Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሕግ ማስከበር እክል ሲያጋጥም ዝምታ መፍትሔ አይደለም

የሕግ ማስከበር እክል ሲያጋጥም ዝምታ መፍትሔ አይደለም

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ በተለመደና በተቋቋመ አሠራር ዲፕሎማቲክ ሊስት የሚባል በየጊዜው ወቅታዊ እየተደረገ የሚዘጋጅና ለሕዝብ ይፋ የሚሆን የመረጃ መጽሐፍ አለ፡፡ የእያንዳንዱ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመለከተው አካል (ለምሳሌ የፕሮቶኮል መምርያ/ዳይሬክቶሬት) ሥራዬ ብሎ፣ ሥራውም አድርጎ የሚያዘጋጀው የመረጃ ሰነድ ነው፡፡ የቆየ ቢሆንም የኢትዮጵያን ዲፕሎማቲክ ሊስት አይቻለሁ፡፡ የየአገሮቻቸው መልዕክተኛ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከእነ ሙሉ ክብራቸው እንኳን ደህና መጣችሁ ተብለው፣ ተቀባይነት አግኝተው ሹመታቸው የታወቀላቸው አምባሳደሮች በክብር ቅደም ተከተላቸው ተዘርዝረው፣ እንዲሁም ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ ሚሲዮኖች ከእነ አድራሻቸውና ከእነ ዋና ዋና ኃላፊዎቻቸው ጋር ተመዝግበው ይፋ የተደረጉበት ከ500 በላይ ገጽ ያለው ጥራዝ ነው፡፡ ሚሲዮን ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የሌላ አገር የዲፕሎማቲክ ሚሲዮን (ኤምባሲ)፣ እንዲሁም የቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት (የበይነ መንግሥታዊ ድርጅት) ወኪል ነውና በዚህ ዲፕሎማቲክ ሊስት ውስጥ በመንግሥታት አባልነት የተመሠረቱ ክልላዊ ወይም አኅጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የበይነ መንግሥታዊ ድርጅቶች ሰፊ ዝርዝርንም እናያለን፡፡  በዚህ በመጨረሻው ሰፊ ዝርዝር ውስጥ ነው የአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ባንክ ግሩፕን (በመጠሪያው የፊደል ተራ ቅደም ተከተል መሠረት) አስቀድሞ ሌሎችንም ዘርዝሮ እነ ወርልድ ባንክ፣ ‹‹WFP፣ WHO›› እያለ እውነትም ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ መቀመጫ መሆኗን ያሳያል፡፡

እውነትም በተለምዶ፣ በተለይም በእኛ በራሳችን ውስጥ በተለምዶ እንደሚባለው፣ አዲስ አበባ በዓለም ሦስተኛዋ ትልቋ የዲፕሎማቲክ ሀብ (እምብርት/ማዕከል) ሆነችም አልሆነችም፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚያወጣው በየጊዜውም ወቅታዊ የሚያደርገው (ማድረግ ያለበት) የዲፕሎማቲክ ሊስት መዝግቦና ዝርዝር የሚያስታውቀው አገር ውስጥ የተሰማራውን የውጭ አገር መንግሥትና በይነ መንግሥታዊ ድርጅት መልዕክተኛ ልክና ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ የ1961 የቪየና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ‹‹ኮንቬንሽን›› የሚያጎናፅፈው/የሚያረጋግጠው ልዩና የማይደፈር መብት (ስፔሺያል ፕሪቪሌጅ ኤንድ ኢሚውኒቲስ) ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋማት፣ እንዲሁም አጥር ግቢያቸውን ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ  በተቀበለችውና የአገሪቱ ሕግ አካል ባደረገችው በዚህ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት መሠረት ልዩ መብት፣ ያለ መከሰስ መብትና የማይደፈር መብት ማለት ለታወቀው ዋና ዓላማ ሊባል (በዚህ ጉዳይ ለውጭ ግንኙነት ሲባል)፣ የመብቱ ባለቤት የሆኑት ሰዎች ለአገር ውስጥ የሕግ ማስከበርና ወይም የዳኝነት ሥልጣን አይገዙም ማለት ነው፡፡ ራሳቸው ሰዎቹ ይህንን መብት አንፈልገውም ቢሉ እንኳን ዋናው የላካቸው፣ የወከላቸው አገር ካልፈቀደ በስተቀር ወንጀል በፈጸሙበት ወይም ፈጸሙ በተባለበት አገር ሕግ አይዳኙም እንጂ ከሕግ በላይ ናቸው ማለት አይደለም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ  የኢሚግሬሽን ሕግ እንደሚደነግገው ለምሳሌ ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የምትሰጠው፣ ከሌሎች መካከል በ‹‹ውጭ አገር በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቋሚ መልዕክተኛ ወይም ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለሚመደቡ አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ወኪሎች፣ አታሼዎች፣ የቆንስላ ወኪሎችና ለእነዚህ የትዳር ጓደኞች›› የቤተሰብ አባል ጭምር በመሆኑ ‹‹ዲፕሎማቲክ ሊስት›› ብዬ ስጀምር ያነሳሁት ሰነድ፣ መረጃ፣ የይፋ መግለጫ ይህንን ሁሉ የሚናገር፣ ድሮ ሳውቀው አንዳንድ ኤምባሲዎች አጥርና ቅጥር ላይ/አካባቢ ተለጥፎ ከምናነበው ‹‹የማይደፈር መብት ያለው›› ከሚለው ማስታወቂያ/ማስጠንቀቂያ በላይ ‹‹ነጋሪ›› ነው፡፡ ቅድም ነገሬን ስጀምር የእያንዳንዱ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚያዘጋጀው ‹‹የዲፕሎማቲክ ሊስት›› መነሻ ምክንያት የተለመደና የተቋቋመ አሠራር መሆኑን ገልጫለሁ፡፡ አገላብጬ ያየኋቸው የሌሎች አገሮች የ‹‹ዲፕሎማቲክ ሊስት›› (በአብዛኛው ኦንላይን) ኅትመቶች ደግሞ የዚህን ግዴታ ምንጭ ራሱን የቪየና የዲፕሎማቲክና የቆንስላ ኮንቬንሽኖችን፣ ከእነዚህም የፈለቁ፣ የተቀዱ የየአገራቸውን ሕጎች እንደሆኑ ይነግሩናል፡፡ ለምሳሌ ያህልና የዚህን መዝገብ አጠቃላይ ይዘት ከሩቁ መረዳት ይቻል ዘንድ የአሜሪካ መንግሥት የስቴት ዲፓርትመንት ያወጣውን የአንድ ወቅት ‹‹ዲፕሎማቲክ ሊስት›› መግቢያ በአጭሩ ላስተዋውቅ፡፡ ይህ ኅትመት የሁሉንም ሚሲዮኖች ዲፕሎማቲክ ስታፍ/ሠራተኞች አባላትና ባለቤቶቻቸውን ስም ይዟል፡፡ የዲፕሎማቲክ ስታፍ አባላት ማለት የዲፕሎማቲክ ማዕረግ ያላቸው የሚሲዮኑ አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የኮከብ ምልክት ከተደረገባቸው በስተቀር በቪየና የዲፕሎማቲክ ኮንቬንሽን መሠረት ሙሉ የዲፕሎማቲክ ኢሚዩኒቲ ያላቸው ናቸው፡፡›› ይልና የኮንቬንሽኑ አግባብ ያላቸው ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው በማለት የአንቀጽ 29 እና 31 እንዳለ ይጠቅሳል፡፡ 

Article 29

The person of a diplomatic agent shall be inviolable. He shall not be liable to any form of arrest or detention. The receiving State shall treat him with due respect and shall take all appropriate steps to prevent any attack on his person, freedom, or dignity.

Article 31

A diplomatic agent shall enjoy immunity from the criminal jurisdiction of the receiving state. He shall also enjoy immunity from its civil and administrative jurisdiction, except in the case of:

  1. A real action relating to private immovable property situated in the territory of the receiving State, unless he holds it on behalf of the sending State for the purposes of the mission:
  2. An action relating to succession in whih the diplomatic agent is involved as an executor, administrator, heir or legatee as aprivate person and not on behalf of the sending State:
  3. An action relating to any professional or commercial activity exercised by the diplomatic agent in the receiving State outside of his official functions.

የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ሊስት የሚዘረዝራቸው ኢትዮጵያ  ውስጥ የሚገኙ ሚሲዮኖች (ኤምባሲ፣ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት፣ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ንግድ ጽሕፈት ቤቶች) የገለጽነውን ዓይነት ልዩ መብት/የማይደፈር መብት (ኢሚዩኒቲና ፕሪቪሌጅ) የሚያገኙበት የሕግ ማዕቀፍ በተጠቀሰው የዲፕሎማቶችና ቆንስላዎች የቪየና ኮንቬንሽን ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ አስተናጋጅ ወይም መቀመጫ አገር/ከተማ ዝም ብሎ የዲፕሎማቲክ መካና መዲና ነኝ ብሎ ‹‹ጉራ ብቻ›› አይሆንም፡፡ ይህንን የሚሸከም/የሚመጥን ‹‹ሆስት ካንትሪ አግሪመንት›› የሚባል ስምምነትና ግዴታ ውስጥ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ብራስልስ ቤልጂየም የሌሎች አገሮች አምባሳደሮች ብቻ ሳይሆኑ ኔቶና አውሮፓ ኅብረትም ዋና መምርያቸው እዚያው ስለሆነ፣ በዓለም ከኒውዮርክ ቀጥሎ ሁለተኛው የዲፕሎማቲክ ማዕከል ትባለች፡፡ ከእያንዳንዱ ዋና መምርያ (ሄድ ኳርተር) ጋር የሆስት/የአስተናጋጅ አገር ስምምነት ትፈራርማለች፡፡ የአስተናጋጅ አገር ፖሊሲ የሚባልም አላት፡፡

ኢትዮጵያም የተጠቀሰውን የቪየና ኮንቬንሽንን ያፀደቀች በመሆኑ፣ ይህ ስምምነት የአገራችን ሕግ አካል ነው፡፡ ይህ ስምምነት የተለያዩ የሕይወት ዘርፎችን በሚገዙ ጉዳዮች ውስጥ (ለምሳሌ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል፣ በጉምሩክ ሕግ፣ ወዘተ) የተካተቱት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ መሆኑ እውነት ቢሆንም፣ ምሉዕ የሆነ ራሱን የቻለ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማቲክ ኢሚዩኒቲስ ኤንድ ፕሪቪሌጅስ አዋጅ የሚባል አለመኖሩ፣ ይህ ከሚታወቀው የተቋማዊ ብቃት ችግራችን ጋር፣ ወዘተ ተረባርቦ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ አልቀረም ሳይሆን በተለይ ከምንነጋገርበትና ዋና ጉዳያችን ከሆነው ሕግ አክብሮ ከማስከበር አኳያ ባለሁለት ስለት ጉዳቱን ስንሰቃየው ኖረናል፡፡ ልዩ መብትና ‹‹ፕሪቪሌጅ›› ብለውትና አደናግረውት ቀርቶ ‹‹ተራ›› እና መደበኛ የመብቶቻችንን ጩኸት መስማት የተሳነው፣ ‹‹እሪ በከንቱ!›› ተብሎ ስም የወጣለትና ‹‹ሐውልት›› የቆመለት፣ አሁን አሁን ዲጂታል ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ‹‹…ጥሪ አይቀበልም›› የሚባለው የሕግ አክባሪነት/አስከባሪነት ህዋሳችን የዲፕሎማቲክ ልዩ መብትን ማስከበርም፣ ወዲያውም በዚህ ልዩ መብት መነገድንና መማገጥን የሚገራበትና የሚቆጣጠርበት ዕውቀትም ፍጥርጥርም ገና አልተጎናፀፈም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተጀመረው ለውጥ ዋና መሠረታዊ ጉዳይ በሆነው ገለልተኛ ተቋማት በመፍጠር ሒደት/ጉዞ ውስጥ፣ በተለይም መንግሥታዊ የሕግ አስከባሪ/የፀጥታ ኃይሉን የሙያ ስላትን የሚፈታተኑ ብልሽቶች ሊረግፉ ቀርቶ ገና መኖራቸው ‹‹አልተደረሰበትም››፡፡

በምሳሌነት ያነሳነው የዲፕሎማቲክ ልዩ መብት የሕግ ማዕቀፍ የቪየና ኮንቬንሽንን መፈረማችን፣ መቀበላችን የኢትዮጵያም ሕግ አካል ማድረጋችን ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዋነኛነት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት/አሁን አፍሪካ ኅብረት ጋር (መሬትን በነፃ መስጠትን የጨመረ) የተፈራረመችው የአስተናጋጅ አገር/ሆስት ካንትሪ ስምምነት አለ (በነገራችን ላይ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ንብረት ያደረገው፣ መሬትን በመላ፣ ቤትን ትርፍ ቤት፣ ያለውን የወረሰው የ1967 ዓ.ም. የሐምሌ 19 አዋጅ በአንቀጽ 43 የዲፕሎማቲክ ይዞታዎች ድንጋጌው ይዞታው የዲፕሎማቲክ፣ የቆንስላ ወይም የኢንተርናሽናል ድርጅቶች የሆነ የከተማ ቦታ ወይም ንብረትነቱ የእነዚህ የሆነ የቤት ሁኔታ ወደፊት ይወስናል ብሎ በቀጠሮ ያሳደረው ጉዳይ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል)፡፡ ከእነዚህ ታላላቅና ወሳኝ ተቋማት በተጨማሪም ኢትዮጵያ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ከተለያዩ በይነ መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር የተፈራረመችው የአስተናጋጅ አገር ስምምነት በጣም ብዙ፣ ምናልባትም ሊከታተሉ ከሚችሉበት በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ግሎባል ፈንድ›› ከሚባለው፣ በሙሉ ስሙ ‹‹ኤድስን፣ ሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመዋጋት [የተቋቋመ] ግሎባል ፈንድ ተብሎ ከሚጠራው ኢንተርናሽናል ፋይናንሲንግ ኤንድ ፓርትነርሽፕ ኦርጋናይዜሽን የሚባለው ድርጅት መቀመጫው ኢትዮጵያ አይደለም፣ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሥራው ግን ከኢትዮጵያ  መንግሥት ጋር ከእነ ‹‹ሪዘርቬሽኑ›› (ከተዓቅቦ ጋር) የልዩ መብቶችና ከለላዎች ስምምነት አድርጓል፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት አግባብ ያለው (የጤና) አስፈጻሚ አካል ያደረገውን ስምምነትም አስፈጻሚ ስምምነቱን የፈረመው ሐምሌ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በአዋጅ ቁጥር 2005/2009 አፅድቋል፡፡ እንዲህ ያለ የልዩ መብቶችና ከለላዎች  ‹‹Privilages and Immunities›› ስምምነት የሚከተለውን የጉዞ መንገድ፣ የሚያልፍበትን መንገድና ፌርማታ ብቻ ሳይሆን፣ በሕግ የሚያጋጥመውን ቁጥጥርና ፍተሻ ማመልከት ስለሚችል ይህ ስምምነት በአስፈጻሚ የመንግሥት የሥልጣን አካል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሕግ አውጪው አካል ደረጃም የሪዘርቬሽን ጥያቄና አቋም የተወሰደበት መሆኑንም መመልከት ያስፈልጋል፡፡፡ ‹‹ሪዘርቬሽን›› ማለት አንድ አገር/መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ስምምነት ሲፈርም፣ ሲያፀድቅ ወይም ሲቀበል ለይቶ በጠቀሳቸው/በዘረዘራቸው የስምምነቱ ድጋጌዎች ላይ ያለውን ቅሬታ ወይም ተቃውሞ የሚያስመዘግብበትና እነዚህ እኔን አይመለከቱኝም ወይም አይገዙኝም ብሎ ያስታወቀበት መግለጫ ነው፡፡

የምንነጋገርበትና ምሳሌ አድርገን ያነሳነው የዚህ የልዩ መብት ከለላ ሕግ የሚገኝበትን ሰፊ ማዕቀፍ ምን ዓይነት ውጣ ውረድ እንዳለበት ተጨማሪ ‹‹ጉብኝት›› ማድረግ የሚፈልግ ካለ የዚህን የግሎባል ፈንድ የልዩ መብቶችና ከለላዎች ስምምነት ማፅደቂያ አዋጅ ቁጥር 1005/2009ን የስምምነቱን መፀደቅ የሚመለከተውን የአንቀጽ 2፣ ሁለት ንዑስ ድንጋጌዎችን እዚሁ አካትቼ አቅርቤያለሁ፡፡   

በስምምነቱ መፅደቅ

  1. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ሐምሌ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. የተፈረመው የግሎባል ፈንድ ኤድስን፣ ሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመዋጋት የልዩ መብቶችና ከለላዎች ስምምነት በአንቀጽ 2 (4) እና (8)፣ አንቀጽ 3 (1) (ረ)፣ በአንቀጽ 3 (3)፣ አንቀጽ 4 (2) (ለ)፣ (መ) እና (ረ)፣ በአንቀጽ 4 (4) እና በአንቀጽ 7 (2) እስከ (6) ላይ ተዓቅቦ በማድረግ ፀድቋል፡፡
  2. የተሰጠው መብትና ከለላ ከምን አኳያ መተርጎም እንዳለበት መግለጫ የቀረበበት ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በስምምነቱ በግሎባል ፈንድ ለመንግሥት ተወካዮች፣ ለኃላፊዎችና ሌሎች ግለሰቦች የተሰጡ ልዩ መብቶችና ከለላዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን ሥራ ለማከናወን በሚያደርጓቸው ተግባራት ላይ ብቻ የሚል መግለጫ እንዲቀርብ ሆኖ ፀድቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ስምምነቶች መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚመለከቱ ከሆነ የሕገ መንግሥቱ የምዕራፍ ሦስት ድንጋጌዎች (የእኛ ቪል ኦፍ ራይትስ) አተረጓጉም ከእነዚህ ከፈረምናቸው ስምምነቶች ጋር ተጣጥሞ መተርጎም እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 13/2 ደንግጓል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ባይሆንም በአጠቃላይ አንድ የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱ ወይም አሠራሩ አካል የሆነ ችግር/እንከን ለማመላከት ‹‹ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው›› ማለት የሕገ መንግሥቱ ለዚያውም የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች፣ በዚያም ውስጥ የሕገ መንግሥቱ የበላይነት ድንጋጌ ቃል ቢሆንም ኢትዮጵያ የምታፀድቃቸው ስምምነቶች የሕጉ አካል ሆነው አይታተሙም፡፡ አይታተሙም ማለት ኅትመት አያውቃቸውም ማለት ሳይሆን የአገር ኦፊሺያል ሕግ መንገሪያ ነጋሪት ጋዜጣ አያውቃቸውም፡፡ በዚህ የአገራችን የሕግ ማውጣት ረዥም ታሪክ ውስጥ ዛሬም ድረስ በነጋሪት ጋዜጣ የታተመው ብቸኛው ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ስምምነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ነው፡፡ ይህንን ጀብድና ሪከርድ የአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሕግ ስላልደገመው ቻርተሩ ይዞት የኖረው ስምና ዝናም ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ይህንን ያነሳሁት፣ ሌላው ቢቀር ከዚህ ጉዳይ አንፃር የግሎባል ፈንድ ድርጅትን የልዩ መብቶችና ከለላዎች ስምምነት በፀደቀበት ሰነድ መጀመሪያ አስፈጻሚው የመንግሥት የሥልጣን አካል ስምምነቱን ሲደራደርና ሲፈራረም፣ በኋላም ሕግ አውጪው አካል ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሕግ አካል አድርጎ ሲያፀድቅ የሪዘርቬሽን ማስወቂያ ያደጉባቸውን ድንጋጌዎች የማናውቀው፣ ስምምነቱን ጭምር ስለማይታተም ነው፡፡

የአፍሪካ የልማት ባንክ ኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሊስት ውስጥ የተመዘገበ፣ እዚያ ውስጥ መመዝገብና መግባት የሚያስገኘው ‹‹መብት›› እና ጥቅም ጭምር ያለው ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ኢትዮጵያም አባል የሆነችበት ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ  የውጭ ግንኙነት ሕግ (አዋጅ) እንደሚለው በመንግሥታት አባልነት የተመሠረተ አኅጉራዊ ድርጅት ነው፡፡ የእኛ አገር ሕግ አውጪዎች ከሁሉም በላይ የእኛ አገር ሕግ አስፈጻሚዎች እንዴት አድርገው ይህንን ተቋም እንደሚያውቁት ትንሽ ለመጠቆም ያህል ዝም ብዬ በምርጫ ሳይሆን የዘፈቀደና በአቦ ሰጠኝ እጄ የገቡትን ሁለት አዋጆች ላሳይ፡፡ አንደኛው አዋጅ ቁጥር 340/1995 ለሐረር ከተማ የንፁህ ውኃ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከአፍሪካ ልማት ፈንድ ብድር ለማግኘት (19, 890,000 ዩኒትስ ኦፍ አካውንት) ሌላው ለመቀሌ – ዳሎልና ሰመራ – አፍዴራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማተላለፊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚል ብድር ለማግኘት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የተደረገ ስምምነት (104,610 ሺሕ ዶላር) ማፅደቂያ (አዋጅ 998/2009) ናቸው፡፡ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ይህንን ያህል እንተዋወቃለን፡፡ ደንበኛ ነን፣ አበዳሪዎቻችን ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በቅርቡ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. (ጃንዋሪ 19 ቀን 2024) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በትዊተር/ኤክስ ገጻቸው እንዳሉት፣ ከአፍሪካ የልማት ፈንድ ጋር ያለን ሽርክና ለኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት ወሳኝ ነው፣ ከወንድሜ (የባንኩን ፕሬዚዳንት ስም ጠቅሰው) ከእሱ ድጋፍ ጋር ከባንኩ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኖች ነን ያሉትን ልብ ይሏል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም በዚያው የቲዊተር (ኤክስ) መድረክ የኢትዮጵያ መንግሥት የተፈጠረውን ‹‹ዲፕሎማቲክ ኢንሲደንት›› ለመፍታት በሁለቱም በኩል የተደረገውን ጥረትና ትጋት ተከትሎ ባንኩ ግንኙታችንን ወደ ነበረበት ጤነኛ/ደኅነኛ ሁኔታ ለመመለስ የወሰደውን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበለው ይገልጻል፡፡ ይህ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ወደ ተፈጠረው አጋጣሚ/ድንገት ይወስደናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ጉዳይ እስካሁን በሰማነውና በምናውቀው ምላሹ/አስተያየቱ ዲፕሎማቲክ ኢንሲደንት ነው ያለው፡፡ ምንድነው? ምን ማለት ነው? ዝም ብሎ በቁሙ እክል ይባል ይሆናል፡፡ የአገራችን የአቪየሽን ሕግ ለዚያው ለራሱ ዘርፍ ‹‹አክሲደንት››ንና ‹‹ኢንሲደንት››ን ይለያል፡፡ የመጀመሪያውን አደጋ፣ ኢንሲደንትን ደግሞ ‹‹አጋጣሚ›› ይለዋል፡፡ ደግነቱ አጋጣሚ ማለትን ያፍታታዋል፡፡ ‹‹አክሲደንት›› አደጋ ነውና፣ ‹‹ኢንሲደንት›› ማለት ከአውሮፕላን አደጋ ሌላ የአውሮፕላን እንቅስቃሴን ደኅንነት የሚያቃውስ፣ ሊያቀውስ የሚችል ክስተት ነው ይለዋል፡፡ ይህ ትርጉም ዲፕሎማሲውም ውስጥ ይሠራል ተብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል የሰጠበት ማስረጃ ነው ብዬ እየተሟገትኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን በአንድ ዲፕሎማቲክ መብት በተሰጠው ዓለም አቀፋዊ ተቋምና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የግንኙነታቸው ደኅንነት የሚያቀውስ/ሊያቀውስ የሚችል እክል ተፈጥሮ እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ እክሉ የፈጠረው/ያስከተለው አንቅጥቅጥ ግን እዚያ ውስጥና እዚያ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ የአገራችንን የሕግ ማስከበር የውኃ ልክ ኧረ ምን ይሻለናል ያሰኘ ነው፡፡

የተባለው አጋጣሚ መነሻ የአፍሪካ ልማት ባንክ አዲስ አበባ ተመድበው የሚሠሩ ሁለት ሠራተኞች ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በባንኩ በራሱ መግለጫ መሠረት በመንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች ያለ ሕግ መያዛቸው፣ የአካል ላይ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑ፣ ለብዙ ሰዓታትም ታስረው መቆየታቸው፣ ይህም ያለ ምንም ይፋዊ መግለጫ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ባንኩ መደበኛ/ደንበኛ (ፎርማል) አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ድርጊቱንም ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ‹‹ኢንሲደንት›› ነው ብሎታል፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፋዊ ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ  እንደሚያነሳም ገልጿል፡፡ ይህንን ሁሉ ምን አመጣው? እዚህ ያደረሰው መነሻ/ምክንያት ምንድነው? ብዙ ግልጽነት የለም፡፡ አቤቱታ የደረሰበትና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያደረሰውን አካላዊ ጉዳት ልክና መልክ በፎቶግራፍ የታየበት ጉዳይ የተፈጸመው፣ ከባንኩ ጋር በቅርብ የሚሠራ እዚያው ገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ/አካባቢ እንደሆነ ከዚህ ጉዳይ ጀርባ ደግሞ የአምስት ሚሊዮን ዶላር ‹‹መሰወር››/ተሰወረ መባል ችግር እንዳለ የሚወሩ ስሞታዎች አሉ፡፡ ደግነቱ ዕድሜ ለባንኩ ሕጋዊ አቤቱታና ተቃውሞ ውስጥ የመፅናቱ ብርታት ከማለት ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ወዲያው ይሰማሉ፣ የታሰሩም ሰዎች ወዲያው እንዲፈቱ ያዝዛሉ፣ ጉዳዩም ወይም ‹‹ድንገቱ››ም ላይ አስቸኳይ ምርመራ እንዲደርግ እንደሚያዙ ቃል ይገባሉ፡፡ የባንኩ መግለጫ እንዳስታወቀው ደግሞ የቀረበውን አቤቱታ መንግሥት በይፋ መቀበሉ፣ እንዲሁም የድንገቱን/የአጋጣሚው ከባድነት መረዳቱ፣ ሕግ መጣስ ውስጥ የገቡት ሁሉ እንዲመረመሩ፣ እንደሚጠየቁ ለሕግና ለፍትሕ እንደሚቀርቡ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ ሁሉ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ እንደሚሆን የተረጋገጠላቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ መግለጫ ሳይጠቅሰው የማያልፈው ትልቁና እስካሁን የተነጋገርንበት/ወይም ዳራውን በሰፊ ያነሳነው የልዩና የማይደፈር መብት ጉዳይ ነው፡፡ በባንኩ መግለጫ መሠረት መንግሥት ባንኩና ሠራተኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመደቡትም ሆነ ለሥራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ሠራተኞች፣ በ‹‹ቪየና ኮንቬንሽን›› እና ባንኩ ራሱ ከአስተናጋጁ አገር ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ልዩ መብታቸው፣ ‹‹ፕሪቪሌጃቸው››፣ የማይደፈር መብታቸው ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ ሆኖ እንደሚቀጥል መተማመኛ እንደተሰጣቸው ገልጿል፡፡

እንዲህ ያለ ዲፕሎማቲክ ‹‹ኢንሲደንት›› የሚባል ቀውስ ውስጥ ለምን ገባን? ችግራችን የሕግ ክፍተት/ሕግ የለም ነው? ወይስ ሕጉ ዝም ብሎ የስም ጌጥ ሆኖ? እንኳንስ ዲፕሎማሲያዊ ጥላ/ከለላ የተሰጠው የተመደበበት የውጭ አገር/የሰው፣ አገር መንግሥት የፀጥታና የደኅንነት አካላት የሕግ ማስፈጸም እጅ አይነካውም ተብሎ ሕግ የወጣለት ዲፕሎማት ቀርቶ፣ ተራ ሰው ላይ ኃይል መጠቀም/ኃይል እጠቀማለሁ ብሎ ማስፈራራት/መዛት ራሱ ሕግ አለው አይደለም ወይ? እስካሁን የሄድንበትን ከአምስት ዓመት በላይ የወሰደ የለውጥ ጉዞ እንዲህ ያለ ዘፈቀዳዊ እልፊትንና እንዳሻ መሆንን የሚመክት፣ አንቅሮ የሚተፋና የሚያጋልጥ፣ ሳይጠየቁ መቅረትን የሚቃወም ዴሞክራሲና ግልጽነት አልቋጠረም ማለት ነው፡፡

አገር በሙሉ በግራም በቀኝም፣ በየጎራው ያለው ሁሉ ስለዴሞክራሲ ይናገራል፡፡ ዛሬ በምንገኝበት ሁኔታ ለዴሞክራሲ የመቆም፣ ስለዴሞክራሲ የመታገል ጉዳይ ባለው ሕግ ውስጥ ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶችና ነፃነቶች ሕይወት እንዲያገኙ፣ መኗኗሪያ እንዲሆኑ መታገል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የገለልተኛ ተቋም ግንባታን ይጠይቃል፡፡ ለዴሞክራሲ እዋደቃለሁ ማለት ትግል ውስጥ የተቋም ግንባታ የዴሞክራሲን መሠረት የመጣል ዝቅተኛው/መንዕሱ ነገር ነው፡፡ ይህ እንዲሆን፣ በተቋማቱ አማካይነትና በእነሱም ውስጥ ሰዎች መብት መተንፈስ እንዲችሉና ይህም እንዲሳካ አስፈላጊ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል በተቋማቱም ውስጥ ከእነሱም ውጪ ያለው የሰው ኃይል አቅምና ባህርይ ማደግና መንቃት ወሳኝ ነው፡፡ ሰውን ለመያዝ፣ ለማሰር፣ ዝም ብሎ ‹‹አሰኘኝ›› ማለት እብሪት እንደመራው መሆን ሕግ ያጠፋል እንጂ ሕግ አያስከብርም፡፡ ሕግ የማስከበር ሥራ ሕግ ማክበርን መነሻውና ተገኑ ካደረገ የሕዝብን አመኔታና ተስፋን የማሸነፍ ከባድና ረዥሙ መንገድ ውስጥ ያስገባል፡፡ ልዩ መብትና ‹‹የማይደፈር ፀጋ›› ሕግ የሰጣቸው ሰዎችም ሆኑ ዜጎች ከግለሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከራሱ ከመንግሥትና ከመንግሥት የሥልጣን አካላት አድራጊ ፈጣሪነት የሚጠብቁት የመንግሥት ሕግ አስከባሪነት፣ የመንግሥት ከሳሽነት፣ የዓቃቤ ሕግ የራሱ ለሕግ ተከራካሪነት ወደ ዜጎች/ሰዎች መብት ድፍጠጣ እንዳይንሸራተት የመንግሥታዊ የፀጥታ ኃይሉን የሙያ ብቃቱን የሚፈታተኑ፣ የአመለካከትና የአደረጃጀት ብልሽቶችን ማራገፍ አለበት፡፡ እንኳንስ ስንትና ስንት ዓይን የሚጠብቃቸው ዲፕሎማቶች ቀርቶ የትኛውም ሰው በበደልና በሌብነት ቢታማ ያለ ሕግና ያለ በቂ ማስረጃ ጫፉ የማይነካበት፣ ዝም ብሎ፣ መሰለኝ ብሎ ወይም ሲብስና ሲከፋ ደግሞ የእኔን ፖለቲካ አላጫፈርክም ወይም የእኔን ተቃዋሚ ደግፈሃል፣ ወዘተ ተብሎ ለጥቃት የማይጋለጥበት፣ እንዲያም ሆኖ ድንገት ቢጠቃ ጥቃቱን የሚፋረድበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ነው ሥራችን መሆን ያለበት፡፡

በተለይ እንዲህ ያለ ጉዳይ ዝምታ ጉድጓድ ውስጥ ስለተቀበረ፣ የዝምታ ሴራ ስለተመታበት አይወገድም፡፡ መግለጫ፣ የተጠያቂነት መልስ ይፈልጋል፣ አጥፊውን ማጋለጥ ይሻል፡፡ ምክንያቱንና መነሻውን ማሳወቅ አጥፊውን ማጋለጥና ተጠያቂ ማድረግ ማለት ‹‹የፍየል ወጠጤ›› ዝፈኑ፣ አስዘፍኑ ማለት አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ወጥተው ድርጊቱን በማውገዝ ሕጋችን ይህ አይደለም፣ እኛም ይህ አይደለንም ማለት ማስተማር አለባቸው፡፡       

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...