Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከሰማንያ ዓመታት በኋላ በአገር ውስጥ ዕውን የሆነው የመጨረሻው ዜና መዋዕል

ከሰማንያ ዓመታት በኋላ በአገር ውስጥ ዕውን የሆነው የመጨረሻው ዜና መዋዕል

ቀን:

‹‹የዳግማዊ ምኒልክና የልዑል አቤቶ ኢያሱን የግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ታሪክ የጻፉ የአገራችን ሰዎችና የውጭ አገር ሰዎችም እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሠሩትን ሁሉ ታሪካቸውን ዜና መንግሥታቸውን የጻፉት ሁሉ በታሪከኞች ዘንድ ፈጽሞ የታመነ ነውን? በሥርዓትስ ተጽፏልን? የሚሉ አሉ፡፡

ከሰማንያ ዓመታት በኋላ በአገር ውስጥ ዕውን የሆነው የመጨረሻው ዜና መዋዕል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ

‹‹እውነት ነው ፍርሐትና አድሏዊነት ካለ ታሪክ እውነት ሊሆንና ሊታመንበት አይችልም፡፡ እኔ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ ከጥንት አሠረ ታሪክ ተከታትዬ ሳለሁ ሁሉንም በእውነት በተራው አድላዊነትንና ፍርሓትን ሳልቀላቅል ራሴ የማውቀውን የዓይን ምስክር በመሆን፣ የማላውቀውን የዓይን ምስክር ለታሪኩ ቅርብ ከሆኑ እውነተኛ ሰዎች እየጠየቅሁ እንድጽፍ ስለታዘዝኩ ዜና መንግሥት ዕቅድ አመራር እጽፍ ዘንድ ፈተንሁ፡፡ የታሪኩንም ሥነ ሥርዓት በ፲፱፻፩ [1901] ዓ.ም. በእግዚአብሔር አጋዥነት ጽፌው ነበር፡፡

‹‹ነገር ግን በ፲፱፻፳፰ [1928] ዓ.ም. ኢትዮጵያን ኢጣልያ በአጥቂነት ገብተው መጻሕፍቱንና ሊቃውንቶቹንም ባጠፉ ጊዜ በመጀመሪያ የጻፍኩት ታሪክ ጠፋ፡፡  አሁን ግን በ፲፱፻፴፯ (1937) ዓ.ም. ድጋሚ እጽፍ ዘንድ ታዘዝኩ፡፡ የፊተኛው ኮፒ ከጠላት ሠውሬ ስለተገኘ በዚያው በፊተኛው ልክ አዘጋጅቼ መስከረም ፩ ቀን ፴፯ ዓ.ም. በታሪክና በቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽሕፈት ቤት አዘጋጅቼ አስረከብኩ፡፡››

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህን ከ80 ዓመታት በፊት በጻፉት እሳቸው ‹‹የታሪክ ማስታወሻ›› ብለው የገለጹት፣ በጀርመን በታተመው ኢንሳይክሎፔዲያ ኤትዮፒካ አገላለጽም፣ ለስድስት ምዕት ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያን ነገሥታት የታሪክ ድርሳን ‹‹ዜና መዋዕል›› የመጨረሻው ጸሐፊ የተባሉት አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ (1887-1962) ናቸው፡፡

አለቃ ገብረ እግዚብሔር ከቤተ ክህነት ትምህርት ቅኔን፣ ሥዕልና ሐረግን ቁም ጽሕፈትንና ድጉሰትን አጥንተው ተመርቀዋል፡፡ የቤተ መንግሥት ሥርዓትና የታዛዥነትን ሕግንም በሚገባ መማራቸው በገጸ ታሪካቸው ተከትቧል፡፡

የታሪክ ማስታወሻቸው ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት ሞልቬር፣ “PROWESS, PIETY AND POLITICS THE CHRONICLE OF ABETO IYASU AND EMPRESS ZEWDITU (1994) በሚል ርዕስ በጀርመን አሳትሞታል፡፡

ከሰማንያ ዓመታት በኋላ በአገር ውስጥ ዕውን የሆነው የመጨረሻው ዜና መዋዕል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሞልቬር ያሳተመው ከአማርኛው ጋር የእንግሊዝኛውን ትርጉምና የግርጌ ማስታወሻ፣ እንዲሁም የጸሐፊውን የሕይወት ታሪክ በመጨመር ነው፡፡

ከሠላሳ ዓመታት ቆይታ በኋላ ዘንድሮ (2016) በዓባይነህ አስፋው አዘጋጅነት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ የልጅ ኢያሱ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና የተፈሪ መኰንን ታሪክ (ከ1901 እስከ 1923) በሚል ርዕስ ታትሞ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡

አዘጋጁ በመቅድማቸው እንደገለጹት፣ አለቃ ገብረ እግዚአብሐር ‹‹የሕይወት ማስታወሻ›› በሚል ርዕስ የዘገቡልን የታሪክ መጽሐፍ በዘመኑ ኖረው ያዩትን በጆሯቸው የሰሙትን፣ ታላላቆቻቸውን ጠይቀው የተረዱትን በመዘገብ አስቀምጠውልናል፡፡ በአገራችን የጽሕፈት ባህል ባልተስፋፋበት ጊዜ እንዲህ በማድረጋቸው ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ በተለይ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ምን ይመስል እንደበረ በቅርበት ዓይተውና ሰምተው እንዲሁም ጠይቀው ለእኛ ታሪክን ለማጥናት ለምንሻ እጅግ በጣም ጥሩ እጅ መንሻ ነው፡፡

‹‹አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ የ20ኛ ክፍለ ዘመን መጀመርያ ያሉትን ሃያ ዓመታት ምን ይመስሉ እንደነበር በጥሩ አገላለጥ ልንረዳው በምንችለውና ጣፋጭ በሆነ መንገድ ጽፈውልናል፡፡ ራሳቸው በሕይወት ታሪካቸው እንደሚነግሩን በንግሥት ዘውዲቱ አሳሳቢነትና ትዕዛዝ ታሪኩን እንዲጽፉ በተነገራቸው መሠረት ትዕዛዙን አክብረው በመጻፍ አበርክተዋል፡፡

አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ መጽሐፋቸውን ‹‹የሕይወት ማስታወሻ›› በማለት ርዕስ የሰጡት፣ በአንድ መቶ አራት ክፍሎች የተከፋፈለ፣ ከ1901 ዓ.ም. መጀመርያ እስከ 1923 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ታሪክ፣ በዘመኑ የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ፣ የባላባቶችን ሁኔት እስከ ቀዳማዊ አፄ ኃይል ሥላሴ የንግሥና ዘመን መጀመርያ ድረስ በስፋት የሚያስቃኝ ነው፡፡

ይህ ‹‹የሕይወት ማስታወሻ›› በማለት የሰየሙት ጸሐፊው የኖሩበትን ዘመን የሚጠቅስ ሲሆን፣ አሁን ላለነውና በቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ ግን ያለፈውን የኢትዮጵያ ታሪክን የሚያሳይ በመሆኑ ርዕሱ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ልጅ ኢያሱ፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና ተፈሪ መኰንን ከ1901 እስከ 1923 ዓ.ም.›› በማለት ለመለወጥ አዘጋጁ የተገደዱት፣ የመጽሐፉ ውስጣዊው ይዘት ከሕይወት ማስታወሻነት ይልቅ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያን የሃያ ሦስት ዓመት የታሪክ ሒደት በስፋት የሚያሳይ በመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በሞልቬር ተተርጉሞ የታተመው መጽሐፍ፣ በውጪ ዓለም ለሚገኙ ታሪክ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ የነበረን የ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ለሚያጠኑ ብዙ የታሪክ አጥኚዎች እንደ መነሻ እያገለገለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ይህ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ልጅ ኢያሱ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና ተፈሪ መኮንን›› የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው ሁለት የተለያዩ ሰነዳትን በማስተያየት መሆኑን የገለጹት መምህር ዓባይነህ፣ የመጀመርያው ሞልቬር የተባለው አጥኚ ካዘጋጀው ሲሆን፣ ሁለተኛው ከደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ (ዶ/ር) ስብስቦች ውስጥ አንዱ በሆነው በማስተያየትና በማመሳከር መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

ዜና መዋዕሉ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ (መግቢያ) ከዳግማዊ ምኒልክ መታመምና መሞት ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ጅማሬ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያን የፖለቲካና የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም እንቅስቃሴ በጥልቀትና በስፋት የሚያሳይ መጽሐፍ ነው ማለት ይቻላል ሲሉም አስምረውበታል፡፡

ታሪክ በብዙ ዓይነት መንገድ ይጻፋል፡፡ ከእነዚያ መካከል በዘመኑ የነበሩት ሰዎች በዓይናቸው ያዩትን፣ በጆሯቸው የሰሙትን ሲጽፉት ጥሩ ምንጭ እንደሆነ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ የሚሉት አዘጋጁ በመቀጠልም፣ ‹‹አገራችን ከሦስት ሺሕ ዘመናት በላይ እንዳስቆጠረች ዘወትር ቢነገርም ያዩትንና የሰሙትን በጽሑፍ ያስቀሩልን በጣት የሚቆጠሩት ናቸው፡፡ ከቀደምቱ እንደ አባ ባሕርይ ያሉት ምሁር ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በሃያኛው መባቻ ደግሞ አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ ተጠቃሹ ናቸው፡፡››

አባ ባሕርይ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የኦሮሞ ፍልሰት በማስመልከት በዓይናቸው ያዩትንና በዘመኑ በግእዝ ዘግበው ያስቀመጡትን  ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር) ‹‹የአባ ባሕርይ ድርሰቶች›› በማለት ወደ አማርኛ በመተርጐም ከጥሩ ማብራሪያ ጋር በ1995 ዓ.ም. ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...