Sunday, March 3, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹አንጭቆረር ድረሽ››

በደረጀ ገብሬ (ረዳት ፕሮፌሰር)

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ አብዛኛው ሰው፣ የመሀሉም ሆነ የዳር አገር ነዋሪው ‹‹አንጭቆረር ድረሽ›› እያለ በተለምዶ የሚጠቀምበት አባባል የሚጠቁማትን አንጭቆረርንና አካባቢዋን መግለጽና ማስተዋወቅ ይሆናል፡፡

‹‹አንጭቆረር ድረሽ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

፩. ስያሜ – አንጪቆረር ማለት

ከስያሜው እንጀምር፣ እንጭቆረር ምንድን ነች? እንጭቆረር የቦታ ስም ነች፡፡ ሰሜን ሸዋ፣ ዋዩ አካባቢ የምትገኝ አንዲት የገጠር ከተማ የምትጠራባት ስም ነች፡፡ ስለስያሜዋ ምንነት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ2000 ዓ.ም. አካባቢ የአካባቢ ሽማግሌዎች ተጠይቀው የሰጡት መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሽማግሌዎቹ ደግሞ እኛን ያሳደጉ አባቶችም ስለነበሩና ‹‹አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው››ም ስለሚባል በአክብሮት በመቀበል በእኔ አስተያየት ለየት ያለ ትርጓሜ ለመስጠት የሞከርኩበትን ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡

በእኔ ግምት ‹‹አንጪቆረር›› የሚለው ስያሜ የተገኘው ከሁለት ቃላት ተጋጭቶ ይመስለኛል፡፡ ቃላቱ የተገኙት በአካባቢው ካለ ትልቅ የገበያ ቦታ እምብርት ይመስለኛል፤ በጥንት ጊዜ ገበያ ውስጥ የንግድ ልውውጡ ሲከናወን እንዳሁኑ የገንዘብ ሥርዓት እንዳልነበረ ከታሪክ ትምህርታችን እናስታውሳለን፡፡ የጥንቱ ግብይት ሥርዓት ይከናወን የነበረው ዕቃን በዕቃ በመለዋወጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ የልውውጥ ሒደት ‹አነሰኝ ጨምር፣ ጨምሪ› የሚል ሐሳብ መኖሩ አይቀርም፤ መቼም በንግድ ዓለም ከግብይቱ ብዙ ማትረፍን የማይፈልግ የለምና ‹አንቺ ጨምሪ፣ አንተ ጨምር› ለማለት በዱሮ ጊዜ ‹‹ቆርር›› የሚል ቃል ሳይጠቀሙ አይቀርም ብዬ አሰብኩ፡፡ ምክንያቴም ‹‹ቆረረ›› የሚለው ቃል መጨመርን፣ መደረብን፣ ማነባበርን፣ መቆለልን የሚያመለክት ጽንሰ ሐሳብ እንዳለበት አውቃለሁ፡፡ በመዝገበ ቃላት ፍቺውም ይኸው የተረጋገጠ ነው፡፡

በተጠቆመው የግብይት ሒደት እህል ይዞ ጌሾ የሚለውጥ ብዙ ጌሾ ለማግኘት ሲል አንተ ‹‹ቆርር›› ማለቱ፣ ባለጌሾውም ብዙ እህል ለማግኘት አንተም አምጣ፣ ቆርር፣ አንቺም አምጪ ‹‹ቆርሪ›› እየተባባሉ መከራከራቸው አይቀርምና ከእነዚህ ሁለት ቃላት ‹‹አንጪ›› እና ‹‹ቆርሪ›› ከሚባባሉት ውስጥ ‹‹አንጪቆርሪ – አንጪቆረር››  የሚለው  ስያሜ የተገኘ ይመስለኛል፡፡

‹‹አንጭቆረር ድረሽ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

፪. አካባቢያዊ ገለጻ

ስለስያሜው አመጣጥ ግላዊ ትርጓሜየን ይዤ ወደአካባቢው ገለጻ ልለፍ፡፡ አንጭቆረር ምን ዓይነት አካባቢ ናት?

