Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በንጉሡ ዘመን “ጃንሆይ ሜዳ” ተብሎ ይጠራ እንደነበረ ይነገራል። በኋላም ጃንሜዳ በሚል ስያሜ ይታወቃል። በደርግ ዘመን በጃንሜዳ አምስት ሜዳዎች የነበሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ቦታዎች የሁለተኛ ዲቪዚዮን፣ የከፍተኛና የቀበሌ ቡድኖች ድንቅ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ይካሄዱ ነበር። የጥምቀት በዓል በየዓመቱ ይከበርበታል። አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ውድድሮች በየዓመቱ ይካሄዱበታል።

የደርግ ሥርዓት መባቻ ድረስ የሞተር ብስክሌት ውድድሮች ይከናወኑበት ነበር። በተጨማሪ ትልቅ የፈረስ እሽቅድምድም (Horse Racing) በዋናነት ይጠቀሳል። ከተለያዩ የወታደር ክፍሎች፣ ከውጭ አገር የተለያዩ ኤምባሲዎች፣ ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ የፈረስ ተወዳዳሪዎች ይካፈሉና ይሽቀዳደሙ ነበር። ግርማዊ ጃንሆይና መኳንንቶቻቸው በክብር እንግድነት ይገኙ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ እማኞች ይናገራሉ።

በጃንሜዳ የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የተለያዩ የባህላዊ ስፖርቶች ውድድሮች ይደረጉ ነበር፡፡ በተጨማሪም በየዓመቱ የኢትዮጵያ ቼዝ ጨዋታ ሻምፒዮናም ይካሄድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጃንሜዳ የበርካታ ስፖርታዊ ፉክክሮች መድረክ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፈረስ ተወዳዳሪዎች ከሚሽቀዳደሙበት ትይዩ ለዓይን ማራኪ የሆነ ባለአንድ ፎቅ የተንጣለለ ሰፊ ሕንፃ አለ። ጃንሆይን ጨምሮ ከውጭ አገሮች የመጡ የክብር እንግዶች ከአናት ተቀምጠው ውድድሩን ይመለከቱ ነበር፣ ለአሸናፊዎችም ሽልማት ከዚሁ ቦታ ያበረክቱ ነበር። ይህ ሕንፃ ሬሲንግ ክለብ (Racing Club) በሚል ስያሜ ይጠራል። ዙሪያውን በመካከለኛ የሽቦ አጥር የታጠረ ሲሆን፣ ግራና ቀኝ በተለያዩ ችግኞችና አበቦች ያማረ ነበር። በሥፍራው ቁጭ ብሎ ነፋሻማ ንፁህ አየር ማግኘት ለነፍስ የምግብ ያህል እንደነበረ ብዙዎች ያስታውሳሉ።

ወደ አዳራሹ ሲዘልቁ ቅድሚያ ዓይኖች የሚያርፉት ግርማዊ ጃንሆይ ፈረስ ላይ ተቀምጠው የተቀረፀው ምሥል በትልቁ ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ በሬስቶራንቱ ከሳንዱች አንስቶ እጅ የሚያስቆረጥሙ ምግቦች፣ እንዲሁም ለስላሳና ቢራ መጠጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ለእንግዶች ይቀርቡ ነበር። ልጆች ሳንቲም ከተው ሽልማት የሚያገኙበት ካዚኖ መሰል መጫወቻ፣ ለአዋቂዎች ደግሞ ከረንቡላና ቢንጎ በመሳሰሉ መዝናኛዎች የእረፍት ጊዜን የሚያሳልፉ እጅግ ብዙ ነበሩ። ከደርግ አንዳንድ ባለሥልጣናት አንዳንዶች ቀዝቃዛ ቢራ እየተጎነጩ በነፋሻው አየር ዘና የሚሉ ነበሩ።

ከጃንሆይ ሥርዓት መገርሰስ በኋላ ሥልጣን የጨበጠው ደርግ ይህን መዝናኛን ጨምሮ ጃንሜዳን በሚገባ ተንከባክቦና ጠብቆ ከመያዙም ባሻገር የፈረስ ውድድሮችን፣ የእግር ኳስና የአትሌቲክስ፣ ወዘተ ውድድሮች አስቀጥሎበታል፡፡

ከረጅም ዓመታት በኋላ ጃንሜዳ ጎራ አልኩ። በተለምዶ ላይኛው ሜዳ ተብሎ ይጠራ በነበረውና ድንቅ የእግር ኳስ ጨዋታ ይካሄድበት የነበረው ሜዳ በብሎኬት የታነፀ አዳራሽ ተገንብቷል። በውስጡ የታዳጊዎች ሰርከስ ስፖርት እንደሚካሄድበት ተነገረኝ። እልፍ ብሎ መሠረት ተጥሎ ፌሮ ብረቶች ተገትረው የሚታዩበት በጅምር የቆመ ግንባታ ይታያል። በፊት ከነበሩ ኳስ ሜዳዎች ሁለት ብቻ በጃልሜዳ ታችኛው ክፍል ይታያሉ። በቀድሞው አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አቅጣጫ መውጫ በተገነባ አዳራሽ የቢንጎ ጨዋታ ይደረጋል።

በመቀጠል ያመራሁት ወደ ሬሲንግ ክለብ (Racing Club) ነበር። የፈረስ እሽቅድምድም አወዳዳሪ ዳኞች የሚቀመጡባትና በድምፅ ማጉያ መልዕክት የሚያስተላልፉባት ከጠንካራ እንጨት የታነፀች ማማ እርጅና ተጫጭኗታል። ወደ መዝናኛው መግቢያ ግራና ቀኝ የነበረው መናፈሻ የለም። ሕንፃው በአሳዛኝ ሁኔታ ውልቅልቁ ወጥቷል።

ወደ አንደኛ ፎቅ መውጫው በፈራረሱ የቤቱ ቁሳቁሶች በመጋረዱ ማለፍ አይቻልም። ክፍሎቹን እየተዘዋወርኩ ስመለከት ይበልጥ አዘንኩ። የበፊት ግርማ ሞገሱን አጥቶ ጨርሶ ለመውደምና “ታሪክ” ሆኖ ለመቅረት ጥቂት ወራትን የሚጠብቅ ይመስላል ብል አላጋነንኩም::

ቅርስነቱ ጨርሶ ከመጥፋቱ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ፈጥነው ሊደርሱለት፣ የቀድሞ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይቀይር ሊጠግኑት፣ ቢቻል ወደ ቀድሞው መዝናኛ ማዕከልነቱ ሊመልሱት ይገባል እላለሁ:: በጃንሆይ ዘመን በሥፍራው ያዘወትር ከነበረው አዛውንት ወዳጄ ጋር ባየነው ነገር አዝነን ስንወጣ ለማስታወሻ የሚሆን ፎቶ እያስቀረሁ ነበር::

(ገላውዲዎስ ነጋ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...