Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ የዳያስፖራ የባንክ አገልግሎት ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ ማቅረብ በጀመረው የባንክ አገልግሎት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱንና ይህን አገልግሎቱንም የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል አዲስ የዳያስፖራ የባንክ አገልግሎት ይፋ አደረገ፡፡ 

ባንኩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ባለበት አገር ሆኖ ብድርን ጨምሮ የተለያዩ የባንክ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበትን አዲስ ፕላት ፎርም ትናንት ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርግ እንዳስታወቀው፣ ለዳያስፖራው የማኅረበሰብ ክፍል በአገር ውስጥ ብድር እንዲያገኝ ለማስቻል አመቻችቶት በነበረው አሠራር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ሰጥቷል፡፡ ይህ ብድር የተሰጠው ለተለያዩ የንግድ ሥራዎች፣ ለቤት መግዣ፣ ለመኪና ግዥና ለመሳሰሉት እንደሆነ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ድርቤ አስፋው ገልጸዋል፡፡ 

ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ ባለበት ቦታ የባንክ አገልግሎቶችን ለማመቻቸትና በኢትዮጵያ ለሚያካሂደው ኢንቨስትመንት በቀላሉ ብድር ለማመቻቸት እንዲቻልም፣ በዕለቱ ይፋ የተደረገውን አዲስ ፕላት ፎርም ሥራ ላይ ሊያውል መቻሉ ተገልጿል፡፡

እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኅብረተሰብ በአገር ውስጥ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚነቱ አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲህ ያሉ አዳዲስ የአገልግሎትና ፕላት ፎርሞች ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ተብሏል፡፡  

በውጭ ያለው ዳያስፖራ ያለበት ቦታ ሆኖ በአገር ውስጥ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶችና ሌሎች ግዥዎች የሚሆኑ ብድርን ጨምሮ፣ ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በዲጂታል የባንክ አገልግሎት በመታገዝ አገልግሎት እንዲያገኝ የተቀረፀው ይህ አዲስ ፕላት ፎርም፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በቀላሉ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ አዲስ የዳያስፖራ የባንክ አገልግሎት መስጫ ፕላት ፎርም፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የሚያገለግል ጭምር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ባንኩ በዚህ ፕላት ፎርም ጋር የተለያዩ የሪልስቴት አልሚዎች፣ የመኪና ሽያጮችና በሌሎች ቢዝነሶች ላይ የሚሠሩ ኩባንያዎችን ያስተሳሰረ ሲሆን፣ ዳያስፖራው ከእነዚህ ኩባንያዎች ሊገባቸው የፈለጋቸውን ሁሉ እንዲገዛ የሚያስችል ዕድል የሚሰጥ አሠራር መሆኑንም ተገልጿል፡፡ 

ሌሎች ኩባንያዎችንም በተመሳሳይ በማስተሳሰር፣ ባንኩ ብድር እያቀረበ ኩባንያዎቹ የሚሸጡበት ዳያስፖራውም በቀላሉ የሚገበያዩበትን ዕድል እያሰፋ እንደሚሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

ከዚህ ቀደም ባንኩ ለዳያስፖራው የባንክ አገልግሎት ሊሰጥ የቆየው ዳያስፖራው በአካል ቀርቦ ወይም በወኪል በመሆኑ፣ በተፈለገው ደረጃ አገልግሎት ለመስጠት ያላስቻለ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ድርቤ፣ አሁን ግን ካለበት ቦታ ያውም በፍጥነት አገልግሎቱን ለማግኘት እንደሚያስችለው ጠቅሰዋል፡፡ 

ትናንት ይፋ የተደረገው የዳያስፖራ የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ ከተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ የዳያስፖራ የባንክ አገልግሎት በድረ ገጽ በሚል ይጠቀስ እንጂ፣ ከተለመደው የድረ ገጽ የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ፕላት ፎርም በአካል ወይም በወኪል መቅረብ ሳያስፈልጋቸው፣ ያለ ውጣ ውረድ ካሉበት ሆነው በቀላሉ በኮምፒዩተር ወይም በእጅ ስልካቸው አማካይነት ሒሳብ መክፈትና ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸውም ነው፡፡

ባንኩ የሚሰጣቸው ሌሎች አገልግሎቶች ላይም መረጃና የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት ይህ ዲጂታል ፕላት ፎርም፣ የሒሳብ ለመክፈት ሦስት ደቂቃ ብቻ የሚጠይቅ ነው፡፡ ፕላት ፎርሙ የብድር ጥያቄዎችን፣ ስለብድሩ አከፋፈልና መቋረጥ፣ በባንኩና በደንበኛው መካከል መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያለው ‹‹ቻት ቦት›› ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የብድር አፈቃቀዱም ቢሆን በዲጂታል የሚፈጸም ሲሆን፣ አንድ ተበዳሪ የሚፈልገውን የብድር መጠን በምን ያህል ጊዜ መክፈል እንደሚፈልግና ከብድሩ ምን ያህል ወለድ እንደሚከፍል ሁሉ በቂ መረጃ የሚሰጥ ነው፡፡ የብድር መክፍያ ጊዜው ሲያጥርና ሲረዝም የሚጠየቀው ወለድ ምን ያህል እንደሆነ 24 ሰዓት ውስጥ በቂ መረጃ የሚሰጥ እንደሚሆንም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በዚህ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የዳያስፖራ ማኅበራት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ እንዲህ ያለው አገልግሎት ሊሰጥ የሚችልውን ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ ገልጸዋል፡፡      

የዳያስፖራው ኢንቨስትመንትና ሬሚታንስ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ስለመሆኑ በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ በላይነህ አቅናው፣ በአፍሪካ ውስጥ እንደ ግብፅና ናይጄሪያ ከዳያስፖራ የሚያገኙት ሬሚታንስ ምን ያህል እንደደረሰ ጠቅሰዋል፡፡ በእሳቸው ገለጻ፣ የናይጄሪያ ዓመታዊ ሬሚታንስ 20 ቢሊዮን ዶላር፣ የግብፅ ደግሞ 10 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህ የሚያመላክተው ለዳያስፖራው የሚሆን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ማመቻቸት ለሬሚታንሱ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ነው፡፡  

የኢትዮጵያ የሬሚታንስ ገቢ ከግብፅና ከናይጄሪያ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለውም አመልክተዋል፡፡ አቶ በላይነህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ዋቤ በማድረግ እንደጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በባንክ የላኩት ዓመታዊ የሬሚታንስ ገቢ አራት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የሬሚታንስ መጠኑ ይህንን ያህል ብቻ የሆነበት አንዱ ምክንያት፣ የዳያስፖራው ማኅረበሰብ በዕለቱ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ እንደተገበረው ዓይነት ዳያስፖራው በቀላሉ ሊገለገልባቸው የሚችሉ የባንክ አገልግሎት ፕላት ፎርሞች በሚፈለገው ደረጃ ካለመስፋፋት ጋር የተያዘ ነው፡፡ 

ዳያስፖራው የተሻለ አገር ከመኖሩ አንፃር እንደ እዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂዎችን በማዘጋጀት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ከተቻለ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችልም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ዳያስፖራውን የሚያመለክቱ የዲጂታል አገልግሎቶች ጊዜ የሚወስዱ ከሆነ ሊሰለች የሚችል ከመሆኑ አንፃር አገልግሎቱን በደቂቃዎች ለማግኘት የሚችልበት ዕድል ካገኘ በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚችል በመሆኑ እንዲህ ያለው ዕድል በመፈጠሩ ማኅበራቸው ያመሠግናልም ብለዋል፡፡

ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ እንዲያውቁ፣ እንዲሁም በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው እንዲሳተፉ መንግሥት ጥሪ እያደረገ መሆኑን በማስታወስም፣ የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ ዳያስፖራዎች በሚመጡበት ሰዓት እንዲህ ያለው ፕላት ፎርም መዘጋጀቱ በዳያስፖራው የሚከፈቱ አዳዲስ አካውንቶች እንዲጨምሩ ያደርጋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃም ወደ 30 ሺሕ የሚሆኑ ዳያስፖራዎች አካውንት በመክፈት 42 ሚሊዮን ዶላር ቁጠባ መቆጠባቸውን አቶ በላይነህ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ 

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 3.4 ቢሊዮን ብር የተረፈ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት 12 ሚሊዮን በላይ አስቀማጭ ደንበኞች ያሉት የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው አስቀማጮችን በማፍራት በቀዳሚነት የሚቀመጥ ነው፡፡ አጠቃላይ የካፒታል መጠኑም ከ14.9 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች