Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናና የኢትዮጵያ ተሳትፎ

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናና የኢትዮጵያ ተሳትፎ

ቀን:

የዓለም አትሌቲክስ ከሚያሰናዳቸው ዓመታዊ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የቤት ውስጥ የመም (ትራክ) እና የሜዳ ላይ ተግባር ሻምፒዮና አንዱ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1985 የዓለም የቤት ውስጥ ጨዋታ የሚል ስያሜን ይዞ በፈረንሣይ ፓሪስ በተጀመረ በሁለተኛው ዓመት፣ ስያሜው የአይኤምኤፍ ተቀይሮ  የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በ2019 በአሁኑ ወቅት ያለው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ስያሜን በመያዝ እየተከናወነ ይገኛል፡፡  

ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ በተለያዩ ከተሞች የሚሰናዳ ሲሆን፣ የአጭርና የረዥም ርቀት፣ እንዲሁም የሜዳ ተግባር ውድድሮች ይስተናግዱበታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሻምፒዮናው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የውድድር ዓይነቶቹ ሳይቀነሱና ሳይጨመሩ መከናወን የቀጠሉ ሲሆን፣ በተለይ በትራክ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የራሳቸውን አሻራ ማኖር ችለዋል፡፡

በርካታ አትሌቶች በአጭር ርቀት መወዳደር መጀመራቸውን ተከትሎ፣ የቤት ውስጥ ውድድሩ የግል ብቃትን ለማሳደግ ምቹ ሆኗቸዋል፡፡

የዘንድሮው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በስኮትላንድ ግላስጎ ይከናወናል፡፡

በርካታ የስፖርት ኩነቶችን በማሰናዳት የተዋጣለት ግላስኮው እ.አ.አ በ2014  የኮመን ዌልዝ ጨዋታዎችን ባዘጋጀ በአሥር ዓመቱ ከየካቲት 22 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ውድድሩን ለማስተናገድ ተሳታፊዎችን እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

በዓለም ላይ የሚገኙ ምርጥ አትሌቶች በታዋቂው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና  ባለድል ለመሆን ይፎካከራሉ፡፡

ከ130 በላይ አገሮች የተውጣጡ ከ700 በላይ ተወዳዳሪዎችም በሚሳተፉበት ሻምፒዮናው በአጠቃላይ በሁለቱም ጾታ 26 ውድድሮች ይከናወናሉ፡፡

የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በስኮትላንድ ሲካሄድ የመጀመሪያው እንደመሆኑ መጠን፣ አዘጋጇ አገር ለአትሌቶች ምቹ የሆነ የውድድር መድረክ ማሰናዳቷን፣ አትሌቶችና አድናቂዎችም በሦስት ቀናት ቆይታቸው አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥረት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በ2012 የተገነባው የግላስኮው ኤምሬትስ ስታዲየም በርካታ ውድድሮች ማስተናገዱ ተጠቅሷል፡፡ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የተገነባው ስታዲየሙ 5,500 መቀመጫዎች አሉት፡፡ ስታዲየሙ የ2019 የአውሮፓ አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፤ የብሪቲሽ የአትሌቲክስ የቤት ውስጥ ግራንድ ፕሪክስ ከማዘጋጀት ባሻገር፣ የዓለም የባድሜንተን ሻምፒዮና፤ የግላስኮ ጂምናስቲክ ዓለም ዋንጫና ዴቪስ ካፕ ውድድሮች ማስተናገድ ችሏል፡፡

የአንድ ወር ዕድሜ የቀረው በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ የኢትዮጵያ አትሌቶችን ጨምሮ የበርካታ አገሮች አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ኢትዮጵያና የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሻምፒዮናው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ውድድሮች (በ1985 እና በ1987) መካፈል አልቻለም፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው በ1989 ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በተደረጉ ሦስት ተከታታይ ሻምፒዮናዎች ቢወዳደርም አንድም ሜዳሊያ ማሳካት አልቻለም፡፡

በ1997 በፓሪስ በተካሄደው ሻምፒዮና ኃይሌ ገብረ ሥሳሴ በ3000 ሜትር  በማሸነፍ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቁ ኢትዮጵያ አሥረኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

በቀጣዩና በጃፓን ማበሺ በተከናወነው ሻምፒዮና ኃይሌ በ1500 እና 3000 ሜትር ሁለት ወርቅ ሲያመጣ፣ ሚሊዮን ወልዴ በ3000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ማሳካት ችሏል፡፡

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ በድምሩ ሦስት ሜዳሊያዎች ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ አስችሏታል፡፡

በየሻምፒዮናዎቹ እየተሻሻለ የመጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፣ በ2003 በርኒገሃም በተካሄደው ሻምፒዮና በሴቶቹም ውጤት ማሳካት ተችሎ ነበር፡፡ በወንዶች ኃይሌ በ3000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያን ሲያመጣ፣ በሴቶች ብርሃኔ አደሬ በ3000 ሜትር ወርቅ፣ እንዲሁም መሠረት ደፋር የብር ሜዳሊያ ማሳካት የቻሉበት ዓመት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ደረጃዋን ከስድስተኛ ወደ አምስተኛ ከፍ ማድረግ የቻለችበት ነው፡፡

በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ላቅ ያለ ውጤት ካሳኩ የዓለም አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያውያኑ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ መሠረት ደፋርና ገንዘቤ ዲባባ በቀዳሚነት ስማቸው ሠፍሯል፡፡

ገንዘቤ በሴቶች 1500 ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች፣ እንዲሁም በ3000 ሜትር ሦስት የወርቅ በድምሩ አምስት ሜዳሊዎችን ከ2012 እስከ 2018 በማሳካት ቀዳማዊት አትሌት ነች፡፡

ኃይሌ በ3000 ሜትር ሦስት ወርቅ ሜዳሊያዎችን፣ እንዲሁም በ1500 ሜትር አንድ የወርቅ፣ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በታሪክ ስሙ መመዝገብ ችሏል፡፡

ሌላዋ ኢትዮጵያዊት  መሠረት ደፋር ስትሆን፣ በ3000 ሜትር አራት ወርቅ፣ አንድ የብርና አንድ የነሐስ፣ በድምሩ ስድስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በታሪክ ስሟ ከሠፈሩት መካከል ትገኛለች፡፡

ከዚህም በላይ በሻምፒዮናው በተለያዩ ርቀቶች ክብረ ወሰን ከጨበጡ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል፡፡

በ1997 በፈረንሣይ በተከናወነው ሻምፒዮና በወንዶች 3000 ሜትር ኃይሌ ገብረ ሥላሴ 7፡34፡71 በመግባት ክብረ ወሰን በመጨበጥ ሳያስደፍር ቆይቷል፡፡

በ2022 በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው ሻምፒዮና ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር 3፡32፡77 በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ችሏል፡፡

በሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ በቤልግሬዱ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር 3፡57፡19 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ችላለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሻምፒዮናው መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ2022 በሰርቢያ ቤልግሬድ የተከናወነ የቤት ውስጥ አትሌክስ ሻምፒዮና አራት ወርቅ፣ ሦስት ብር፣ እንዲሁም ሁለት ነሐስ፣ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በመሰብበሰ ከዓለም አንደኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችበት ስኬታማው ሻምፒዮና ነበር፡፡

በዘንድሮ ሻምፒዮና ድርቤ ወልተጂ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ጉዳፍ ፀጋይ፣ ለምለም ኃይሉ፣ ሒሩት መሸሻ የመሳሰሉ አትሌቶች ተጠባቂ ናቸው፡፡

በወንዶች ለሜቻ ግርማና ሳሙኤል ተፈራ እንደሚሳተፉና ቅድመ ግምት ያገኙ አትሌቶች ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በርቀቱ በወንዶች አትሌቶች ክፍተት እንዳለበት ይተቻል፡፡ 

በዘንድሮ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌቶች ለመለየት በተለያዩ አገሮች የቤት ውስጥ ውድድር እየተከናወኑ ሲሆን፣ በሚያመጡት ሰዓት ኢትዮጵያን ወክለው እንዲካፈሉ ይደረጋል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶችን መርጦ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...