ጭው ያለች በረሃ፣ ለበስማም ወልዴው የተክል ዓይነት የማይታይባት፣ የዕንባ ጠብታ ያህል ውኃ የሚናፈቅባት፣ ጸሐይ ከግለቷ የተነሳ ድንጋይ የምታቀልጥባት፣ አሸዋው ከቆሙበት እንደ ባህር የሚውጥባት፣ የመጥፎ ፍጡራን – አጋንንትና ሰይጣናት መናኸሪያ የሆነችና የጠሉት ሰው እዚያ ቢሄድ የማይመለስባት ትመስል ይሆናል፡፡

አለበለዚያ ደግሞ ጥቅጥቅ ያለ ደንና ጭልጥ ያለ ገደል የሚገኝባት ሆና በውስጧ ልዩ ልዩ አራዊት አንበሳ፣ ነብር፣ ቀበሮ፣ ጅብ፣ ዋልጋ፣ ተኩላ፣ አማንኮሲ፣ ሽኮኮ፣ ሸለምጥማጥ፣ የተጠራቀሙባት – ልዩ ልዩ መርዛማ ፍጡራን – ዘንዶ፣ እባብ፣ ጊንጥ፣… ልዩ ልዩ ነፍሳት ንዳድ፣ ዳሞትራ፣ ወባ፣ የሚንቧቸሩባት ልትመስል ትችላለች፡፡ እናንተም ይህንኑ ታስቡ ይሆናል፡፡

ሌላው ደግሞ ጫፉ ሰማይን ደግፎ የያዘ ተራራ ቅስም ሰባሪ የሆነ ብርድና በረዶ ያለበት፣ የተቀየመ ቆሌ ከላይ ሆኖ ቁልቁል በወስፈንጥር ህያው ጠላቱን የሚዋጋባት፣ በጣዕረ ሞት ከአካሏ የተለየች ነፍስ ወደ ሰማይ ቤት ስትስፈነጠር ቀድሞ አፍኖ ይዞ ወደ ገሀነም የሚወስዳት የዳቢሎስ መልዕክተኛ እስቲመጣ የሚያቆይባት ልትመስለው ትችላለች፡፡ እኩያን መናፍስትና አጋንንት ሁሉ የሚጠራቀሙባት የምድር ሲዖል ልትመስለውም ትችላለች፡፡ እናንተም ይህንኑ ታምኑ ይሆናል፡፡ ግን ሁሉም ግምቶች፣ መላምቶች ናቸው፡፡ ታዲያ አንጭቆረር ምን ገጽታ አላት?

ይልቅየስ፣ አንጭቆረር ለጥ ባለሜዳ፣ በትናንሽ ኮረብታዎችና ወንዞች የተከበበች፣ በተስማሚ ነፋሻ አየር የተሞላች ትንሽ የገጠር ከተማ ነች፡፡ ከሰኔ ግምታ ጀምሮ እስከ

‹‹እዳር እዳር ወተትሽ እማር

 እዳር ኮበለለች፣

 እንቅቧን አዘለች፣

 ልጇን አስከተለች፡፡››

ተብሎ በእረኞች እስከሚዘፈንበት የኅዳር ሚካኤል ድረስ አንጭቆረርና አካባቢዋ በዕፀዋት የተጌጠ፣ በአበባ በእንቡጥና በእሸት የተዋበ፣ ከየጉብታው ሥር እየተነሱ ሚፈስሱትን እየተቀበለችና እያዋሀደች የዋናው የዠማ ወንዝ ገባር ለሆነው የዝንጀሮ ውኃ የምታቀብል ጨለለቂት የምትባል ወንዝ ያለችባት ነች አንጭቆረር፡፡ ጨለለቂት ከሰኔ እስከ መስከረም አፈር የተበጠበጠበትን፣ ከዚህ በኋላ መግሞ ኩል የመሰለ፣ እንደ ጠበል የጠራ ውኃ የምታንቆረቁር፣ ለአካባቢዋ ነዋሪዎች ለዕለት ተዕለት መገልገያ የመጠጥ ምንጭ፣ ለልብስ ማጠቢያ፣ ለመታጠቢያ ንጹህ ውኃ የምትለግሥ፣ ለከብት ማጠጫ ባህር ያላት፣ ለጥምቀት እንጠመቅበት፣ አያ ሽቦ እየተባለ የሚዘፈንበት  ባህረ ጥምቀት የሚገኝባት የእንጭቆረር ህልውና የተመሠረተባት አንዷና ዋናዋ ወንዝ ናት፡፡ የውላውላ ምንጭም አንዷ የመጠጥ ውኃ የሚገኝባት፣ ጨፌም እንዲሁ ሌላዋ የመጠጥ ውኃ ለጋሽ መሆኗን ባልጠቅስ ትዝታቸው ያንቀኛል፡፡

በየእርሻ ማሳው የአዝርዕት ዓይነት ስንዴ፣ ባቄላ፣ ጤፍ፣ ምስር፣ ገብስ፣ አተር፣ ተልባ፣ ጓያ የሚበቅልባት፣ ከግንቦት የጤፍና የገብስ አዝመራ እስከ መስከረም የጠቀምሽኝ ዝሪት ድረስ የእህል ዘር በየማሳው የሚበተንባት- የሚዘራባት፣ የሚበቅልባት፣ ጭልጭል እያለ የክረምትን ዶፍና የእኝኝብላን ካፊያ የሚቀበልባት ነች አንጭቆረር፡፡ ከዚያ በኋላ ከመስከረም ጥቢ ጀምሮ ሰብሉ እያደገ፣ የገበሬ ዓይን አበባውን የሚያይባት፣ አበባ ሲያብብ፣ ሲያደበድብ፣ ሲያዘረዝር፣ ሲያሸት አካል ከህሊና በጣምራ የሚረካባት ነች፡፡ አንጭቆረር ሞቶ የተነሳ የእህል ዘር አለሁ፣ ደረሰኩ እያለ የሚገማሸርባት፣ የጥቅምትና የኅዳር ወር ለዓይን ተስፋውን እየቸረ ለታኅሣሥና ለጥር መኸር የሚያሻግርባት ናት፡፡ ገበሬ እንዳዝመራውና የአረም ወቅት ሁሉ በአጭር ታጥቆ መኸሩን ለመሰብሰብ የሚናውዝ- የሚባትልባት ነች፡፡

የአካባቢው ተዳፋት ላይ ለሰፈረው ኅብረተሰብ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ እነዠነቄ ማርያም፣ የዥብ ዱር ኢየሱስ፣ የዱብራ ጊዮርጊስ፣ የከምቦልሻው ገብርኤል፣ የጥራጥር አቦ አካብበው የሚገኙባት፣ በመካከሏ በሚገኘው ጉብታ ላይ ቀደም ሲል የወይራ አድባር እየተባለ የአማኞቹን ቅቤ ሲለቀለቅ የኖረ ትላልቅ የወይራ ዛፍ የተከማቸባት፣ የምክትል ወረዳውን ጽሕፈት ቤትና ፖሊስ ጣቢያ ያማከለ ያስተዳደር መዋቅር የነበረባት፣ በአሁኔ ጊዜ ደግሞ፣ የአድባሩም ፊት ለፊታዊ እምነት ቀርቶ፣ በጽሕፈት ቤቶቹ ምትክ የእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ተተክሎባት፣ ሕዝብ በውልደቱና በህልፈቱ መካከል ያለ መንፈሳዊ ሕይወቱን የሚመራባት ነች- አንጭቆረር፡፡

ከክረምት የአዝመራ ወቅት እስከ በጋ መኸር ክታች ድረስ ሲባትል የኖረ ገበሬ እፎይ ሲል፣ ሲያርፍ፣ ደግሞ ከገና የልደት በዓል ጀምሮ እስከ ፋሲካ ድረስ ቀስ እያለ ወደ ማኅበራዊ ኑሮው ተመልሶ ዘመድ ለዘመድ፣ ወገን ለወገን እየተፈላለገ የሚጠያየቅበት ወቅት ያላት ነች አንጭቆረር፡፡

#ለገና እንብላ ደንዳና አያ ሽ… ቦ

ለጥምቀት እንጠመቅበት አያ ሽ… ቦ

ላስተሮ እንብላ መተሮ

አያ ሽ… ቦ…

እየተባለ የሚዘፈንባት፣ የሚጨፈርባት፣ ጎረምሳ ልቡን ለፍቅር በሩን የሚከፍትባት፣ ኮረዳ ዓይን የምትስብ- የምትማርክባት፣ የደረሱ የሚታጩባት፣ የታጩትም የሚዳሩባት ነች፡፡

ማኅበራዊ ግንኙነት ደርቶ፣ ተደግሶ፣ ሰው ተጠራርቶ፣ አብሮ እየበላ፣ እየጠጣ የሚጨፍርበትና አዝማሪ፣

#እምዬ አንጭቆረር ወርቅ ይዝነብብሽ

በእንቁላል ቢሸመት ስስት የለብሽ፣

አበጀሽ! አበጀሽ! አበሽ!

እያለ የሕዝቡን ተደጋገፎና ተፋቅሮ አብሮ ኗሪነት የሚመሰክርላት ነች አንጭቆረር፡፡ ማኅበራዊ ኑሮው ነግሦ በየቤቱ በሚደገሠው የክርስትና፣ የሠርግ፣ የሰንበቴ ወይም የተዝካር ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በበዓላትና በሰንበት ቀናት የአካባቢው ሕዝብ የሚገናኝባት መናኸሪያም ነች፡፡ ለዚህም፣

#መገን አንጭቆረር ችምችም ያለው መንደር

መጠጫው ብረሌ መቀመጫው ወንበር

አበጀሽ! አበጀሽ! አበጀሽ! አበጀሽ!

እየተባለ የሚዘፈንባት፣ የሚጨፈርባት ናት፡፡ ኮረዳ አውጥታ አውርዳ፣ አማርጣ፣ ልቧ ያረፈበትን ጎረምሳ፣

#ካንጭቆረር ወዲያ ካንድ ግራር ወዲህ

ፍቅር ባንተ ይርጋ ይደምደም እንግዲህ

አበጀሽ! አበጀሽ! አበጀሽ!

ስትል ሌላው ደግሞ ፈልጎ አፈላልጎ ያጣትን ኮረዳ ለማግኘት ቆርጦ መነሳቱን ሲገልጽ፣

#አንጭቆረር ሲሏት ሄደች እነዋሪ

እነዋሪ ሲሏት ሄደች መራቤቴ

ሄጄ አመጣታለሁ እያልኩ እመቤቴ፤

መራቤቴ ሲሏት ተሻገረች መንዝ

ከኚያ ከኃይለኞች ካራ ታማዝዝ

አበጀሽ! አበጀሽ! አበጀሽ!

በማለት በነአባዬ ጥሩነሽ፣ በነማማ የሺ ጠላና አረቄ የተንቧቸባት፣ በከበደ ተሰማና በተንሳይ ዋቀዮ ጠጅ የተንፏለለባት፣ በአካሉ ደምሴ፣ በአበበ ጠጋዬና በተስፋዬ ምትኩ ልኳንዳ ቤት ታላቅ ከታናሽ፣ ጎድን ተዳቢት ያወረደባት፣ ጮማ የቆረጠባት ናት አንጭቆረር፡፡ ጠግበው የሚጫወቱባት፣ አለበለዚያም በነገር ተጎሻሽመው የሚዣለጡባት፣ እነ አባባ ወርቁ በሪዎ፣ እነ አቶ ምትኩ ዋቀዮ፣ እነ አቶ ሲሳይ ደሴ፣ እነ አቶ ገዝሙ ባየህ፣ እነ ጋሸ ይልማ መኩሪያ በጊዚያዊ የዕለት ግጭት ፊት የተነሳሱ፣ እንዲያም ሲል የተፈናከቱ ጎረምሶችንና የአካባቢውን ነዋሪዎች የሚሸመግሉ፣ የሚዳኙባት ናት አንጭቆረር፡፡

ችግሩ ከእነዚህ አዛውንቶች አቅም በላይ ከዘለለም የምክትል ወረዳው ገዢ ወደ ሆኑት ባላምባራስ ለገሠ ዘንድ ይሰዳል፡፡ እሳቸውም ባንድ በኩል የሕግን ተፈጻሚነት በሌላ በኩል የአስተዳዳሪነት ሚናቸውን በመጠቀም የተባባሰ ችግር እንዳይኖር የዳኘንነቱንም፣ የአባትነቱንም ሚና ይወጡ እንደነበር ሳስታውስ ያለፈውን ዘመን በጎነት ለዛሬ ቢያደርገው እያልኩ እመኛለሁ፡፡

#ብሄደው ብሄደው ሁለት እግሬ ደማ፣

የዝማሞች አገር እንዴት ነው ገደማ፣

ብሄደው ብሄደው ሁለት እግሬ ሳሳ፣

የቆንጆዎች አገር እንዴት ነው መሴንሳ፣

ብሄደው ብሄደው ሁለት እግሬ ነቃ

የዝማሞች አገር እንዴት ነው ወዳምቃ፣

እየተባለ ከሚዜምላቸው የተጉለት ክፍሎች የሚመጡ በቅዳሜ ገበያዋ ቀን የዕለት ጉርስ፣ ያመት ልብስ የሚሆናቸውን ነገር የሚገዙ የሚሸጡባት፣ የሚያራዝሙ የሚያቃኑባት ናት – አንጭቆረር፡፡

   በነገር የሚጎሻመጡ ባልና ሚስቶችም

   ‹‹በሬውን ግረፈው ደሙ እስቲነዠረዠር

   ዋዩ ገበያ ላይ ቴሶ ከመሰንዘር፡፡››

ለምትል ሚስት ባል በበኩሉ፣

   ‹‹በሬውን ብገርፈው ደሙ እስቲንዘረዠር

   አሻራሽ ደግ ነው፣ አሳጣሽኝ ለዘር››

እየተባባሉ የሚወቃቀሱባት፣ እኔ እበልጥ፣ እኔ እሻልን፣ ጥረትንና ዕድልን አጣምረው የሚገልጹባት ናት አንጪቆረር፡፡

ሕዝቡ ቁሳዊውንም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወቱን በሰላም፣ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚመራባት፣ የሚያርስ የሚቆፍርባት፣ የሚገዛ የሚሸጥባት ናት፡፡ ከጅሩ፣ ከደነባ፣ ከተጉለት፣ ከመርሀቤቴ፣ ከሳሲት፣ ከሰላሌ፣ ከጊዳ፣ ከመንዲዳ ከአብደላና ከጎሸባዶ አካባቢ ድረስ እየመጡ የሚገበያዩበት ረዥም ዘመን የቆየ የቦኪሳ ገበያ የሚባል ትልቅ የንግድ መገናኛ ማዕከል ያለባት ናት፡፡ ለተጠማና ለተራበ የዕለት ጉርስ የማይታጣባት፣ ለመሸበትም ማደሪያ የእግዜር እንግዳ የሚያርፍበት የማያጣባት ናት አንጨቆረር፡፡

፫. የአሉታዊነት ሰበቦች

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው አንጭቆረር በመልክዓምድራዊም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮ ገጽታዋ እጅግ የተገጣጣመ ሕይወት የሚመራባት ናት፡፡ ታዲያ በዕለት ዕለት ግንኙነት ውስጥ ‹‹መሄዴ ነው፣ ወይም ልሄድ ነው›› ለሚል ግለሰብ ‹‹አንጪቆረር ድረስ/ድረሽ›› የሚሉ አሉታዊ መድረሻነት እንዴት ሊሰጣት ቻለች?

ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ግምቶችን ማስፈር ይቻል ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቆመው በአካባቢው ረዥም ዘመን የቆየ የገበያ ማዕከል የሚገኝባት ነች፡፡ ይህ የገበያ ቦታ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በተደረገው የኦሮሞ የመስፋፋት እንቅስቃሴ ወቅት የተመሠረተ እንደሆነ፣ መሥራቹም በአካባቢው የሰፈረው ኃይል መሪ የነበረው ቦኪሳ የሚባል ሰው እንደነበረ በአፈታሪክ ሲተላለፍ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህ ዘመን ታዲያ የመገበያያ ቦታዎች በየአካባቢው እንደልብ የማይገኙበትና ቢገኙም መጓጓዣ ዘዴው እጅግ ኋላቀር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በእግር ወይም በጋማ ከብት ጀርባ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደነበርም ጨምሮ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም፣ ከላይ እንደተጠቆመው፣ በዘመኑ የግዢና የሽያጭ ሥርዓቱ የሚከናወነው በአንድ ማዕከላዊ የገንዘብ ሥርዓት ሳይሆን ዕቃን በዕቃ የሚለዋወጡበት የመገበያያ ሥርዓት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነጋዴዎች በርበሬ ከማረቆ፣ ጥጥ ከይፋት፣ ጌሾ ከመርሀቤቴ፣ ባና ከመንዝ፣ የጋማ ከብት ከጊዳና ሰላሌ ወዘተ ወደ አንጪቆረር ገበያ ያመጡ ነበር፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ያመጡትን ዕቃ በሚፈልጉት ነገር ለውጠው ወደየቀያቸው የመመለሳቸውን ያህል በአንዳንድ አጋጣሚ እንደወጡ እንደሚቀሩ መገመት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ ከይፋት ጥጥ ይዞ የሚመጣ ነጋዴ የሞፈር ውኃን ጅረት፣ የይፋትንና የጣርማ በርን ዳገትና ቁልቁለት፣ የሳሲትንና የተጉለትን ወጣገባ የዓባይ ወንዝ ገባር የሆኑትን የበሬሳንና የጫጫን ወንዞች አደባልቆ የሚፈሰውን የዠማን ሸለቆ ሁሉ አልፎ ነው አንጪቆረር የሚደርሰው፡፡ ከማረቆም የሚመጣ ዛሬ አዲስ አበባ የምትገኝበትን አካባቢ ለማለፍ እንኳን ስንትና ስንት ውጣ ውረዶች ያጋጥሙታል? አዲስ አበባን አልፎ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሲጉዋዝ የሚያቋርጣቸው ወንዞች ለገሮቢ፣ ብለት፣ አራጌሳ፣ ዝንጀሮ ውኃ፣ ጋመኛ የመሳሰሉት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወንዞች በተለይ ዝናብ ከጣለ አሰስ ገሰሱን ይዘው የሚጓዙ በመሆናቸው አደጋ አድራሾች ናቸው፡፡ ከባሌ ተነስቶ መሀል ኢትዮጵያን ለሁለት የሚከፍለው የተራራ ሰንሰለትም ያደርስ የነበረው የጉዞ እንቅፋትነት መገመት የሚሳን አይሆንም፡፡

ከመርሀቤቴ የሚመጡትም ቁልቁለት ወርደው፣ ታላቁን የዠማ ወንዝ ተሻግረው፣ እንቅርት አፍርጥ የሆነውን የደብረ ሊባኖስ ዳገት ወጥተው፣ ሀሞት አፍሳሽ የሆነውን የጅሩ ሜዳ አቋርጠው ነው አንጭቆረር የሚደርሱት፡፡

እነዚህ ከተጠቃቀሱትና ከሌሎችም አካባቢ የሚመጡ ገበያተኞች ቀናት ምናልባትም ወር ወይም ያለፈ ጊዜ ፈጅተው አንጭቆረር ይደርሱ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ ደግሞ የወንዝ መሙላት፣ በጫካ የሚገኝ አውሬ መተናኮል፣ የወባና የመሳሰሉ ተውሳኮች መናደፍ፣ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም የሽፍታና የዘራፊ ድንገተኛ አደጋ፣ ባደሩበትና በልዩ ልዩ አጋጣሚ በሚሰነባብቱበት አካባቢ በሚያጋጥም መተሳሰብ፣ ፍቅርና ምቾት ሁሉ ጥቂት ሰዎች ወደተነሱበት ቦታ ላይመለሱ ይችላሉ፡፡ እንደወጡ ይቀራሉ፡፡

በሌላም በኩል አካባቢው ለግብርና ተግባር እጅግ አመቺ በመሆኑ፣ ሰዎች በተለይም ብዙም ጓዝ ምንጓዝ የሌላቸው ወጣቶች፣ ቀደም ሲል ከሚኖሩበት አካባቢ የተሻለ የመኖሪያ ሥፍራ እንደሆነ ተገንዝበውና በልምላሜውና በአመቺነቱ ተማርከው ኑሮአቸውን በዚያው ለመመሥረት ወስነው ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ በእርሻ ሥራም ሆነ በከብት ዕርባታ ተሰማርተው ተደላድሎ ለመኖር ዕድል እንዳላቸው አምነው ወደመጡበት ሳይመለሱ ሊቀሩ መቻላቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የዚህ እኔ ጽሑፍ አቅራቢ በልጅነቴ ያጋጠመኝን ያንድ ቤተሰብ በአንጭቆረር ድንገት መገኘት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ ሦስት ሰዎች ያሉበት አንድ ቤተሰብ በከተማዋ እምብርት ተገኙ፣ ሰውየው ዓሊ ይባላሉ፡፡ ልጃቸው መስቱ፣ ባለቤታቸው ሸምሲያ ይሰኛሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእምነታቸው ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ አካባቢው ደግሞ መቶ ከመቶ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች የሚኖሩበት ነበር፡፡ የእነዚህ ሰዎች በአንጭቆረር መገኘት ሰበቡ ምን እንደሆነ ባላውቅም ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ግን ተስማምተው፣ ተከብረውና ተወድደው ይኖሩ እንደነበረ፣ አብዬ ዓሊ የተቀደዱ ብረት ድስቶችንና በቀላጭ ነገር (በኋላ እርሳስ እንደሚባል ለማወቅ የቻልኩት) እየጠገኑ፣ የተሰነጣጠቁና የተሸነቆሩ ሸክላዎችን በስሚንቶ እየደፈኑ የዕለት ገቢ በማግኘት መተዳደር መቻላቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ ሳሰላስለው ይህ የአብዬ ዓሊ ሙያ በዚያን ጊዜ ለዘካባቢው አዲስ ቴክኖሎጂ እንደነበረና ኅብረተሰቡም በአዲሱ ቴክኖሎጂ መገልገሉ ትዝታዬ ነው፡፡

ሌላው ወንድሙ ደገኛው የሚባሉ ይፋት ከሚባል አካባቢ የመጡ ሰው፣ የዋዩ ትምህርት ቤት አዳዲስ ክፍሎች ሲሠሩለት ስሚንቶ አቡኪና ግድግዳ ለሳኝ ሆነው ሲሠሩ ከከራረሙ በኋላ ሥራው ሲያልቅ ወደ አንድ ጠላ ሻጭ ወ/ሮ ቤት ጎራ ብለው፣ ተዋደውና ተፋቅረው ሙያቸውን ወደ አናጢነትም፣ መሬት ተጋዝቶ ወደማረስም አሸጋግረው  ወደመጡበት አልተመለሱም፡፡ በቅርብ ዘመን እንኳ አካባቢው በማናቸውም ምክንያት ወደ አንጭቆረር የመጡ ሰዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋህደው ሊቀሩ መቻላቸውን ህያው ምስክር እንደሆነ ያስረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ የእነዚህ ሁለት ዓይነተኛ አጋጣሚዎች እንደወጡ መቅረትን ጠቋሚዎች ናቸው፡፡

በሩቅ ዘመን የነበሩትም ሆኑ የቅርቦቹ ሰዎች ዘመዶችም ‹‹አንጭቆረር እሄዳለሁ›› ብለው ከየቤታቸው መነሳታቸውን እንጂ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ ያጋጠማቸውን የሚያውቁበት ውለኛ መረጃ ያገኙ ነበር ለማለት ባለመቻሉ፣ እንደወጡ መቅረታቸው ብቻ ሀቅ በመሆኑ፣ የጉዞአቸው መድረሻም አንጭቆረር ገበያ መሆኑ ቀደም ሲል የታወቀ በመሆኑ ሲቀሩባቸው ‹‹አንጭቆረር ሄዶ ቀረ፣ አልተመለሰም፤›› ማለታቸው አይቀርም፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቃቀሱትና በሌሎችም ታሳቢ ሰበቦች ሰዎች ወጥተው ሲቀሩ አንጭቆረር ‹‹ሄደው የማይመለሱባት፣ አስፈሪ አካባቢ›› ሆና የታየችና አሉታዊ ግምትም የተሰጣት እንደሆነች ጉዳዩን አራዝሞ መገመት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደወጡ መቅረት ደግሞ ተደጋፊ እንዳልሆነ የሚከተለው ቃል ግጥም የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡

‹‹ተነሱ እንነሳ፣ እንግባ አገራችን

እንደወጡ ቀሩ፣ አይበል ጠላታችን፡፡››

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ የተለያዩ መጻሕፍትንም ማለትም ጠይም ዕንቁ (አጭር ልቦለድ መድበል)፣ ተግባራዊ የጽሕፈት መማሪያ፣ በተማሪዎች የቤት ሥራ የመምህራንና የወላጆች ሚና፣ የማንበብ ክሂል ማበልጸጊያ የሆነ ‹‹መራሔ ንባባ›› እና ሌሎችንም አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles