Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሁለመናዊ ፋይዳ ያለው የጥምቀት ክብረ በዓል

ይህ ጽሑፍ ዩኔስኮ የሚባለው የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም የጥምቀት በዓልን የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ አድርጎ ሲመዘግበው የተዘጋጀ ነው፡፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አማካይነት የተዘጋጀው የምዝገባ ሰነድ በእንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በዩኔስኮ ድረ ገጽ አማካይነት ለዓለም ተሠራጭቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጉዞና በአደባባይ ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መሠረት አለው፡፡ ‹‹ጥምቀት›› ማለት በውኃ ውስጥ መጠመቅ፣ መጥለቅ፣ መንጻት ማለት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል የሚከበረው በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ጥር 11 ሲሆን አከባበሩ የሚጀምረው ከተራ በመባል ከሚታወቀው የዋዜማ ዕለት (ጥር 10) ጀምሮ ነው፡፡ ‹‹ከተራ›› መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ በጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባብ ስለሚያድር የየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን ሕዝብ እየሰበሰበ በወንዝ ዳርና ውኃ ባለበት አካባቢ ድንኳን ይተክላል ወይም ዳስ ይጥላል፡፡ በየአጥቢያው ቦታ ተይቶና ተከልሎ ታቦታተ ሕጉ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የታቦት ማደሪያ፣ ውኃ የሚከተርበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ሥፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት›› እየተባለ ይጠራል፡፡

ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ታሪካዊ መሠረቱን ሳይለቅ አሁን እንዳለው መከበር የጀመረው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሐ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብለው የአገሪቱ ብሔራዊ ሃይማኖት ሲያደርጉ በዓለ ጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በአገራችን በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ሲከበር የኖረ ‹‹የበዓለ መጸለት(የዳስ በዓል››) የሚባል ስለነበር ጥምቀት በእሱ ምትክ የጉዞና የአደባባይ በዓል ሆኖ እንዲከበር አድርገዋል፡፡

እነዚህ ቅዱሳን ነገሥት ለሃይማኖቱ ማደግ ብቻ ሳይሆን ለበዓሉም መስፋፋት ተግተው ሠርተዋል፡፡ በዓሉ በየዘመኑ እያደገ መጥቶ በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ያሬድ በዘመኑ ይፈጸም የነበረውን የበዓሉን አከባበር ሥርዓት በማየት ለበዓሉ አከባበር የሚስማማ የዜማ ሥርዓት አዘጋጅቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለበዓሉ ያዘጋጀው የዜማ ድርሰትም ከበዓሉ ዋዜማ (ከተራ) ጀምሮ የሚፈጸም በመሆኑ ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀትንና ሥርዓትን ሰጥቶታል፡፡ ቅዱስ ላሊበላም በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአንድ ወጥ ዓለት ፈልፍሎ ባነፃቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ውስጥ በዓሉን ሁሉም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት የሚያከብሩበትን ቦታ በዮርዳኖስ ወንዝ ስም ምሳሌነት አካቶ መሥራቱ በዓሉ ምን ያህል ደማቅ እንደበር ለመረዳት ያስችላል፡፡ እስካሁንም ድረስ ይህ ቦታ ዮርዳኖስ በመባል ይታወቃል፡፡

ከዛጉዌ በኋላ የተነሱ ነገሥታት እንደ አፄ ይኩኖ አምላክ (በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን)፣ አፄ ዘርዓ ያዕቆብና አፄ ናዖድ (በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ካህናቱና ሕዝቡ ታቦታቱን አጅበው በአንድነት የሚያከብሩትን ይህንን ጥንታዊና መንፈሳዊ በዓል በየዘመናቸው ደምቆ እንዲከበር የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም በጎንደር የነገሡት አፄ ፋሲል ለመዋኛ ገንዳ ያሠሩት የበዓለ ጥምቀት በዓል ማክበሪያ የተደረገ ሲሆን፣ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ከነገሡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጀምሮ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በዓሉ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

የጥምቀት በዓል በመላ ኢትዮጵያ ጥር 10 እና 11 ይከበራል፡፡ በጥር 10 ላይ ጧት ጀምሮ የታቦት ማደርያ የሊቃውንትና የምዕመናን መጠለያ ዳስ ይጣላል ወይም ድንኳን ይተከላል፡፡ ጥር 10  ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠበቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለመዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ ‹‹ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን›› የሚለውን ዋዜማ ከነሙሉ ሥርዓቱ እስከ ሰላም ያለው በሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያደርሳሉ፡፡ በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን ለማክበር የተመደቡ ካህናት በፆም ተወስነው ይውላሉ፡፡ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ ታቦታት የወርቅና የብር መጎናጸፊያ ተጎናጽፈው በተለያየ ኅብረ መልክእ በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የወርቅ፣ የብርና የዕፅ መፆር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ ባሕረ ጥምቀት ለመጓዝ ሲነሱ፣ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምዕመናን ከሕፃን እስከ አዋቂ ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው ታቦተ ሕጉን በማጀብ ለማክበር ይሰበሰባሉ፡፡ ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ሲነሳ ‹‹ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት›› የሚለው ሰላም በሊቃውንቱና በወጣቱ እየተዘመረ ጉዞ ይቀጥላል፡፡ የወርቅ ካባ ላንቃ የለበሱ ቀሳውስትና መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦቱ ጎን መስቀልና ጸናጽል የያዙት ከታቦቱ ፊት ይሄዳሉ፡፡ ልብስ ተክህኖ የለበሱ ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ይጓዛሉ፡፡ ከእነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ፣ ጥንግ ድርብ፣ መጠምጠሚያ የለበሱ ሊቃውንት የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጽናጽል ከበሮ ይዘው ‹‹ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት›› የሚለውን ዜማ እያሸበሸቡ ከዲያቆናቱ በፊት ይጓዛሉ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአድባራት አለቆች፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ታቦቱን በማጀብ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው ‹‹ወረደ ወልድ፣ ሖረ ኢየሱስ›› እና ሌሎች መዝሙራትን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች እየዘመሩ ከፊት ይጓዛሉ፡፡ እናቶች ‹‹አለው አለው ሞገስ››፣ ‹‹እሰይ ስለቴ ደረሰ››፣ ‹‹ነይ ወደ እኛ ማርያም››፣ ‹‹በሆት ግባ በሆት አንተ ያገሬ ታቦት››፣ ‹‹መድኅኑ ብትሰጠኝ ዕድሜ፣ በሸኙሁህ ደግሜ›› እያሉ ምዕመናን በሆታ ሌሎችንም ምሥጋናዎች እያቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ባሕረ ጥምቀት ይሆናል፡፡

ታቦታቱ ከየአቅጣጫው እየመጡ ሲገናኙ እነሱን አጅቦ የመጣው ሰው አንድ ላይ እየተቀላቀለ ጭብጨባው እልልታውና ሆታው ይደምቃል፡፡ የከተማ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡ ከተሸበሸበ በኋላ ትምህርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገቡና ኪዳን ይደረሳል፡፡ ታቦታቱ ከገቡ በኋላ ታቦታቱን አጅቦ የመጣው ሰው ሁሉ በጋራ በተዘጋጀው ድግስ ይስተናገዳል፣ ይሁን እንጂ የሚቀድሱና የሚቆርቡ ምዕመናን እራት አይበሉም፡፡ ድግሱ ከተጠናቀቀ በኋላ ማታ ከ1፡00 ሰዓት ጀምሮ የሌሊቱ ማኅሌት ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ካህናትም በአንድ ድንኳን ውስጥ በመሆን ሌሊቱን እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑና ጥምቀትን የሚመለከት ቃለ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ ምዕመናኑም አብረው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ቅዳሴ ይከናወናል፡፡ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ሲሆን የጥምቀት ባሕሩ ሥርዓተ ቡራኬ በሥርዓተ ቅዳሴ ይጀመራል፡፡ የጥምቀቱን ታሪክ የሚገልጹ ከአራቱም ወንጌላውያን ይነበባሉ፡፡

ቀጥሎ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባሉበት ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ካልሆነም በታላቅ ካህን ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› በማለት ባሕሩ ተባርