፈጠረው የምርምር ፕሮግራም ተሳታፊ የነበሩት እነ አልበርት አይንስታይን፣ ኦፕንሃይመር ከመሳሰሉ የጠቀሰው የማንሃተን ፕሮጀክት ሳይንቲስቶችና ኢንጂነሮች ላይ የደረሰው የጥፋተኝነት ስሜትና ፀፀት ነው፡፡ የሰው ልጅ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ፣ እንደ እሳት ያገኘው/የደረሰበት ግኝት እንደ እሳት፣ ከእሳትም በላይ የማይከላከለው፣ በፍጥርጥሩ ምክንያት መከላከል የማይችለው፣ ስለዚህም ‹የጫረው እሳት ሲበላው› ታያቸውና ይህንን መንገር፣ ነጋሪ መሆን፣ ማስጠንቀቅ፣ ማስተማር ጀመሩ፡፡ የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ቡለቲን የሚባል ልሳን አቋቁሙ፡፡ በዚህም የኅትመት ውጤት አማይነት በሳይንስ፣ በጥናትና በምርምር በተደገፈ ጥናት ገደል አፋፍ ላይ፣ ራስን በራስ ማጥፋት ሒደት ውስጥ የት ላይ እንዳለን በየዓመቱ ሲያውጁ እነሆ ሰባ ሰባት ዓመት ሆናቸው፡፡ ከ1947 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ በእያንዳንዱ ዓመት መባቻ ወር ላይ ጃንዋሪ መጨረሻ ሳምንት ውስጥ የአቶሚክ ሳይንስ ቡለቲን በሰዓቱ የዓለማችንን ደኅንነት ወይም ፀጥታ (ሴኪዩሪቲ) ይለካል፡፡ መጀመሪያ በተለካበት ጊዜ በ1947 ለመንፈቀ ሌሊት ማለትም ለጥፋት/ለዕልቂት ሰባት ደቂቃ ጉዳይ ነበር፡፡ ዘንድሮ ሰዓቱ የሚያሳየው 90 ደቂቃ ጉዳይ ላይ ነው፡፡  

ወደ ያዝነው ዋናው ጉዳይ ዘልቀን በምንገባበት በዚህ አጋጣሚ የተቋም ግንባታን፣ የሲቪክ ምኅዳርን፣ የሕዝብ ንቁ ተሳትፎንና ያገባኛል ባይነትን የሚመለከት አንድ እኛ ፍጥርጥራችን አድርገን ገና የማናውቀውን፣ የታደሉትና ሻል ያለ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮች ኅብረተሰቦች ባህል ሆኖ ሲነገር እንኳን ከእነ ሙሉ ክብሩና ማዕረጉ፣ ወጉ አጣጥመን የማናደንቀውን አንድ ነገር ላንሳ፡፡ የዱምስደይን፣ የዕለተ ደይን፣ የቂያማ ቀንን ተምሳሌታዊ ሰዓት የፈጠረው፣ በዚህም አማካይነት የዓለምን ሕዝብ፣ የምድራችንን የራሱን፣ የሥልጣኔያችንን የልብ ትርታ ብቻ ሳይሆን፣ ሳይንሱ ቫይታል ሳይንስ (Vital Signs) ወይም ትዕምርተ ሕይወት የሚላቸውን (እንደ የሰውነት ሙቀት፣ የልብ ትርታ፣ የአተነፋፈስ ምጥመት፣ የደም ግፊትን የመሳሰሉ) ወሳኝ ጉዳዮቻችንን የሚለካው፣ ይህንንም የሚያስታውቀውና የሚያስተጋባው በመላው ዓለም ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ መድረኮችን ሚዲያ ውስጥ የማይናቅ ሥፍራ የተጎናፀፈው ይህ የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ቡለቲን ማለት የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ የፕሬስ ድርጅት ነው፡፡ ሰዓቱ ደግሞ በየዓመቱ የሚወጣ ምን አለ? ምን ይል ይሆን? ተብሎ የሚጠበቅ፣ በመላው ዓለም ያሉ ስም ያላቸው ሌሎች ሚዲያዎች ርዕሰ አንቀጽ የሚጽፉለት አሳታሚ ተቋም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለምሳሌ ታይም (TIME) የሚባለው የአሜሪካ ሳምንታዊ መጽሔት (ከ2020 ወዲህ በየሁለት ሳምንት ሆኗል) ከአንድ መቶ ዓመት በላይ የኖረ የፕሬስ ውጤት ነው፡፡ ይህ መጽሔት ከሁሉም በላይ የሚታወቀው፣ ወይም ያቋቋመው ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1927 ጀምሮ እስካሁን ድረስ የዓመቱ ሰው ብሎ የሚሰይምበት፣ ‹‹ውሳኔ›› ወይም ‹‹ፍርድ›› ወይም ‹‹ምርጫ›› ውጤቱን የሚያሳውቅበት የዓመት አንድ ጊዜ ኅትመት (ቁጥሩ) ነው፡፡ በአጭሩ ‹‹ፐርሰን ኦፍ ዘ ይር›› የሚባለው በዓመት አንድ ጊዜ የሚወጣው የታይም መጽሔት የሚያወጣው ሰው፣ ወይም ቡድን፣ ወይም ሐሳብ ወይም ነገር በዓመቱ ውስጥ በክፉም በደግም (በክፉም ወይም በደግም) ተፅዕኖ አሳድሯል ተብሎ የሚበየንለት ነው፡፡ የ1935 የዓመቱ ሰው ሆነው መጽሔቱ የሽፋን ገጽ ላይ የወጡት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ ከዋናው የሚዲያ/የፕሬስ ሥራና ተግባር የተለየ፣ ነገር ግን ዋናውን ሥራ የሚያራምድ የተቋቋመና ለዚህን ያህል ጊዜ የዘለቀ የ‹‹ሽልማት›› ሥርዓት መፍጠር፣ ከዚህም ጋር አብሮ የሚሄድ አጣማጅ አቻ በሚስጥር የተጠበቀ ሒደት ማቋቋም፣ ይህንንም ከዚህ ውጪ ከሚገኙ የሌሎች የውጭ ተቋማት፣ ድርጅቶች ግምገማ፣ የሕዝብ አስተያየት መለኪያ ጋር አቻችሎ በነፃነት መዝለቅ እኛን ለመሰለ የፕሬስ ነፃነትና ኃላፊነት ገና እንግዳና ባዳ ለሆነበት አገር ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ የሚደነቅ ወግና ባህል ነው፡፡ እና ይህንን የመሰሉ የመታመንና የመከበር ቦታ የተሰጠው ሰዓቱን የመለካት፣ ሰዓቱ ስንት ነው የሚለውን የህልውና ጥያቄ በዕውቀትና በተቋቋመ አሠራር የመመለስና አፍታትቶ የማብራራት የሥራ ድርሻ ያገኘው፣ ለሰባ ሰባት ዓመትም የተዋጣለት ሥራ ሲሠራ የኖረው የመንግሥት ድርጅት አይደለም፡፡ በግሉ ዘርፍ ውስጥ የሚመደብ የሚዲያ ተቋም፣ አሳታሚ ድርጅት ነው፡፡

ሰዓቱ የሠራ አካላታችንን እየመረመረ የምንገኝበትን፣ አሁን ደግሞ እየከፋ እየባሰበት የመጣ የሞት የሽረት ሁኔታችንን የምርመራ ውጤት የሚናገረው፣ አምጦ የወለደውን የኑክሌር አደጋ በሚመለከት ረገድ ብቻ አይደለም፡፡ አሁንም መጥፊያችን የኑክሌር የጦር መሣሪያ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዓቱ ተረባርበው ሥልጣኔን፣ የሰው ልጅን ከእነ ሥልጣኔው የሚያጠፋ ለዕልቂት የሚዳርጉ ሌሎች አደጋዎች አሉ ይላል፡፡ ኢንቫይሮሜንታዊ ጥፋት ሌላው መጥፊያችን ነው፡፡ የዴሞክራሲ መሸርሸር፣ ‹‹ትሻል››ን ትቶ ወደ ‹‹ትብስ›› እየተደጣደፉና እየተንደረደሩ መንጎድ ራስን በራስ የማጥፋት የተያያዝነው የጉዞ አቅጣጫ ነው፡፡

በአጠቃላይ የሥልጣኔያችንን፣ የሰው ልጅን ህልውና እያጣደፈና እያዳፋ ወደ ጥፋት የሚያራውጠው ሰው ማዘዝ ያልቻለበትንና ለሕግ ሊያስገዛው ያልቻለውን መሣሪያ መታጠቁ ብቻ አይደለም፡፡ የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ስለሚባለው ስለጄኖሳይድ ሲወራ ሰምተናል፡፡ አሁን የምንነጋገረው ከዚህ የባሰ ስለሆነው ስለኦምኒሳይድ (Omnicide) ነው፡፡ ጄኖሳይድ የእኛ ሕግ በአማርኛ ‹‹ዘርን ማጥፋት›› ብሎ የሚጠራው በዚያ ሕግ የተደነገገው ዓይነትና እዚያው ውስጥ የተካተቱትን አለባዎች የሚያሟላው ነው፡፡

ኦምኒሳይድ ሁሉንም አካትቶ ጨርሶ ማጥፋት ነው፡፡ ‹‹The total extinction of the human species as a result of human action.›› የሚባለው ነው፡፡ ይህንን ጠፍቶ ማጥፋትና አጥፍቶ መጥፋት መፍትሔ ያለሽ ያስመሰለው ዓለም፣ በተለይም ዋና ዋናዎቹ አፄ በጉልበቴዎች ለሕግ ተገዥ አለመሆናቸው፣ ዓለም የሚሠራው እንደ ማፍያ መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ሌሎቹ በየዘርፉ የጠቀስናቸው ችግሮች ተረባርበው አባብሰውታል፡፡ የምድራችን ለሕይወት ምቹ ሆኖ መቀጠልን አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡ ይህንን የሚያሳዩ አንዳንድ ጠቋሚ ነገሮችን እናሳይ፡፡

የሰው ልጅ ከዘመን ዘመን፣ ከማኅበራዊ ሥርዓት ወደ ማኅበራዊ ሥርዓት እየተሸጋገረ፣ እየተስፋፋና እየተመነደገ በመጣ ቁጥር ራስ ወዳድና ስግብግብ ፍላጎቱ ምድሪቱን እያራቆተ፣ ራሱንም ሌላውንም ህያው ነገር ሁሉ የመጥፋት አፋፍ ላይ አድርሷል፡፡ እዚህ አደገኛ ደረጃና ውጤት ላይ ያደረሱት ድርጊቶች ደግሞ ብዙና ተወራራሽ ናቸው፡፡

ሰው የራሱን ቁጥር ያለ ልክ እያበዛ ወደ ዋልታዎች እስከ መቅረብና በባህር ላይ ተንሳፍፊ ቤት ሠርቶ እስከመኖር ድረስ ምድሪቱን ወሯታል፡፡ በዚህም የሌሎች ህያው ነገሮችን ከዕፅዋት እስከ እንስሳት ድረስ ያሉትን መድረሻ አሳጥቷል፡፡ ጠንቀኛነቱ በሥፍራ ማጣበብ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከሚያስፈልገው በላይ የሚያመርትና የሚያጋብስ፣ ከሚበላው በላይ የሚያሰናዳ ባለአዕምሮ (አዕምሮ ያለው) አንበጣ ሆኗል፡፡ በኑሮው የሚፈጥረው ቆሻሻና የመብል ትራፊ ሁሉ የምድሪቱና የተፈጥሮ ችግር ሆኗል፡፡ አግበስብሴነቱና አባካኝነቱ፣ ንፉግነትና ጨካኝነት ባለው ማኅበራዊ ሥርዓት ውስጥ የሚካሄድ እንደመሆኑ የሀብትና የቴክኖሎጂ ባለቤትነቱ በጥቂቶች መዳፍ ውስጥ እየገባ ብዙዎች ደግሞ ሀብት የለሾች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የሀብት የለሽነቱ ደረጃ በከፋ ድህነትና በጥንታዊ አኗኗር ውስጥ የመዳከርና በረሃብ የመርገፍም ፈርጆች ያሉት ነው፡፡ ስለዚህም የሚደርሰው ጥፋት ከተቀናጣ ድሎትም አኳያ፣ በሞትና ሕይወት መሀል ሆኖ በጥንታዊ መንገዶች ከመቅበዝበዝም ማዕዘን ጭምር ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ቅጥ አምባሩ የጠፋ ልዩ ልዩነቱ የጎላና ጫፍ የረገጠ በድህነት አዘቅት ውስጥ መዘፈቅንና በሀብትና በድሎት ‹‹ጭምልቅልቅ›› ማለትን (ስለቃል አመራረጡ ይቅርታ) ደግሞ ዘንድሮ ጃንዋሪ ላይ የወጣው የኦክስፋም አዲሱ የአለመስተካከል እኩል አለመሆን ወይም ‹‹ኢንኢኳሊቲ›› ሪፖርት አጋልጦታል፡፡ ሪፖርቱ የወጣበት ጊዜና አጋጣሚ ደግሞ ራሱ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ በየዓመቱ በዚህ ወር (ሪፖርቱ በወጣበት በጃንዋሪ – ታኅሳስ/ጥር) ወር ውስጥ ስዊዘርላንድ የሸርተቴ መዝናኛ (የክረምት ስፖርት) ቦታ በሆነ ቦታ ላይ ሀብታሞችና ጉልበተኞች ተሰብስበው ይወያያሉ፡፡  የዳቮስ ስብሰባ ይባላል፡፡ ከዚህ ቅንጡና ቅምጥል ስብሰባ ጋር እንዲገጥም ተደርጎ የወጣው የኦክስፋም ሪፖርት አምስቱ የዓለማችን ቢጠሯቸው የማይሰሙ ሀብታሞች፣ እ.ኤ.አ. ከ2010 ወዲህ ባለው የአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሀብታቸውን ከእጥፍ በላይ አሳድገዋል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ወደ አምስት ቢሊዮን የሚጠጉ ድሆች ይበልጥ ያጡ የነጡ፣ መናጢ ድሆች ሆነዋል፡፡ በዚህ ፍጥነትና አካሄድ ዓለም የመጀመሪያውን ትሪሊዮነር በዚህ አሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚያሳይ ሲሆን፣ በአንፃሩም ድህነትን በቃ ለማለት ሁለት ሴንቸሪ  (ሁለት መቶ ዓመት) ይወስዳል ብሎናል፡፡

የሰው ልጅ በእርስ በርሱና በምድሪቱ ላይ የሚያካሂደው ማራቆትና መራቆት ያለበት ግብግብ በኃይልና በጉልበት መንገድም ሲከናወን የኖረ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሲካሄድ የኖረውና የሚካሄደው የኃይል ብልጫ እሽቅድምድም ኬሚካልን፣ ሕይወትንና የደቂቀ ቁስን ኑክሌራዊ ቅንብር ወደ ጅምላ ጨራሽ/ጅምላ ፍጅት ጦር መሣሪያ እስከ መቀየርም የደረሰ ነው፡፡ የሰው ልጅ መሬትን ያጣበበ ተስፋፊነት ከዚህ በፊት ካልቀረባቸው ህያው ነገሮች፣ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች ጋር የመነካካት ዕድሉን በማስፋፋቱና የምድርን አየር ንብረት እየለወጠ በሚገኘው በካይ ተፅዕኖው የህያው ነገሮችን የአኗኗር ባህርይ ከደቂቅ እስከ ግዙፎቹ እየቀየረ/እያስቀየረ መጥቷል፡፡ ምድሪቱ የተጀቦነችበትን ኡዞናዊ ቡልኮ እየሳሳም፣ በብክለት ክምችት እያጣበበም ከዚህ በፊት ለማያውቃቸው ወይም የረባ ሚና ላልነበራቸው በሽታዎች ራሱን የማጋለጡ አደጋ ከጊዜ ጊዜ የቀጠለ መርዶ ሆኗል፡፡ የከዚህ ቀደም የዘመናት ምርምሩና ፈጠራው ያደራጀው የፀረ ተህዋስያን የፈውስ ሀብቶች በትርፍ አሳዳጅነት ግፊት ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ፣ በቀጥተኛና ኢቀጥተኛ መንገዶች ተህዋስያን እየተለማመዳቸውና የፈውስ አቅማቸውም እየደከመ ቀድሞ ተሸንፈው በነበሩ ተህዋስያን እንደገና በገፍ የመጠቃት አደጋን በራሱ ላይ እየጠራና በበሽታ እየተጠቃ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ የሰው ልጅ የማይጎደፍረው፣ የሚያቃጥለው፣ የሚያጓጓው፣ የማይሞክረው፣ የማይፈጥረው፣ የማያመርተው፣ የማይበላው፣ በሌለ አኗኗሩ የብስን፣ ባህርን፣ አየርን፣ በብክለቱ እያጣበበና ሚዛን እያበዛ የምድሪቱን ህልውና መመለሻ ወደ ሌለው ሕይወት አልባነት እያስጠጋ፣ የራስን ጠቅላላ ጥፋት እያፋጠነ የሚገኝ ጠፊ ፍጡር ሆኗል፡፡ ከዚህ የሞት ጉዞው እንዲመለስ የምርምር ሥራዎች፣ ሳይንሳዊ ንቃትንና ግንዛቤን የሚያስፋፉ ጥናቶች፣ ውሳኔዎችና ቅዋሜዎች ሁሉ ብዙ ብዙ ብለዋል፣ ጩኸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በአብዛኛው የለበጣ ጆሮ፣ የይስሙላ ‹‹ማረሚያ›› ከማግኘት ያለፈ መደመጥ አልቻሉም፡፡ ለምን? በተለይም አሁን የምንገኝበት ጊዜና ሁኔታ አሳምሮ እንደሚያስገነዝበው ታላላቅና ኃይለኛ መንግሥታት ፖሊሲ ወይም የፖሊሰ ውሳኔ ውስጥ የሕዝብ አስተያየት ከቁጥር አለመግባቱ ነው፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አውሮፓ ኅብረት፣ እንዲሁም እነዚህ የሚሳተፉበት ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ውስጥ ፐብሊክ ፖሊሲና ፐብሊክ ኦፒኒየን አይተዋወቁም፡፡ ዩክሬንን የጦር ሜዳው ያደረገው አሜሪካ/ኔቶና የሩሲያ ጦርነት፣ በተለይም ደግሞ የእስራኤል ጥቃትና የፍልስጤም ጥያቄ የሕዝብ ፈቃድና የመንግሥት ፖሊሲ የተፈነጋገጡ፣ የተቃረኑ መሆናቸውን የሚሳይ ነው፡፡ ይህንን ለመገንዘብ ሰፊው የዓለም ሕዝብ በእያንዳንዱ የመንግሥታቱ አባል አገሮች ድምፅ አማካይነት በጠቅላላ ጉባዔው የሚወስነውን፣ መንግሥታት በተለይም የቬቶ ድምፅ ያላቸው አገሮች ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ዩኤስ አሜሪካ ያሉ አገሮች በፀጥታው ምክር ቤት አማካይነት የሚያሳልፉትን ውሳኔ ማነፃፀር ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ተኩስ ማቆም ብሎ ነገር አይሞከርም ብሎ ድምፅን በድምፅ የመሻር ‹‹መብት›› ባለው አገር አማካይነት የሌሎችን የአሥራ አራት ወይም አብዛኛው አገሮች ሐሳብ ደፍጥጦ ይህም የዓለም ማኅበር ሕግ ሲሆን፣ ጠቅላላ ጉባዔ ውስጥ እጅግ በጣም አብላጫው ከመቶ በላይ ያለው ተኩስ ማቆምን የሚወስን ነው፡፡ ዴሞክራሲ ነን፣ ናቸውም በሚባሉ የሦስት መቶና ያን ያህል ዕድሜ ባላቸው አገሮች ውስጥ መንገድ ላይ፣ የሕዝብ አስተያየት ጥንቅር ላይ የምየናው አስተያየት የመንግሥት ፖሊሲ ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲገለጽ፣ ሲወጣና ሲያስገድድም አናይም፡፡ በሚሠራ፣ ሕይወት ባለው፣ ‹‹ሲጠሩት በሚሰማ…›› ሲላወስና ሲንቀሳቀስ በሚታይ ዴሞክራሲ ውስጥ እነሱ (Functioning Democaracy) በሚሉት ያወቁና የነቁ፣ ጉዳዬ ነው፣ ያገባኛል ብለው በጋራና በውል በተለያዩ ተቋሞቻቸው ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መንግሥት ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር፣ ለውጥ ሲመጣ፣ ወዘተ ማየት እውነትም እዚያ የሠለጠነው ዓለም ውስጥ አዳዲስ ነገር አይደለም፣ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን የተሸረሸረውና አደጋ ያጋጠመው ይህም ጭምር ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ያቀረበችው ክስና ከዋናውም ክስ ጋር፣ ክሱ ተሰምቶ ጉዳዩ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ይቆይ ቢባል ክሱ በቀረበበት መብትና ነፃነት ጥበቃ ላይ ፈፅሞ የማይጠገን አደጋ ይደርሳል፡፡ ከዚያ በፊትና አሁኑኑ በአስቸኳይ ጊዜዊ ትዕዛዝ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ አለ ብላ ባቀረባቸው አቤቱታ ላይ የተሰጠው ትዕዛዝ፣ ያገኘው አቀባበል፣ የተሰጠው ምላሽ ብዙ የሚናገር፣ የዚህን ‹‹ሕግ›› ላይ የተመሠረተ ‹‹የዓለም ሥርዓት›› ችግር ዘክዝኮ የሚናገር ነው፡፡ አንዳንዶቹን ጉዳዮች እያነሳን እናውጋ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ከሳሽ መሆን ራሱ ያስነሳው የተለያየ ‹ምላሽ› አንዱ ራሱን የቻለ ሰፊ ጉዳይ ነው፡፡ ፍልስጤም የተመድ አባል አገር ባትሆንም ጄኖሳይድን ለመከላከልና ለመቅጣት የተደረገው ኮንቬንሽን አባል ነች፡፡ አንድም አገር ጉዳዬ ሳይለው፣ እንዲያውም ሃያ ሁለት የዓረብ፣ እንዲሁም የሙስሊም አገሮች ከአንደበት ወግ በላይ የረባ ነገር በማያሳዩበት ወቅት ደቡበ አፍሪካ ጉዳዩን ለፍርድ ማቅረቧ ኮንቬንሽኑን በመላው አባል አገሮች ላይ የጣለውን ተራ ግዴታ ከመውጣት በላይ ትልቅ ጀብድ (Feat) ነው፡፡ በተራ ጉዳይ፣ በሌላው የኑሮ ዘርፍ የሚታየውና የሚያጋጥመው ደቡብ አፍሪካ ምን አገባት? አንቺ ምንሽ ተነካ? ምን ቤት ነሽ አንቺ? ማለት ዓይነት ጥያቄዎች፣ ማጣጣያዎችና መከራከሪያዎችን የመሳሰሉ አቻ መከራከሪያዎች/ጉዳዮች ክሱን የመስማት ሒደትና ውሳኔው ዝርዝር ውስጥ ዓይተናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ደቡብ አፍሪካ ራሷ ምን አለች ምን፣ እኔ በበኩሌ በዚህ ለመብት የመታገል የመቆርቆር ድርቅ በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ ደቡብ አፍሪካ የተበደሉና የተገለሉ ሕዝቦች መኩሪያና መታፈሪያ ሆና ስትቆም አይቻታለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ዋጋ ያልተከፈለበት ነገር አይደለም፡፡ አገሩን፣ መንግሥቱን፣ ፓርቲውን የሃማስና የኢራን ‹ነገረ ፈጅ› ካደረገ ‹‹ክስ›› ጀምሮ ሌሎችንም ‹‹ጉድ›› ነገሮች እለድፋለሁ እስካለ መከራከሪያ፣ ክስ፣ ስሞታ በይፋ ጭምር ሰምተናል፡፡ እዚያው አገር ውስጥ ከመንግሥትና ከፓርቲ አንፃር የቆመ ተቃውሞና ቅሬታ ከሌሎች ነገሮች ሲሸራረቡ ሰምተናል፡፡ ዓለም አቀፋዊው ግንኙነት ውስጥ ባለው ዝምድና ላይ እንኳንስ ሌላ ነፃ ሐሳብ፣ ነፃ አስተያየት፣ ነፃ መከራከሪያ ተጨምሮ ክስ መቅረቡ በገዛ በራሱ ምክንያት ‹‹ነብር አየኝ›› በል የሚል የማስጠንቀቂያ ደውል የሚያሰማ ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ በዓለም ፍርድ ቤት ክስ የመሠረተችው ደግሞ ዝም ብሎ በተራ አገር ላይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጋምቢያ በሚየንማር ላይ ተመሳሳይ ጭብጥ ያለው ክስ መሥርታለች፡፡ ሚየንማርን ግን በዚህ ጉዳይ እንደምናየው ብዙና ከበድ ከበድ ያሉ ወዳጆች የሚጮሁላት አይደለችም፡፡

ክስ በቀረበበት ጉዳይ ላይ የተሰጠው የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ፣ ወይም ብይን እንዴት እንዴት እንደተሳለ፣ እንደተኮላ ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት የ‹አቀባበል› ድግስ እንደተደረገለት ማየትም የሚገርም ተሞክሮ ነው፡፡ የምንገኝበት ዓለም የሌላውን ወገን/ሕዝብ በደል ጥቅሜ ብሎ ከመያዝ ፖሊሲ በላይ የፍርድ ቤት ውሳኔንና ትዕዛዝን ወሊድ ላይ፣ መናገርና መስማት ሒደት ውስጥ፣ ወዘተ ማጨናገፍን፣ ማደናገርን፣ ጥንብ እርኩስ ማውጣትን ሲያካትት ዓይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ካቀረበቻቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ግጭት ማቆምን የሚመለከተው አንዱ ነው፡፡ እውነት ነው እስራኤል ተኩስ ወይም ጦርነትን እንድታቆም አልታዘዘችም፡፡ ይህንን ግን ወስዶ ደቡብ አፍሪካም/እስራኤልም ያጣችው/ያገኘችው አለ ብሎ ሚዛኑን ‹‹ውዝዋዜ›› ለማሳየት መሞከር የማይወዳደሩ ነገሮችን ማወዳደር ነው፡፡ የተከሳሽ አገር ዋና ግንድ መከራከሪያ ክሱን ውድቅ አድርጉልኝ ነው፡፡ ክሱን ውድቅ አድርገን ከሳሽ ተከሳሽን አሰናብተናል የሚል ድል ላይ ለመድረስ እስራኤል ፍርድ ቤቱ ባለመብት አይደለም (የዳኝነት ሥልጣን የለውም) በሁለታችን መካከል አለመግባባት (ዲስፒዩት) የለም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ  ክሱ የዘር ማጥፋት (የጄኖሳይድ) ቅንጣት ምልክት የለበትም የሚል ሁሉ ቀርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹ጊዜያዊ ዕርምጃ›› የሚመለከተውን ወይም የ‹‹ዕግድ›‹ ትዕዛዝ በሰጠበት ውሳኔው በፓራግፍ 11 እና 12 እንደገለጸው ተከሳሽ አገር በቃል ክርክሩ መጨረሻ ላይ አንደኛ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ እንዲያደርገው፣ ሁለተኛው ደግሞ መዝገቡንም ዘግቶ እንዲያሰናብተው መጠየቁን ዘርዝሮ በውሳኔው ተራ ቁጥር 32 ላይ ይህንን መዝገቡን ዘግቶ ያሰናብተኝ ጥያቄን ያልተቀበለው መሆኑን ወስኗል፡፡

ከሁሉም የገረመኝ የምንገኝበት ዓለም ምን ዓይነት የጉልበተኞች ዓለም መሆኑን የሚያሳየው የፍርድ ቤቱ፣ ዓለም በጉጉት የጠበቀው የጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ውሳኔ የቀጥታ ሥርጭትና ዜና ከኡንሩዋ (UNRWA) የ‹‹ቅሌት›› ዜና ጋር ተዳብሎ፣ ተበርዞ፣ እንዲያውም የኡንሩዋ ‹‹ክስ›› (ወሬ የውሳኔው ግርዶሽ ሆኖ የቀረበበት የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ይሁነኝ ተብሎ የተሠራው ያለማጋነን ‹ዓለም› በሙሉ (የአሜሪካና የምዕራብ ዓለም) የተሳተፈበት ሴራና ደባ ነው፡፡ ዓለም እንዴት እንደሚሠራ ከጥቃት ስሜቱ ጋር ተረድተናል ኡንርዋ ማለት የመንግሥታቱ ድርጅት የዕርዳታና የሥራ ኤጀንሲ (ለፍልስጤማውያን በቅርብ ምሥራቅ ውስጥ) ማለት ነው፡፡ የፍልስጤም ጥያቄና ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዳይ ከሆነበት፣ ይኼው ድርጅትም በዚሁ ምክንያት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲሠራ የኖረ የዚህን ሕዝብ የስደተኞች ጉዳይ አደራ ይዞ የኖረ ተቋም ነው፡፡ ከ13 ሺሕ በላይ ሠራተኛ ባለው በዚህ የስደተኞች ድርጅት ውስጥ በ12 ሠራተኞች ላይ የቀረበ ገና በፍርድ ያልተወሰነ ክስ መላውን ሠራተኛ፣ መላውን የስደተኞች ድርጅቱን መዋቅር እስራኤል እንደምትለው በእስራኤል ቋንቋ አሸባሪ ማለት በዕለቱም፣ በተከታይ ቀናትም እነ አንቶኒዮ ጉተሬስን፣ ማርቲን ግሪፊሰን ጨምሮ መላውን የተመድ ሰው ያሳዘነ ነው፡፡ ይህንንም ጥር 22/Janwary 31 በተሰበሰበው የፀጥታ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ሰምተናል፡፡

ይህንን የግፈኞች ዓለምን ግን በዚህ መካከል የሚቀጣጠልና እየተባባሰ የሚሄድ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ዓይነት (ምርጫ 2024 አሜሪካን) ሥሌት አቀጣጥሎና አንገብግቦ ለጥፋት እንደዳረገን የአገራችንም አጀንዳ ማድረግ አለብን፡፡ አገራችን የረሷትን ሰዎች/አገሮች ረስታ የምትኖር አገር አይደለችም፡፡ ወይም ይህ  ይባል የነበረበት ወቅት አክትሟል፡፡ የአጠቃላይ የሔጉ ፍርድ ቤት ውሳኔ/ትዕዛዝ አካል የሆነው የተለያዩ ዳኞች በተናጠል ከሰጧቸው ዲክላሬሽኖች መካከል አንዱ የዳኛ/XUEHANQIN የቻይናዊቷ ዳኛ) የብቻ አስተያየት ነው፡፡ እኚህ የተመድ ፍርድ ቤት ዳኞች አባል የሆኑት ዳኛ አሥራ ስድስት ለአንድና አሥራ አምስት ለሁለት በሆነ ድምፅ የተሰጠውን ዋናውን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ደግፈው ድምፃቸውን ከመስጠታቸውና ከማስመዝገባቸውም በተጨማሪ፣ ነገሩን ለማጠናከር ይበልጥ ጉዳዩን ‹ለማብራራት› የሚል ዓይነት የኃላፊነት ስሜት በመነሳት አምስት ፓራግራፍ/አንቀጽ ያለው ባለሁለት ገጽ ዲክላሬሽናቸውን አሥፍረዋል፡፡ ከዚህ ተጨማሪ ‹‹ማብራሪያ››ቸው ሲበዛና ክፉኛ ያስረገጡት የጄኖሳይድ ኮንቬንሽን ፈራሚ አባል አገሮች ከሳሽ ሆኖ የመቅረብ ወይም ክስ የመመሥረት መብት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህንን በመሰለ አንብጋቢ ምክንያት መነሻነት ከ60 ዓመት በፊት ኢትዮጵያና ላይቤሪያ በናሚቢያ ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ላይ የመሠረቱትን ክስ አስታውሰው፣ ይኼው ፍርድ ቤትም በዚያ ጉዳይ ላይ የሁለቱን አገሮች አቤቱታና ማመልከቻ በጉዳዩ ውስጥ ያላቸውን/አለን የሚሉትን ጥቅም አላስረዳችሁም ብሎ የከሳሽ/አቤቱታ አቅራቢነት መብታቸውን ውድቅ ያደረገበትን ትዕዛዝ አውስተው፣ ይህም ፍትሕን የመንፈግ አሠራር የተመድ አባል አገሮች በፍርድ ቤቱ ላይ ያሳዩትን ቁጣ በውጤትነት ማስከተሉን የፍርድ ቤቱን ዝና ማጠልሸቱን ገልጸው፣ ይህ የሕግ ጭብጥ ግን ፍርድ ቤት በሚያስተናግዳቸው ጉዳዮች ሒደትና ክርክር ውስጥ እየጠራ መጥቶ አሁን የተጎናፀፈውን ይዘትና መልክ ያብራሩበት መግለጫ ነው፡፡ የዘር ማጥፋትን ወንጀል መከላከልና መቅጣት ምን አግብቶህና አንተ ምንህ ተነካ የሚል ጥያቄ የማይነሳበት፣ ሁሉንምና እያንዳንዱን አገር የሚመለከትና የተለየ ጥቅም አሳየ የማይባልበት ጉዳይ ነው ብለው ይህንን ‹‹ተጨማሪ እሴት›› ካሉበት ማብራሪያ ነው፡፡

ዓለም አቀፋዊ ሕግ አፈጻጸምና አተገባበር ውስጥ ተራና ፍዝ ሳይሆን፣ ይህንን የመሰለ ብርቱና ንቁ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን፡፡ ሕግ ማክበርና ማስከበር ግን ሁለመናችን ውስጥ መኗኗሪያችና መረማመጃችን፣ የሥራና የዘወትር እንጂ የአደባባይና የክት ልብሳችን መሆን የለበትም፡፡ ሕግ ማክበራችን የሚገዛውና ህልውናውንም የሚያንቀሳቅሰው መርህ ላይ የተመሠረተ እምነታችን እንጂ፣ ሲጠቀም ይጠቅመናል ስንል ብቻ የምንገዛው፣ የቢሻን ውሳኔ የሚመራው አይደለም፡፡ ዓለምንም ራሳችንንም ከጥፋት ማዳን የምንችለው የሕግ ማክበር ወግና ባህል ሁለተኛው ወይም ሌላው ተፈጥሯችን ሲሆን ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...