Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ አለመከልከሉን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ነዳጅ የሚሠሩ አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ መከልከሉን ተናግሯል

በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ አለመከልከሉን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊ ተናገሩ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ እንደገለጹት፣ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ እንዳደይገቡ በመከልከል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲገቡ የሚፈቅድ ምንም ዓይነት መመርያም ሆነ ውሳኔ የለም፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እየተከናወነ ያለው ሥራ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ለማበረታታትና በነዳጅ የሚሠሩት ደግሞ በብዛት እንዳይገቡ ተስፋ ለማስቆረጥ፣ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ የተደነገገበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ዋሲሁን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማገድ በዓለም የንግድ ድርጅት ሕግ መሠረት የማይቻል በመሆኑ፣ የአገሪቱን የቀረጥ ሥርዓት በመጠቀም ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚጠቅሙትን ማበረታት፣ ጎጂ የሆኑትን ደግሞ እንዳይስፋፉ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው ወደ አገር እንዳይገቡ ክልከላ ከተደረገባቸው 38 ምርቶች ውስጥ ተሽከርካሪዎች ይገኙበታል፡፡ ከሞተር ነክ ምርቶች የቤት አውቶሞቢሎችና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ይህ ዕገዳ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን አላካተተም ነበር፡፡

ይህ ዕገዳ ከወጣ ከወራት በኋላ ነሐሴ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ተፈርሞ ለሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ለኮሚሽኑ ዲፓርትመንቶች በተላለፈ ደብዳቤ መሠረት ‹‹የውጭ ምንዛሪ ክልከላ የተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች ከክልከላ በፊት የተሰጠ የቆየ ባንክ ፈቃድን በባንኮች በኩል በማራዘምና በስም ተመላሽ ግለሰቦች ስም ተሽከርካሪዎች በብዛት ወደ አገር እየገቡ መሆኑ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ክልከላ የተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች በማንኛውም መንገድም ሆነ በፍራንኮ ቫሉታ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፓርላማው የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ በኢትዮጵያ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት፣ በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ አውቶሞቢሎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ነዳጅ ለማስመጣት የምትጠቀመው የውጭ ምንዛሪ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ፣ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከነዳጅ ኃይል ይልቅ አዋጭ ስለመሆኑ ውሳኔው መተላለፉን ተናግረዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርህን በምትደግፍበት ወቅት በመሆኑ የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ የሚደረግ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለው፣ ‹‹የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዳቸውን አልሰማንም›› በሚል ምክንያት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ማንኛውም ነጋዴም ሆነ ግለሰብ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ማስገባት የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ብቻ እንዲያስገባ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አገልግሎት የሚሰጠው በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ አቶ ዋሲሁን በበኩላቸው፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አማካይነት ለፓርላማ ስለቀረበው ጉዳይ ምንም እንደማያውቁ በመግለጽ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ በስፋት እንዲገቡ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

አዋጁ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የአምስት በመቶ ኤክሳይስ ታክስ፣ እንዲሁም ተበታትነው ገብተው በአገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ ደግሞ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚያስችል ነው፡፡ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንደሚጠቀሙት የነዳጅ ፍጀታ መጠን አሥር በመቶና ከዚያ በላይ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የኤክሳይስ ታክስ አዋጁን ነጋዴዎች ተግባራዊ ማደረግ የሚጀምሩት፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት 38 የተለያዩ ምርቶች የባንክ ፈቃድ (Letter of Credit) እንዳይከፈትላቸው የሚከለክለው ዕገዳ ከተነሳ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉ ተሽከርካሪዎች ክልከላው ከመደረጉ በፊት ተከፍቶ በነበረ ኤልሲ እንጂ፣ በልዩ ሁኔታ ተፈቅዶላቸው የሚያስገቡ ነጋዴዎች የሉም ብለዋል፡፡

ዕገዳው ካልተነሳ በስተቀር ለንግድ ወይም ለመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ዕውቅና ብቻ እንደማይገቡ አቶ ዋሲሁን ገልጸዋል፡፡

ክልከላው የማይመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGO) ቢሆኑም፣ በነዳጅ የሚሠራ ተሽከርካሪ በሚያስገቡበት ወቅት በኤክሳይስ ታክስ ተስተናግደው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፓርላማ የተሰጠውን ማብራሪያና ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘውን መረጃ በተመለከተ ከትራንስፖርትና ሎጂስትክስ ሚኒስቴር ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት ጥረት ተደርጓል፡፡ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ኃላፊ ዕገዳው በመመርያ ወይም በውሳኔ የተገለጸ አይደለም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በተደረገ ግምገማ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት፣ በነዳጅ የሚሠሩ የቤት አውቶሞቢሎች እንዳይገቡ መከልከሉን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በብሔራዊ ባንክ የወጣው ውሳኔ በመሆኑ፣ ውሳኔው በተዘዋዋሪ በነዳጅ የሚሠሩ አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ የተከለከለው፣ አሁን አዲስ በተሰጠ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ብቻ አይደለም ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጉምሩክ ኮሚሽን ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች