Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ መስክን እስከማስለወጥ የደረሰው የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ መዳከም

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ በእጅጉ ተጎድቶ ቆይቷል፡፡ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያደረሰው ጉዳት አሁንም ድረስ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያጠላው ጥላ አልገፈፈም፡፡ 

ከዚህ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው አለመረጋጋትና የሰሜኑ ጦርነት የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ በመግታቱ ከዘርፉ ሊገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም አሳንሷል፡፡ ከሌሎች የንግድ ዘርፎች በተለየ ይህንን ዘርፍ ያጋመጡት ተደራራቢ ችግሮች የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ አንቀሳቃሾችን ጨምሮ በአስጎብኚ ድርጅቶችና ተያያዥ በሆኑ ንግዶችን አሁንም ድረስ እያንገራገጨ ነው፡፡ 

የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ እየተጎዳ የመጣው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የሚገልጹት የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደ ሰንበት (ዶ/ር)፣ በወቅቱ ከነበረው ለውጥ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው አለመረጋጋት አንድ ምክንያት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የባሰው ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለምን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በእጅጉ መጉዳቱ ነው፡፡ ወረርሽኙ እንቅስቃሴን የገታ በመሆኑ ኢትዮጵያም የዚህ ተጎጂ ሆናለች፡፡ ይህ ክስተት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ያስቆመ ነው ተብሎም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ኮቪድ ከወጣ በኋላም ቢሆን የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀስ ነገሮችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳደረገውም ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ጉዳት ደግሞ ትልልቅና ስመጥር ሆቴሎች፣ ከባንኮች ባገኙት ብድር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርገው ከተገነቡ በኋላ የብድር መመለሻው ጊዜ እና ዘርፉ የተዳከመበት ወቅት መገጣጠሙ ነው፡፡  

ለሆቴል የሚሰጠው ብድር በአብዛኛው ከ10 እስከ 15 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚመለስ በመሆኑ፣ ብድር መመለስ በሚጀምሩበት ሰዓት ገበያው መጥፋት ትልቅ ፈተና ሊሆን መቻሉን ፍትሕ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ በኮቪድም ወቅት ሠራተኞች ላለመበት የተዳረጉ ጥረቶች ሥራውን በእጅጉ በመጉዳቱ ሥራውን ጎድቶት መቆየቱንና ይህ ችግር ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡   

የዚህ ዘርፍ ችግር በዚህ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ብዙዎች ቀድሞ በነበረው የአገልግሎታቸው ልክ እየሠሩ ባለመሆኑ ሥራቸውን እንዲያቋረጡ እስከማስገደድ መድረሱ ሊያወሳስበው ችሏል፡፡ አንዳንዶቹም ቢዝነሳቸውን እንዲቀይሩ እያስገደደ መምጣቱ ደግሞ ኢንዱስትሪው እየገጠመው ያለውን ችግር የሚጠቁም ነው እየተባለ ነው፡፡   

አሁን ባለው የሥራ እንቅስቃሴ ሥራው አዋጭ አለመሆኑን የተረዱ አንዳንድ ባለሀብቶች ቢዝነሳቸውን ለመቀየር ወይም የሆቴል አገልግሎታቸውን ለመቀየር ጭምር ተገደዋል። ከ15 ዓመታት በላይ አገልግሎት ላይ የቆየውና ከሁለት ሳምንት አገልግሎቱን ያቋረጠው የአምባሳደር ሆቴል ባለቤት አቶ ሠይድ መሐመድ 15 ዓመታት ሲያገለግል የቆየውን ሆቴላቸውን የዘጉት ቢዝነሱ አዋጭ ሊሆንላቸው ባለመቻሉ ነው፡፡ 

እንደ አምባሳደር ሆቴል ሁሉ ሌሎች ባለቤቶቹም በተመሳሳይ ሁኔታ የሆቴል ዘርፍን የሚያበረታታ አሠራር ባለመኖሩ ወደ ሌሎች ዘርፎች እንዲያማትሩ እያደረገ ነው፡፡ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ከተሰማሩት በተጨማሪ በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሳተፍ ትልልቅ ግንባታዎችን ሲያካሂዱ የነበሩ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ውጥናቸውን ቀይረው ወደ ሆቴል አገልግሎት ለመግባት የጀመሩትን ግንባታ ወደ ሌላ ቢዝነስ እስከማዞር መገደዳቸውን ይህም ዘርፉ በመቀዛቀዙ ምክንያት የመጣ እንደሆነ ይነገራል።

ዓለም አቀፍ የሆቴል ብራንድ ይዘው ዘርፉን ለመቀላቀል ግንባታ የጀመሩና ውል ገብተው ወደ ሥራ የጀመሩ ሆቴሎች ሳይቀሩ በሥጋት ቢዝነሶቻቸውን ለመለወጥ እየወሰኑ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ትልልቅ ከሚባሉ ባለኮከብ ሆቴሎች መካከል አንዱ ይሆናል ተብሎ የተገመተውና በዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለንብረት ግንባታው ተጀምሮ የነበረው ስታውድ ሆቴል (የሸራተን  ግሩፕ አባል) ውል አቋርጦ ጅምር ግንባታውን ለአፓርትመንት አገልግሎት ለማዋል መወሰኑን ለዓብነት ይጠቅሳሉ፡፡  

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቀደም ብለው ለሆቴል ተብለው የተገነቡ ሕንፃዎች አሁን ላይ ለአፓርታማ አገልግሎት በማዋል ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ 

ፍትሕ (ዶ/ር)ም በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማበራሪያ፣ በእርግጥም ለሆቴል ተብለው ሲገነቡ የነበሩ ሕንፃዎች ለሌላ ዓላማ እየዋሉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ 

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እየታዩ ስለመሆኑ የጠቀሱት ፍትሕ (ዶ/ር)፣ ይህንንም ከሁለት ዓመት በፊት እንዲህ ባለው ተግዳሮት ከፊት ለፊታችን እየመጡ ነው ያሉት በሚል ሲገለጽ ነበር፡፡

ሆቴሎች እንዲህ ባለው መልክ ከገበያ የመውጣታቸው ዕድል እየሰፋ እንደሚመጣም ተገምቶ እንደነበር ፍትሕ (ዶ/ር) ያስታውሳሉ፡፡ አብዛኛው ሆቴሎች አዲስ አበባ ውስጥ በመሆናቸውና ሲገነቡም ታሳቢ ያደረጉን ሁለት ነገሮችን እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ 

አንደኛው የዲፕሎማቲክ መቀመጫነቷን ተከትሎ የሚመጡ ኮንፈረንሶች ታሳቢ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦችን ትራንዚት የሚያደርጉ በመሆኑ ይህም ጥቅም የገቢ ምንጭ ተደርጎ በመወሰዱ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለት ነገሮች መዳከም ገቢን አቀዛቅዟል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የነበረውን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት አዳዲስ ሆቴሎች በብዛት ወደ ግንባታ ገብተው እንደነበርም የፍትሕ (ዶ/ር) ማበራሪያ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ይህ በተፈጠረው ችግር ሊቀጥል አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትራንዚት ያደረጋቸው የነበሩ እንግዶችም በራሱ ሆቴል ማሰተናገድ መጀመሩም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በትራንዚት የሚገቡ እንግዶችን እናገኛለን ያሉ ሆቴሎች ከአንድ ሺሕ በላይ አልጋዎች ባሉ የአየር መንገዱ ሆቴል የሚስተናገዱ መሆኑ ለገበያቸው መቀዛቀዝ አንድ ምክንያት መሆኑን የፍትሕ (ዶ/ር) ማበራሪያ ያስረዳል፡፡ 

ሌላው ለመቀዛቀዙና ሆቴሎች ሌላ ቢዝነስ እንዲመላከቱ እያደረጋቸው ካሉ ተጠቃሽ ነጥቦች መካከል በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከሌሎች አገሮች ጋር እየተደረገ ያለው ውድድር ጠንከር ብሎ መምጣቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኮንፈረንስ ቱሪዝሙን ሌሎች ነገሮችም መጋራት መጀመራችውም የችግሩ አንድ አካል ሆኗል፡፡ እንደ ፍትሕ (ዶ/ር) ገለጻ ኮቪድ ከወጣ በኋላ፣ ወደ 20 የሚሆኑ ትልልቅ ሆቴሎች የግንባታ ማጠናቀቂያ ላይ ደርሰው እያለ የማጠናቀቂያ ዕቃዎችን ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ ሥራቸውን ቀይረዋል፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የገጠማቸው ችግርና ወቅታዊ የገበያ ሁኔታ በቢዝነሱ ለመቀጠል ስላሠጋቸውና የብድር የመክፈል ጫናውን ሲስተም የግድ ሌላ አማራጭ መፈለግ ግድ ሊላቸው ችሏል፡፡

