Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወረርሽኞችን ለመከላከል የ113 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ወረርሽኞችን ለመከላከል የ113 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ቀን:

  • ክትባት ለሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ወረርሽኞችን ለመከላከል፣ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችልና አቅምን ለማጠናከር ያለመ የ113 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡

ፕሮጀክቱ በዋናነት የላቦራቶሪና የባለሙያ አቅምን የማጠናከር፣ የቅኝትና ዳሰሳ ተግባሮችን መሠረት አድርጎ ለሦስት ዓመታት በጤና እና በግብርና ሚኒስቴሮች የሚሠራ ይሆናል፡፡

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ለሆነው ፕሮጀክት ማከናወኛ ከተያዘው በጀት ውስጥ 50 ሚሊዮን ዶላሩን የሸፈነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ፓንደሚክ ፈንድ ሲሆን፣ የቀረውን 63 ሚሊዮን ዶላር የሰጡት ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የምግብና እርሻ ድርጅት እንዲሁም ዩኒሴፍ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ፓንደሚክ ፈንድ በዓለም ደረጃ የተቋቋመው፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ አገሮች ከመከላከል ጀምሮ ወረርሽኞችን ቶሎ ለይቶ ጠንካራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ለማስቻል እንደሆነ ያስታወሱት፣ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡  

ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፉ የፓንደሚክ ፈንድ ለማግኘት ኢትዮጵያን ጨምሮ አገሮች የተሳተፉበት በወረርሽኝ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህም ውድድር የጤናና የግብርና ሚኒስቴሮች በመተባበር ያዘጋጁት ትልመ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለውድድር ቀርቦ በማሸነፉ ድጋፉን ለማግኘት ተችሏል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ወረርሽኝ ከሰው ወደ እንስሳትና ከእንስሳትም ወደ ሰው የመተላለፍ አቅሙ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ሁለቱ ሚኒስቴሮች በጋራ መሥራታቸው ወረርሽኞችን በመከላከል፣ በመለየትና ምላሽ በመስጠት በኩል ፍሬያማ ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት፣ ሥልጠናዎችን የመስጠት፣ የእንስሳት በሽታዎች ሲከሰቱ በቅድሚያ የመለየትና ምላሽ የመስጠትን አቅም የማጠናከር፣ የላቦራቶሪዎችን አገልግሎቶች የማጠናከርና ተደራሽነታቸውንም ማስፋፋት በፕሮጀክቱ መካተቱን ጠቁመዋል፡፡

የእንስሳት ምርትና ተዋጽኦ ጥራታቸውና ደኅንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች በማቅረብ ረገድ ፕሮጀክቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ክትባት ለማምረት የሚያስችልና ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት የሚደረግበት፣ የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተቀምጧል፡፡

ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተገኘው ትምህርት የጠንካራ የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማትና ክትባት የማምረት አቅምን አስፈላጊነት አጉልቶ ማሳየቱን የጠቆሙት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ በዚህም ምክንያት ሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ በነሐሴ 2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በይፋ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ ተቋቁሟል ብለዋል። አክለውም የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ መመሥረት አሁን ባሉትና ወደፊት ለሚመጡ የጤና ሥጋቶች የመከላከል አቅምን ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

‹‹ክትባት ለማምረት ስንጀምርም ከባዶ የተነሳን ሳይሆን አገራችን ያላትን ክትባት የማምረት ዕውቀትና ልምድ መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህም ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ተቋም የእንስሳት ክትባትን በማምረት ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ያለውና ከአገርም ባለፈ ለበርካታ አገሮች ኤክስፖርት የማድረግ ልምድ እንዳለው መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የእብድ ውሻ በሽታን (ሬቢስ) መከላከል የሚያስችል ክትባት የማምረት አቅምና የረዥም ጊዜ ልምድ እንዳለው ገልጸው፣ ከዚህ አገራዊ ነባር ዕውቀት፣ ልምዶችን በማዋሃድና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት የአገሪቱን የጤና ፍላጎት ማሟላትና ለቀጣናውና ለአኅጉሪቷ የበኩሉን አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ፋብሪካው ወቅቱን የጠበቀ፣ የመልካም አመራረት ሥርዓትን የሚያሟላ ተቋም ሆኖ እንደሚገነባ፣ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2026 መገባደጃ ላይ ክትባት የማምረትና የማሸግ፣ በ2027 መጨረሻ የክትባት መድኃኒት ንጥረ ነገር ሙሉ ለሙሉ የማምረት ተግባር እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ሥራ ለማቀላጠፍ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ውጤታማ ሥራዎችን መተግበር መጀመሩን ጠቁመው፣ ከዚሁ አኳያ የተያዘው ዕቅድ በአፍሪካ ሲዲሲ ከተነደፈው አኅጉራዊ ስትራቴጂ ዕቅድ ጋር የተጣጣመና ለዚህም አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ሚኒስተር ዑስማን ዲዮን  የዓለም ባንክ የሚያደርገውን ዕገዛና  ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው የሚገነባው ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...