Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተማሪዎች የሚሹት ምገባ

ተማሪዎች የሚሹት ምገባ

ቀን:

በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ፣ እንዲያቋርጡና ጥሩ ውጤት እንዳያስመዘግቡ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል ርሃብ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።

ረሃብ ታዳጊ ተማሪዎች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ችግሩን የበለጠ አጉልቶት ለትውልድ የሚሸጋገር ዕዳ መሆኑ አይቀርም። ይህንን ችግር ለመቅረፍም በርካታ የአፍሪካ አገሮች ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ይተገብራሉ፡፡ ኢትዮጵያም አንዷ ናት፡፡

ተማሪዎች የሚሹት ምገባ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ፎቶ ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ
ኤጀንሲ

በኢትዮጵያ የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም በልማት ፖሊሲ ተካቶ ወደ ተግባር ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መካተታቸውን በ2015 ዓ.ም. የአፍሪካ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የምገባ ቀን ሥነ ሥርዓት ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) መናገራቸው ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ በበኩሉ፣ በ2016 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማና በሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 176 ትምህርት ቤቶች ከ750 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ እየቀረበላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ በጀት የተያዘለት የአዲስ አበባው የምገባ ፕሮግራም፣ ለተማሪዎች ምግብ ከማቅረብ ጋር ተያይዞ ከ16 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ፣ የአዲስ አበባ ምገባ ኤጀንሲ የምግብ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ስንታየሁ ማሞ ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎች የምገባ አገልግሎት በርካታ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ሲያደርግ፣ በችግር ውስጥ ሆነው ለሚያስተምሩ ወላጆችም ትልቅ ዕፎይታን መፍጠሩ ሲነገር ቆይቷል፡፡

በዚህም ከትምህርት ቤት የሚቀሩና የሚያረፍዱ፣ ዝቅተኛ ውጤት የሚያስመዝገቡ ተማሪዎች ቁጥር መቀነሱን የተናገሩት ወ/ሮ ስንታየሁ፣ ለቀጣይነቱም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ እንደ አገር እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት በእጅጉ እየፈተናቸው እንደሚገኝ፣ ለአንድ ተማሪ በቀን ሁለቴ ለመመገብም 23 ብር እንደተመደበ አክለዋል፡፡

ኤጀንሲው ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ ቢሆንም፣ በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ የሚያደርጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ዕርዳታ በማቋረጣቸው ፕሮግራሙ ችግር እየገጠመው መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ  (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥርዓተ ትምህርት ያስፈልጋል?›› በሚል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ሚኒስትሩ ስለተማሪዎች ምገባ ባነሱት ሐሳብ፣ ሁሉንም ተማሪዎች መመገብ ቢፈልጉም፣ ከሚጠይቀው ከፍተኛ በጀት አንፃር እንደማይቻል፣ በጀት ከመንግሥት ከተገኘ በሚልም እየሞከሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለተማሪዎችና ለወላጆች ትልቅ እፎይታን እንደፈጠረ የሚነገርለት የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም፣ እንደ አገር በተከሰተው የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የተናገሩ የአንድ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

አንድ እንጀራ ከ20 ብር በላይ በሆነበት ወቅት ሽንኩርት በኪሎ መቶ አርባና መቶ ሃምሳ ተገዝቶ አንድን ተማሪ በ23 ብር በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ በጣም አስቻጋሪ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ እናቶች ወጪውን ለማብቃቃት በሚያደርጉት ጥረት አንዳንድ ጊዜ ምግቡ ከሚፈለገው ጥራት ዝቅ ማለቱ እንደማይቀር ያክላሉ፡፡

የምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲያስመዘግቡ ጥሩ ዕድልን የፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለተማሪዎች እየቀረበ ያለው በጀት ከኑሮ ውድነቱ ጋር አብሮ የማይሄድ፣ ከምግብ ባሻገር ሌሎች የመመገቢያ አዳራሽን ጨምሮ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት መኖሩ ሥጋት ላይ እንደጣላቸው ገልጸዋል፡፡

ችግሩን በራሳቸው ለመፍታት እየሞከሩ መሆኑን፣ በዚህም የመመገቢያ ሳህን ዕገዛ ወላጆች እያደረጉ ስለመሆናቸው አክለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የተማሪዎች የደንብ ልብስና ደብተር በወቅቱ ካለመድረሱም በላይ የደንብ ልብሱ በልካቸው የማይሰፋ በመሆኑ፣ ከመጠን በላይ ሲጠባቸው ወይም ሲሰፋቸው ማየታቸውንና በርካታ ተማሪዎችም እንደገና በራሳቸው ወጭ እያሠሩ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ዳይሬክተሩ ሌላው ከባድ ችግር ሆኖብናል ያሉት፣ በትምህርት ቤታቸው በቂ የመብራት ኃይል ባለመኖሩና እንጀራ መጋገር ባለመቻላቸው እንጀራ ከውጪ በግዥ ማምጣታቸውን ነው፡፡

ይህ ደግሞ የእንጀራውን ጥራት ከማጓደሉ ባሻገር ከፍተኛ ወጭን የሚያስከትል በመሆኑ መፍትሔ እንደሚያስፈልገውም ያክላሉ፡፡

ከጥራት መጓደል ጋር ተያይዞ ከጋጋሪ እናቶች ጋር በተደጋጋሚ ጭቅጭቅ እንደሚፈጠር፣ ካለው የበጀት ሁኔታ በመነሳት ውሳኔ ለመወሰን መቸገራቸውንም ይናገራሉ፡፡

በየጊዜው በሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ፈታኝ ቢሆንም፣ ከተማ አስተዳደሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ እየሠራ መሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ  ወ/ሮ ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር ላይ የአንድ ተማሪ የቀን ፍጆታ ከነበረበት 20 ብር ሦስት ብር በመጨመር ወደ 23 ብር ከፍ እንደተደረገ አስታውሰው፣ በየጊዜው እየጨመረ ካለው የዋጋ ንረት በመነሳት በቀጣይ ምን ያህል ብር እንደሚጨመር ባይገለጽም፣ በቅርቡ ገበያውን ያማከለ ጭማሪ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ለጭማሪው ጥናት እንዳደረጉ፣ በጥናቱ ላይም የዋጋ ንረቱን እናቶች እየተቋቋሙት እንዳልሆነ መመላከቱን፣ የጥናት ውጤቱንም ለከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ማቅረባቸውን አክለዋል፡፡ ካቢኔው የጥናቱን ውጤት አይቶ ውሳኔ ሲያሳልፍና ሲያፀድቀው ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናልም ብለዋል፡፡

ዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ብቻ በቂ አይደለም የሚሉት ወ/ሮ ስንታየሁ፣ የእናቶችን ሸክም ሊቀንሱ የሚችሉና እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ልዩ ልዩ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡

ለዚህም እንደ ዱቄት፣ ዘይትና ቅንጬ የመሳሰሉትን ግብዓቶች በቀላሉ እንዲያገኙ ከአምራቾች ጋር በቀጥታ የገበያ ትስስር እየፈጠሩላቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሸገር ዳቦ ብቻ በየቀኑ 20 ሺሕ ዳቦ እያቀረበ መሆኑን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ከንግድ ቢሮ ጋር በመሆን በየ15 ቀን ከአምስት ሺሕ በላይ ጀሪካን ዘይት እንዲሁም ከ20 ሺሕ ኩንታል በላይ ዱቄት እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በየትምህርት ቤቶቹ የውኃ፣ የመብራትና የምግብ ማብሰያና መመገቢያ አዳራሾች ችግር መኖሩን ተናግረው፣ ለችግሮቹም መፍትሔ በማፈላለግ ላይ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡

በሚቀርቡ ምግቦች ላይ ስለሚነሳው ጥራት ችግር ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ስንታየሁ፣ ምንም እንኳን ቁጥጥርና ክትትል ቢደረግም፣ በአንዳንድ ማኅበራት የሥነ ምግባር ጉድለት መኖሩ እንደማይቀር፣ ያልተገባ ትርፍ በመፈለግ በተማሪዎች ምግብ አቅርቦት ጥራት ያጓደሉ ከስድስት በላይ ማኅበራት ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በማኅበራት ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ወ/ሮ ስንታየሁ፣ የሥነ ምግባር ጉድለት በሚያሳዩ ማኅበራት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን አክለዋል፡፡

‹መንግሥት አርበኛ እናቶች ብሎ አሰባስቦ ሥራ ካስጀመረን በኋላ የኑሮ ውድነቱን የምንቋቋምበት አሠራር አልዘረጋም፤›› በማለት ቅሬታ ያቀረቡት ደግሞ ስማቸው እንዳይጠቀስ የተናገሩ በተማሪዎች ምግብ ማብሰል ሥራ ላይ የተሰማሩ እናት ናቸው፡፡

ለአንድ ተማሪ በ23 ብር ቁርስና ምሳ የማቅረብ ኃላፊነት የእነዚህ እናቶች ነው፡፡ በተመደበላቸው 23 ብር አንድን ተማሪ ካስተናገዱ በኋላ አንድ ብርም ሆነ ሁለት ብር የተረፈውን በጋራ አጠረቃቅመው እንደሚወስዱ የተናገሩት እኝህ እናት፣ ትርፍ ሳይገኝ ሲቀር ከተማሪዎች ጋር ቁርስና ምሳቸውን ተመግበው እንደሚሄዱ ገልጸዋል፡፡

‹‹የበላይ አካላት እኛን ሊያስቡን ይገባል፣ ‹‹23 ብር በውጭ ሻይና ዳቦ አያበላም ነገር ግን የምንሠራው ለልጆቻችን ብለን ነው›› ይላሉ።

ምግብ የሚያበሉት በሳምንት አንድ ቀን ቁርስ ላይ የሚቀርበውን አንድ ዕንቁላል 12 ብር ገዝተውና ዳቦ በሰባት ብር በማውጣት መሆኑን፣ ምሳ ሲጨመር ከስረው እንደሚቀሩ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...