Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹አገራዊ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል›› የአትሌቶች ማናጀር...

‹‹አገራዊ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል›› የአትሌቶች ማናጀር ዮናስ አያና

ቀን:

አትሌቶች በአገር አቀፍ ውድድሮች ከተካፈሉ በኋላ በዓለም አቀፍ መድረክ ለመካፈል የማናጀሮችን ደጅ መጥናት ግድ ይላቸዋል፡፡ በውጭ አገር በሚከናወኑ የግል ውድድሮች መርጦና ለይቶ አትሌቶች ማስመዝገብ የማናጀሮች ኃላፊነት ነው፡፡ ውድድሮችን ከማመቻቸት በዘለለ አትሌቶችን ከተለያዩ የትጥቅ አምራች ድርጅቶች ጋር የስፖንሰርሺፕ ውል እንዲያስሩ ማድረግ የማናጀሮች ሥራ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን መልምሎ ለማሰናዳት ከዓለም አትሌቲክስ ፈቃድ አግኝተው፣ በዚህ ሥራ የተሰማሩና ዓለም አቀፍ ልምድ ያካበቱ በርካታ ማናጀሮች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የውጭ አገር ዜጎች ቢሆኑም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የኢትዮጵያውያን ማናጀሮች በዘርፉ እየተሰማሩ ይገኛል፡፡ ዮናስ አያና ቀድሞ አትሌት የነበረ ሲሆን፣ ሩጫን ካቆመ በኋላ ፊቱን ወደ ማናጀርነት አዙሮ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ወክለው የሚሳተፉ ከ20 በላይ  አትሌቶች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ የአትሌቶች ማናጀር ከሆነው ዮናስ አያና ጋር በአጠቃላይ ስለ አትሌቲክስ ማናጀርነትና ተያያዥ ጉዳዮች ለመወያየት ከዳዊት ቶሎሳ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአትሌቲክስ እንዴት ወደ ማናጀርነት ገባህ?

አቶ ዮናስ፡- እ.ኤ.አ. በ2006 ለግማሽ ማራቶን ወደ አሜሪካ ባቀናሁበት ወቅት ከውድድር በኋላ እዚያው ለመቅረት ወሰንኩ፡፡ በዚያም የተለያዩ ትምህርቶችን መውሰድ ቀጠልኩ፡፡ በትርፍ ጊዜ ለውድድር ወደ ዋሽንግተን፣ እንዲሁም ኒውዮርክ የሚመጡ በርካታ አትሌቶች ስለነበሩ እንዳስመዘግባቸውና የውድድር ቦታ እንድወስዳቸው ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ምንም ክፍያ ሳልጠይቃቸው ከሁለት ዓመት በላይ ስረዳቸው ከቆየሁ በኋላ፣ በ2012 የማናጀር ፈቃድ አውጥቼ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በ2013 የዓለም አትሌቲክስን የማናጀር ፈቃድ ካገኘሁ በኋላ ወደ ሥራ ገባሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ የአገር ውስጥ ፈቃድ ለማግኘት ሁለት ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ፈቃድ ለማግኘት ለምን ያንን ያህል ጊዜ ወሰደብህ?

አቶ ዮናስ፡- የአገር ቤት ፈቃድ ለመውሰድ አንዳንድ ማጣራቶች ያስፈልጉ ነበር፡፡ ይህም ዮናስ ማን ነው? በአግባቡ ይሠራል ወይ? የሚባሉ ጉዳዮች እስኪጣሩ ጊዜ ይፈልግ ነበር፡፡ በሒደት ስፖርቱን በደንብ እየለመድኩና እየተግባባሁ ስመጣ ወደ ሥራ ገባሁ፡፡ ፈቃዱን ለማግኘት፣ የአትሌቶችንም እምነት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንተ አንድ አትሌት ለማስሮጥ የማሳመን ሥራ ሠርተህ ብታስሮጥና አትሌቱ ውጤት ሲያመጣ በዘርፉ ከ30 ዓመት በላይ ያሳለፉ ልምድ ያካበቱ ማናጀሮች አትሌቱን አባብለው ሊወስዱብህ ይችላሉ፡፡ በተለይ አዲስ አትሌት በግል ውድድሮች ላይ እንዲካፈል ማስቻል ውጣ ውረዱ ብዙ ነው፡፡ የውድድር አዘጋጆች ለአዲስ አትሌት የአየር ቲኬት አይሸፍኑም፡፡ የአየር ቲኬት መሸፈን፣ ትጥቅ ማቅረብ፣ የሆቴል ክፍያ፣ እንዲሁም አትሌትን በውድድር ማስመዝገብ የማናጀር ኃላፊነት ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ የለፋህበትን አትሌት ልምድ ያላቸው ማናጀሮች በትንሽ ነገር አማልለው ሊወስዱብህ ይችላሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአትሌቶች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የቻልክበት አጋጣሚ እንዴት ነበር?

አቶ ዮናስ፡- አትሌቶችን ለማሳመን ብዙ መስዋዕትነት ከከፈልኩ በኋላ እጅጋየሁ ታዬን መያዝ ቻልኩ፡፡ እሷንም ከእጄ ለመወሰድ የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርቡ የነበሩ ማናጀሮች ነበሩ፡፡ በአንፃሩ አትሌቷ ከእኔ የምታገኘውን አገልግሎትና ከውጭ አገር ማናጀሮች የምታገኘውን አገልግሎት ካመዛዘነች በኋላ እኔ ጋ ለመቆየት ወሰነች፡፡ ምክንያቱም ውድድሮች በተገቢው መንገድ እየተዘጋጁላት ሲመጡ፣ ኮንትራት ሳስፈርማት፣ የተሻለ ነገር ሲደረግ ስትመለከት፣ እንዲሁም ውጤታማ ስትሆን አብራኝ መቆየት ጀመረች፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች አትሌቶችም ሥራችንን እየተመለከቱ መምጣት ጀመሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የማናጀር ፈቃድ አውጥተው ወደ ዘርፉ የገቡ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ቢታወቅም ስኬታማ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ የሚፈተኑባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው?

አቶ ዮናስ፡- የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው በውጭና በአገር ውስጥ ያለው ሲሆን፣ ይህም የውድድር አዘጋጆች ትልልቅ አትሌቶችን ይዘህ ስትቀርብ አይቀበሉም፡፡ ማነው አትሌቱ? አንቀበልም ይላሉ፡፡ ሁለተኛው የትጥቅ አምራች ቶሎ ብለው አትሌቶቹን አይቀበሉም፡፡ ሌላው ለረዥም ዓመታት በማናጀርነት የሠሩ 26 ማናጀሮች አሉ፡፡ እነዚህ ማናጀሮች ከውድድር አዘጋጆች ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ አንዱ ማናጀር ውድድር ሲያሰናዳ ሌላው አትሌቶቹን የማሳተፍ ዕድል አለው፡፡ እርስ በእርስ አትሌቶቹን እየተለዋወጡ ይደጋገፋሉ፡፡ በዚህ መሀል አንተ አዲስ ማናጀር ሆነህ ስትቀርብ ትፈተናለህ፡፡ በተለይ አንድን አትሌት ውድድር ልታስገባው ካልቻልክ ጥሎ ሊሄድ ይችላል፡፡ የትጥቅ ካምፓኒዎች አዲስ አትሌት ለመቀበል ጊዜ ይፈጅባቸዋል፡፡ በአገር ውስጥ ያለው ችግር አዲስ ማናጀር ስትሆን ኮንትራት ሊያመጣ አይችልም በማለት አትሌቶች አብረው እንዳይሠሩ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ በዘርፉ የሚፈታተኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል አትሌቶች አሉህ?

አቶ ዮናስ፡- አሁን 20 አትሌቶች በሥሬ አሉ፡፡ ሁሉም አትሌቶች በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አትሌቶች በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አትሌቶች በ1500፣ በ5000 እና በ10000 ሜትር አገራቸውን ይወክላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከዓለም አቀፍ የትጥቅ አምራች ካምፓኒ ጋር ያለህ ስምምነትና ለአትሌቶች የምታመቻቸው አገልግሎት ምን ይመስላል?

አቶ ዮናስ፡- እኔ ከናይኪ ትጥቅ አምራች ጋር እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ ናይኪ ከሚተማመንባቸው አምስት ማናጀሮች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ አንድ ማናጀር አዲስ አትሌት ሲያመጣ ትጥቅ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡  እንደሚታወቀው የአትሌቶች ትጥቅ በጣም ውድ ነው፡፡ የስፖርት ትጥቆቹ በአገር ውስጥ ገበያ ማግኘት አዳጋች ከመሆኑም በላይ በጣም ውድና ጥራታቸውን የጠበቁ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እኛ ከካምፓኒው ጋር ስለምንሠራ የምንተማመንባቸው አትሌቶች ሲመጡ ሙሉ ትጥቅ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ በዚህም መሠረት አንድ አትሌት ከማናጀር ጋር ሲሠራ የትጥቅ ችግር አይኖርበትም፡፡ ሌላው አትሌቱ ውድድር ማድረግ ሲፈልግ በማናጀሩ አማካይነት ውድድር እንዲሳተፍ ይመቻቹለታል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የማናጀሩ ጥቅም ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- በዓለም ደረጃ የዓለም አትሌቲክስ የሚፈቅድልን አሠራር አለ፡፡ አትሌቱ ከሚያገኘው ጥቅም ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆን ኮሚሽን እናገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ አትሌቱ ከሚያገኘው ከየትኛው ጥቅም ታገኛላችሁ?

አቶ ዮናስ፡- በአጠቃላይ አትሌቱ ከሚያገኘው ጥቅም ኮሚሽን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ናይኪ ለአትሌት ኮንትራት ሲሰጥና በውድድር ከሚገኝ ጥቅሞች በተቀመጠውና የዓለም አትሌቲክስ በፈቀደልን መሠረት ኮሚሽን እናገኛለን፡፡ በፈቃዱ መሠረት ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ውስጥ አትሌቶችን እያሳተፍን እናገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የዓለም አትሌቲክስ ከማናጀሮች ጋር በተያያዘ ያወጣውን ሕግ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተለይ ለአትሌቶች ለቪዛ የድጋፍ ደብዳቤ አልጽፍም ማለቱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ያለህ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- አዲስ የወጣው ሕግ በፊት ለማናጀርነት ፈቃድ ለማውጣት ወደ ዓለም አትሌቲክስ ካመራህ በኋላ፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካይነት ማጠናቀቅ የሚገባ አሠራር ነበር፡፡ አሁን ይህ አካሄድ ቀርቶ የዓለም አትሌቲክስ የተማከለ  አሠራር ይፋ አደረገ፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ማናጀር በየትኛውም አገር መሥራት የሚያስችለውን ፈቃድ ነው ያስጀመረው፡፡ ቀድሞ ማናጀሮች ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ስምምነት ማድረግ የሚያስገድድ አሠራር ነበር፡፡ ለምሳሌ እኔ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጋር ስሠራ 5000 ዶላር በዓመት እከፍላለሁ፡፡ ከኬንያ ጋር ስሠራ 3000 ዶላር እከፍላለሁ፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ለአባል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስንከፍል የነበረውን ዓመታዊ የፈቃድ ክፍያ ቀጥታ ለዓለም አትሌቲክስ እንድንከፍል የሚያስችል አሠራር ነው የመጣው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀድሞ ከነበረው አሠራር አንፃር እናንተ ላይ የመጣው ለውጥ ምንድነው? ጥቅሙና ጉዳቱን እንዴት ትመለከተዋለህ?

አቶ ዮናስ፡- ለእኛ ያመጣው ለውጥ ለዓለም አትሌቲክስ ፈቃድ 2000 ዶላር ከከፈልን ከየትኛውም አገር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር መሥራት ያስችለናል፡፡ ለእኛ እንደ አስተዳደር ለሁሉም አገር ፌዴሬሽኖች የምንከፍለውን ክፍያ አስቀርቶልናል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አትሌቲክስ አዲስ ሕግ ለማውጣት ያስገደደው ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- የዓለም አትሌቲክስ አዲስ አሠራር እንዲያወጣ ያስገደደው የአባል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈሉ በመምጣታቸው ነው፡፡ ፌዴሬሽኖቹ ከአምስት ሺሕ እስከ ሃያ ሺሕ ዶላር ድረስ ያስከፍሉ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለዓለም አትሌቲክስ የተለያዩ ቅሬታዎች ይቀርቡ ነበር፡፡ በመጨረሻ የተለያዩ ጥናቶችና አስተያየቶችን ከተቀበለ በኋላ፣ ‹‹እንዴት አድርገን ፈቃድ እንስጥ?›› በሚል ውሳኔ ላይ ከደረሰ በኋላ በማዕከላዊነት ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አዲስ አሠራር ዘረጋ፡፡

ሪፖርተር፡- ከብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ስትሠሩ የምታገኙት አገልግሎት ምን ነበር?

አቶ ዮናስ፡- በእርግጥ አገልግሎቱን እኛ ሳንሆን አትሌቶቹ ነበሩ የሚያገኙት፡፡ አትሌቶቹ ኤምባሲ ሲገቡ የድጋፍ ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ ያገኛሉ፡፡ ይህ የድጋፍ ደብዳቤ አትሌቶቹ ቪዛ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ በአንፃሩ የዓለም አትሌቲክስ በየአገሩ ለሚገኙ ኤምባሲዎች የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍ ሒደቶችን እንደሚመቻች ገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ከፍተኛ ውጤት ያላቸው አትሌቶች ከዓለም አትሌቲክስ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲያገኙ ያስችላችዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንፃሩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ለማይታወቁ አትሌቶች ነን ለሚሉ ለሕገወጥ አትሌቶች ያላግባብ የድጋፍ ደብዳቤ እየተጻፈ ነው የሚል ክስ በመቅረቡ እንደሆነ የሚያነሱ አሉ?

አቶ ዮናስ፡- እውነት ለመናገር በተወሰነ መልኩ በሐሳቡ እስማማለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ኤምባሲዎች ላይ አትሌት ሳይሆኑ አትሌት ነን በማለት ገብተው ሲያዙ ይደመጣል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ዕውቅና ውጪ የድጋፍ ደብዳቤ አስመስለው በመጻፍ የተያዙ አሉ፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ በጣም የጎላ አቅም አለው፡፡ በተለይ አዲስ አትሌት ይዘን ስንቀርብ የጀርመን፣ የስፔን፣ የፈረንሣይ ኤምባሲዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ኤምባሲዎች ቪዛ ይፈቅዳሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥሩ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ቪዛ ሲከለከሉ ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ተስፋ የተጣለበትን አትሌት ከዓላማው እንዲቀር ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አትሌቲክስ ያወጣው አዲስ አሠራር አዳዲስ አትሌቶችን ቪዛ ከማግኘት አንፃር የሚያስከትለው ችግር አይኖርም?

አቶ ዮናስ፡- እውነት ለመናገር አዳዲስ አትሌቶች ፓስፖርት ለማውጣትና ቪዛ ለማግኘት አስቸጋሪ ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ፌዴሬሽኑ ፓስፖርትና ቪዛ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ መተባበር ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር የቪዛው ጉዳይ በጣም ያሳስባል፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ለአትሌቲክሱ ተጠሪ ስለሆነ ለፈቃዱ የትብብር ደብዳቤ መጻፍ ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ካደረገው አሠራር ጎን ለጎን ፌዴሬሽኖች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ውድድር ማሰናዳት ይኖርባቸዋል የሚሉ አሉ? ከዚህ አኳያ እንዴት አጣጥሞ ማከናወን ይቻላል?

አቶ ዮናስ፡- የዓለም አትሌቲክስ የሚለው እያንዳንዱ ፌዴሬሽን ደረጃውን የጠበቀ ውድድር ማዘጋጀት አለበት የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የተከናወነው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ደረጃውን ያሟላና ተቀባይነት ያለው ውድድር መሆን እንደሚገባው ተቀምጧል፡፡ የአገር ውስጥ ውድድር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ከሆነ አዳዲስ አትሌቶች በቀላሉ ወደ ውጭ አገር አምርተው እንዲወዳደሩ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰናዱ ውድድሮች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ፣ ዘመናዊ የውድድር መሣሪያዎችን ማሟላት ይጠበቃል፡፡ አገራዊ ውድድሮቹን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...