Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ በስድስት ወራት ከ14 ሺሕ በላይ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱ...

በአዲስ አበባ በስድስት ወራት ከ14 ሺሕ በላይ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱ ተነገረ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለስድስት ወራት ባከናወነው ሥራ፣ በተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች ተሳትፈዋል ባላቸው ከ14 ሺሕ በላይ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

ቢሮው ይህንን ያስታወቀው ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በኤሊያና ሆቴል የስድስት ወር ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ሲሆን፣ በከተማው ወንጀልን ለመከላከል ከ20 የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ባከናወናቸው ተግባራት በበርካታ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ የቢሮው ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቢሮው በቅንጅት አብሮ ከሚሠራቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የንግድ ቢሮ፣ የትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ቢሮ፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የመሳሰሉት እንደሆነ ባቀረቡት የስድስት ወራት ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በጋራ በተከናወነ ሥራ 19 ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሕፃናትና ልጃገረዶች ላይ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራ መሠራቱን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ቢሮው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ባከናወነው ሥራ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ፣ በሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር፣ እንዲሁም ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የወንጀል ድርጊት 5,127 ተጠርጣሪዎችን መያዙን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ከንግድ ቢሮ ጋር በተሠራ ሥራ በትልልቅ መጋዘኖች ምርቶችን በማከማቸት እጥረት እንደተፈጠረ አድርገው ዋጋ የሚጨምሩ 3,001 ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡  

ቢሮው ከትምህርት ቢሮ ጋር በቅንጅት በሠራው ሥራ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በ200 ሜትር ከባቢ (ራዲየስ) ውስጥ የነበሩ 1,967 የጫት መቃሚያ፣ የሺሻ ማስጬሻ፣ የጋራዥ፣ እንዲሁም የቤቲንግ መጫወቻዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድና በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ሲል ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በከተማው ወንጀልን ለመከላከል፣ ከአስፈጻሚ ተቋማት መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን በከተማዋ የወንጀል ማስፋፊያ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ሥራ መከናወኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታሁን አበራ ተናግረዋል፡፡

የንግድ ቢሮ ተወካይ የሆኑ ግለሰብ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመጣውን ውጤት መልካም መሆኑንና የአሠራር ሥርዓት ላይ ማስተካከያዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሕገወጥ በሆኑ ድርጊቶች የማሸግ ሥራ በሚከናወንበት ወቅት የተጠርጣሪውን ጥፋት በግልጽ ለይቶ በማቅረብ፣ የሚወሰደውን ዕርምጃ ሁሉም አካላት የሚያውቁት በማድረግ፣ እንዲሁም የታሸገውን ድርጅት የማስከፈት ሥራ ላይም የመናበብ አሠራር ካልተፈጠረ ለሙስና ወንጀል ተጋላጭ ሊዳርግ ስለሚችል ሁሉም አካላት የሚያውቁበት መንገድ መፈጠር አለበት፤›› ሲሉ የንግድ ቢሮ ተወካይ ገልጸዋል፡፡

በስብሰባው ከተሳተፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ የተነሳው ሐሳብ የአደባባይ በዓላት ሲኖሩ የሚፈጠረው የደኅንነት ሥጋት በተመለከተ ሲሆን፣ የአደባባይ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት ቢሮው በቅንጅት ከሚሠራቸው ተቋማት ጋር ሥራውን በማስቀጠልና ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ኅብረተሰቡ ያለ ፍርኃት እንዲያከብር የማድረግ ኃላፊነት ተወጥቷል ተብሏል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ በበኩላቸው የሰላም ግንባታ አንዱ መሠረት ጥናቶች ስለሆኑ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ በርካታ ጥናቶች እየተሠሩ መሆናቸውን፣ ቢሮው የሚያከናውነው ሥራ ለማቀላጠፍ ጥናቶቹን  የሚያገኝበት መንገድ እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...