Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ነፃነት የታገለችውን ያ­ህል ለማንም አገር አልታገለችም›› ፍሰሐ አስፋው (ዶ/ር)፣ አንጋፋ የወታደራዊ ሳይንስና የሶሺዮሎጂ ምሁር

በወጣትነታቸው ሆለታ ወታደራዊ ማሠልጠኛ በካዴትነት ሠልጥነው በምክትል የመቶ አለቅነት ተመረቁ፡፡ ኮንጎ በሰላም ማስከበር ዘምተው ለ14 ወራት በስመ ጥሩው የኮሪያ ዘማች የያኔው ኮሎኔል በኋላ ሜጀር ጄኔራል ተሾመ እርገቱ ሥር እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ ተመልሰው በአስመራ በሁለተኛ ክፍለ ጦር አዛዥ በሌተና ጄኔራል አበበ ገመዳ ሥር የቅርብ ረዳት ሆነው ሠሩ፡፡ አዲስ አበባ ተመልሰው የመድፈኛ ኮርስ ከወሰዱ በኋላ ወደ ሚሊታሪ ፖሊስ ተዛውረው ሠርተዋል፡፡ ከዚያ አሜሪካ ሄደው ለ14 ወራት የሲቪክ አክሽን ኮርስ ተከታትለዋል፡፡ ከዚያ መልስ የማከብራቸው ለኢትዮጵያ ብሩህ አሳቢ የሚሏቸው ሌተና ጄኔራል አሰፋ አየለ የሲቪክ አክሽን አማካሪ ሆነው ሲሠሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለአራት ዓመት ትምህርት አሜሪካ ተመልሰው ተላኩ፡ ሆኖም በዚያው ለ12 ዓመታት ቆይተው የፒኤችዲ ዲግሪ ትምህርት ጨርሰው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተገልብጦ ደርግ ሥልጣን በያዘበት፣ ሁሉም ወደ ውጭ እንጂ ወደ አገር ቤት ማሰብን በተወበት ጊዜ መመለሳቸው ብዙዎችን እንዳስገረመ ያስታውሳሉ፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አስጠርተው አመሠገኑኝ የሚሉት ፍሰሐ አስፋው (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመድበው በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኃላፊነት መሥራት ቀጠሉ፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት ውስጥ በወቅቱ ምርጥ ከተባሉ ምሁራን ጋር ለአሥር ዓመታት መሥራታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ከናቅፋና ከደደቢት ውጪ ያልረገጥኩት የኢትዮጵያ ምድር የለም የሚሉት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን በማጥናት፣ ለኢትዮጵያ ይበጃል ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር ሲያዘጋጅና ሕገ መንግሥት ሲያረቅ ተሳታፊ እንደነበሩም ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም በሰሜን ያለው ውጊያ ተባብሶ መንግሥት ፈረሰ፣ ኢንስቲትዩቱ ተዘጋ፣ ጥናቱም ዳር ሳይደርስ ቀረ ይላሉ፡፡ ካካበቱት ወታደራዊ፣ አካዳሚያዊ፣ የዲፕሎማሲ ልምድ፣ በጥናት ካገኙት ብቻ ሳይሆን ኖረው ካለፉበት ተሞክሮ ተነስተው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን ያነሱበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ፈተና እንዴት ይገልጹታል?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ከባድ ችግር የገጠማት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ችግሩ ምንም እንኳን ቀደም ብሎ የተጠነሰሰ ቢሆንም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ግን እየከፋ ነው የሄደው፡፡ በተለይም የውስጥ ችግራችን በግልጽ የሚታይ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ብዙ ግጭት አለ፣ የሰላም ዕጦት አለ፡፡ ምናልባትም አዲስ አበባ ካልሆነ በስተቀር ሰላም ያለበት ቦታ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ብዙ ዓይነት ጥያቄዎች  አሉ፡፡ የፖለቲካ፣ የሕገ መንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የሙስና፣ በአጠቃላይ ሰብሰብ ስናደርገው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ንግግር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት፣ ተቃዋሚውም ሆነ ሕዝቡ፣ ልሂቃኑም ሆኑ ሌላው ይመለከተኛል የሚለው ተቀራርቦና ተወያይቶ ለመፍታት ያለው ፍላጎት አነስተኛ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት መንግሥት አባት ነው፡፡ ልጅ ባለገ፣ ውጪ አደረ፣ አልማር አለ፣ ሌባ ሆነ ተብሎ አይጣልም ሥጋ ነውና፡፡ መንግሥትም አባት በመሆኑ በአባትነቱ ምንድነው የሕዝብ ፍላጎት ብሎ በየት በኩል ብንሄድ ይሻላል የሚለውን ጠይቆና መክሮ ነው መወሰን ያለበት፡፡ መንግሥት ይህን ማድረግ ሲገባው አንዳንድ አደረግኩ የሚላቸው ውይይቶች የለበጣና ጊዜያዊ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በዲፕሎማሲው የገጠመውን ፈተናስ እንዴት ይገልጹታል?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- የውጪ ዲፕሎማሲያችን በአገር ውስጥ ሁኔታ የሚመሠረት ነው፡፡ በኢኮኖሚ ጠንካራ ስትሆንና ሰላም ስትሆን የዲፕሎማሲ ዕርምጃህ ተደማጭነት ይኖረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በዲፕሎማሲው ገናና የነበረችው ኢትዮጵያ፣ አሁን ግን ምንድነው እያደረገች ነው ያለችው የምትባልበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ኅብረትን ለመመሥረት የተደረገው ጥረት በትልቁ ይወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣናው በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የነበረው ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ብዙ ጊዜ ይዘለላል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ፖሊሲ ነበር ስትከተል የቆየችው የሚለውን መለስ ብለው ቢነግሩን?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወይም ለአፍሪካ ምን ነበረች የሚለውን ቀድመን እናንሳው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ ከነበሩ አገሮች ብቸኛዋ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት የነበራት አገር ናት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች ናት፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ናት፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ይህን በማሰብ በሰንደቅ ዓላማዎቻቸው ላይ ሳይቀር፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን በተለያዩ መንገዶች ይጠቀሙታል፡፡ ለቅኝ ተገዢ አገሮች በብዙ መንገዶች የቆመችና የአፍሪካ አባት የሆነች አገር ናት፡፡ ከአፍሪካ አልፎ ከካሪቢያን እስከ አሜሪካ ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያ የነፃነት ዓርማና ተምሳሌት ናት፡፡

ወደ ቀጣናችን ብንመጣ በምሥራቅ አፍሪካም ቢሆን በእኔ ዕድሜ ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች ነፃ አገር፡፡ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያ፣ ራቅ ስትል ደግሞ ኮንጎ እነዚህ ሁሉ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የቀጣናው አገሮች የነፃነት ታጋይ የነበረችው ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለኬንያ መሣሪያና ገንዘብ ሰጥታ፣ የፖለቲካ ድጋፍ አድርጋ የማኦ ማኦ ትግላቸውን ደግፋለች፡፡ በእኔ ጊዜ ኬንያ የኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ቤት ነበረች፡፡ ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ክፈሉ መባላቸውን እሰማለሁ፣ ያኔ ግን ኬንያዊያን ኢትዮጵያውያንን ያለቪዛ ነበር የሚቀበሉት፡፡ እንዲያውም አንድ ነን እስከማለት ይደርሱ ነበር፡፡ ታንዛኒያም ብትሆን ለኢትዮጵያ ልዩ አቀባበል ነበራት፡፡ ኡጋንዳም እንደዚያው ነው፡፡ እኔ ኮንጎ በሄድኩ ጊዜ ኡጋንዳን አርፌባታለሁ በደንብ አውቃታለሁ፡፡ አንድ ጥቁር የጦር መኮንን ወታደር ይዞ ሬስቶራንት ሲገባ ሲያዩ ልክ እንደ ተዓምር ከየኩሽናው ወጥተው ነበር ሰላምታ የሚሰጡትና ደስታቸውን የሚገልጹት፡፡ ይህ ለእነሱ የነፃነት ትግል ብዙ ሞራል የሚሰጥ ነበር፡፡ ጥቁር መዋጋት፣ ማዘዝና ማዝመት ይችላል የሚል ስሜት ቀስቅሶባቸዋል፡፡ ወደ ሶማሊያ በምንመጣበት ጊዜም ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ነፃነት የታገለችውን ያህል ለማንም አገር አልታገለችም፡፡ ፖለቲከኞቹን እዚህ አዲስ አበባ አምጥታ አስቀምጣ ወደ አንድነት እንዲመጡና ሶማሊያን ነፃ እንዲያወጡ ስትደግፍ ኖራለች፡፡ ሶማሊያ በቅኝ ገዥዎቹ የኢጣሊያና የብሪቲሽ ሶማሊያ ተብላ የተከፋፈለች ነበረች፡፡ ለእንግሊዝ ሶማሊያ ለብቻው ለኢጣሊያም ሶማሊያም ለብቻው የነፃ አገርነት ዕውቅና ለመስጠት ቅኝ ገዥዎች ፈልገው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሶማሊያ አንድ ናት፡፡ በባህልም፣ በሃይማኖትም ሆነ በቋንቋም አንድ ሕዝብ ነው ያላት፡፡ እናንተ ለራሳችሁ ጥቅም አትከፋፍሉትም ብላ ታግላቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ሶማሊያ አንድ እንድትሆን ስትደግፍ ቆይታለች እያሉ ነው?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- አዎን አንድ እንዲሆኑ ታግላለች፡፡ ይህንን ማንም የሶማሊያ ምሁርም ሆነ ፖለቲከኛ ሊክደው አይችልም፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ሸርማርኬ ይባላል፣ እዚህ አዲስ አበባ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ቤቱን እንኳን መጠቆም እችላለሁ፡፡ ራስ መኮንን ድልድይ የፈረሰው ባለፎቁ የግሪኮች ቤት እዚያ ነበር የሚኖረው፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ናቸው እንደ ሶማሊያዊያን ሆነው ለሶማሊያ አንድነት የተዋጉት፡፡ ጂቡቲ እንደሚታወቀው ለ99 ዓመታት በውል ነበር የተሰጠችው፡፡ በዚያው ግን ነፃ አገር ሆናለች፡፡ አገሪቱ ግን ከኢትዮጵያ ጋር የቅርብ ዝምድና ያላትና ለኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛ ቤት የምትታይ ናት፡፡ የአሁኑ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ድሬዳዋ ያደገና አማርኛ ጭምር አቀላጥፎ የሚናገር ነው፡፡ ጂቡቲ ከቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ ከኢትዮጵያ ጋር መቀላቀል ሲገባት የፈረንሣዮች ፍላጎት በዚያን ጊዜ ሻርል ደጎልም ለመፍቀድ ዝግጁ ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን እኔም ሆንኩ ብዙዎች በማናውቀው ሁኔታ ችግር ተፈጠረ፣ ጂቡቲም ነፃ አገር ሆና ቀረች፡፡ ሆኖም ጂቡቲና ኢትዮጵያ ተሳስበው የሚኖሩ ወንድምና እህት ጎረቤት አገሮች ናቸው፡፡ ጂቡቲ ተመልሳ የእኛ የምትሆንበት ዕድሉ ነበር፡፡ ለማጠቃለል ያህል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እጅግ የተከበረች አገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በውትድርናው እንበለው በዲፕሎማሲ በቀጣናው ኃያል አገር ነበረች፡፡

ሪፖርተር፡- ከሱዳን ጋር የነበረው ግንኙነትስ?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ጥሩ ግንኙነት የነበረን ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ጄኔራል አቡድ በነበረ ጊዜ ከንጉሡ ጋር ጥሩ ዓይነት ወዳጅነት ነበራቸው፡፡ ከግብፅ ጋር የነበረን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚታወቀው የሳሳ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ከግብፆቹ ጋር ያለን ግንኙነት ተበጥሶ ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይገባ ጥንቃቄ የተሞላበት መንገድ ነበር የምንከተለው፡፡ በዓባይ ጉዳይ በጣም ስሜታዊ ናቸው፡፡ አንዲት ጭልፋም እንዳይነካብን የሚሉ ናቸው፡፡ እኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ክፍል ምክትል በነበርኩ ጊዜ የግብፅ ዲፕሎማቶች ሁልጊዜ ወደ ሰሜን አካባቢ ይሄዱ ነበር፡፡ ለምንድነው የሚሄዱት የሚል ሥጋት አደረብኝ፡፡ በየጊዜው የሚሄዱት በኢትዮጵያ ከሚተከለው ዛፍ ጀምሮ የዓባይን ፍሰት የሚያጎድል ነገር መሠራት አለመሠራቱን ለመሰለል ነበር፡፡ ወንዙ ቦይ ተቀደደለት ወይ ብለው ያጠኑ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ጠንካራ ወታደርም ዲፕሎማትም ነበሩ፡፡ ለእሳቸው ይህ የግብፆቹ ሁኔታ ታስቦበታል ወይ የሚል ምክር አቀረብኩ፡፡ ቆይ ከደኅንነት ጋር እንነጋገር ብለው ግብፆቹ ወደዚያ የኢትዮጵያ ክፍል ያለ ፈቃድ እንዳይንቀሳቀሱ አድርገናቸው ነበር፡፡ ግብፆቹ ይህን ሲያደርጉ የነበረው ለብዙ ዓመታት ነው፡፡ ከዚህ ከሙገር ጀምሮ ዛፍ መተከሉን ሲቆጥሩና ወንዙ መጉደሉን ሲሰልሉ ነው የኖሩት፡፡ ግብፆች ከእኛ ጋር በዚህ ደረጃ የመጠራጠር ግንኙነት ነው የፈጠሩት፡፡ ከሱዳን ጋር የነበረንን ግንኙነትም ይኼው የግብፆቹ ተፅዕኖ ሲጫነው ቆይቷል፡፡ ሱዳን ከቅኝ ግዛት እንድትወጣ ኢትዮጵያ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ መረሳት የሌለበት ደግሞ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ሱዳኖች ባለውለታችን ነበሩ፡፡ ያኔ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዥ የነበሩ ቢሆኑም ነገር ግን ለሱዳኖች ነው ባለውለታነቱን የምንሰጠው፡፡ በወረራው ዘመን ሱዳን ለእኛ መረማመጃችን ነበረች፣ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ተቀብላለች፣ ብዙ ድጋፍ በሱዳን አግኝተናል፡፡ ይሁን እንጂ የኤርትራ ተገንጣዮች በግብፅ ገፋፊነት ሲፈጠሩ ሱዳን አስጠልላለች፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያ ሽምቅ ተዋጊዎች ድንኳን ሆና ኖራለች፡፡ በዚህ ምክንያትም አንድ ጊዜ በውይይት፣ ሌላ ጊዜ ውል ሲፈርስ ወጣ ገባ በሚል ግንኙነት ነው የቆየነው፡፡ ወደ ጦርነት ደረጃ የሚያደርስ ነገር የለንም፡፡ አሁን እንደምናየው ብዙ ኪሎ ሜትሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተው ተቀምጠዋል፡፡ ያን ጊዜ ግን አይደፍሩንም ነበር፡፡ ሱዳን ውስጥ ያልተጠለለ ሸማቂ አልነበረም፡፡ ሆኖም ብዙም አይደፍሩንም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከሶማሊያ ጋር የነበረው ግንኙነት በብዙ ውጣ ውረድ የተሞላ ነው፡፡ አሁንም ፍጥጫው ቀጥሏልና ይህ ለምን ሆነ?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ከኬንያ ጋር ችግር የለብንም፣ ከኡጋንዳም፣ ከጂቡቲም ጋር ችግር የለብንም፡፡ ብዙ ጊዜ ከሱዳንና ከሶማሊያ በኩል ያለው ግንኙነታችን ነው ችግር ሲገጥመው የቆየው፡፡ ኢትዮጵያ ያን ያህል ውለታ ሠርታና ያን ያህል ለነፃነቷ ታግላ ሶማሊያዎቹ ግን ወዲያውኑ ነበር ነገር መቆስቆስ የጀመሩት፡፡ ግሬተር ሶማሊያ (ታላቋ ሶማሊያ) በሚል ትርክት የኢትዮጵያን ሶማሌ ክፍል፣ እንዲሁም የኬንያን ሶማሌ ግዛት መውሰድ አለብን የሚል ዘመቻ ከፈቱ፡፡ ይህን ሐሳብ የፈጠሩት የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ አንዳንድ የዓረብና የምዕራባዊያን አገሮች ናቸው፡፡ በእኔ አመለካከት በዚህ ጉዳይ ጣሊያን ጉልህ የሆነ ሚና አልነበረውም፡፡ ግልጽ ሆኖ ለመናገር ያህል እንግሊዝና ግብፆች ናቸው የዚህ ሐሳብ ጠንሳሾች፡፡ በዚያ በኩል እንድንወጠርና ወደ ዓባይ ወንዝ ጉዳይ ፊታችንን እንዳናዞር ታስቦ ነው የተፈጠረው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቁስቆሳቸው ሳይሳካ ነው የቆየው፡፡ በ1960ዎቹ ግን በእኛ ውስጥ ብዙ ችግር ተፈጠረ፡፡ ኢሕአፓ፣ አብዮት፣ ፖለቲካዊ ለውጥ፣ ንጉሡ ወርደው ወታደር ተተካ፣ ይህ ሁሉ ሲፈራረቅብን ደካማ መስለን ለሶማሊያዎቹ ታየናቸው፡፡ በቃ አሁን ነው ጊዜያችን ብለው ወረሩን፣ አዋሽ ለመድረስም ተንደረደሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን አንድ መሠረታዊ ትርክት አለን፡፡ ኢትዮጵያውያን በደህናው ጊዜ ቢለያዩም ሆነ ቢሻኮቱም በችግር ጊዜ ግን ቁርሾአቸውን ወደ ጎን ብለው በጋራ ይሠለፋሉ የሚል የቆየ ጠንካራ ብሂል አለን፡፡ ይህ በአሁኑ ጊዜ እንኳ አይሠራም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ብሂል ከሕወሓት ጋር በተደረገው የህልውና ዘመቻ ወቅት አልሠራም?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- አሁን አይሠራም እንጂ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ አላልኩም ነበር እኮ፡፡ ከሕወሓት ጋር በተደረገው ዘመቻ ይህ ብሂል ባይሠራ ኖሮማ ሕወሓት አይሸነፍም ነበርኮ… (ሳቅ)፡፡ ወደ ሶማሊያ ስንመለስ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ ተወራ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ዝም ትላለህ ብለው ገበሬውንም ሠራተኛውንም አስተባብረው አሠለፉ፡፡ የኢትዮጵያን መፍረስ የማይፈልጉት ፊደል ካስትሮና ኩባዎች፣ እንዲሁም የመኖች በሚቻለው ረዱን፡፡ የሶማሊያን ወረራ ቀልብሰን ወደ ቦታዋ ተመለሰች፡፡ በሶማሊያ የተማረኩ ኢትዮጵያውያን ምርኮኞች ለአሥር ዓመታት ታስረው ሲመለሱ ነፍሱን ይማርና የአየር ኃይሉን ጄኔራል [ብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ] ጨምሮ ብዙ ሰዎችን ሲቀበሉ ጓድ መንግሥቱ አንድ ነገር ቃል ገቡ፡፡ ዕንባ በተናነቀው ስሜት ተውጠው እነዚያን የተጎሳቆሉ ጀግኖች እያፅናኑ ሲናገሩ አጠገባቸው ነበርኩ፡፡ እነኛን ምርኮኞች ሐረር ሲቀበሉ በቁጭት ስሜት በሕይወት እያለን የእናንተን ብድር ሳንመልስ አንቀርም አይዟችሁ ብለው ቃል ገቡላቸው፡፡ ምርኮኞቹ የተፈጸመባቸውን ነገር ሲናገሩ ያሳዝናል፡፡ የአየር ኃይሉን ጄኔራል ለአሥር ዓመታት ጨለማ ቤት ውስጥ ነበር ያቆዩት፡፡ ሌላም አብራሪ ነበር፡፡ ታሪኩን ሲነግረን ከማሳዘን ይልቅ ያስቀን ነበር፡፡ እዚያ ጨለማ ቤት ሆኖ በየጠዋቱ እየተነሳ ዩኒፎርሙን ለብሶ፣ ኮክ ፒት ውስጥ ገብቶ፣ ሞተር አሙቆ፣ በሮ ድሬዳዋ አርፎ ድጋሚ ዞሮ እንደሚመለስ በሐሳቡ የሚፈጥረውን ነገር ሲናገር እያዝናና አንጀት ይበላል፡፡ ለአሥር ዓመታት ጭለማ ውስጥ ኖሮ ለምን እንዳላበደ የሚገልጽበት መንገድ ይገርም ነበር፡፡ ሁለቱ ፓይለቶች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያኑ ምርኮኞች ብዙ ጉስቁልና ቢገጥማቸውም ልባቸው ግን ፍጹም አልተሰበረም ነበር፡፡ በሚያስደንቅ የአገር ፍቅር ስሜትና ፅናት ያን ጊዜ እንዳሳለፉ ይነግሩን ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ይህን የኢትዮጵያውያን ምርኮኞች ታሪክ ሰምተው አዘኑ፡፡ በዚያው ጊዜም ለሶማሊያ ብድሩን እንደሚከፍሉ ለሕዝቡ ቃል ገቡ፡፡ መንጌ ምን አደረጉ የሚለውን ትጠይቀኛለህ ልቀጥል?

ሪፖርተር፡- አዎ እንዴታ?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- በጣም ጥሩ፡፡ ቅድም ሱዳን ለብዙ የኢትዮጵያ ሸማቂዎች መሸሸጊያ ነበረች እንዳልነው ሁሉ ኢትዮጵያም በዚያድ ባሬ መንግሥት ላይ የተነሱ ኃይሎችን መደገፍ ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከማስጠለል ጀምሮ ማስታጠቅና መደገፍን አጠናከረች፡፡ በደኅንነት ረገድ ደግሞ ለዚህ ወሳኝ ሥራ አንድ መኮንን በአምባሳደርነት ተመደበ፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሎኔል አስማማው ቀለሙን (ዶ/ር) ነው የሚሉት?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- አዎን ኮሎኔል አስማማው፡፡ መጀመሪያ ወደ ኬንያ ሄደው ራሳቸውን ቀይረው አምባሳደር ተብለው ወደ ሶማሊያ ገቡ፡፡ የሶማሊያን ተጋላጭ ሁኔታዎች አጥንተው፣ የሶማሊያ ሸማቂዎችን የመርዳት ዕቅድ ነድፈው አዘጋጁ፡፡ በዚህም የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ ላደረሰው ግፍ ምላሽ እንዲሰጠው ተደረገ፡፡ ሆኖም የዚያድ ባሬ መንግሥት ተፍረከረከ፡፡ በዚህ የተነሳም ሶማሊያ ተባታተነች፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሊያ እንድትበታተን ከመጀመሪያው አልፈለገችም፡፡ እንዲያውም ለሶማሊያ አንድነት ስትታገል ኖራለች፡፡ ይሁን እንጂ የዚያድ ባሬ መንግሥት የፈጸመው ወረራና ግፍ ኢትዮጵያ ምላሽ እንድትሰጥ የሚጋብዝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን የሶማሊያ አንድነትን ታከብራለች፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር ኢትዮጵያ የተፈራረመችው ስምምነት ከሶማሊያ ጋር  ከባድ ፍጥጫ ፈጥሯል፡፡ ይህ የሶማሊያ ግዛትን መውረርና ሉዓላዊነት መዳፈር ተደርጎ በሞቃዲሾ ሰዎች እየታየ ያለ ጉዳይ ሲሆን ቀጣናዊ ውጥረትም አስከትሏል፡፡ ይህ ለምን የተፈጠረ ይመስልዎታል?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ኮሎኔል መንግሥቱ ከሥልጣን ወርደው መለስ ዜናዊ በነበሩ ዘመንም ኢትዮጵያ የሶማሊያ አንድነትን ስትደግፍ ኖራለች፡፡ ሶማሌላንዶች በኮንፌዴሬሽን የመዋሀድ ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና መለስ እንዳልተቀበሉት ሰምቻለሁ፡፡ በነገራችን ላይ መለስ ዜናዊ የመሩት የኢሕአዴግ መንግሥት ከአንድ ትልቅ ስህተት በስተቀር የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ፖሊሲ አስጠብቆ ነው የዘለቀው፡፡ ሶማሊያ እንድትገነጣጠል አልደገፈም፡፡ አልሸባብ በሚመጣ ጊዜም የኢትዮጵያን ጦር ልኮ ለሶማሊያ መጠናከርና አንድነት ተዋግቷል፡፡ ይህ ታልፎ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ የሚገርም ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ከአንድም ሦስት የባህር በሮች የነበሯት አገር ነበረች፡፡ አሁንም ቢሆን የባህር በር ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ሳይሆን የቀረው ደግሞ በመንግሥታት ስህተት ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት አሰብን አልፈልግም፣ ኤርትራም ትገንጠል ብሎ አገሪቱን ወደብ አልባ አደረጋት፡፡ የመለስ ዜናዊ መንግሥት በግሌ የኢትዮጵያን አንገቷን (ኤርትራን) እና ሆዷን (አሰብን) ቀዷል ነው የምለው፡፡ አሁን የባህር በር ያስፈልገናል፡፡ ነገር ግን ባህር በር የምናገኘው እንዴት ነው የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ዛሬ የዓለም ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ ዛሬ በማስፈራራት የሚፈጸም ነገር የለም፡፡ ዛሬ እኛ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ቢኖረንም ጂቡቲን እንኳ ማስፈራራት አንችልም፡፡ የባህር በር ከፈለግክ ጂቡቲም ሆነ ሌላ አገር በሰላማዊ መንገድ አጥንተህና የሚያሳምን የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርተህ መሆን አለበት፡፡ በውስጥም በውጭም ግራ ቀኙን ዓይተህ የምትወስነው ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሰላም ሽልማት ያስገኘ ብቻ ሳይሆን፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ያሻሻለ አጋጣሚ ነበር፡፡ በጊዜው ኤርትራውያንን አሰብን ለመስጠት ዝግጁ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሮም ነበር፡፡ በስምምነት በተቋጠረ መንገድ ወደቡን ለመስጠት እኛ አልምተን እንድንጠቀምበት ለማድረግ ለምን አልተቻለም የሚለው ጉዳይ መጠየቅ አለበት፡፡ በኬንያ በኩልም ቢሆን በሞምባሳና በሌሎች ወደቦች ለመጠቀም መንገድና ሌላም መሠረተ ልማት መገንባት ከጀመረ ቆየ፡፡ ይህ ምን ደረጃ እንደደረሰም መጠየቅ አለበት፡፡ አሁን ከዚህ አልፈን ያውም ከተገነጠለች፣ የዓለም መንግሥታት ካላወቋት፣ እንዲሁም ራሱ የሶማሊያ መንግሥት የእኔ ግዛት ናት ከሚላት አገር ጋር ሄዶ ስለባህር በር መወያየቱ በእኔ ግምት ተገቢ አይደለም፡፡ ለመንግሥት አክብሮት አለኝ፣ ሆኖም ይህ ትክክለኛ የዲፕሎማሲ አሠራር አይደለም፡፡ ይህን ነገር ለመንግሥት ያማከሩ ሰዎችም ቢሆኑ ለአገር ሰላምና አንድነት በማሰብ ያደረጉት አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ የተነሳ ፀብ አጫሪ ተደርጎ እንዲታይ ከማድረግ በዘለለ፣ የኢትዮጵያን ክብርና ተቀባይነት የሚጎዳ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሐርጌሳም ካስፈለገ መንግሥት ብለን ካወቅነው የሶማሊያ መንግሥት ጋር በመነጋገር መፍትሔ መፈለግ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ አንድ ክልል ልገንጠል ቢልና ሶማሊያ፣ ኬንያ ወይም ሱዳን ዕውቅና እንስጠው ቢሉ በእኛ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን ፍጥጫውን ያመጣው የስምምነት ጉዳይም ስህተት ነው እላለሁ፡፡ ለምሳሌ በሱዳን በዚህ ወቅት ከባድ ጦርነት በመደረግ ላይ ነው፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ጎራ ለይተው እየተዋጉ አገር እያወደሙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የድሮዋ ኢትዮጵያ ብትሆን ኖሮ ሱዳኖችን መሸምገል ነበረባት፡፡ ነገር ግን ከዚያ ይልቅ አሁን ኢትዮጵያ ካለች አንሸማገልም የሚሉ ኃይሎች በአካባቢያችን እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምንይዝ የምንጨብጠውን ባጣ የዲፕሎማሲ ሥራ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ከኬንያ ጋር ችግር አለብን፡፡ ኦነግ በሙሉ ኬንያ ሠፍሯል፡፡ በቀደም ኢጋድ ስብሰባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን አልሄድም ብላ ቀርታለች፡፡ ኢትዮጵያ በስብሰባው ተገኝታ የራሷን አቋም ከማንፀባረቅና ሌሎችን ሞግቶ ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ አልገኝም ብላ ቀርታለች፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ስህተት ነው፡፡                

ሪፖርተር፡- የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን የጂኦ ፖለቲካ ከባቢ አየር ሁለት ነገሮች እንደሚበይኑት ይወሳል፡፡ የቀይ ባህርና የዓባይ ጂኦ ፖለቲካ ወሳኞቹ ናቸው ይባላል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ቀጣናውን ተፅዕኖ ውስጥ የከተቱ ጉዳዮች ምንድናቸው?

ፍሰሐ (ደ/ር)፡- ዓባይን ችግር የምናደርገው እኛው ነን እንጂ ሌላው አይደለም፡፡ መለስ ዜናዊን በዚህ ላይ አደንቀዋለሁ የዓለም መንግሥታት ባትረዱኝም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይገነባዋል ብሎ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ጀምሮታል፡፡ በየጊዜው ፉከራና ዛቻ ቢመጣም አስቀጥሎታል፡፡ ሆኖም ሕዝቡ ዓባይ ዓባይ እንዲል የሚደረገው ለፖለቲካ አቅጣጫ ማስለወጫ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም ዓባይ ዓባይ ሲል መሠረታዊ የአገር ችግሮች በዚያው ይረሳሉ፡፡ የመንግሥቱ ዘመንን የውስጥ ፖለቲካ ያረገበለት የሶማሊያ ወረራ ነበር፡፡ የመለስ ዜናዊን ዘመን የውስጥ ፖለቲካ ያሰከነው ደግሞ አንዱ የባድመ ወረራ ነበር፡፡ በአገሪቱ ትልቅ ውጥረት በነበረ ጊዜ ኢሳያስ አፈወርቂ ድንገት ዘሎ ድንበር ሲወር፣ እሱ ነው አገራችንን ለዚህ የዳረገ ተብሎ ሁሉም በአንድነት ሊዘምት ተነሳ፡፡ አሁንም ቢሆን በውስጥ የተፈጠሩ የፋኖ፣ የኦነግ ሸኔና የሌሎችም ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማርገብ ዓባይን፣ እንዲሁም ቀይ ባህርን ለማስተንፈሻነት የመጠቀም ዝንባሌ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቀይ ባህር ይባላል፣ ነገር ግን ቀይ ባህር ምንድነው የሚያደርግልን፣ ‹‹ቀይ ባህር ሳይሆን ቀይ ሽንኩርት ነው የሚያስፈልገን›› ያሉ አሉ፡፡ ያለቀይ ባህር ይህ ሁሉ ሕንፃ ሲገነባና ኢኮኖሚው ሲያድግ ዓይተናል፡፡ ቀይ ባህር በሌለ ጊዜ የሽንኩርት መዘዋወር ችግርም አልነበረም፡፡ ኢኮኖሚስት አይደለሁም፣ እንዲያውም ምጽዋና አሰብን ካጣን በኋላ ኢኮኖሚው ማደጉን መታዘብ ይቻላል፡፡ በግሌ ቀይ ባህር አያስፈልገንም አልልም፡፡ ሆኖም መቅደም ያለበት ፈረሱ ወይስ ጋሪው የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡ መጀመሪያ አገር ውስጥ ሰላምን መሥርተህ፣ ሕዝብህን አንድ አድርገህና ውስጣዊ አቅምህን አጠናክረህ ነው የባህር በር መጠየቅ ያለብህ፡፡ ስትጠይቅም ቢሆን በቂ ጥናትና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርተህ መሆን አለበት፡፡ ይህን ካደረግክ በኋላ የጦር ብቻ ሳይሆን የሕዝብም ድጋፍ ይኖርሃል፡፡ በነገራችን ላይ ወታደራዊ ጥንካሬ አለ፣ ሕዝብ ድጋፍ አይመጣም፡፡ እኔ ወታደር ነበርኩና አውቀዋለሁ፡፡ ወታደር ጠንካራ የሚሆነው ሕዝብ ሲደግፍህ ነው፡፡ ወታደር ከሰማይ አይወርድም፣ ከሕዝብ ውስጥ የሚወጣ ነው፡፡ ማዕረግ ስለኮለኮልክለት ወታደር ጠንካራ አይሆንም፡፡ ከልቡ አገሬ ብሎ የሚዋጋ ወታደር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ዘምቼ ስመለስ ሕዝቤ ወይም አካባቢዬ ይቀበለኛል ብሎ የሚተማመን ወታደር መፍጠር አለብህ፡፡ እኛ ለምሳሌ ኮንጎ ሄደን ነበር፡፡ ከኮንጎ በተመለስን ጊዜ በየቡና ቤቱ የሚከፍልንን ሰው አናውቅም ነበር፡፡ ሕዝቡ ለወታደሩ ፍቅር ይሰጥ ነበር፡፡ ያን ጊዜ አገሪቱ በኢኮኖሚም የጠነከረች፣ ወታደሩም የሕዝብ ድጋፍ ስለነበረው ነው፡፡

እኛ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ሊኖረን ይችላል፡፡ እስራኤል ግን ከእኛም ሆነ ዙሪያዋን ከከበቧት ዓረቦች ኣንፃር ስትታይ በእጅጉ ትንሽ አገር ናት፡፡ ሆኖም እስራኤል ከልብ አገሬ ብለው የሚፋለሙ ወታደሮችን መፍጠር በመቻሏ ሊያጠፏት የተነሱ ኃይሎችን ተፋልማ መኖር ችላለች፡፡ ብዙ ሕዝብ አለህ ማለት ወታደራዊ ጥንካሬ አለህ ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብ ቢበዛም መንጋ ነው፡፡ ከበዛው ሕዝብ ውስጥ ሊዋጋ የሚችለው ውስን ነው፡፡ ወታደራዊ ጥንካሬ ደግሞ ያለ ኢኮኖሚ ጥንካሬም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሁለቱም ኖሮህ ደግሞ የሕዝብ ድጋፍ ከሌለህ ወታደራዊ ጥንካሬ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡

ወደ ዋናው ቁምነገር ስመለስ የቀይ ባህር ጉዳይ አሁን ባለንበት አገራዊ ሁኔታ ለፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣልን ነገር የለም፡፡ ዓባይን በተመለከተም ቢሆን ጉዳይ ማድረግ የለብንም፡፡ ግድቡ ሳይገነባም ሆነ ተገንብቶም ግብፆቹ ከዚያ ላይ ዓይናቸውን አይነቅሉም፣ ውኃው ሕይወታቸው ነውና፡፡ ወታደራዊ ጥበቃ የሚያስፈልገውን ወታደራዊ ጥበቃ ልናደርግለት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ጉዳዮቻችንንም በፖለቲካው መፍታት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ እነዚህን አጀንዳዎች ለጥጠን ፖለቲካዊ ማድረግ የለብንም፡፡ የህዳሴ ግድቡ ራሱን ይጠብቃል፡፡ ላፍርስ ቢሉ ሱዳኖቹ በጎርፍ ይጠረጋሉ፡፡ ከተፈለገ ደግሞ እዚያም ቤት እሳት አለ፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዚያድ ባሬን እንደተበቀለው ተሸሎክሉከን አስዋን ግድብን ማፈንዳትም እንችላለን፡፡ ስለዚህ የቀይ ባህር ወይም የዓባይ ጉዳይ የሚባሉ አጀንዳዎችን ለጥጠን ዋና የፖለቲካ ጉዳዮች አናድርጋቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ቀንድ ከባድ የኢኮኖሚ ድህነት የተጫነው አካባቢ ነው፡፡ በዚህ ቀጣና የብሔር ፖለቲካና የሃይማኖት ጽንፈኝነት የገነገነ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በቀጣናው የሰፋ ነው፡፡ ዓረብ የራሱን አጀንዳ ይዞ ይመጣል፣ ፋርሶች፣ ምዕራባዊያኑም የራሳቸውን ጥቅም ለማስፈጸም ይመጣሉ፡፡ ጥንት ምፅዋ፣ ዘይላና አሰብ ወደቦችን በመውረር የሚታወቁት ቱርኮች ዛሬም ቢሆን በቀጣናው ፍላጎታቸውን ሊያስፈጽሙ ይጥራሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በተሞላው የአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ እንደ መኖሯ ምንድነው የሚበጀው ይላሉ?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- አሁን ወደ ሌላ ታሪክ ልትወስደኝ ነው፡፡ አለመታደለ ሆኖ ኢትዮጵያ ወዳጅ አድርጋ የቀጠለችው ታሪካዊ ጠላቶቿን ነው፡፡ ቱርክ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት፡፡ ወደቦቻችንን ከመቀማት በዘለለ ወራናለች፡፡ የዓረብ ኤምሬትስ በጃንሆይ ላይ ትልቅ ቅራኔ ነበራቸው፡፡ ጃንሆይ ሌሎች የዓረብ አገሮችን ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ ዕውቅና ሰጥተው ሲጎበኙና ከነገሥታቶቻቸው ጋር ሲገናኙ ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዓረብ ኤምሬትስ ጋር ግንኙነት ለማጠናከር አልተቻኮሉም፡፡ በዚህ የተነሳ ለእኛ ቦታ አይሰጡም ብለው ቅሬታ አድሮባቸዋል፡፡ ከዓረብ ኤምሬትስ ጋር ኢትዮጵያ ለዘብ ያለ ግንኙነት ነው የነበራት፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ነው የአምባሳደር ልውውጥ እንኳን የተደረገው፡፡ በዚህ የተነሳ የዓረብ ኤምሬትስ የመናቅና የመገፋት ስሜት አድሮባቸው ነው የቆየው፡፡ ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው የእስላምም የክርስቲያንም አገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በእምነቱ ቀናዒነት ብቻ አንዳንድ ለኢትዮጵያ ክፉ የሚመኙ አገሮችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ሲመለከት ይታያል፡፡ ተራ በተራ ሲወድቁ ያየናቸው ኢራቅና ሶሪያ የሚባሉ አገሮች ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ፖሊሲ ወደኋላ ተመልሶ ታሪክን መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢራኖች በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ የተነሳ ካልሆነ በስተቀር ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ያሻከሩበት ጊዜ የለም፡፡ ለዚያም ቢሆን ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥታ አልፋለች፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ የተጠጋቻቸው አገሮች ቢፈተሹ ወዳጅ መስለው ታሪካዊ ጠላትነትን ከእኛ ጋር ፈጥረው የቆዩ አሉ፡፡ የእኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን፣ የፈጣሪ ጥበቃ ታክሎበት ነው ብዙ የታሪክ ውጣ ውረድን አገራችን የተሻገረችው ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡

ከሰሞኑ ከሶማሊያ ጋር የገባንበትን ፍጥጫ ተከትሎ ድሮን ይሰጡናል የምንላቸው ቱርኮች፣ ወዳጅ ያደረግናቸው ዓረብ ኤምሬትስም ሆኑ ሌሎች የቅርብም የሩቅም አገሮች ያራመዱትን አቋም ኢትዮጵያውያን በጥንቃቄ መታዘብ ይኖርብናል፡፡ ጎረቤታችን ጂቡቲ ከጃፓን ጀምሮ የአሜሪካ፣ የፈረንሣይ፣ የቻይና፣ የሌሎችም ብዙ አገሮች ጦር ኃይል ሠፍሮ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጂቡቲ የተቀመጡት ወፍ ለመጠበቅ አይደለም፡፡ ቀጣናውን ለመቆጣጠር ባላቸው ፍላጎት ነው እዚያ የሠፈሩት፡፡ እኛ ዘለን እዚያ እሳት ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ነባር የዲፕሎማሲ ብሂል የሸምጋይነት ሚና ነው ሊኖረን የሚገባው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በፊት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሆኖ ሲመሠረት በቻርተሩ ላይ የመገንጠል ጥያቄን አይቀበልም፡፡ ይህንን መርህ መለስ ዜናዊ ለኤርትራ ሲል ባይጥሰው ኖሮ ኢትዮጵያ የመገንጠል ጉዳይን ደግፋ አታውቅም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አገሮች በሒደት የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ድርጊትንም የሚከለክል ሕግ አውጥተው እየተገበሩት ይገኛል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት መመሥረቻ ቻርተር ከተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎች ሌላው የቅኝ ግዛት ድንበር ተጠብቆ ይቆያል የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ አኅጉራዊ ሕግ ስትሟሟት ኖራለች፡፡ አሁን ይህንን መልሰን ጥሰን እንዴት ነው ከተገነጠለ አገር ጋር ስምምነት የምንፈራረመው? ኢትዮጵያ የአፍሪካ አባት የምትባል አገር ናት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ችግር ሲፈጠር በቀንዱም ሆነ በሌላ አካባቢ የማሸማገሉ ሥራ የኢትዮጵያ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ምን ይበጃል ተብሎ ምክር ተጠያቂ አገር ነበረች፡፡ የሰጠችው ሐሳብ ደግሞ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ በአስማሚ አገርነት እንጂ ጠብ ውስጥ ገብታ በማንደድ በፍጹም አትታወቅም፡፡  

ከኤርትራ ጋር ሰላም ሲፈጠር ሁሉም ሕዝብ ኢሳያስና ዓብይን የሰላም አባት ብሎ ተደሰተ፡፡ ከኤርትራ ጋር ደም መቃባቱና ለ20 ዓመታት በጠላትነት መኖሩ ተረስቶ ብዙ ሕዝብ በናፍቆትና በፍቅር ሲላቀስ ነው የታየው፡፡ ይህ የሆነው ሕዝቡ መጣላት አልነበረብንም ብሎ በውስጡ ለረዥም ጊዜ ሲቆጭና ሲንገበገብ በመኖሩ ነው፡፡ የመገንጠል ስሜት ብዙዎች ዘንድ ቢኖርም ሰላም መፈጠሩ ግን ብዙዎችን አስደስቶ  ነበር፡፡ ዕርቅ ማውረዱ በራሱ ወንድም የማግኘት ስሜትን የፈጠረ ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ልንደጋገፍ ነው፣ ወደብ ልንጋራ ነው፣ በጋራ ልንነግድ ነው፣ የውጭ ጠላቶችን የሚያርቅ ነው የሚልና ብዙ አዎንታዊ ስሜትን በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መካከል የፈጠረ ነበር፡፡ አሁን ተመልሶ ከሌሎች ጋር መቃቃርና መፋጠጥ ሲመጣ ደግሞ በሕዝቡ ውስጥ አሉታዊ ስሜት ነው የሚፈጠረው፡፡ እኔ ሽማግሌ ነኝ፣ በዚህ ዕድሜዬ ጦርነት የማውጅ ሰው አይደለሁም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ጦርነት የሰለቸው ይመስለኛል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጅ የምለው ምክረ ሐሳብ መንግሥት በረጋ መንፈስ፣ በሰከነ አዕምሮ፣ ሽማግሌዎቹ ቁጭ ብላችሁ መጽሐፍ ጻፉ ሳይባል ያለፉትንም የአሁኖቹንም አሰባስቦ፣ ምክረ ሐሳብ ጠይቆ፣ ከራስ ሐሳብ ጋር ደምሮ መሥራቱ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ዲፕሎማሲ ያካበተችውና መገለጫዋ የሆነውን በማንም ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ወይም ገለልተኝነትን እየተወች መጥታለች ስለመባሉ ይስማሙበታል?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ጠፍቷል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የገለልተኛ አገሮች ስብስብ (ነን አላይንድ) ሲቋቋም ከመሥራች አባላት አንዷ ነበረች፡፡ እነ ቲቶ፣ ኔሩ የመሳሰሉ መሪዎች ሲንቀሳቀሱ ጃንሆይም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ ዓለም ኮሙዩኒስትና ካፒታሊስት በሚባል ሁለት ጎራ ሲከፋፈል ኢትዮጵያ ከሁለቱም አልወግንም ከሚሉት አገሮች ጋር መሰባሰብን ነበር የመረጠችው፡፡ ጃንሆይ ቻይና ገብተው ማኦ ዜዱንግን ለማግኘት፣ ሶቪየት አምርተው ክሩስቼቭን ለማናገር፣ አሜሪካ ሄደው ደግሞ ኬኔዲና አይዘንሀወርን ለመገናኘትም ሆነ የአውሮፓ አገሮችን እንደ ልብ ለመጎብኘት የማይቸገሩ መሪ ነበሩ፡፡ ይህን ያመጣው የኢትዮጵያ ገለልተኛ ፖሊሲን መከተል ነው፡፡ በገለልተኝነታችን ተከብረን ነፃነታችንንም ሆነ ኢኮኖሚያችንን አስጠብቀን መኖር ችለናል፡፡ አሁን ከየትኛው ወገን እንደሆንን አይታወቅም፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ከማንም ትዕዛዝ አትቀበልም ነበር፡፡ እኔ የውጭ ጉዳይ ሠርቻለሁ፣ ምክረ ሐሳብ እንጂ የምንጠየቀው ይህን ካላደረጋችሁ ብሎ የሚደፍረን አልነበረም፡፡ በጃንሆይም ሆነ በመንግሥቱ ዘመን ይህ ተጠብቆ ነው የቀጠለው፡፡ ጃንሆይን ወደ ምዕራባዊያን አገሮች ሄደው ብድር እንጂ አውሮፕላን አንሰጥም አሏቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ግን ወደ ሞስኮ ነበር ያቀኑት፡፡ ሞስኮ ሲደርሱም የተደረገላቸው አቀባበል አሜሪካኖቹን ጭምር ያስደነገጠ ነበር፡፡ ይህ ልዩ ታሪክ ነው፡፡ ከሞስኮ ሳይመለሱ የጠየቁትን ገንዘብ አፈሰሱላቸው፡፡ ሶቪየቶቹ ደግሞ እዚህ መጥተው ባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክና ሌላም የመሠረተ ልማት ግንባታ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ጃንሆይ ቻይና ሲገቡም በተመሳሳይ የቻይና መንግሥት ምን እናድርግ ብሎ ጠየቀ፣ ግድ የለም እንጠራችኋለን ነበር የተባሉት፡፡ ይህን ያመጣው ገለልተኝነታችን ነው፡፡ በማንም ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባታችን የሚያዘን ኃይልም አልነበረም፡፡

አሁን ግን በውስጥ ጉዳዮቻችን ጣልቃ የመግባት ፈተና ነው የገጠመን፡፡ በሰሜኑ ጦርነት የገጠመን ሁኔታ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጦርነቱን አቁሙ፣ ኮሪዶር ክፈቱ ወይም ተደራደሩ ሲል የነበረው የውጭ ኃይል ነው፡፡ ከዚያ ወዲህም ቢሆን በሱዳን ጦርነት ወይም በሶማሌላንድ ጉዳይ የገጠሙን ሁኔታዎች የውጭ ኃይል ተፅዕኖ ያለበት ስለመሆኑ በሰፊው ይታማል፡፡ ይህ ማስረጃ ማቅረብ የሚጠይቅ ቢሆንም በእኔ ግምት ግን የቀደመው የገለልተኝነት ፖሊሲያችን በቦታው አለ የሚለውን እጠራጠራለሁ፡፡ መለስ ዜናዊን በብዙ መንገዶች እቃወመዋለሁ፡፡ ሆኖም ካለፈ በኋላ ሳየው በምዕራባዊያኑም ሆነ በሌሎቹ የውጭ ኃይሎች በቀላሉ የሚታዘዝ ሰው ነበር ብዬ አላምንም፡፡ ዲፕሎማሲ የአንድ ወገን ብልጠትና ማታለል ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሌም ቢሆን ሰጥቶ መቀበል ይኖራል፡፡ አንዳንዶች ለሶማሌላንድ ዕውቅና ሳንሰጥ ነው ወደቡን የምንወስደው ብለው ሕዝብ ለማሳመን ሲጥሩ ታዝቤያለሁ፡፡ ነገር ግን ሐርጌሳ ያሉትም በቀላሉ የሚታለሉና የሚፈልጉትን ሳያገኙ ወደ ስምምነቱ ገብተዋል ብሎ ለማመን ያስቸግረኛል፡፡ ዛሬ በእኔ ግምገማ ገለልተኝነታችንን አጥተናል እላለሁ፡፡ የምንመካበት ወዳጅና አጋርም የለም ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ልክ ውኃ ውስጥ ገብተህ ዋና ሳትችል እንደምትንቦጫረቀው ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡  

ሪፖርተር፡– በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት መርህ መከተል አስፈላጊ አይደለም?

ፍሰሐ (ዶ/ር)፡- ዲፕሎማሲ በጽሑፍ አለ፣ ዲፕሎማሲ በመርህ ደረጃ በምትከተላቸው ነገሮችም ሊመሠረት ይችላል፡፡ የእኛን ሦስት ጉዳዮች እንደ መርህ የሚያስቀምጥ ነበር፡፡ አንዱ ኢትዮጵያ በማንም ሌላ ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም የሚለው መርህ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ከማንም ጋር የማትወግን ገለልተኛ አገር ናት የሚለውም ሌላ መርህ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ግንድ የሆኑ መርሆችን ተከትለህ ታስፋፋዋለህ፡፡ የውጭ ጉዳይን በሚመለከት የጥናት ኢንስቲትዩት አለ፡፡ የሊቢያው ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በደርግ ጊዜ የአፍሪካ ኅብረትን ከአዲስ አበባ አስነቅሎ ወደ ሊቢያ መውሰድ ፈለገ፡፡ ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት ብዙ ሚሊዮን ዶላር ያፈሰሰ ሰው ነበር፡፡ በጊዜው ጉዳዩ ይጠና ተብሎ ዲፕሎማቱ ሁሉ ተሰብስቦ ከግራም ከቀኝም ተመከረ፡፡ ይህን ብናደርግ የጋዳፊ ዶላር ይቀራል ከሚለው ጀምሮ ተቃራኒ ሐሳቦች በግልጽ ተስተናገዱ፡፡ ከሦስት ወራት ጥናት በኋላ በመጨረሻ አንድ ዶክመንት ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቀረበ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ፈለቀ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ መሪዎች በደንብ ሞገቱት፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ መሪዎች ጭምር የሚፈሩት ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መሪዎች በደንብ ነበር የሞገቱት፡፡ አፍሪካውያን በሙሉ እስኪደነቁ ድረስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የግዴታ ኢትዮጵያ ልትሆን እንደሚገባት የማሳመን ሥራ ሠሩ፡፡ በሚኒስትሮቹ ስብሰባም ሆነ በመሪዎቹ ጉባዔ ላይ ይኼው በደንብ ተንፀባረቀ፡፡ አፍሪካዊያኑ ከእንቅልፋቸው ነቅተው ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠንካራ ሥራ ነበር የተሠራው፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሙአመር ጋዳፊ ወዳጃቸው ነበር፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ሲሟገቱት የጋዳፊ ታንክና የጦር መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመጣ አሳምረው ያውቁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከአገር ጥቅም አይበልጥም ብለው ሞገቱት፡፡ መንግሥቱ የኢትዮጵያን ጥቅም ከመንግሥታቸው ጥቅም አስበልጠው ለመታገል የቆረጡት በጥናት የተመረኮዘ ሰነድ ይዘው ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫን ለሊቢያ ሰጥተው የሻዕቢያና የወያኔ ሸማቂዎችን የሚያዳክሙበትን ጦር መሣሪያና ብር ማግኘት ይችሉ ነበር፣ ሆኖም አላደረጉትም፡፡ መንግሥቱ ለሥልጣናቸው ቢሰስቱ ኖሮ ጋዳፊን አስደስተው መሣሪያ በታጠቁ ነበር፡፡ ሆኖም ጉዳዩን አጥኑና ክፉና ደጉን ለይታችሁ ለአገር የሚበጀውን አቅርቡልኝ ብለው በጠየቁት መሠረት፣ ተጠንቶ የተሰጣቸውን ሰነድ ይዘው የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ውጪ የማይታሰብ ነው ብለው ጋዳፊን ተከራከሩ፡፡ ይህን በማድረጋቸው አገሪቱ ዛሬ ድረስ በዚህ ውሳኔያቸው ትጠቀማለች፡፡ እሳቸው ግን ሥልጣናቸውን በልዋጩ ሰውተዋል፡፡ ጋዳፊ በመንግሥቱ አቋም ተናዶ ብዙ መሣሪያና ዕርዳታ ለሽምቅ ተዋጊዎቹ ማዝነቡ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የኮሎኔል መንግሥቱን መንግሥት አዳክሟል፡፡

አገር የሚመራ መንግሥት ወይም መሪ የአገሩን ጥቅም ነው ከምንም በላይ የሚያስቀድመው፡፡ መሪዎችና ዲፕሎማቶች ከፕሮቶኮል ጀምሮ ነው የአገር ገጽታና ጥቅም መጠበቅ ያለባቸው፡፡ ከምትለብሰው ልብስ ጀምሮ እስከ አጨባበጥህ በሌሎች አገሮች ባለሥልጣናት ፊት የምትቀርብበት መንገድ፣ የአገርህን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚወስን ነው፡፡ መሪዎችና ዲፕሎማቶች ፕሮቶኮል የሚመደብላቸውና ረዳቶች የሚታዘዝላቸው ወዶ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በዓይኔ ያየሁትን ለመመስከር መንግሥቱ ናይሮቢ ሲሄዱ ያጋጠማቸውን ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡ የኮንጎው ሞቦቱ ሴሴኮ ኢትዮጵያ ሳይመጣና መንግሥቱን ሳይጨብጥ ያለፈ መሪ ነው፡፡ መንግሥቱን የአባቴ ገዳይ ነው ይል ነበር፡፡ ገና በሩቁ ሲያያቸው የጎሪጥ ዓይቶ ተገላምጦ ነበር በአጃቢዎቹ እየተመራ በሩቁ የሄደው፡፡ መንግሥቱ ደግሞ በተቃራኒው በጊዜው የሶማሊያውን ዚያድ ባሬን በፍጹም ማግኘት አይፈልጉም ነበር፡፡ ናይሮቢ ወደ ስብሰባው አዳራሽ የሚገባና የሚወጣበት መንገድ የተመደበ ሲሆን፣ ፕሮቶኮሎቹም መሪዎቻቸውን አጅበው ዲፕሎማሲያዊ ወግና ማዕረግ በተከተለ ጥንቃቄ ነው እንቅስቃሴ ሲደረግ የነበረው፡፡ በድንገት ግን ዚያድ ባሬ ሊወጣ መንግሥቱ ደግሞ ሊገቡ ሲሉ መተላለፊያው ላይ ተያዩ፡፡ የኬንያ ሰዎች እለፉ እያሉ የኢትዮጵያ ፕሮቶኮሎች ግን መንግሥቱና የአጀባቸውን አስቆሙ፡፡ ሆኖም ይህን ሁሉ ጥሶ መንግሥቱ ወንድሜ፣ አትንኩኝ ላግኘው እያለ ዚያድ ባሬ እጁን እያወናጨፈ መጣ፡፡ ፕሮቶኮሎቹ በመከላከል መንግሥቱ እንዳያገኙት ብዙ ጥረው የነበረ ቢሆንም፣ የዚያድ ባሬን አመጣጥ ዓይተው በታላቅ የመሪነት ርህራሄ ተውት ላግኘው ብለው መንግሥቱ ፈቀዱ፡፡ መንግሥቱ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ መሪ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ትልቅ ጦር ስለነበራቸው በአፍሪካ ይከበሩ ነበር፡፡ ፕሮቶኮል የዲፕሎማሲ አንዱ ክፍል ነው፡፡ አጨባበጥህ፣ አበላልህ፣ አጠጣጥህ፣ ሁለመናህና የእንቅስቃሴ ሁኔታህ ለዲፕሎማሲህ እጅግ ወሳኝነት አለው፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...