ባንኮም ብድሩ ለማራዘም ያለመቻላቸው ወደ ተለያዩ የገበያ አማራጭ ሕንፃዎቻቸውን እያዞሩት ነው፡፡  ባንኮች ማሻሻያ ካላደረጉ ሥራ ላይ ያሉትም ወደ እዚህ መንገድ ሊገቡ የሚችሉ መሆኑን ያላቸውን ሥጋት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

እንዲህ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ የሚሆነው ከዘርፉ እየወጡ ነው ስንል ለአገር ኢኮኖሚ የሚሰጠውን ጥቅም ሁሉ እየቀነሰ መጥቷል ማለት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በቸልታ ሊመለከተው የማይገባ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ 

 እንዲህ ያለው አካሄድ ግን ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ሁለት ገጽታዎች ያሉት መስሏል፡፡ አንደኛው የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ እያስገኘ ያለውን ያህል ጥቅም አሁን እየተገኘበት ባለመሆኑ መቀዛቀዙን የሚያመለክት ነው፡፡ አሁን በሆቴልና ለቱሪዝም ዘርፍ ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ ባለሀብቶች ከዘርፉ ወጣ ያሉ ቢዝነሶችን እያማተሩ ያሉትም ገበያው በተሳበው ልክ መሆን ባለመቻሉ ነው፡፡

በአንፃሩ ይህ እየተጎዳ መሆኑ እየተነገረለት ያለው ዘርፍ ተስፋ ያለው ነው የሚሉ ወገኖች ደግሞ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተሠሩ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘርፉ አሁንም ተስፋ ያለው መሆኑን የሚያለክቱ ናቸው፡፡

በዋናነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አፍላቂነት እየተገነቡ ያሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ አሁን ላይ ለዘርፉ መቀዛቀዝ ምክንያት ናቸው የተባሉ ተግዳሮቶች ሲቃለሉ ዘርፉን መልሶ እንዲንሠራራ ያደረጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

እነዚህ ሁለት የተለያዩ ምልክታዎች ዘርፉን በተግዳሮትና በተስፋ መካከል እንዲዋልል ያደርገዋል የሚሉት ወገኖች፣ አሁንም ግን ተስፋ የተጣለበት ኢንቨስትመንትና አሁን ያለው ኢንቨስትመንት በታሰበላቸው ልክ እንዲረማመዱ ለማስቻል ሰላም ወሳኝ ስለመሆኑ ያመለክታሉ፡፡ 

ፍትሕ (ዶ/ር) በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሰላምንና መረጋጋትን የሚፈልገው ይህ ኢንዲስትሪ ለኢትዮጵያ ወሳኝ የሚባል የኢኮኖሚ ምሰሶ እንደሚሆን የመታመኑን ያህል በተግባር የሚታይ መፍትሔ የሚያሻውና ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አንድ ሺሕ ፐርሰንት ሊባል የሚችል ተስፋ ያለው መሆኑን በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ተስፋ አለው የምንለው ብዙ ነገሮች ስላሉንም ነው፡፡ ምክንያም ማንኛውም ቱሪስት፣ ማንኛውም የቱሪዝም ኮንፈረንስ ሊፈልገው የሚችል መዳሻዎችና ፋሲሊቲዎች አሉ›› የሚሉት ፍትሕ (ዶ/ር)፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ አለን፡፡ ስለዚህ ተስፋ የሚያሳጣን ነገር የለም ይላሉ፡፡ ዋናው ተግዳሮት ግን እነዚህ ይህንን ተስፋ ዕውን ለማድረግና ለማድረስ አሁን እየታየ ያለውን ችግር እንዴት እንሻገራለን የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ያለውን ዕድል ባለመጠቀማችን ነው እንጂ ዕድሎችን አጥተን እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡

ስለዚህ በዚህ ረገድ ፌዴሬሽናቸው አሉ የተባሉ ተግዳሮቶችን ለሚመለከተው አካል በተከታታይ የሚያቀርበው ዕድሉ ስላለ በዚህ ዕድል እንጠቀም ለማለት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ፌዴሬሽናናቸው በአዲስ መልክ ሲዋቀር ዘርፉን የሚያመላክቱ ጥናቶች ቀርቧል፡፡ ይህ ጥናት ያለንበትን ደረጃ የሚያመላክት ጭምር ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የተደረሰበት ነጥብ ይህንን ጊዜ ለማለፍ የሚያስችሉ ዕድሎች ያሉ በመሆኑ ላሉ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጥ ነው፡፡ አሁን ያለውን ችግር ለማለፍም አንዱ መፍትሔ ለዘርፉ የተሰጠው የባንክ ብድር መመላለሻ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ማግኘት ቢችል በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ሌላ ቢዝነስ ለመቀየር ባላሰቡ ነበርም ብለዋል፡፡ ይህ ጥያቄያችን የተወሰደው ብድር እንዳለ ሆኖ የብድር መመለሻ ጊዜ ብቻ እንዲራዘም የሚል ቢሆንም፣ ይህ ምላሽ ባለማግኘቱ በጅምር ያለ ብቻ ሳይሆን ሥራው ላይ ያሉም ቢሆን ይህንን አማራጭ በግዴታ ሊተገብሩት መቻላቸውን አይቀርም የሚል ሥጋት አላቸው፡፡  

የብድር ማራዘሚያ ጊዜ መስጠት ጫናው እንዲቀንስ ዘርፉን እንዲነቃቃ በማድረግ ሥራውን በማጠናከር ወደሚቀጥለው ምዕራፍ መሸጋር ይቻላል ከሚል እምነት ነው፡፡ ጥያቀያችንን ያቀረብነው ከእነመፍትሔ ሐሳቡ መሆኑን የሚገልጹት ፍትሕ (ዶ/ር)፣ ጥያቄዎቹ በደንብ ታይተው ምላሽ ቢያገኙ ተስፋውን የሚያለመልም ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አዎንታዊ መልሱ በሚያደራድር መልኩ ኢኮኖሚን ሊደግፍ የሚችል ነው፡፡

አሁን በመንግሥት እየተካሄዱበት ያሉት ግንባታዎችን በተመለከተም አሁን ደግሞ መንግሥት ደግሞ እጀግ ትልልቅና ዘመናዊ የሆኑ አዲስ የሆኑ ቱሪስት መዳረሻ እየሠራ መሆኑ መንግሥትን የሚያስመሠግን እንዲሆነ ፍትሕ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ያሉበትንም ምክንያት ሲያብራሩ አሁን ላይ ትልልቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ተብለው በዩኔስኮ ተመዝግበው የምንኮራባቸው አብዛኛው የቱሪስት መዳረሻዎች ያለፉት መንግሥታቶች ትኩረት ሰጥተው የሠሯቸው ናቸው፡፡   

ዛሬም በዘርፉ ለተሰማራነው የገቢ ምንጭ አድርገን የምንሸጣቸው እንደዚህ በመሆኑ ስለዚህ አሁን እየተሠሩ ያሉት አዳዲስ መዳረሻዎች ኦፕሬተሩ ያልደረሰባቸው ቦታዎችን እያሳየ ስለሆነ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ አዳዲስ መዳረሻዎች ሥራ እንዲያገኙና አሁን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የገጠማቸው ተግዳሮቶች እንዳይገጥማቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ተስፋ የተጣለባቸው አዳዲስ የቱሪስቶች መዳረሻ ሥፍራዎች በታሰበላቸው ልክ ውጤታማ እንዳልሆኑ፣ ግን መሠረታዊው ነገር ሰላም መሆኑን ያስገነዘቡት ፍትሕና ሰላም ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ ትልቅ ዕድል ይዘው የመጡ ናቸው፡፡  

የቱሪዝም ዘርፉ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ዋነኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማግኛ ተብለው ከተለዩት መካከል እንደ መሆኑን ተስፋውን ያሳያል፡፡ በዚህ ደረጃ የተቀመጠ የኢኮኖሚ የሚመራ ነው ተብሎ ከታሰበ ግን ያሉበትን ችግሮች መፍታት ግድ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ምክንያቱም ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፍጠር የአገልግሎት ዘርፍ እንደሚሆኑ በልዩ ትኩረት ሊታይ ይገባል የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ‹‹ትንሽ የምንለው ሆቴል ከ50 እስከ 60 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ትልልቆቹ ደግሞ በአማካይ እስከ 600 ሠራተኞችን ይቀጥራሉ፡፡ ከእነዚህ ሠራተኞች የሚሰባሰብ ግብርም በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛም ነው፡፡ ዘርፉ የአገር መልካም ገጽታ ማሳያ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች