Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዓመት 40 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣ የነበረውን የእርጎ ማቆያ ኬሚካል የሚተካ አዲስ ግኝት ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለወተትም ሆነ ለእርድ የሚያስፈልጉ የዳልጋ እንስሳትን በቤተ ሙከራ ማምረት መቻሉ ተገልጿል

በእርጎ ምርት የተሰማሩ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ቁልፍ የእርጎ ማቆያ ‹‹ላክቲክ አሲድ›› የተባለ ኬሚካል ወደ አገሪቱ ለማስገባት፣ በዓመት የሚወጣውን 40 ሚሊዮን ዶላር ያስቀራል የተባለ አዲስ የኬሚካል ግኝት በብሔራዊ የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል መሠራቱ ተነገረ።

በምርምር ማዕከሉ በዓይን የማይታዩ ህዋሳት ባዮ ቴክኖሎጂ (Microbial Biotechnology) ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት የግኝቱ ባለቤት አቶ አዳነ እሸቱ፣ ምርምሩ ሰባት ዓመታት እንደፈጀባቸውና በአሁኑ ወቅት በብዛት ተመርቶ ለማሠራጨት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራማሪው ስለግኝታቸው ምንነት ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ላክቶባሲለስ የሚባሉ ከላክቲክ አሲድ የወጡ ባክቴሪያ ነው ወተት ለማርጋት የሚያስችለውን ንጥረ ነገር መፍጠር ያስቻለን። በምርምር ሒደቱ መጀመሪያ የሚያስፈልገውን ለመለየት በብዙ ዝርያዎች ላይ ምርምር አድርገን ነው ያገኘነው። ከልየታው በኋላ የተፈለገውን ዓላማ ለማሳካት ይሆናል ተብሎ የተመረጠውን ዝርያ ባህሪ የማድረግ ሥራ በተለያየ የአየር ሁኔታ መጠን፣ በተለያየ የጨው ልኬት (salt Concentration)፣ እና ሌሎችም የተለያዩ ባህሪ መለኪያ ሳይንሳዊ መንገዶች ተለይተዋል። በመቀጠልም የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ ስኬታማ የሆነው ልዩ ዝርያ (stray) ታውቋል። በዚህም ኢንዱስትሪዎች በአሁን ወቅት የሚጠቀሙትን የወተት ማርጊያ ኬሚካል የሚተካውን ግኝት ፈጥረናል፤›› ብለዋል።

የእርጎ ማቆያው እስካሁን ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በሱሉልታና ሐዋሳን ጨምሮ በአምስት የእርጎ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ጥቅም ላይ ውሎ ውጤታማነቱ መፈተሹ የተገለጸ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪዎችም ምርቱ መርዛማነት የሌለው፣ በጤና ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያደርስና ከውጭ አገሮች ከሚገቡት እኩል ውጤታማ መሆኑን የማረጋገጫ ደብዳቤ ለምርምር ማዕከሉ መስጠታቸውም ተጠቅሷል።

ግኝቱን በብዛት አምርቶ ለኢንዱስትሪዎችና ምርቱን ጠያቂ የወተት ተዋጽኦ አምራች ኢንዱስትሪዎች በጠቅላላ በብዛት አምርቶ ለማዳረስ የሚያስችለው ባዮ ሪአክተር የሚባል ማባዣ ማሽን ለመግዛት፣ የምርምር ማዕከሉ በሒደት ላይ መሆኑን ተመራማሪው አብራርተዋል።

‹‹ይህ ባዮ ሪአክተር ከመጣ ብዙ ልኬት አዘጋጅተን፣ ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት መጠንና ጊዜ ገበያው የሚፈልገውን ያህል ማቅረብ እንችላለን፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል የብሔራዊ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል በእንስሳት ዘረመል ምርምር ክፍል፣ ለወተትም ሆነ ለእርድ የሚያስፈልጉ የዳልጋ እንስሳትን በተፈለገው ፆታ በቤተ ሙከራ ውስጥ በሰው ሠራሽ ዘረመል የማዳቀል ሒደት (Artificial Insemination) አምስት መቶ ጥጆችን ማምረት መቻሉም ተገልጿል።

የምርምር ክፍሉ የተፈለገው እንስሳ ለወተት ከሆነ ከፍተኛ የወተት ምርት ካላቸው የላም ዝርያዎች እንቁላላቸውን በመውሰድና ከወንዴው ዘር ጋር በቤተ ሙከራ በማገናኘትና ጾታውም ሴት እንዲሆን በማድረግ፣ እንዲሁም ለዕርድም ከተፈለገ የተፈለገውን መርጦ በመለየት ጥጆችን እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርምር ክፍሉ ከዚህ በተጨማሪ ፈንግል በሚል ስም የሚታወቀውን የዶሮ በሽታ፣ ከዶሮዎች ላይ የደም ጠብታ በመውሰድ መመርመርና ውጤቱን ወዲያው ማወቅ የሚያስችል ቀላል የምርመራ መሣሪያ ገንብቶ የውጤታማነት ደረጃው ምን ያህል እንደሆነ በመስክ የዶሮ ዕርባታዎች ላይ እየተፈተሸ መሆኑም ተጠቅሷል።

በፍተሻ ሒደት ላይ ያለው የመመርመሪያ መሣሪያ ለዶሮ አርቢዎች አጠቃቀም ቀላል በሆነ መንገድና በአንድ ጊዜ ሥልጠና ጥቅም ላይ ማዋል እንዲችሉ ተደርጎ የተዘጋጀ ነውም ተብሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች