Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ፋይዳ

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ፋይዳ

ቀን:

በሱፈቃድ ተረፈ

ባለፈው ጽሑፍ ስለካፒታል ገበያ ምንነት፣ ፋይዳና ታሪካዊ ዳራ በመጠኑ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። በማስከተል ስለካፒታል ገበያ ተዋናዮች እንደምጽፍ ጠቁሜ የነበረ ቢሆንም፣ ቅድሚያ ሰጥቼ አንባቢያን ማወቅ አለባቸው ያልኩትን ጉዳይ አብራራለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ የካፒታል ገበያ የቁጥጥር መሣሪያዎች ከሆኑት አንዱና ዋነኛ ስለሆነው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች፣ ማለትም በተለምዶ የአክሲዮንና የቦንድ ሰነዶች የሚባሉትን በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ማስመዝገብ ስለሚኖረው ፋይዳ፣ አውጪዎች (Issuers) እነዚህን ሰነዶች በባለሥልጣኑ የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸው ስለመሆኑ፣ እንዲሁም በገበያ ላይ ስላሉ ነባር የአክሲዮን ሰነዶች የምዝገባ ሁኔታ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ ይህም የምዝገባ መሥፈርቶችን ሳያሟሉና የደንበኛ ሳቢ መግለጫቸውን (Prospectus) በባለሥልጣኑ ሳያስፀድቁ ለሕዝብ አክሲዮን በሚሸጡ ድርጅቶች ገዥው ላይ ሊደረስበት የሚችለውን ኪሳራ፣ ብሎም የቁጥጥር መሣሪያዎቹ ገዥውን እንዴት ከኪሳራ ሊታደጉት እንደሚችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡

የካፒታል ገበያ ተቆጣጣሪ ተቋም

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የካፒታል ገበያ እንደየአገሩ ግብይቱንና ገበያውን ለመቆጣጠርና ለመደገፍ በመንግሥት በተቋቋመ አካል ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን፣ አሠራሩን በተመለከተ ዓለም አቀፍ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ተቆጣጣሪዎች ድርጅት (International Organization of Securities Commissions-IOSCO) የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የቁጥጥር ዓላማዎች መሠረት በማድረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን አውጥቷል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ለሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ቁጥጥር ያወጣቸው ሦስቱ ዓላማዎች ለሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስተሮች ከለላ መስጠት፣ የግብይት ሥራው ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽነት የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግና መዋቅራዊ የአደጋ ሥጋቶችን መቀነስ ናቸው፡፡ እነዚህን የቁጥጥር ዓላማዎችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ለማሳካት በአገር ደረጃ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፣ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን (ከዚህ በኋላ «ባለሥልጣን» ተብሎ የሚጠረው) በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን የተጠቀሱት የቁጥጥር ዓላማዎች በአዋጁ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

የባለሥልጣኑ ሥልጣንና ተግባር በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 በግልጽ ተመልክቷል፡፡ በአዋጁ ከተዘረዘሩት መካከል ባለሥልጣኑ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት ለሚከናወንበት ገበያና ለገበያው ተዋናዮች ፈቃድ መስጠት፣ ፈቃድ መሰረዝና ማገድ፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይን የመመዝገብ (Securities Registration)፣ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የሚከናወነውን የምዝገባና ከምዝገባ የመሰረዝ ሥራ መቆጣጠር (Supervise Listing & Delisting)፣ የገበያ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ በገበያው ተሳታፊዎች በሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ትስስር እንዲፈጠር የሚያደርግ የመረጃ ቴክኖሎጂ አውታሮችን በማበልፀግ የገበያ መረጃ ለተጠቃሚዎች አንዲተላለፍና እንዲሠራጭ ማድረግ፣ ለሽያጭ የሚቀርቡ አክሲዮኖችንና ቦንዶችን ለግብይት ምቹ እንዲሆኑ በኤሌክትሮኒክ ዓይነት የሚያዙበትንና የሚተላለፉበትን መንገድ ማመቻቸት፣ የካፒታል ገበያ ተሳታፊዎችን ሒሳብ የሚሠሩ ኦዲተሮችን መሥፈርት በማውጣትና በመለየት መመዝገብ፣ የኢንቨስተሮችን ንቃት የማሳደግ፣ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰድ እንዲሁም እነዚህንና ሌሎች ሥራዎችን ጨምሮ አዋጁን ለማስፈጸም የሚጠቅሙ ማናቸውንም መመርያ የማውጣት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

አዋጁን መነሻ በማድረግ በአገሪቱ የአክሲዮን፣ የቦንድና የሌሎች ገንዘባዊ ሰነዶች ግብይት የሚመራበት «የሕዝብ ሽያጭ አቅርቦትና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት ረቂቅ መመርያ» በባለሥልጣኑ ተዘጋጅቶ ከሕዝብ ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በአዋጁና በዚህ ረቂቅ መመርያ ከተደነገጉ የካፒታል ገበያ የቁጥጥር መሣሪያዎች አንዱ ስለሆነው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ማየት ፋይዳውን ከመረዳት አንፃር ጠቃሚ ይሆናል፡፡ 

ለሕዝብ የሚሸጡ አክሲዮኖችን ማስመዝገብ ግዴታ ስለመሆኑ

ባለሥልጣኑ ከተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ አንዱ በገበያው ሊያጋጥሙ የሚችሉ መዋቅራዊ የአደጋ ሥጋቶችን መቀነስ ነው፡፡ ይህን ስንል በአገራችን የተማከለ፣ በሕግና በተቋም የሚመራ የአክሲዮን ገበያ ባለመኖሩ በተለያዩ ጊዜያት ዜጎች፣ አክሲዮን፣ ማኅበር፣ እናቋቁማለን በሚሉ ግለሰቦች ጥረው ግረው ያካበቱት ሀብት ተበልቶ እንደቀረ የምናስታውሰው ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ እንደ ማንኛውም ንግድ በጥንቃቄና በዕውቀት ካልተካሄደ ኪሳራ ሊያመጣ የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ ምሥረታ ላይ ከሚገኝ ወይም ካፒታሉን ለማሳደግ ከወሰነ አንድ የሕዝብ ኩባንያ (Public Company) አክሲዮን ሊገዛ የሚፈልግ ሰው አስቀድሞ ድርሻ ስለሚገዛበት ድርጅት በቂ መረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡ አክሲዮን ገዥው ይህን መረጃ ሊያገኝ የሚችለው በአክሲዮን ማኅበሩ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ላይ ነው፡፡ ይህ መግለጫ በካፒታል ገበያ አዋጅና በረቂቅ መመርያው መሠረት ባለሥልጣኑ ፈቃድ በሰጠው ባለሙያ የተዘጋጀና ስለአውጪው ድርጅቱ አጠቃላይ ቁመና፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ ኦዲት ሪፖርት፣ ትርፍ፣ ዕዳና ሌሎች መሠረታዊ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ ሆኖ ድርጅቱ ይህንኑ ለባለሥልጣኑ አቅርቦ ያስፀደቀና ያስመዘገበ መሆን አለበት፡፡ መግለጫው በባለሥልጣኑ ፀድቆ ሲመዘገብ ለሕዝብ ይፋ የሚወጣ በመሆኑ አክሲዮን ገዥዎች ግብይት ከመፈጸማቸው በፊት፣ ስለሚገዙት ሰነድ ሙሉ መረጃ ኖሯቸው ግብይት መፈጸም እንዲችሉ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

በሌላ በኩል አክሲዮን ማኅበሩ ከዚህ ቀደም አክሲዮን ለሕዝብ ሽያጭ ያወጣ ከሆነ እንዴት ሊያስመዘግብ ይችላል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት ለሽያጭ የቀረቡና አሁን ገበያ ላይ የሚገኙ ነባር አክሲዮኖች የሚመዘገቡበት ሁኔታ ከላይ በተጠቀሰው ረቂቅ መመርያ በግልጽ ተመልክቶ ይገኛል፡፡ ረቂቅ መመርያው ነባር በገበያው የሚገኙ የሕዝብ ኩባንያ አክሲዮኖች ይህ ረቂቅ መመርያ በፀደቀ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአውጪው ድርጅት በኩል በባለሥልጣኑ መመዝገብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ነባር አክሲዮን ያላቸው የሕዝብ ኩባንያዎች ሰነዶቹን ሲያስመዘግቡ ምሥረታ ላይ እንዳሉ፣ ወይም ካፒታላቸውን ለማሳደግ እንደወሰኑ የሕዝብ ኩባንያዎች የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ማቅረብ አይጠበቅባቸውም፡፡ ይልቁንም የማቋቋሚያ ሰነዶቹን፣ የተቋቋመበትን ዓላማ፣ አጠቃላይ በድርጅቱ የወጡ ሰነዶችንና የተከፈለ ካፒታል፣ የድርጅቱን አመራሮች ቁመና፣ የሰነዶቹን አጭር መግለጫ፣ የአክሲዮን መደቦቹን (Class of Shares) ዓይነት፣ አጠቃላይ ካፒታል፣ ባለአክሲዮኖቹን፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት ኦዲት ሪፖርትና ሌሎች መሠረታዊ መረጃዎችን ያካተተ የነባር አክሲዮን ደንበኛ ሳቢ መግለጫ  (Non-Offering Prospectus) በማዘጋጀት ለባለሥልጣኑ አቅርቦ ማስፀደቅና ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ መግለጫ በዓይነቱ ከደንበኛ ሳቢ መግለጫ የተለየና አነስተኛ ግዴታዎችን የሚጥል ሲሆን፣ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 447 ከተገለጸው ዝቅተኛ መመዘኛዎችን ከሚያስቀምጠው መግለጫ በተጨማሪ ከላይ የተዘረዘሩትን ሌሎች የአውጪው ድርጅት መረጃዎችን የሚያካትት ነው፡፡

የምዝገባ ሥርዓቱ የአውጪው መረጃዎችን ባለማወቅ አክሲዮን በሚገዙ ሰዎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ሊያስቀር ይችላል፡፡ ይህ ሥርዓት ግልጸኝነትን በመፍጠር በአጠቃላይ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያውንና ተዋናዮቹን ከጉዳትና ከውድቀት ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ የምዝገባ ሥርዓቱን በመደንገግ፣ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ ለባለሥልጣኑ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋነኛው የቁጥጥር መሣርያ መሆኑን ከተለያዩ መጻሕፍት ለመረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ የምዝገባ መሥፈርቶችን ሳያሟሉና የደንበኛ ሳቢ መግለጫቸውን በባለሥልጣኑ ሳያስፀደቁ ለሕዝብ አክሲዮን ለመሸጥ ካወጡ ድርጅቶች አክሲዮን በመግዛት ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ «የእኛን አክሲዮን ከገዛችሁ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንሰጣለን» የሚሉና የተጋነኑ ማማለያዎች እንዲሁም እውነተኛ የማይመስሉ ማስታወቂያዎችን መመርመር ይገባል፡፡ በተጨማሪም አክሲዮን ገዥዎች በአውጪው ድርጅት የተዘጋጀውን መግለጫ በመፈተሽ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ 

በመርህ ደረጃ ለሕዝብ የሚሸጥ አክሲዮን ከመሸጡ በፊት በአውጪው ድርጅት በኩል በባለሥልጣኑ የማስመዝገብ ግዴታ መኖሩ ተብራርቷል፡፡ የዚህን መርህ ተጨማሪ መነሻ ምክንያቶች ለመረዳት ከተለያዩ የአዋጁ ድንጋጌዎች መንፈስ አንፃር መመርመር ተገቢ ነው፡፡ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ለገዥውና ለአገር ኢኮኖሚ የሚኖረው ፋይዳ፣ ከተፈቀደለት ገበያ ውጪ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ መገበያየት የተከለከለ ስለመሆኑ፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሳይመዘገብ በማንኛውም መንገድ ማስተላለፍ ሊኖር ስለሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ በአዋጅ ለባለሥልጣኑ ከተሰጠው ሥልጣን አንፃር ለማስረዳት እሞከራለሁ፡፡

የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ለገዥውና ለአገር ኢኮኖሚ የሚኖረው ፋይዳ

ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለሕዝብ ሽያጭ የሚያቀርብ አካል በባለሥልጣኑ በተዘጋጀው ቅጽ መሠረት የምዝገባ መግለጫው እንዲመረመርና እንዲፀድቅ ባለሥልጣኑ የሚጠይቀውን አስፈላጊ መረጃዎችንና ሰነዶችን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የምዝገባ ሰነዶቹ አክሲዮን መግዛት ለሚፈልጉ ሰዎች ስለአክሲዮኖቹ ትክክለኛ ዋጋ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል፡፡ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ግልጸኝነት በመፍጠር ገበያው እምነት እንዲጣልበት የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን መመዝገብ ሌላኛው ፋይዳ የገበያውን መጠን (Market Size) ለማወቅና ለመወሰን፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ማዕቀፍ ለማበጀት፣ እንዲሁም አጠቃላይ ቁጥራቸውን ለማወቅና ጤናማ ግብይት እንዲፈጠር ይረዳል፡፡

በአንፃሩ አክሲዮን የካፒታል ሀብት እንደመሆኑ አውጪ ድርጅቶች ለሽያጭ ያቀረቡትን ሰነድ ሳያስመዘግቡ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ መንግሥት የካፒታል ሀብቶችን በማስተላለፍ በሚገኝ ጥቅም ላይ የሚከፈል ግብርን ያሳጣል፡፡ በተለይ ነባር ሰነዶች የማይመዘገቡና ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ያገኛሉ ተብለው ወደ የሚጠበቁት የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ወይም ወደ ያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ የማይመጡ ከሆነ፣ በሁለቱ መደበኛ ገበያዎች ሰነዶች ዋጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ይኖራቸዋል፡፡ የገበያ ዋጋ የሚወሰነው በአቅርቦትና በፍላጎት ብቻ እንደመሆኑ ነባር የሕዝብ ኩባንያዎች የነባር አክሲዮን ደንበኛ ሳቢ መግለጫ በማዘጋጀት በባለሥልጣኑ የማይመዘገቡ ከሆነ፣ እየተደራጀ በሚገኘው የተማከለ ገበያ አርተፊሻል ዋጋ እንዲፈጠር በማድረግና የጎንዮሽ ሐሰተኛ ገበያ በመፍጠር የገበያውን ተዓማኒነት ሊሸረሽር ይችላል፡፡ ስለዚህ ነባርም ሆነ አዲስ የሚወጡ የድርሻም ሆኑ የዕዳ ሰነዶችን ለሦስተኛ ወገን ከመተላለፋቸው በፊት በተቀመጠላቸው የምዝገባ መሥፈርቶች መሠረት መመዝገባቸው የሰነዶቹን ትክክለኛ ዋጋ በመወሰን ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡

በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 75 (አራት) (ሀ-ሠ) የተዘረዘሩት ልዩ ሁኔታዎች ካላጋጠሙ በስተቀር ነባርም ሆነ አዲስ ለሕዝብ ሽያጭ የሚቀርቡ ሰነዶችን ማስመዝገብ ግዴታ ነው፡፡ በአዋጁ ልዩ ሁኔታዎች ተብለው የተቀመጡት በኢትዮጵያ መንግሥት ለሽያጭ በቀረቡ ሰነዶች፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ በሚሸጡ ሰነዶች፣ መክሰራቸው የታወጀባቸው ኩባንያዎች ሰነዶች፣ በግል ለሽያጭ የሚቀርቡ ሰነዶችና ባለሥልጣኑ በየጊዜው በሚያወጣቸው መመርያዎች መሠረት ከምዝገባ ነፃ የሚደረጉ ሰነዶችን ያጠቃልላል፡፡ 

ከተፈቀደ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ውጭ መገበያየት የተከለከለ ስለመሆኑ 

ከላይ እንደተብራራው ለሕዝብ የሚሸጥ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ መግለጫው በባለሥልጣኑ መመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ በግልጽ ተመልክቷል (የአዋጁ አንቀጽ 75)፡፡ ለሕዝብ የሚሸጥ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ማለት በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ወይም ባልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ ላይ የሚሸጥ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ሽያጭ አቅርቦትና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት ረቂቅ መመርያ የሕዝብ ኩባንያ የሚላቸው አክሲዮን ማኅበር ሆነው አክሲዮኖቻቸውን ከሃምሳ (50) ሰው በላይ ሽያጭ ያወጡ ወይም የሸጡትን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች መንፈስ የምረዳው ሰነዶቹን ለሕዝብ ሽያጭ ላወጣ ኩባንያ ከሁለቱ ገበያዎች ውጪ አክሲዮን መገበያየት የተከለከለ እንደሆነ የሚያመላክት ሲሆን፣ በሁለቱ ገበያዎች ሰነዶቹን ለሕዝብ ለመሸጥ በቅድሚያ ከማስመዝገብ ውጪ ምንም ዓይነት አማራጭ እንደሌለው ለመረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚገናኘው የአዋጁ አንቀጽ 106 (ሦስት) ሲሆን ፈቃድ ከተሰጣቸው የግብይት ሥርዓቶች ውጪ ግብይት ማከናወን ክልክል መሆኑንና የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው ፈቃድ በሌለው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ወይም ያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ ፈቃድ የሌለው መሆኑን እያወቀ የተገበያየ እንደሆነ፣ ከብር 100 ሺሕ በማያንስና ከብር 150 ሺሕ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ፣ እና ከ5 ዓመት በማያንስና ከ12 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ የዚህ አንቀጽ መንፈስ ባልተፈቀደ ገበያ መገበያየት የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የሚደነግግ ቢሆንም መገበያየት ማለት ምን ማለት እንደሆነ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት በሰነደ ሙዓለ ንዋይ መገበያየት ማለት ለራስ ወይም ለሌሎች ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን መሸጥ ወይም መግዛት፣ ማውጣት ወይም ለሽያጭ ማቅረብ፣ ማስቀመጥና መጠበቅ፣ ክፍያ ማጣራትና መፈጸም፣ ማበደር ወይም ማስያዝ፣ ወይም ሌላ ማንኛውም ባለሥልጣኑ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ የሚደረግ ግብይት ነው ብሎ የሚወስነውን ሥራ ያካትታል፡፡ በመሆኑም ምዝገባ አያስፈልጋቸውም ተብለው ከተጠቀሱት በስተቀር በአውጪዎች ለገበያ የቀረቡም ሆኑ አዲስ የሚወጡ ሰነዶች ሳይመዘገቡ በማናቸውም ዓይነት ማስተላለፍ መገበያየት ነው ሊባል ስለሚችል፣ መደበኛውን ገበያ በማዛባት ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡

በአጠቃላይ በባለሥልጣኑ የሚደረግ የሕዝብ ኩባንያዎች የአክሲዮንና የቦንድ ሰነዶች ምዝገባ በሰነዶቹ ግብይት ግልጸኝነት ከመፍጠር አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ ኩባንያዎች ስለድርጅታቸው ጠንካራና ደካማ ቁመና ለሕዝብ ይፋ በማውጣት ለሥራቸው የሚፈልጉትን ገንዘብ በካፒታል ገበያ በኩል የሚሰበስቡበት፣ ገዥዎችም የሚፈልጉትን ድርጅት አክሲዮን ሲገዙ ስለሚገዙት ድርጅት ሙሉ መረጃ ኖሯቸው እንዲገዙ፣ ገንዘባቸው ተበልቶ እንዳይቀርና ኪሳራ እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ይረዳል፡፡ በተለይ አውጪዎች ስለድርጅታቸው ዝርዝርና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ይፋ የሚያወጡና በባለሥልጣኑ የሚመዘገቡ መሆኑ ከሕዝቡ ተዓማኒነትና ተመራጭነት እንዲያገኙ በማድረግ ራሳቸውን በየጊዜው እንዲፈትሹ ዕድል በመስጠት እንዲያድጉና ለኪሳራ እንዳይዳረጉ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

ስለዚህ ነባርም ሆኑ አዲስ ሰነዶችን ለሕዝብ ሽያጭ በሚያወጣው ድርጅት በኩል ተገቢው መግለጫ ተዘጋጅቶ ቅድሚያ በባለሥልጣኑ ማስመዝገብና ማስፀደቅ የሕግ ግዴታ ሲሆን፣ ይህን በሚመለከት በባለሥልጣኑ የተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ፀድቆ ወደ ሥራ እስከሚገባና የምዝገባ ሥራ እስከሚጀመር ድረስ የአክሲዮን ግብይቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው  bterefe@ecma.gov.et ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...