Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሰላም ዕጦት የተጎዳው የንግዱ ዘርፍ ሰላምን ለማስፈን የድርሻውን አልተወጣም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰላም ዕጦትና ግጭት የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ እንዲጎላ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የንግዱ ማኅበረሰብ በሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ማበርከት የሚገባውን በበቂ ሁኔታ ባለመወጣቱ ነው ተባለ።

ይህ የተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ‹‹ለሰላማዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የንግዱ ኅብረተሰብ ሚና›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ 

በዚህ መድረክ ሰላምና የንግዱ ኅብረተሰብን የተመለከቱ ሦስት የተለያዩ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ‹‹ሰላም ለቢዝነስና ቢዝነስ ለሰላም ያለው ሚና›› በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረቡት የኢንሼቲቭ አፍሪካ ንግድ ለሰላም ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ዳንኤል መኮንን፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የሰላም ዕጦት ንግድ ኅብረተሰቡን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሚና እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ የንግዱ ማኅበረሰብ በሰላም ግንባታ ረገድ እያደረገ ያለው ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ነው ያሉት የጥናቱ አቅራቢ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ሚናውን ካለመወጣቱ ባሻገር በአገሪቱ በሚከሰቱ ግጭቶች ውስጥ እጁ አለበት ብለዋል፡፡ ንግድ ኅብረተሰቡ በሰላም ዙሪያ ሊሠራባቸው ይገቡ የነበሩ ሥራዎች አለመኖር በራሱ ለሰላም መደፍረስ አንድ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀስ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡   

በቅርቡ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ ጦርነቶችና አለመረጋጋቶች በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ያስከተሉት እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ሰላም ለንግድ ማኅበረሰቡ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው የሚያንፀባርቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ጦርነቱ የተካሄደባቸው አካባቢዎችን በአካል ሄደው መጎብኘታቸውን የጠቀሱት አቶ ዳንኤል፣ በነበረው ግጭትና የሰላም ዕጦት የንግዱ ማኅበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ መሆኑን ባደረጉት ጉብኝት ማስተዋላቸውን ገልጸዋል።

የጦርነቱ ዋነኛ ተጎጂ የንግድ ማኅበረሰብ ግጭቶች እንዳይፈጠሩና ሰላም እንዳይደፈርስ ማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው ቢሆንም ይህንን አቅሙን እየተጠቀመበት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደውም ለግጭቶቹ መባባስ የንግዱ ማኅበረሰብ የራሱ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡  

ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመን መንግሥት ጀምሮ  እስካሁን ድረስ በውስጥና በውጭ ጦርነት በብዙ መልኩ የተፈተነች መሆኑን ያስታወሱት ጥናት አቅራቢው፣ ይህ ሁኔታም የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችንና የንግድ ልውውጦችን ችግር ውስጥ ሲከት የቆየ መሆኑን አንስተዋል። ሰላም ባልነበረባቸው ወቅቶች ሁሉ ቀዳሚ ተጎጂ ነጋዴው ወይም የንግድ ማኅበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚስተዋሉት ግጭቶችም ሆነ በሰሜኑ ጦርነት በርካታ የንግድ ተቋማትን ማውደሙን ተናግረዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የሰላም ዕጦት የኢትዮጵያ ብቻ ያለመሆኑን የተናገሩት ጥናት አቅራቢው፣ የሰላም ዕጦት የዓለማችን ተግዳሮት የሆነበት ጊዜ ላይ ቢደርስም ሰላምን ለማስፈን የተቀናጀ አሠራር አለመኖሩ በኢትዮጵያ ጉዳት እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ 

የሰላም ዕጦት ያስከተለው ጉዳት እንደ አገር ብዙ ነገር እንዲታጣ ማድረጉን በተለያዩ ምሳሌዎች ተንትነዋል፡፡ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ካሉት 1,600 አካባቢ ከሚሆኑ ዓመታት ውስጥ ወደ 329 ዓመታት በጦርነት ውስጥ ታልፏል፡፡ ከ1983 ወዲህ ደግሞ ግጭቶች ስለመጨመራቸው በማስታወስም፣ በተለይ ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት ከምንጊዜውም በላይ ግጭቶች በመጨመራቸው ጉዳቱን ከፍ አድርጎታል፡፡

የሰላም ዕጦት የሚፈጥረው ቀውስ ሌላውንም የኅብረተሰብ ክፍል ጉዳት እንዲጨምር በማድረጉ፣ በአሁኑ ወቅት የትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የሰላም ጥያቄን ቀዳሚ አጀንዳ ሊያደርገው ይገባል ብለዋል።

‹ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ነው› ቢባልም ሰላም ከዚህም በላይ መገለጫ እንዳለው የጠቀሱት ጥናት አቅራቢው፣ ሰላም በተለይ ለንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ 

‹‹የቢዝነስ ዋነኛ ግቡ ትርፍ ማምጣት ቢሆንም የተሟላ ሰላም አለ ለማለት ግን የማኅበራዊ የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መረጋጋት ያስፈልጋል፤›› በማለትም፣ ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ 

ለቢዝነስ ዕድገት ሰላም ወሳኝ የመሆኑን ያህል ሰላም ለማስፈን ደግሞ የንግድ ማኅበረሰቡም የራሱ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ይህም ማለት የንግድ ኅብረተሰቡ አጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴውንና ምልከታውን መቀየር የሚኖርበት መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ አካሄዱን ማስተካከል የግድ መሆኑን እያሳየ ነው፡፡ 

‹‹እስካሁን ሲጓዝበት በነበረው መንገድ ሊቀጥል የማይችልና የቢዝነስ ሥራው ከትርፍ በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችን መከተል ይኖርበታል፤›› በማለት፣ ተጨማሪ ሥራዎቹ ደግሞ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመሥራት መገለጽ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሱት ቢዝነሱ ወይም የንግድ ድርጅቱ ከሚገኝበት ማኅበረሰብ ጋር በቅርብ መገናኘት ጭምር መሥራት ይጠይቃል፡፡ ለሰላም መስፈንም የበኩሉን ማድረግ ካልቻለ አሁንም የንግድ ዘርፉ እየተጎዳ መቀጠሉ አይቀርም ይላሉ፡፡

በሥራቸው አጋጣሚ ከተለያዩ የንግድ ኀብረተሰብ አባላትና ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር መገናኘት ያገኙት መረጃ ያመላከታቸው፣ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለሰላም ሥራ ላይ ያለው ተሳትፎ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን ነው፡፡ ትልቁ ችግርም በአብዛኛው የንግድ ኅብረተሰቡ ውስጥ የሰላም ማስፈን ሥራን የመንግሥት ሥራ ብቻ አድርጎ መመልከት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ዕሳቤ አደገኛ መሆኑን ጭምር ያብራሩት ባለሙያው፣ በሰሜኑ ጦርነት ከሰብዓዊ ጉዳቱ ባሻገር እንደ ቢዝነስ የጎዳው ነገር እንደሌለው ጠቅሰዋል፡፡ ተዘዋውረው እንዳዩትም የንግድ ዘርፉ ደቋል በሚባልበት ደረጃ የሚገለጽ ነው ብለዋል፡፡ ሰላም ለማምጣት የሚሠሩ ሥራዎች የመንግሥት ብቻ ተደርገው መወሰዳቸው ብዙ ዋጋ ማስከፈሉን የሰጡት ማብራሪያ ያመለክታል፡፡  

በሰላም ግንባታ ላይ ከመንግሥትም በላይ ሊሠራ የሚገባው የንግድ ኅበረተሰቡ ነው ያሉት ጥናት አቅራቢው፣ ለዚህ አገር የሰላም ዕጦት አንዱ ምክንያት በዚህ ወሳኝ ጉዳይ ላይ የንግድ ኅብረተሰቡ ያለመሳተፉ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሰላም ማስፈንን የፖለቲካ ጉዳይ አድርጎ የመመልከት ሁኔታና በሰላም ማስፈን ሥራዎች ላይ የንግድ ኅበረተሰቡ ኢንቨስት እያደረገበት አለመሆኑ የንግድ ማኅበረሰቡ ራሱ ተጎጂ እየሆነበት ነው፡፡  

የንግድ ኅብረተሰቡ የሰላም ግንበታ ላይ ያለው አስተዋጽኦም በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን፣ ቢዝነሱ ባለበት ቦታ አዎንታዊ ሥራዎችን በመሥራት የሰላም ማስፈን የሚችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ይህንን ባለማድረጉ ደግሞ ግጭት እንዲፈጠርና ሰላም እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ጉቦ በመስጠት፣ አካባቢ ያለን ማኅበረበስ አለመቅጠር፣ ለአካባቢና ለማኅበረሰቡ ባለመጨነቅ፣ የንግድና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ኅብረተሰቡ የግጭት ምንጭ የሚሆንበት ዕድል ስላለ ከዚህ መቆጠብ በራሱ ሰላምን ለማስፈን ተደርጎ እንደሚቆጠር ከገለጿቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡  

ከዚህም ሌላ የንግድ ኅብረተሰቡ ለሰላም ለማስፈን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ የኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት ነው፡፡ ሠራተኞችን የሚቀጥር ኢንቨስትመንት ማስፋፋት በራሱ ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡ 

የቢዝነስ ዋነኛ ትልሙ ትርፍ ስለሆነ ትርፍ ለማግኘት በሚደረጉ ድርድሮችና ንግግሮች ሰላምን ለማስፈን የራሳቸው የሆነ አቅም እንዳላቸውም ጥናት አቅራቢው ተናግረው የአንዱ አካባቢ ነጋዴ ከሌላው አካባቢ የሚያደርገው የንግድ ልውውና ንግግር ግጭት እንዳይኖር ይረዳል በማለት አስረድተዋል፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለሰላም ዕጦት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን የተለያዩ ነጥቦች ያነሱ ሲሆን፣ እሳቸውም ለሰላም ግንባታ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ ሊወጣ አለመቻል ችግሮችን ማባባሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በሰላም ግንባታ ሥራ ላይ ተሳትፎ እያሳየ ያልሆነው የንግድ ኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ማኅበረሰብ በዚህ ወሳኝ ሥራ ላይ ተሳታፊ ያለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ባሉበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳይቀር ምሁራን በዚህ ወሳኝ ጉዳይ ድምፃቸው አለመሰማቱ የሚዲያ ተቋማት ዘገባዎች ሰላማዊ አለመሆን ጭምር ለሰላም ዕጦቱ ምክንያት እንደሆኑ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡  

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በሰላም ዕጦት ምክንያት የንግድ ኅብረተሰቡ ምን ያህል ተጎጂ እንደሆነ ለማሳየት በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎችም ራሳቸውን አስረጅ አድርገው ሐሳባቸውን የገለጹበት ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል በአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት መሆናቸውን የገለጹ አስተያየት ሰጪ አንዱ ናቸው፡፡ ቱሪስቶችን አስጎበኝበታለሁ ብለው የገዟቸውን ተሽከርካሪዎች ያለ ሥራ መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹን ለማንቀሳቀስ በየቦታው የተከሰቱ አለመረጋጋቶች ሥራቸው ላይ እንቅፋት ስለመፍጠሩ በመግለጽ ሰላም ቢዝነሳቸውን ምን ያህል እንጎዳባቸው ተናግረዋል፡፡ 

ሌላው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የንግድ ምክር ቤቱ አባል ደግሞ ያመረቱትን ምርት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማጓጓዝና ለመሸጥ እየተፈተኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ሰላም በመጥፋቱ ሥራችንን በአግባቡ ለመሥራት አልቻልንም ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ ብዙ እየተጎዳን ነው ብለዋል፡፡ ሰላም ቢኖር በነፃነት ተንቀሳቅሰን በመሥራት ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን የማሳደጉ ዕድል ሰፊ ቢሆንም፣ አሁን እያየን ያለነው የሰላም መደፍረስ ግን ንግድ ለማትረፍ አላስቻለንም ይላሉ፡፡ 

በሰላም ዕጦት ገቢያችን በመቀዛቀዙም ይዘዋቸው የነበሩ ሠራተኞችን እስከመቀነስ መገደዳቸውን በማመልከት፣ እንዲህ ያለው ችግር እየጎዳ ያለው አጠቃላይ ማኅበረሰቡን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ስለዚህ በሰላም ዙሪያ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲህ ያለውን መድረክ በማዘጋጀት መመካከር መጀመሩን እንደ ትልቅ ነገር የሚወስድ መሆኑን የጠቀሱት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ የተንሠራፋውን ሙስናና ብልሹ አሠራር ለማስተካከል ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በመሆን መፍትሔ የማፈላለግ ሥራ ቢሠራ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

ሌላው የንግድ ምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ሰላም አክሊሉ በበኩላቸው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በንግድ ምክር ቤቱ በኩል ስለሰላም ለመምከር በመጋበዛቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ሙስና በሰፈነበት አገር የሙስና ኮሚሽን፣ ሰላም ባልሰፈነበት የሰላም ሚኒስቴር ያለን ተብሎ የገለጹት አስተያየት፣ እሳቸውም እንደሚጋሩት ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ ነጋዴ ደግሞ፣ ድርጅታቸው በነበረበት አካባቢ በተፈጠረ ችግር ድርጅታቸው እንደተቃጠለባቸው በማስታወስ አስተያየታቸውን ጀምረዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የሰላም ዕጦት እያስከፈለ ያለውን ዋጋ በተጨባጭ አመላካች ሆኖ የታየው፣ በዕለቱ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻንቆ ደሳለኝ የቀረበው ማብራሪያ ነው፡፡ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት የፈጠረው ቀውስ የቀድሞ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ብቻ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወይም ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ 

ኮሚሽኑ ከ371 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ፐሮግራሞችን ለማስፈጸም የዚህን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ መሆኑ በሰላም ዕጦት የተፈጠረ መሆኑን ለመገንዘብ አስችሏል፡፡ 

በዕለቱ የተካሄደው የውይይት መድረክ አንደኛው ዓላማ ለሰላም ዕጦት የሚያስከፍለውን ዋጋ በመገንዘብ፣ ሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ማድረግ እንዳለበት ለማመላከት ነው፡፡  

ኮሚሽኑ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት የግድ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ዕገዛ ግድ በመሆኑ፣ በዕለቱ የንግድ ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ሊፈርም ችሏል፡፡ 

ያለ ሰላም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ማከናወን እንደማይቻል የገለጹት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር አቶ ተሾመ ቶጋ፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ መደበኛው ሕይወታቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የግል ዘርፉ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው፣ የሰላም ዕጦት ኢኮኖሚውን በተለይም የግል ዘርፉ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ተናግረዋል፡፡ 

አያይዘውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተስተዋለውን የሰላም ዕጦት በውጭም ሆነ በአገር በቀል ኢንቨስትመንት ላይ ጋሬጣ መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል፡፡ 

‹‹ችግሩ በረዘመ ቁጥር ኢንቨስትመንቱን እየጎዳው እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም፤›› ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ ሰላም ለኢንቨስትመንት መስፋፋት የማይተካ ሚና አለውና በግጭት ውስጥ የነበሩ አካባቢዎችንና ዜጎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የንግድ ኅብረተሰቡ አስተዋኦ ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ረገድ ከኮሚሽኑ ጋር አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡     

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻንቆ ደሳለኝ በሰጡት አስተያየት ሰላም በመንግሥት ጥረት ብቻ የማይመጣ በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰቡ ክፍል ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። አክለውም፣ ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችንና ተግባራትን ፖለቲካዊ አድርጎ መመልከት ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች