Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አማራ ክልል በመደበኛ ሕግ አንዲመራ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ ቢቀርብም አዋጁ ተራዝሟል

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በመጀመሪያው ዙር አፈጻጸም ከ7000 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር መዋላቸው ተገልጿል

ከስድስት ወራት በፊት በአማራ ክልል በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ሐምሌ 2016 ዓ.ም. የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ ክልሉ በመደበኛ ሕግ እንዲመራ ከአባላቱ ጥያቄ ቢቀርብም ፓርላማው አዋጁን በአብላጫ ድምፅ አራዝሞታል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በሁለት ተቃውሞ፣ በሦስት ድምፀ ታዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አዋጁ አንዲራዘም አፅድቋል።

ባለፉት ወራት የታየውን የፀጥታ ሁኔታ ለማሻሻል፣ ለማጽናትና ወደ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ በዕቅድ የተያዙ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ፣ እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አዋጁን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት እንዲራዘም የሚል ውሳኔ ያቀረቡት፣ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ምሕረቱ ሻንቆ (ረዳት ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

በተጨማሪም የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ስለአዋጁ መራዘም አስፈላጊነት ሲያብራሩ፣ የክልሉ መስተዳድርና መንግሥት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሙሉ ለሙሉ የማፍረስ ሥጋት ተደቅኖ እንደነበርና ይህንን ሁኔታ በመቀልበስ የክልሉን መስተዳድርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን መታደግና የክልሉን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መዋቅር መልሶ እንዲደራጅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ‹‹በሕገ ወጥና ጽንፈኛ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ወድቀው የነበሩ የክልሉ ትልልቁ ከተሞችና አብዛኛዎቹ ዞኖች ወደ መንግሥት እንዲመለሱ›› ማድረግ መቻሉንና ተቋርጠው የነበሩ በረራዎችና እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

ይሁን አንጂ ከአማራ ክልል ውጪ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ አንዳንድ አዝማሚያዎችና የፀጥታ ሥጋቶች በመኖራቸው እነዚህን ታሳቢ በማድረግና ቀሪ ሥራዎች በመኖራቸው ተጨማሪ ጊዜ በማስፈለጉ፣ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳትና አዋጅን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ መመርያ ጠቅላይ ዕዙ አዋጁ ቢራዘም ለሕዝብ ደኅንነትና ሰላም ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ አቶ አበባው ደሳለው የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በመቃወም ባቀረቡት ንግግር፣ ከዚህ በፊት የፀደቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ምን አመጡ፣ የባሰ የሰላም ዕጦትንና መባባስን ፈጠሩ እንጂ ብለዋል፡፡

 በመሆኑም ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጫን ሳይሆን መነጋገርና መደራደር ነው የሚያስፈልገን መነጋገርና መደራደር፣ የሕዝብን ጥያቄ ጠጋ ብሎ መስማት ነው የሚያስፈልገው፤›› ብለዋል፡፡

የመጀመርያ ዙር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳይታወጅ ቢጠየቅም፣ ከታወጀ ወዲህ ችግሩ ተባብሶ በሁሉም የአማራ ክልል ከተሞች ንፁኃን መጨፍጨፋቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ያለመከሰስ መብት ያላቸውና መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸው የምክር ቤት አባላት ተደብድበውና ተንገላተው ወደ ከርቸሌ እንዲወርዱ መደረጋቸውንና ተጨማሪ ያለመከሰስ መብት ያላቸው የኦሮሚያ ጨፌ አባል በቅርቡ እንዲሁ ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

 በመሆኑም አሁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቀጥል ከሆነ ይህ የመንግሥት ተግባር የሚቀጥል በመሆኑና አዋጁ ለውጥ ባለማምጣቱ መንግሥት ተረጋግቶ የተለያዩ ወረዳዎችን ማስተዳደር አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አቶ አበባው እንደገለጹት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አላስፈላጊ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡ ‹‹በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ዳር ድንበር የሚያስከብሩ ለክፉ ቀን ይሆናሉ ተብለው የሠለጠኑ ኃይሎች የበለጠ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች በብዛት እየሞቱ ነው፡፡ ለማንም እየጠቀሙ አይደለም፣ ድርድር የሚያስፈልግ ቢሆንም መንግሥት የጀመረው ድርድር የለም፡፡ አዋጁ የአገሪቱን ልማት ወደኋላ ስለማስቀረቱም ተናግረዋል፡፡

‹‹መንግሥት ሰከን ይበል፣ ፊት ለፊት ይዋጣልን የሚል ጦርነት ውስጥ መግባት የለበትም፤›› ብለው አዋጁን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌላኛው የምክር ቤት አባል አዋጁ መታፈንን ያመጣል፣ የመንግሥት አቅም የደከመ በመሆኑ ነው ይህ አዋጅ የሚታወጀው የሚል መንፈስ ስለመነሳቱ ተናግረዋል፡፡

 በመደበኛው ሕግ ሥራ መሥራት አይቻልም ወይ? ለምን ይራዘማል? የሚል ጥያቄ አቅርበው የሕግ ማስበር ሥራው ከተሻሻለ ቀሪ ሥራው በመደበኛ ሕግ ለምን አይጠናቀቅም በሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አብዛኛው ሰው የመታፈን ስሜት እየተሰማው መሆኑን ገልጸው ጥያቄዎቻችን በሰላማዊ መንገድ ሊፈታልን አልቻለም የሚሉ አካላት ተነስተው ጫካ ሊገቡ ቢችሉም፣ እነዚህ አካላት ኢትዮጵያውያን በመሆናቸውና የሚገዳደለው ወገን ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ከትግራይ ጦርነት ትምህርት ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡ በትግራይ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ እናቶች የደም ዕንባ ማንባታቸውን ጠቅሰው፣ በአማራ ክልል በቀጣይ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል አይታወቅም ብለዋል፡፡

‹‹በአማራ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልል ባለው ጦርነት ሕዝቡ የተቆለፈበት ሳጥን ሆኗል፤›› የሚሉት የምክር ቤት አባሉ፣ ሕዝቡ መንቀሳቀስ አለመቻሉንና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዴት መፍትሔ የለውም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ዓመታት ከምንዋጋ 20 ዓመት መነጋገር አለብን ብለው መናገራቸውን አውስተዋል፡፡

በአስቸኳ ጊዜ አዋጂ መርማሪ ቦርድ እንደተገጸው ከሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ 7196 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ከእነዚህ መካከል በተለያየ ጊዜ 5000 ተጠርጣሪዎች በተሃድሶና በሥልጠና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች