Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በውጭ አገሮች የሚጠፉ መርከበኞች የአዲስ ሥራ ፈላጊዎችን ዕድል እየዘጉ ነው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ውስጥ ሠልጥነው በውጭ አገር መርከቦች ተቀጥረው የሚሠሩ መርከበኞች እየጠፉ በመሆናቸው ምክንያት፣ የአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎችን ዕድል እየዘጉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ሲያቀርብ ነው፡፡

መርከቦች ወደብ ከደረሱ በኋላ ጥለው በሚጠፉ ኢትዮጵያውያን መርከበኞች ምክንያት ቀጣሪ ኩባንያዎች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ማስታወቃቸውን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ መርከብ ጥለው በሚጠፉ ባለሙያዎች ምክንያት በአገር ላይ ትልቅ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሥራ ላይ እንዳሉት የመርከብ ሠልጣኞች ሁሉ በተመሳሳይ ባለሙያዎችን አሠልጥነው የማሰማራት ፍላጎት ያላቸው የመርከብ ወኪሎች፣ ከውጭ መጥተው እንዳይሠሩ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡

ለወደፊት ሠልጥነው በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን መርከበኞች በተሻለ ደመወዝ እንዳይቀጠሩና የሥራ ቦታ አማርጠው እንዳይሠሩ፣ በየደረሱባቸው ወደቦች የሚጠፉ መርከበኞች ከራሳቸው በተጨማሪ የብዙ ሰዎችን እንጀራ እየዘጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሪፖተር ለምን ይጠፋሉ በማለት ጥያቄ ያቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ፣ የመጀመሪያው ቅሬታ ደመወዝ ያንሰናል የሚል ቢሆንም፣ ደመወዝ ስለሚያንሳቸው ነው የሚለው አሳማኝ አይደለም ብለዋል፡፡

ብዙ ጊዜ ከ3,000 ዶላር በላይ የወር ደመወዝ የሚከፈላቸው ቢሆንም፣ እነዚህ ባለሙያዎች ከጅምሩ አሠልጥነው ለላኳቸው ወኪሎች ለወጭ መጋራት በተስማሙት መሠረት ሥራ ሲጀምሩ ከደመወዛቸው መቀነስ ሲጀምር፣ ‹‹ደመወዝ አነሰን›› በማለት ሥራቸውን እንደሚተው ተናግረዋል፡፡

ማሪታይም ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጋር መርከበኞችን በጋራ ለማሠልጠን መስማማቱን በማስታወቅ፣ በአገር ውስጥ በባህር ዳር፣ በባህር ሎጂስቲክስ ተቋምና በሌሎች በግል ተቋማት ሥልጠና ይሰጣል ብሏል፡፡ እስካሁን ከ5,000 በላይ የመርከብ ካፒቴኖችና ሌሎች ባለሙያዎች በተለያዩ አገሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ወደ ሥራ በገቡ በስድስትና በስምንት ዓመታት ወደ ካፒቴንነት አድገው 10,000 ዶላር ድረስ ማግኘት የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እያላቸውና ባለሙያ ሆነው መቀጠል ሲችሉ፣ በድንገት ወደብ ላይ በመጥፋት ራስን ከሥራ ውጪ ማድረግ የማይጠቅማቸው በመሆኑ ባለማወቅ የሚፈጸም ውሳኔን ለመቀነስ ከወዲሁ ከመሄዳቸው በፊት ሥልጠና በመስጠትና ችግሩን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ወደፊት ትልልቅ የመርከብ ድርጅቶች የኢትዮጵያ የመርከብ ባለሙያዎችን አንቀበልም ቢሉ አገር የምትጎዳ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የባህርና የባቡር ትራንስፖርትን በማስተሳሰር የመንገዶኞች አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት አሠራር ተዘጋጅቶ መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ለማስፋፋት በባሮ ወንዝ ላይ ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ጥናት ተሠርቶ በጀት ማፈላለግ መጀመሩ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች