Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ የሚኖረውን ሰላምና መረጋጋት ተመርኩዞ የሕዝብና ቤት ቆጠራን እንደሚካሄድ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቀጣይ ዓመታት በኢትዮጵያ የሚኖረውን የሰላምና መረጋጋት በመመልከት በ2018 ዓ.ም. አጠቃላይ የአገሪቱን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ ዕቅድ መውጣቱ ተገለጸ፡፡

ከተካሄደ ከ16 ዓመታት በላይ የተቆጠረውን የቤትና ሕዝበ ቆጠራ በድጋሚ ለማካሄድ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን ባዘጋጁት የሦስት ዓመታት የስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም ውስጥ ነው የተካተተው፡፡

ሁለቱ ተቋማት ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ ባደረጉት ወደ 35 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ የሚያስፈልገው የሦስት ዓመቱ የስታስቲክስ ልማት ፕሮግራም፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራን ጨምሮ አምስት አጠቃላይ የጥናት ዕቅዶችን ይዟል፡፡

የሦስት ዓመቱ ፕሮግራም ከያዛቸው የጥናት ፕሮጀክቶች የኅብርተሰብን ጤና ሁኔታ የሚለካ (Demographic Health Survey)፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚና ቢዝነስ ድርጅቶች ቆጠራ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ መሠረትና የድህነት መለኪያ ስታትስቲክስ፣ አጠቃላይ የግብርና ቆጠራ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ናቸው፡፡

የሕዝብና ቤት ቆጠራው ‹‹የአገራችን ሰላም በሰከነ ሁኔታ መካሄድ ያለበትና አጠቃላይ የአገራችን ሕዝብ ሥነ ልቦና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው›› ያሉት የኢትዮጵያ ስታስትቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ እንደገለጹት፣ ቆጠራው ሊካሄድ በታቀደበት ወቅት በኢትዮጵያ የሚኖረው መረጋጋት፣ የኅብረተሰቡ ሥነ ልቦናና አጠቃላይ ሁኔታ ይካሄድ አይካሄድ የሚለውን የሚወስን ነው የሚሆነው፡፡

በሦስት ዓመቱ ፕሮግራም መጨረሻ (2018 ዓ.ም.) ሊካሄድ ዕቅድ ሲወጣለትም በአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ምቹ እንደሚያደርገው ተስፋ ተይዞ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የሕዝብ ቁጥር ሣይንሳዊ ዘዴ በመጠቀምና በትንበያ በመገመት እየገመተ ሲሆን፣ ይህም ትንበያ ‹‹የራሱ የሆነ ውስንነት ያለውና ብዙም የማይደገፉ›› እንደሆነ በከር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹መረጋጋት ካለ ቤት ለቤት ሄዶ መላው የአገራችንን ሕዝብ ለመቁጠር ምቹ ሁኔታ ይሰጣል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የቆጠራ ዕቅዱን ‹‹በጊዜያዊነት ይዘነዋል፣ ነገር ግን ሁኔታውን በደረስንበት የምናየው ይሆናል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ሌላኛዋ አስቻይ ሁኔታዎች ካሉ እንደሆነ ቆጠራው የሚካሄደው ፍንጭ የሰጡት ደግሞ የፕላን ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ መንግሥት በከፍተኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ቆጠራውን ማካሄድ እንደሚፈልግ ነው፡፡

‹‹ይሁንና ቆጠራው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድና [ከቆጠራው] የሚገኘው መረጃ ተዓማኒ እንዲሆን ዓለም አቀፉ መሥፈርቶች መሟላት አለባቸው›› ብለዋል ሚኒስትሯ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ፡፡

ከዚህ በፊት ሊደረግ የነበረው የሕዝብና ቤት ቆጠራ የፀጥታ ሁኔታዎች ምቹ ባለመሆናቸው ምክንያት ሊካሄድ አለመቻሉንና መተላለፉን ያስታወሱት ሚኒስትሯ አሁንም በቀጣይ በየአካባቢው ያለውን ሁኔታ አጥንተውና በቴክኖሎጂ ተደግፈው ተግዳሮቶችን በመወጣት ነው ቆጠራውን ሊያካሂዱ ያቀዱት፡፡

አንዳንዶቹን ጥናቶች መንግሥት ካካሄዳቸው አሥርት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ እነዚህን ጥናቶች ማካሄድን ሌሎች በቴክኖሎጂ መደገፍና የስታስቲስክ ልማቶችን ማካሄድ ጨምሮ በርካታ ክንውኖችን የያዘው ፕሮግራም ነው 35 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ (622 ሚሊዮን ዶላር) ገንዘብ እንደሚያስፈልገው የተገለጸው፡፡

መንግሥት 50 በመቶውን (17.4 ቢሊዮን ብር) የሚሸፍን ሲሆን፣ በአጋር ድርጅቶች (በድጋፍና ብድር) ደግሞ 40 በመቶውን (14 ቢሊዮን ብር) ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ ከተለያዩ የገንዘብ ማስገኛ ምንጮች ደግሞ አሥር በመቶውን (3.4 ቢሊዮን ብር) ለማግኘት ነው የታቀደው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች