Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በታሪካዊ ጠላት ፊት መዝረክረክ ዋጋ ያስከፍላል!

ግብፅ የሰሞኑን የሶማሊያ ጩኸት ተገን አድርጋ ታሪካዊ ጠላትነቷን ለኢትዮጵያ በግልጽ ስታስተጋባ፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በጠላት ፊት ያለ መንበርከክ ታሪካዊ የጋራ እሴቶቻቸውን ይዘው የመንቀሳቀስ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያውያን መካከል በበርካታ ውስጣዊ ጉዳዮች አለመግባባቶች አሉ፡፡ እነዚህ አለመግባባቶች ከንትርክ አልፈው ግጭት በመቀስቀስ ደም እያፋሰሱ ነው፡፡ በዚህ መሀል ሁኔታዎች የተመቻቹላት ግብፅ በግላጭ ወጥታ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ስትነሳ፣ ልዩነቶችን በሰከነ መንገድ ገታ አድርጎ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር በአንድነት አለመነሳት ከባድ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ የሰሞኑ የግብፅ ገደብ አልባ መወራጨት እንደ ቀልድ የሚታይ አይደለም፡፡ አገር ከሚመሩ ወገኖች ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሊያቆሟቸው የሚችሉ የጋራ ጉዳዮች እንዳሉ በመተማመን፣ በፍጥነት ለጠላት ከሚያጋልጡ አላስፈላጊ እሰጥ አገባዎች ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን በተለይ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትና ተገዳዳሪዎቹ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በንግግርና በድርድር ፈጥነው መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ አጣዳፊ ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው የሁሉም ወገኖች ትኩረት የአገር ህልውና ላይ ይሁን፡፡

ኢትዮጵያ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ መግባባት አለባቸው ሲባል፣ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት በሚወስደው እያንዳንዱ ዕርምጃ ቀጥተኛም ሆነ የውክልና ተሳትፏቸው በአስተማማኝ ሁኔታ ሲረጋገጥ መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቻርተርም ሆነ ሕጎች እያከበረች፣ ከጎረቤት አገሮች ጋርም በሰጥቶ መቀበል መርህ ስምምነት እየፈጠረች ዲፕሎማሲው በብልኃትና በስክነት እንዲመራ የጋራ ምክክር ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ አካሄድ የጎረቤት አገሮችን ይሁንታ ማግኘት ካልቻለና ሥጋት ከገባቸው፣ ግብፅ ያገኘችውን አጋጣሚ በመጠቀም ከበባ ማድረጓን ትቀጥላለች፡፡ የግብፅን ታሪካዊ ጠላትነት ማስቆም የሚቻለው ከውስጣዊ ፖለቲካ እስከ ውጭ ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ስምምነት ሲፈጠር ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ተቀናቃኞቹ የአገር ህልውናን ጉዳይ ለፖለቲካ ልዩነታቸው ሒሳብ ማወራረጃነት መጠቀም የለባቸውም፡፡ ማንም እንደሚያውቀው መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፡፡ አገር ግን እንደዚያ ስላልሆነች የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን አድርገው የአገር ጠላቶችን የመከቱበትን ታሪክ ያስታውሱ፡፡

የአሁኑ ትውልድ ከአገር ህልውና በታች የሆኑ ቅራኔዎችን መልክ በማስያዝ አገሩን ከታሪካዊ ጠላት ሴራ መከላከል አለበት፡፡ ጥንታዊያኑ ኢትዮጵያውያን አንድም ጊዜ ቢሆን በልዩነቶቻቸው ምክንያት አገራቸውን አላሳፈሩም፡፡ ይልቁንም ተስፋፊዎችና ወራሪዎች በየተራ ኢትዮጵያን ለመድፈር በሞከሩባቸው ጊዜያት፣ ልዩነቶች ሁሉ ወደ ጎን ተደርገው ነበር አገር ከጥቃት የተመከተችው፡፡ ይህም በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ በተመለከተ በተለይ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ አመራሮች በዚህ ታሪካዊ ወቅት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በየቦታው የተዘራውን ጥላቻና የክፋት ድርጊት በሙሉ በማስወገድ፣ ለአይረቤ ጥቅሞች ማስከበሪያ ፍጆታነት የሚውለውን አክራሪ ብሔርተኝነት ማስቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ፀንታ የምትቆመው ኢትዮጵያውያን በጥንካሬ ሲተባበሩ እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው በተከፋፈለና በተዝረከረከ አቋም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አሳሳቢ ጊዜ ትልቅ ብሔራዊ ምክክር ያስፈልጋታል፡፡ ምክክሩ አጓጉል ትርክቶችን አስወግዶ በኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል ሥር በእኩልነትና በአንድነት የሚያቆም መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ንግግር ያስፈልጋል፡፡

አክራሪና ጽንፈኛ ብሔርተኝነት የተጠናወተው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብሔራዊ ሥጋት መደቀኑን በመተማመን፣ በሰከነ መንገድ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ጥርጊያውን ማመቻቸት ይገባል፡፡ የአክራሪ ብሔርተኞች ከፋፋይ አጀንዳ ኢትዮጵያን የግጭት መናኸሪያ ከማድረግ አልፎ፣ ለጠላት ቀላል ዒላማ እንድትሆን እያደረጋት ነው፡፡ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚለውን ከፋፋይ አጀንዳ በማራመድ፣ በኢትዮጵያ ምድር ከእኩልነት ይልቅ የተረኝነት ስሜት እየገነፈለ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር መግባባት አልተቻለም፡፡ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ በተፈራረሙት የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ ግብፅ በግላጭ ወጥታ ጠላትነቷን ስታሳይ፣ ሥር በሰደደ ቅራኔ ምክንያት ‹‹ማን ያቦካውን ማን ይጋግረዋል?›› እየተባለ ጀርባ መሰጣጠት ነው የተከተለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቅራኔ በጊዜ በንግግርና በድርድር ሁሉንም ወገኖች የሚያስማማ መፍትሔ ካልተፈለገለት፣ የአገር ህልውና ያበቃለት ያህል ይቆጠራል፡፡ መንግሥት ለአፍታ ቆም ብሎ አገር ውስጥ የሚካሄዱትን ደም አፋሳሽ ግጭቶች ለማስቆም የሚረዳ ተነሳሽነት ያሳይ፡፡ ለቅራኔና ለጥላቻ መፈጠር ምክንያት የሆኑ ብልሹ አሠራሮችን ያስወግድ፡፡ ብሔራዊ መግባባት ሳይኖር አንድ ዓይነት አቋም ማራመድ ስለማይቻል፣ የተበላሹ ነገሮችን በፍጥነት ማስተካከል የግድ መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚስተዋለው ጥልቅ መከፋፈል መላ ሊፈለግለት የሚገባው፣ ሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ባለመቻሉ ምክንያት አገር እየተጎዳች ስለሆነ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከተቀናቃኞቹ ጋር መስማማት አቅቶት ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ሲገባ ለአገር አደጋ ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር መስማማት ያቃታቸው ወገኖች የትጥቅ ትግልን አማራጭ ሲያደርጉ የአገር ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ የሚስተናገዱበት ምኅዳር ጠፍቶ እያንዳንዱ ችግር በጠመንጃ እንዲፈታ የሚፈለግ ከሆነ፣ ለአገር ህልውና ጠንቅ ከመሆኑም በላይ ታሪካዊ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ ለማግኘት አይቸገሩም፡፡ በኢትዮጵያና በአካባቢው ሠራዊቶች ጥበቃ ነፍሱን ቢዘራም ፀንቶ መቆም ያቃተው የሶማሊያ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ላይ ጠላቶችን ከየአቅጣጫው ለማሰባሰብ ሁሉንም በሮች አንኳኳለሁ ሲል የአገር ውስጥን ትርምስ አስቁሞ ሰላም አለማስፈን መዘዙ ከባድ እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ መንግሥት የደፈረሰውን ሰላም ለማረጋጋት ከማንም በላይ አቅም ስላለው ያስብበት፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከአገራቸው ህልውና የሚቀድም የለምና ለመፍትሔ ይትጉ፡፡

እዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባ አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ በነፃነቷ ኮርታና በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ ስትራመድ የኖረችው፣ ጥንታውያኑ ጀግኖች ልጆቿ በጋራ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህ መስዋዕትነት ተንቆ በአይረቤ ትርክቶች የአፍሪካውያን የነፃነት እናት የረሃብ፣ የጦርነትና የድህነት ተምሳሌት ተደርጋ ከፍተኛ ውርደት ደርሶባታል፡፡ አሁንም ከዚህ አዙሪት ውስጥ መውጣት አልቻለችም፡፡ የራስን ጀግኖች ከማክበር ይልቅ ማራከስ ሙያ ይመስል አጉል ትርክቶችን ማዕከል አድርጎ አገርን ማድማት ቁምነገር ሆኗል፡፡ ለረጅም ጊዜ ሊላቀቅ ያልቻለ በሽታ አገር ውስጥ ተሰንቅሮ፣ በበርካታ ታሪኮች ያሸበረቀችን አገር ታሪክ አልባ ማድረግ በአፍሪካውያን ዘንድ ሳይቀር ለትዝብት እየዳረገ ነው፡፡ ሰሞኑን ኬንያ በጣም ዘመናዊ የሚባል የፍጥነት መንገድ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም በመሰየም ማስመረቋ ይታወሳል፡፡ ‹‹የአፍሪካ አባት›› በመባል የሚታወቁትን ንጉሠ ነገሥት በኢትዮጵያ የሚያስታውስ ጠፍቶ፣ ኬንያ ኢትዮጵያውያንን አንገት የሚያስደፋ ታሪካዊ ተግባር ስትፈጽም ማነው ማፈር ያለበት? ጥልቅ ክፍፍሉ በተጠናከረ ቁጥር የሚጎዳው ማነው? ግብፅን በግልጽ ለመደንፋት ያበቃት ይህ መከፋፈል አይደለምን? በኢትዮጵያ መከፋፈል ተጠቃሚው ማን ይሆን? በታሪካዊ ጠላት ፊት መዝረክረክ ዋጋ እንደሚያስከፍል ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...