Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

የሕይወት ፍልስፍና ከሚባለው ይልቅ የሕይወት መርህ በጣም ይቀርበኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ነፃነቱን በእጅጉ የሚፈልግ ግዴታውንም ጠንቅቆ መረዳት አለበት›› የሚለው አባባል የሕይወቴ መርህ ነው፡፡ እኔ ዓለሙ በሙሉ የሚደግፈውን ወይም የሚነቅፈውን ጉዳይ፣ ፈጣሪ በሰጠኝ አዕምሮ በማመዛዘን በራሴ መንገድ ብይን እሰጥበታለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የማንም ጣልቃ ገብነት ወይም አስገዳጅነት የምታገስ አይደለሁም፡፡ ከወጣትነቴ ዘመን ጀምሮ በጅምላ መነዳትም ሆነ በነፈሰበት የመንፈስ አባዜ ስላልነበረኝ፣ አሁንም በጉልምስናዬ ዘመን በዚሁ አኳኋን ነው የምመራው፡፡ በተለይ በተለይ የአገራችንን ፖለቲካ በሚመለከት ደግሞ በጥራዝ ነጠቅነት የሚሰነዘሩ ውዳሴዎችና ትችቶች አይመቹኝም፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ነው የሚጥመኝ፡፡ ያላነበበና ያልተመራመረ የሚያወራው ከንቱ ስለሆነ፣ ጊዜዬን ከጥራዝ ነጠቆች ጋር አላጠፋም፡፡ ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ያነሳሳኝም ይኼው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት አካባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ በተለይ በስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ ከሚያናድዱኝ ድርጊቶች መካከል አንዱ በብሔር መቧደንና በመንጋው አስተሳሰብ ውስጥ ራስን የመደበቅ አባዜ ነበር፡፡ በእርግጥ ሁላችንም ወደን ሳይሆን በአጋጣሚ የተገኘንበት ማኅበረሰብ አለን፡፡ በማኅበረሰቡ ወይም በማንነቱ መታወቅ የሚፈልግ ካለ መብቱ እንደሆነው ሁሉ፣ የሌላውንም እንደፈለገ የመሆን መብት ማክበር ለተማረ ወይም ነቃ ላለ የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠፋው አይደለም፡፡ ነገር ግን ዓለም በፈጣን ግስጋሴ እየጠበበ በመጣበት ዘመን አንድ ቦታ ላይ ተገትሮ ከዚያ ንቅንቅ አልልም በሚል ስሜት፣ ሌላውን የመጥላትና በጠላትነት መፈረጅ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጎልቶ መታየቱ፣ አንደ አገር አብሮ የመቀጠል ብሎም ከዓለም ጋር የመደባለቅን መንፈስ የሚጣረስ ነበር፡፡ ብቻ በየቀኑ በብሔር እየተቧደኑ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መቧቀስ አሳፋሪ ታሪካችን ነበር፡፡ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት፡፡

አንድ ቀን የዚሁ የቡጢና የእርግጫ ተሳታፊ የሆነ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ‹‹ጋሼ አሴ›› ካፌ ውስጥ አግኝቼው ስሜቱን ለማወቅ አወራው ጀመር፡፡ ብዙ እንዲናገር በሰጠሁት ዕድል የተረዳሁት፣ ከብዙ ዓመታት በፊት ከዘመነ መሳፍንት ዘመን ማክተም በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት ሲመሠረት በግዛት ማስፋፋት ስም የተፈጸመው በደል ቁርሾ መሆኑን ነው፡፡ እሱ ‹‹የትምክህት ኃይል›› የሚላቸው የዘመኑ ሰዎች ከአያቶቻቸው ባለመማራቸው ዛሬም ረግጦ የመግዛት አባዜ አለቀቃቸውም አለ፡፡ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር በአንድ አገር ከመኖር ይልቅ የራስን ሪፐብሊክ መመሥረት ወሳኝ መሆኑን አሰመረበት፡፡ ለዚህም የተጀመረው ፕሮጀክት ግቡን እንደሚመታ በእርግጠኝነት ነገረኝ፡፡ ይህ የ20 ዓመት ወጣት የነበረ ተማሪ በዚህ ምክንያት ሁሌም ፀብ ያለበት ሥፍራ እንደማይጠፋ ማረጋገጫ ሆነኝ፡፡ በተለየ መንገድ በመነጋገር የአገር አንድነትን ማስቀጠል አይቻልም ወይ ብዬ ራሴን በምሳሌ ሳቀርብለት፣ ‹‹እባክህ እሱ የተባነነበት የተበላ ዕቁብ ነው…›› ብሎኝ ተሰናበተኝ፡፡ ወደ የለመደው የቡድን ጦርነቱ የሚያመራ ይመስል እጆቹ ለቡጢ የተመቻቹ ይመስሉ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወጣቶቻችን አዕምሮ ውስጥ የተዘራው የግንጠላ ፕሮግራም እስካሁን ተግባራዊ ባይሆንም፣ አሁንም ፕሮጀክቱ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የተዘነጋ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በተለይ ፌስቡክንና ቲክቶክን ማሰስ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት ይህንን ዓላማ ያነገቡ ወጣቶች አርጅተው ፕሮጀክቱ እየተረሳ ነው ሲባል፣ አጀንዳው አሁንም እንዳለ ማሳያዎች በጉልህ ይታያሉ፡፡ በአሁኑ ዘመን የአገራችን ፖለቲካ ትልቁ ችግር የመደማመጥ መጥፋት ነው፡፡ በስመ ዴሞክራሲ አንዱ የራሱን አጀንዳ እያስተጋባ፣ ለሌላው ዕድል መስጠት አይፈልግም፡፡ የራሱን ነፃነት እየጠየቀ የሌላውን ማዳፈን ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲ ግልጽ ውይይትና ክርክር ነው የሚያስፈልገው እየተባለ፣ እኔ የምለውን አዳምጥ የሚል ትውልድ እየነገሠ ነው፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ሲቧቀስ የነበረው ወጣት ዛሬ አገር ውስጥና ውጭ አገር ሆኖ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ጦርነት ሲቀሰቅስ ለሚያይ ዕድገት ነው ወይስ ውድቀት ያስብላል፡፡

ግለሰቡ የሚፈልገውን በመመኘቱ እየወቀስኩት አይደለም፡፡ እዚህ እሱ ያኔ በቀሰቀሰው ብጥብጥ ስንቶቹ ጥርሳቸው እንደ ወላለቀ፣ ስንቶቹ እጃቸውና እግራቸው እንደ ተሰባበረ፣ ስንቶቹ ከትምህርት ገበታቸው እንደ ተባረሩ፣ ወዘተ. ለሚያስታውስ ለእንደ እኔ ዓይነቱ ሰው በጣም ያሳቅቃል፡፡ ይህንን የማነሳው ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በተነሳ አመፅ ምክንያት ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ ሆኖ ከቢጤዎቹ ጋር ‹‹ግፋ በለው›› እያለ ሁከት ሲያቀጣጥል የነበረው አንዱ እሱ ነበር፡፡ በስመ ነፃነት ፍለጋ ዲቪውን ሞልቶ አሜሪካ የገባው ያ የያኔው ጎረምሳ፣ ከዩኒቨርሲቲ ወጥቶ ሥራ ላይ ከሰነባበተ በኋላ በአንድ የታወቀ ባንክ ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ነበረው፡፡ ግን እንቅልፍ የሚያሳጣው ዓላማው ይሁን ሌላ አሁን አሜሪካ ነው ያለው፡፡ እሱ ነፃነት ያለበት አገር ውስጥ በሰላም እየኖረ፣ አላሳካ ያለውን ፕሮጀክት ሌሎች እንዲጨርሱት እሳት ውስጥ ይማግዳቸዋል፡፡ የሆነውም ይህ ነው፡፡ ነፃነትና ግዴታ አልተገናኙም፡፡

ነፃነት ትልቅ ተፈጥሯዊ ሀብት ነው፡፡ ይህ ለሰው ልጅ የተቸረ ሀብት በአግባቡ ካልተያዘ ትርጉም የለውም፡፡ እንኳን አፍሪካ ውስጥ አሜሪካ ውስጥም ነፃነት አንፃራዊ ነው፡፡ ለምን ቢባል በስመ ነፃነት የማኅበረሰቡ ሰላም አደጋ ውስጥ መግባት ስለሌለበት ነው፡፡ የሰው ልጆች መብት የሚከበረው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አማካይነት ነው ሲባል፣ ቢያንስ የዴሞክራሲን ካባ መላበስ ያስፈልጋል፡፡ የፈለገውን ያህል ትግሉ መራር ቢሆንም፣ በሠለጠነ መንገድ መብትን ለማስከበርና ነፃነትን ለመጎናፀፍ መሥራት የበለጠ ነው፡፡ የዓለም ታሪክ እንደሚያሳየን በኃይል የሚደረግ ትግል ውጤቱ አምባገነንነትን ማምጣት ነው፡፡ ሕዝብን እወክላለሁ በሚል ሰበብ ሩቅ አገር ሆኖ በኢንተርኔት እሳት ለማንደድ መሞክር ከአጥፍቶ ጠፊነት አይለይም፡፡ ነፃነትን የሚፈልግ ግዴታውንም ማወቅ አለበት፡፡ የራሳቸውን ግዴታ ሳይወጡ፣ የሌሎችን መብት ሳያከብሩ፣ አገርን የምታህል የጋራ መኖሪያ ቤት ለማፍረስ በስመ ነፃነት ሲነግዱ ቆይተው፣ አውሮፓና አሜሪካ ተሰደው በሰው ሕይወት መቆመር ኃጢያት ነው፡፡ የሠለጠነ አገር እየኖሩ እንዳልሠለጠነ ሰው ማሰብ ኋላቀርነት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ አሳሳቢ ጊዜ ይኼ አደገኛ አስተሳሰብ ካልተቀየረ ከፊታችን አሳር እንደሚጠብቀን አንጠራጠር፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል እላለሁ፡፡

(አሰፋ ሶርሳ፣ ከቱሉ ዲምቱ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...