Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሥዕልን እንደ ወጌሻ

ሥዕልን እንደ ወጌሻ

ቀን:

በየማነ ብርሃኑ

ጦርነት የሰው ሕይወት ከመቅጠፉ፣ አካል ከማጉደሉና ንብረት ከማውደሙ ባሻገር በሰዎች ሥነ ልቦና ላይ የሚያደርሰው ጠባሳ በቀላሉ የሚሽር አይደለም፡፡ ጦርነት የሚፈጥረው የአዕምሮ ሕመምና ቁስል በዋዛ አያገግምም፡፡ የልብ ስብራቱም በሰፈር ወጌሻ ልጠግንህ የሚሉት ዓይነት አይሆንም፡፡

ጦርነት በሰው ልጆች ሕይወትና ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊና አስቀያሚ መልክ ይዞ የሚገኝ ነው፡፡ ቤተሰብ ይበትናል፣ ወላጅ ያለ ጧሪ ያስቀራል፣ ሕፃናትን ጎዳና ላይ ያወጣል፣ ከቀዬ ያፈናቅላል፣ ልጆችን ከትምህርት ገበታ ያርቃል፣ ህልምና ተስፋን ያጨልማል፣ የመሳሰሉት የጦርነት አስከፊ ገጾች ስለመሆናቸው በቅርቡ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ብቻ በቂ ማሳያ ይሆናል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሰሜኑ ጦርነት በሕፃናትና በታዳጊዎች ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ ለመግታት፣ ሁነቱ የፈጠረባቸውን ሥነ ልቦናዊ ጠባሳ ለማከምና ለነገ የሰነቁት ራዕይ፣ ተስፋና ህልም እንዲያቆጠቁጥ ለማስቻል ሥዕልን እንደ ወጌሻ (ቴራፒ) ዓላማውን ያደረገ የሕፃናት የሥዕል ዓውደ ርዕይ ከጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሒልተን አዲስ አበባ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆኖ በመጎብኘት ላይ ይገኛል፡፡

‹‹የወደፊት ብሩህ ተስፋ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ዓውደ ርዕይ ሲከፈት የተገኙት የአሜሪካ የልማት ድርጅት የዘርፍ ኃላፊ ጣሰው ዘውዴ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ የሰሜኑ ጦርነት በፈጠረውና ባስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ተማሪዎችን ከሥነ ልቦና ጉዳት ለመታደግ፣ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና ያቋረጡትንም እንዲጀምሩ በማድረግ ረገድ የሥዕል ጥበብ የተጫወተው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ በመሆኑ ድርጅታቸው ይህንን በመረዳት በተማሪዎች የተሣሉ ሥዕሎችን ለዓውደ ርዕይ ማብቃቱን ይገልጻሉ፡፡

ጦርነቱ በተካሄደባቸው የትግራይ፣ የአማራና የአፋር አካባቢዎች የሚገኙ አብዛኞቹ ሕፃናት በጦርነቱ ወላፈን የተጎዱ፣ የአዕምሮ ጭንቀት፣ መታወክና መረበሽ የበዛባቸው እንደነበሩ የሚገልጹት ኃላፊው፣ እነርሱን ለማከምና ያለፈውን ሰቆቃ እንዲረሱ ለማስቻል፣ ተስፋን የሚጭሩ፣ ወደፊት የተሻለ እንደሆነ እንዲያስቡና ነገ ብሩህ ቀን መሆኑን እንዲረዱ ለማስቻል ሥዕሎችን እንዲሥሉና እንዲያዘጋጁ ማድረግ እንደተቻለ ይናገራሉ፡፡

ሕፃናቱ ጦርነቱ ጥሎባቸው ያለፈውን ክፉ ጠባሳና መጥፎ ትዝታ ከአዕምሯቸው እንዲፍቁት ለማድረግና ወደ ጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው እንዲመለሱ ለማስቻል፣ በትምህርት ቤት በመናገርና በመጻፍ ከሚሰጠው የመማር ማስተማር ሒደት ባሻገር ድራማዎች፣ ሙዚቃዎች፣ ስፖርቶችና ሥዕሎች ከቃላት ይልቅ ብዙ ሐሳቦችን ማስተላለፍና መግለጽ የሚችሉ በመሆናቸው በዚህ ልክ ተማሪዎችን እያዘጋጀን ሥነ ልቦናቸውን ለማከም፣ ተስፋና ራዕያቸውን ብሩህ ለማድረግ ታስቦ የተሠራ ሥራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የአሜሪካው የተራድዖ ድርጅት ከሚረዳቸውና ከሚደግፋቸው ከትግራይ፣ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአራተኛና የአምስተኛ ክፍል ታዳጊ ተማሪዎችን የትናንቱን ሰቆቃ የሚያስረሳና ነገ የተሻለ ቀን መሆኑን የሚያመለክት ሥዕል እንዲሥሉና እንዲወዳደሩ በማድረግ፣ ለአሸናፊ ተማሪዎችም ዕውቅናና ሽልማት በመስጠት፣ ሥዕሎቻቸውም ለዓውደ ርዕይ እንዲያቀርቡ ለማድረግ እንደተቻለ አስተባባሪው ይገልጻሉ፡፡

ከሦስቱም ክልሎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከትግራይ 15፣ ከአማራ 20፣ ከአፋር 20 ሥዕሎች በባለሙያ ተገምግመው አሸናፊ የሆኑት እንደተለዩና በውድድሩም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተማሪዎች ሜዳሊያና ለእያንዳንዳቸው የሳይክል ሽልማት እንደተበረከተላቸው ጣሰው (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸው በእነዚህ በታዳጊ ዕድሜ ላይ ባሉ ሕፃናት የተሣሉ ሥዕሎች በአገሪቱ ለሚገኙ ተማሪዎች ወደፊት መልካም እንደሆነና ነገ የተሻለ እንደሚሆን መልዕክት የሚያስተናግድ መሆኑን በመረዳት ከሥዕል ሥራዎች ውስጥ ሠላሳዎቹን መርጦ ማቅረቡንና በሰዎች እንዲታዩ ለማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል

ሥነ ጥበብን እንደ ፈውስ በታዳጊ ተማሪዎች የቀረበው የሥዕል ዓውደ ርዕይ እስከ ጥር 29 ቀን ድረስ ለሥዕል አፍቃሪያን ክፍት ሆኖ የሚቆይና በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሚማሩ ተማሪዎች የሚጎበኝ ይሆናል፡፡

በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአሜሪካ ኤምባሲና ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተወከሉ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...