Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር“የተሻሻለው” የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት በወፍ በረር ቅኝት                       

“የተሻሻለው” የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት በወፍ በረር ቅኝት                       

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በወንድዬ ከበደ

በክፍል አንድ በቀረበው ጽሑፍ፣ “የተሻሻለው”ን የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት በወፍ በረር ቅኝት” በሚል ርዕስ ሥር አንዳንድ ነጥቦች መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ የቆየ መሆኑን፣ ከቅድመ መደበኛ ወደ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ሽግግር መደረጉ፣ በዚህ ዓመት መተግበር የጀመረው የተሻሻለው የተቀናጀ ሥርዓተ ትምህርት ስድስት ጭብጦችን አካቶ መምጣቱን፣ ከተሻሻለው ሥርዓተ ትምህርት አንፃር ምን ጨምሮ/ቀንሶ እንደመጣ በአጭሩ ለማየት ተሞክሯል፡፡ በማጠቃለያም ከተደረገው ቅኝት አኳያ፣ የተሻሻለው ሥርዓተ ትምህርት ሲለበስ ካለበት የገነገነ የአርትኦትና የይዘት ዕጭቅታ ችግር ባሻገር የተቀረፁት ጭብጦች ከሌሎች እኩያ አገሮች ጭብጦች አንፃር ሲታይ የአድማስ ጥበት ያለበት መሆኑ ተመልክቶ፣ ከወዲሁ ቢታይ የሚል ምክረ ሐሳብም ቀርቧል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱ የተቀናጀ ነው ተብሏልና በዚህስ ረገድ ያለው ነገር ምን ይመስላል? የሚለውን እንመለከታለን ባልኩት መሠረት እነሆ ቀጣይ ክፍሉ ቀርቧል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት (Theme-Based Curriculum)

ስለቅድመ አንደኛ ደረጃ የተቀናጀ ሥርዓተ ትምህርት ከማውሳታችን በፊት ትንሽ ስለጭብጥ፣ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት በተለይም የጭብጥን ምንነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ ጭብጥ ማለት የተለያዩ የመማር ተግባራትን አቀናጅቶ በማደራጀት ሕፃናትን ለማስተማር የምንጠቀምበት መንገድ ወይም ዘዴ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጭብጥን መሠረት ያደረገ የሥርዓተ ትምህርት አወቃቀር ከተለመደው የትምህርት ዓይነትን መሠረት ያደረገ (Subject-Based Curriculum) የሥርዓተ ትምህርት አወቃቀር በመሠረታዊነት የተለየ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጭብጥ፣ ተኮር አሠራር የአካዳሚያዊ ክህሎት አጠቃቀምን እንደ አስፈላጊ የሚወሰድ ነው፡፡ ማለትም በጭብጥ፣ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት አወቃቀር ውስጥ መጻፍ፣ ማንበብ፣ መሣል፣ ወዘተ. ውሰጥ የሚገኙት ሐሳቦችና ክህሎቶች የሚቀርቡት በነጠላነታቸው ወይም በተናጠል አይደለም፣ ተቀናጅተው እንጂ፡፡ በተቃራኒው የትምህርት ዓይነትን መሠረት ያደረገ ሥርዓተ ትምህርት በአጠቃላይ ትምህርትን የሚመለከተው ‹‹መማር ለመማር›› ወይም ‹‹ለፈተና ምዘና ለመቀመጥ መማር›› በሚለው ዕሳቤ መሠረት ይሆናል፡፡

የእነዚህ ቁልፍ ዕሳቤዎች መዛነቅ ነው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን በእጅጉ እያወከው የሚገኘውና ከወዲሁ ዕልባት ሊደረግለት የሚገባው፡፡ በፖሊሲ ደረጃ የተቀናጀና ጭብጥ ተኮር እንላለን፣ በተግባር ግን (አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት) ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች የሚከተሉት የትምህርት ዓይነትን መሠረት ያደረገ ሥርዓተ ትምህርት ሆኖ ይገኛል፡፡ የዚህ ችግር መንስዔዎች ብዙ ቢሆንም፣ ዋና ዋና ተብለው የሚገመቱት የሥርዓተ ትምህርቱ አወቃቀር፣ የቆየንበት የትምህርት ባህል እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ፣ የዘርፉ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ያላቸው የብቃት ውስንነት ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩ ከዚህም በላይ ሠፊና አገራዊም ስለሆነ ጠለቅ ያለ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ሲጠቃለል ሁላችንም በተማርንበት (የትምህርት ዓይነትን መሠረት ያደረገ ሥርዓተ ትምህርት) ለማስተማር እንጂ እንድናስተምርበት በሚጠበቀው (ጭብጥ መር ሥርዓተ ትምህርት) ለማስተማር በቂ ዝግጁነት ያለን አይመስልም፡፡  

ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት የተለያዩ ቅርፆች ያሉት ቢሆንም፣ ትክክለኛው ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት የነጠላ ትምህርት ዓይነት ኑባሬን ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጭብጥ ተኮር መማርን የሚከተሉ የትምህርት እርከኖች ውስጥ ነጠላ የትምህርት ዓይነቶች (ሒሳብ፣ ቋንቋ ወዘተ.) ተብሎ የሚጠቀስ ትምህርት የጎላ ትኩርት አይሰጠውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ክህሎቶችና ዕውቀቶች በጭብጦች ውስጥ ተካተው ይገኛሉ ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት በእውነታው ዓለም ሕይወት ላይ የሚተገበር ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ለሕፃናቱ የሚሰጠው ትምህርት ሕፃናቱን በማብቃት ዕውቀትና ክህሎታቸውን የሚጠቀሙ በራሳቸው፣ በማኅበረሰባቸው ብሎም በዓለም ላይ ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችል ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት እውነታዎችን እርስ በርስ የሚያስተሳስርና የውስብስብነት ባህሪም ያለው ነው፡፡ ይህም ማለት የተቀናጀ ነው፡፡ ብቁ መምህራንንም ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ስለ “አካባቢ ብክለት” ለማስተማር ከሳይንሳዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ ማኅበራዊና ግላዊ ሁኔታዎችንም ያካትታል ማለት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአብዛኞቹ የዓለም አገሮች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሥርዓቶች የሚከተሉት ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ቢሆንም አንዳንድ አገሮች “ጭብጥ” እና “የመማር ዓውድ” ሲኖራቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ሥርዓተ ትምህርታቸውን የሚያዋቅሩት “በመማር ዓውድ” ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፣ የሞሪሸስ (እ.ኤ.አ. 2013) እና የተባበሩት የታንዛኒያ ሪፐብሊክ (እ.ኤ.አ. በ2016) የቀረፁት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርቶች የመማር ዓውዶች (ሁለቱም በቁጥር ስድስት አላቸው) እንጂ ጭብጥ የላቸውም፡፡ በአንፃሩ ጋና እ.ኤ.አ. በ2019፣ ጃማይካ በ2010 ያዘጋጁት ሥርዓተ ትምህርት ጭብጥና የመማር ዓውድ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከሁለተኞቹ ትመደባለች፡፡

ጭብጥ ተኮር ሥርዓተ ትምህርት በተለይ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ዓይነት የሥርዓተ ትምህርት አወቃቀር መንገድ ወይም ዘዴ ሲሆን፣ በዚህም የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ተቀናጅተው በአንድ ጭብጥ እንዲቀርቡ የሚደረግበት ነው፡፡ ይህም ሚዛኑን የጠበቀና የአጠቃላይነት ገጽታ ያለው የመማር ተሞክሮን ይሰጣል፡፡ ይህ አቀራረብ ብዙውን ጊዜ አዲስ መጤ (Emerging) ሥርዓተ ትምህርት ተብሎ ይጠራል፣ ምክንያቱም የዚህ አተያይ መነሻውና ግቡ ከሕፃናት አጠቃላይ ፍላጎት ጋር የተዛመደ በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ከሚከተላቸው ቁልፍ መርሆች አንዱ “የተቀናጀ” መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ሥርዓተ ትምህርትን ማቀናጀት በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የሚሠራ መርህ ብቻ ሳይሆን ተማሪ ተኮር አካሄድም ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም በግንባታ የመማር ንድፈ ሐሳብ (Constructivist Theory of Learning) ትሩፋት ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ማቀናጀት በቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ምን ይመስላል? የሚለው ሐሳብ ላይ እናተኩራለን፡፡

የተቀናጀ (Integrated) የሚለው ቃል በጥሬው ሲተረጎም፣ የተለያዩ ነገሮችን በማጣመር ወይም በማዋሃድ የተስማማና ግንኙነቱ የጠበቀ ሙሉ ነገርን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ወደ ተቀናጀ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ስንመጣ የቅንጅቱ መነሻ፣ የተቀረፁት ጭብጦችና ለዚህ ማስተላለፊያ ተብለው የተዘጋጁት የመማር ዓውዶች ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት ስለቅንጅት ስናወራ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ስለጭብጥና የመማር ዓውድ እናወራለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ቅንጅት በአብዛኛው የሚወድቀው በጭብጡና በመማር ዓውዱ፣ እንዲሁም በመማር ዓውዱ ንዑሳን ክፍሎች መካከል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ የሚነሱ የተለያዩ የቅንጅት ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ፣ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት አደረጃጀት ውስጥ በድግግሞሽ የሚነሱትና የሚተገበሩት ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም፣ ውጫዊ ቅንጅት (Inter-disciplinary) እና ውስጣዊ ቅንጅት (Intra-Disciplinary) የሚባሉት ናቸው፡፡ 

ውጫዊ ቅንጅት አንድን ጭብጥ በበለጠ ጥልቀትና ስፋት መረዳት ያስችል ዘንድ ከተለያዩ የመማር ዓውዶች ጋር የሚደረገው ቅንጅት ነው፡፡ ይህ የቅንጅት ዓይነት አንድን ጭብጥ ከብዙ አቅጣጫዎች በመመልከት ለመማር የሚያስችል ነው፡፡

በአንፃሩ፣ ውስጣዊ ቅንጅት ደግሞ በአንድ የመማር ዓውድ ውስጥ የሚገኙ ንዑሳን ክፍሎችን በማቀናጀት ሕፃናቱ በዚያ የመማር ዓውድ ዙሪያ ያላቸው መረዳት የተሰላሰለና የጠለቀ ማድረግን ዒላማው ያደርጋል፡፡ ይሁንና በዘርፉ ያሉ ጠበብት እንደሚያወሱት በሥርዓተ ትምህርት ቀረፃውና በመማር ማስተማር ሒደቱ ውስጥ ከውጫዊ ቅንጅት በፊት ውስጣዊ ቅንጅት መቅደም ይኖርበታል፡፡

በአገራችን ከተዘጋጀው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት አወቃቀር አንፃር ስናየው ውጫዊ ቅንጅት የሚመሠረተው በእያንዳንዱ ጭብጥና በተቀረፁት ስድስት የመማር ዓውዶች መካከል ሲሆን ውስጣዊ ቅንጅት ደግሞ በእያንዳንዱ የመማር ዓውዶች ስር በሚገኙ ንዑሳን ክፍሎቻቸው መካከል ነው፡፡

ሁለቱን የቅንጅት ዓይነቶች ማለትም፣ በተቀረፁት የመማር ዓውዶች (Learning Areas) እና ጭብጦች እንዲሁም በመማር ዓውዶችና በሥራቸው በሚመጡ ንዑሳን ክፍሎች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ቅንጅት የተሻሻለውን የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ላይ የተመረኮዙ ምሳሌዎች ከዚህ በሚከተለው መንገድ ቀርበዋል፡፡

ምሳሌ ውጫዊ ቅንጅት         

ከላይ በቀረበው የአንድ ጭብጥ ውጫዊ ቅንጅት ሥዕላዊ ሥስል መሠረት፣ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የተመረጡት ስድስቱ ጭብጦች፣ እያንዳንዳቸው ከስድስቱ የመማር ዓውዶች ጋር ይቀናጃሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሕፃናቱ “ስለእኔ” የሚለውን ጭብጥ (በሥዕላዊ መግለጫው መካከል ላይ ይገኛል) እንዲገነዘቡ ለማስቻል ስድስቱ የመማር ዓውዶች (ጭብጡን ዙሪያውን የከበቡት) በትብብር ይሠራሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ስድስቱም የመማር ዓውዶች እንደ አግባብነታቸው ከጭብጡ ጋር ተቀናጅተው በመቅረብ ለትምህርቱ ግብ (ለጭብጡ) በጋራ ይሠራሉ ማለት ነው፡፡ 

ምሳሌ፣ ውስጣዊ ቅንጅት                                       

በሌላ መልኩ ደግኖ ውስጣዊ ቅንጅት የምንለው የመማር ዓውዶችን የተመለከተ ነው፡፡ ከላይ በቀረበው ሥዕላዊ ምሥል ላይ እንደሚታየው ከስድስቱ የመማር ዓውዶች አንዱ ብቻ ከራሱ ከመማር ዓውዱ ባህሪ በመነሳት ከንዑሳን ክፍሎቹ ጋር እንዴት እንደሚቀናጅ ያሳያል፡፡ ይህ ቅንጅት የመማር ዓውዱና የንዑሳን ክፍሎቹ ቅንጅት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ወደ ውጫዊ ቅንጅት ከመኬዱም በፊት ውስጣዊ ቅንጅት መሠራት አለበት የሚባልበትም ዋና ምክንያት፣ የመማር ዓውዶች የጭብጡ ማስኬጃዎች በመሆናቸውና በአግባቡ ካልተደራጁ በጭብጥነት የተቀመጠውን ዓላማ ለማሳካት ስለሚያስቸግር ነው፡፡

ስለዚህ አግባብነት ያለውንና ተጠየቃዊና ሳይንሳዊ የሆነውን የመማር ዓውዱን ባህሪ ተከትሎ፣ ከቀላል ወደ ከባድ፣ ከቅርብ ወደ ሩቅ፣ ከሚታወቅ ወደ ማይታወቅ ወዘተ. በሆነ መንገድ መደራጀት አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር ከላይ የቀረበውን ምሳሌ ብንመለከት፣ በአገራችን በተደራጀው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ “ቋንቋና ተግባቦት” አንድ የመማር ዓውድ ነው፡፡ ይህ ዓውድ በውስጡ አራት ንዑሳን ክፍሎችን ይይዛል፡፡ እነዚህም “ማዳመጥ፣ ንግግር፣ ማንበብና መጻፍ” ናቸው፡፡ እነዚህ ንዑሳን ክፍሎች ለሕፃናቱ ሲቀርቡ የትኛው ቀድሞ የቱ ይከተላል? በምን መንገድ ይቀርባል? አንዱ ከሌላው ጋር ምን ግንኙነት አለው? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ቁልፍ ጉዳዮች የምናቀናጅበት መንገድ ነው ውስጣዊ ቅንጅት የምንለው፡፡

እንግዲህ ከላይ ከቀረበው አጭር ማብራሪያ እንደምንገነዘበው ቅንጅት የሚለው ፅንሰ ሐሳብና አሠራር በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በአዲስ መልክ እየመጣ ያለና ብዙም ተሞክሮ ያልተወሰደበት ብቻ ሳይሆን፣ ውስብስብም ጭምር ነው፡፡ ከዚህም በላይ አንድም፣ በዚህ ዘርፍ በቂና ብቁ መምህራን የሉንም፣ ሁለትም የተዘጋጀው የመምህሩ መምሪያም ቢሆን መምህራኑ ያለባቸውን እጥረት ከግንዛቤ አስገብቶ ጭብጦችንና የመማር ዓውዶችን እንዴት አድርገው አቀናጅተው እንደሚያስተምሩ አይገልጽም፣ በምሳሌም አያሳይም፡፡

እነዚህ ቁልፍ የቅድመ ትግበራ ሒደቶች ሳይታለፉ ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቶ ከሆነ የተሻሻለው ሥርዓተ ትምህርት ተፈጻሚነት በአጠያያቂ ሁኔታ ላይ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ በቀደመው ጊዜ የነበረ አንድ ቀልደኛ ካድሬ፣ “የት እየሄድክ ነው?” ቢሉት፣ “ተውኝ እባካችሁ ያልገባኝን ላልገባቸው ላስረዳ ነው” እንዳለው ዓይነት ብሂል እንዳይሆን ከወዲሁ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከቅንጅት አኳያ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ምን ይመስላል? የሚለውን በቀጣይ እመለስበታለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የትምህርትና ሥራ አመራር ኮንሰልታንት፣ እንዲሁም የዮናክ የትምህርት ማማከርና ሥልጠና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው wondataww@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...