Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበፈለገ ዮርዳኖስ

በፈለገ ዮርዳኖስ

ቀን:

ዓመታዊው የጥምቀት በዓል በምሥራቁ ዓለም በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ትናንት ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል፡፡ ዛሬ ደግሞ የቃና ዘገሊላ በዓል እየተከበረ ይገኛል፡፡  የምዕራቡ ዓለም በዓሉን ያከበረው ከ13 ቀናት በፊት ነበር፡፡

ክብረ በዓሉ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1985 ዓመታት በፊት እግዚእ ኢየሱስ በተጠመቀበት በቅድስት ሀገር በፈለገ ዮርዳኖስ እንደ ሁሌው የኢትዮጵያ ምዕመናን በተገኙበት በሊቀ ጳጳሱ መሪነት ተከብሯል፡፡

በፈለገ ዮርዳኖስ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጥምቀት በዓል በፈለገ ዮርዳኖስ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን ሲከበር

ፈለገ ዮርዳኖስ ሲገለጽ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ለማክበር በሺዎች የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ዮርዳኖስ ወንዝ ላይ ወዳለው የባህላዊው የጥምቀት ቦታ ወደ ‹ቃስር አል ዩሁድ› ይወርዳሉ፡፡

ቃስር አል ያሁድ ማለት የአይሁድ ቤተ መንግሥት ማለት ሲሆን በሌላ ታሪክ መሠረት፣ ከ3200 ዓመታት በፊት እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተስፋዪቱ ምድር የገቡት በዚህ ቦታ እንደነበር ይወሳል።

የጥምቀት በዓልን ተከትሎ በቅድስት ሀገር እየተከናወኑ ካሉት ሥርዓቶች ሁሉ አስደናቂው በፈለገ ዮርዳኖስ ይታያል። የጥምቀት ቦታ በቅድስት ሀገር ከኢየሩሳሌምና ከቤተልሔም ቀጥሎ እጅግ አስፈላጊው የክርስቲያን ቦታ ነው፡፡

በፈለገ ዮርዳኖስ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በዓሉ በግሪክ የኤጲፋኒ በዓል ሲባል ትርጉሙም ‹‹መገለጥ›› ማለት ነው፡፡ በእግዚእ ኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ሁለት አስፈላጊ ክስተቶችን ያመለክታል፡፡ አንደኛው ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል (ጠቢባን) ወደ ቤተ ልሔም ያደረጉት ጉብኝትና  ወርቅ እጣንና ከርቤ ያበረከቱለት ነው። ከሦስቱ ጠቢባን አንዱ በኢትዮጵያ ትውፊት መሠረት የአክሱም ንጉሥ ባዜን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀበት ቀን ነው። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ  መሠረት እግዚእ ኢየሱስ የተጠመቀው ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም.፣ ከጥንተ ፍጥረት ሲነሳም 5534 ዓመተ ዓለም ነው፡፡

ከአዲስ ኪዳን ወንጌሎች አንዱ በሆነው በማቴዎስ እንደተዘገበው፡- ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፥ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ፡፡ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ። እነሆም ድምፅ ከሰማይ፡ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ መጣ።››

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አካዴሚክ ዲን እና መምህር የነበሩት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ (በኋላ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ) በአንድ መጣጥፋቸው ስለ በዓለ ጥምቀቱ እንዲህ ጽፈዋል፡፡

‹‹በአራቱም ማዕዘን ምዕመናን በአንድ ላይ ሆነው በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ይህም በዓል መገለጥ /ኤጲፋኒያ/ ይባላል። ይህም ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ መገለጥ ሆኗል። የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት ተገልጿል። ክርስቲያኖችም ይህንን በዓል የምናከብረው ለበረከትና ለረድኤት ነው፡፡››

ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ። በዑደታቸውም ምእመናኑ ታቦታቱን በዝማሬያቸው ያጅቡታል።

መምህራኑ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ (ኤጲፋንያ) የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ዋዜማ ያለው ጊዜ ነው (ዘንድሮ እስከ የካቲት 17 ድረስ ይሆናል)። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዓምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ፣ እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል።

ጳውሎስ መን አመኖ የኢየሩሳሌምና የቅዱሳት ቦታዎች ታሪክ ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ለሚሔድ መንገደኛ መሪ እንዲሆን በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ እንደገለጹት፣ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ተወልዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ 30 ዓመት ሲሆነው በዮርዳኖስ ወንዝ ሰማያዊው በመሬታዊው በዮሐንስ እጅ በትኅትና ተጠመቀ፡፡ መሲሕነቱንና አምላክነቱን አስመሰከረ፡፡ ምስክሩም ከሰው አልነበረም ወይም በመልአክ አፍ አልተነገረም፡፡ ነገር ግን ከዘለዓለም ጀምሮ የባሕርይ አንድነት የነበረው አባቱ ይህ ነው ልጄ የምወደው ደስታዬን የማይበት ብሎ መሰከረለት፡፡››

ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመውረድ በዓሉን በየትውፊታቸው ከሚያከብሩት አንዷ በኢየሩሳሌም መንበረ ጵጵስና ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምና በማኅበረ ካህናቱ መሪነት በዚያ ያሉም ሆነ ከኢትዮጵያ የሚሄዱ ምዕመናን በየዓመቱ ሲያከብሩ ያዩ ሚዲያዎች አከባበሩን ‹‹አስደናቂ እና ማራኪ›› ነው ብለውታል። በየዓመቱ  ጥር 11 ቀን የጥምቀት ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሕዝብ ሁሉ ዮርዳኖስ እየወረደ መጠመቅ የጀመረበት ዘመን ከ160 ዓ.ም. ወዲህ ነው ይባላል፡፡ ጌታ የተጠመቀበት ቦታ ዛሬ ኦርቶዶክሳውያን ከሚጠመቁበት እንደነበር፣  በኢያሪኮ ሲኖሩ የነበሩ ሕዝበ ክርስቲያን በየዓመቱ  በጥር 11 በሌሊት ወደ ዮርዳኖስ እየወረዱ ሲጠመቁ ያዩ ቦታውም ይህ ነው እያሉ ሲያሳዩ የሰሙ የኢየሩሳሌም ሳሚዎች በ400 እና በ600 ዓ.ም. በጻፉት ታሪክ ማመልታቸውን አቶ ጳውሎስ መን አመኖ ጽፈዋል፡፡ 

‹‹ፈለገ ዮርዳኖስ መካነ ጥምቀት›› በሚል ርዕስ የጻፉት ሊቀ ካህናት መርዓዊ ተበጀ (ዶ/ር) እንዲህ ያብራራሉ፡፡

‹‹ከቤተልሔም 53፣ ከኢየሩሳሌም 44፣ ከኢያሪኮ ደግሞ 8 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ምንጮች ከሦስት ተራራዎች ማለትም ከዳን፣ ከሄርሞንና ከባንያስ/ቂሣርያ ፊልጶስ/ተነስተው በየአቅጣጫቸው ከፈሰሱ በኋላ ‹ሜሮን› በሚባል ትንሽ ሐይቅ ውስጥ ይገናኛሉ፡፡ ከዚያም በአንድ ላይ ሆነው አካባቢያቸውን እየመገቡ 17 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ከገሊላ ወይም ከጌንሴሬጥ ወይም ከጥብርያዶስ ባህር ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ ከዚያም እንደ እኛ ዓባይና ጣና ሐይቅ፣ የዮርዳኖስ ውኃ የገሊላን ባህር ሰንጥቆ ከወጣ በኋላ 100 ኪሎ ሜተር ያህል እንደተጓዘ ከሙት ባህር/ከጨው፣ ከሎጥ ባህር/ጋር ተቀላቅሎ በዚው ሰጥሞ ይቀራል፡፡

‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባህር ወንዝ ከመጠመቁ ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ሲል ትንቢት ተነግሮለት ነበር፡፡ ‹ባህር አየች፣ ሸሸችም፡፡ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡ ተራራዎችም እንደ ኮርማዎች ዘለሉ› የሚለው ምስባከ በየዓመቱ በጥምቀት ክብረ በዓል በወንዝ ዳር ይሰበካል፡፡ ጊዜው ሊደርስ የዮርዳኖስ ባህር በጌታ ጥምቀት ተባረከ፣ ተቀደሰም፡፡

‹‹ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አሁንም በነቢያት ትንቢት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡ አራቱ ወንጌላውያን ከቅድስት ጥምቀቱ ተባብረው ይመሰክራሉ፡፡

ጌታ ወደ ተጠመቀበት ቦታ ወዲያው በመጀመሪያ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተጠማቂዎች እንደ ጎረፉ ነው፡፡ ከእየቦታው የመጡ ተሳላሚዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ወንዝ ሳይጠመቁ እንደማይመለሱ ስለተሳላሚዎች የሚጽፉ ሁሉ መዝግበውት ይገኛል፡፡

‹‹ቅዱስ ላሊበላም ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም መጥቶ ከኖረ በኋላ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ከመጠመቁም ሌላ በሠራቸው አብያተ ክርስቲያናት አጠገብ የሚገኘውን ሸለቆ ‹ዮርዳኖስ› በሚል ጠርቶታል፡፡ ከቅዱስ ላሊበላ ንግደተ ኢየሩሳሌም በኋላ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ንግደተ ኢየሩሳሌም ለማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ዘመኑም ዓረቦች ቅድስት አገር ኢየሩሳሌምን የያዙበት ዘመን ስለሆነ የተሳላሚ ጉዟቸው ቀላል አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ገድላቸው እንደሚዘረዝረው ያልደረሱባቸው ቅዱሳት መካናት የሉም፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አንዱ ዮርዳኖስ ነው፡፡ 

በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ኤጲፋንያ በመባልም ይታወቃል፡፡ በጥምቀት የክርስቲያኖች ሁሉ ዳግም ልደት ተበሥሮበታል፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል፡፡ ይህንን በማሰብም በየአብያተ ክርስቲያኑ ያሉ ታቦታት ከቅዱስ መንበራቸው  ተነስተው በዓሉ ወደሚከበርበት ባህረ ጥምቀት ይዘልቃሉ፡፡

ዋዜማው ጥር 10 ቀን ከተራ ሲሆን፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደ የጥምቀተ ባሕር የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግሥቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ መገለጫ ነው፡፡.

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...