Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ157 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ድጎማ መታገዳቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በነዳጅ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አይቻልም ተብሏል

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አጠቃቀምን በተመለከተ በሁሉም ክልሎች በተደረገ የክትትል ኦዲት፣ አገልገሎቱን ለማግኘት ከተመዘገቡ 242 ሺሕ ተሽከርካሪዎች መካከል ከ157 ሺሕ በላይ መታገዳቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሲያቀርብ ነው፡፡

ድጎማ ለማግኘት ምዝገባ ባደረጉ ተሽከርካሪዎች ላይ ያለውን አጠቃላይ አሠራር ለማጣራት በተደረገው ኦዲት፣ ክልሎች ድጎማ ይገባቸዋል ያሏቸውን ተሽከርካሪዎች ለይተው እንዲመዘግቡ ቢጠበቅባቸውም፣ ያልተሟላ መረጃ በመገኘቱና ተሽከርካሪዎች ወቅታዊ የሆነ የሥምሪት መርሐ ግብር ላይ መሆናቸው ባለመረጋገጡ፣ 157 ሺሕ ተሽከርካሪዎች በጊዜያዊነት እንዲታገዱ መደረጉን፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የነዳጅ ድጎማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሱሌማን መሐመድ ተናግረዋል፡፡

የድጎማ ተጠቃሚ ለሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚመለስላቸው ተመላሽ ገንዘብ መጠን ሥርዓቱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ለሰባት ጊዜያት የድጎማ ተመላሽ ማስተካከያ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ለድጎማ ተጠቃሚነት ከተመዘገቡት 241,081 ተሽከርካሪዎች መካከል እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የነበሩት 227,370 መሆናቸውን፣ ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በተደረገ ኦዲት 157,205 ተሽከርካሪዎች በጊዜዊነት መታገዳቸውን፣ 16 ሺሕ ተሽከርካሪዎች በቋሚነት ዕገዳ እንደተደረገባቸው፣ 70,165 ተሽከርካሪዎች ደግሞ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ናቸው ተብሏል፡፡ በጊዜዊነት ስለታገዱት ተሽከርካሪዎች ክልሎች አቤቱታ እያቀረቡ በመሆኑ ማጣራት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

የድጎማ ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች በሁለት ምድብ መደልደላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የመጀመሪያውና አረንጓዴ የተሰኘው ምድብ የሚገኙት የድጎማ ተመላሽን ወደ ኅብረተሰቡ በተሻለ መንገድ የሚያስተላልፉ ናቸው ተብሏል፡፡ እነሱም የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች፣ የከተማና ፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቡሶች ሲሆኑ የድጎማ ተመላሻቸው በየስድስት ወራት እየተከለሰ በተቀመጠው መርሐ ግብር መሠረት ከድጎማ ውጪ የሚሆኑ ናቸው ተብሏል፡፡

ሁለተኛውና በቀይ ምድብ የሚገኙት፣ መለስተኛ የከተማ ታክሲዎችና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በሚጠበቀው ልክ የሚያገኙትን ድጎማ ወደ ኅብረተሰቡ የማያስተላልፉ ተብለው የተመደቡ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድጎማ እንዲወጡ ለማድረግ በሰባተኛው ዙር ማስተካከያ አነስ ተደርጎ ድጎማው እንዲስተካከልላቸው መደረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

የድጎማ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ከተጀመረ ወዲህ በተሽከርካሪዎች የተካሄደው ግብይት 109 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ለድጎማ ተጠቃሚ ለሆኑ ተሽከርካሪዎች 28 ቢሊዮን ብር ተመላሽ የተደረገ መሆኑን፣ ባለፉት ስድስት ወራት 55 ቢሊዮን ብር ግብይት ተካሂዶ 11 ቢሊዮን ብር ለተጠቃሚዎች ተመላሽ ስለመደረጉም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ዓለሙ (ዶ/ር) ማናቸውም የቤት አውቶሞቢሎች የኤሌክትሪክ ካልሆኑ በቀር ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል፡፡

ውሳኔው የተላለፈው ኢትዮጵያ ነዳጅ የማታመርትና በጣም ውስን በሆነው የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ገዝታ የምታስገባ ስለሆነች፣ እንዲሁም ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ የሚመረት በመሆኑና ዋጋውም ከነዳጅ ጋር ሲነፃፀር ርካሽ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት አቀንቃኝና በትኩረት የምትሠራ አገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በብዛት በመኖራቸው ሊገጥም የሚችል ችግር እንደሌለ ስለታመነበት፣ በከተሞች አካባቢ በቀላሉ መንቀሳቀስ ስለሚቻልና የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ መሠረተ ልማት በቶሎ መገንባት ስለሚቻል ውሳኔው መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ማንኛውም አካል የግል መገልገያ አውቶሞቢል ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ቢፈልግ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አገልግሎት በዚህ መሠረት የተቃኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰሞኑን አልሰማንም በሚል የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪ ገዝተው የሚመጡ አካላት በመኖራቸው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም ወደ ኢትዮጵያ የቤት አውቶሞቢል ማስገባት ለሚፈልግ ሁሉ መልዕክቱ እንዲደርስ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የግል አውቶሞቢሎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ቢከለከልም፣ በተለየ መንገድ ለምሳሌ በተመላሽ ዳያስፖራዎችና በመሰል ጉዳዮች በሚሸራረፉ አሠራሮች ምክንያት ነዳጅ ተጠቃሚ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ይገቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከኅዳር 2016 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የ100 ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በተደረገበት ጊዜ የግል አውቶሞቢሎች ከኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በማንኛውም ዓይነት ምክንያት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንደማይቻል፣ ለዚህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ ተብሎ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች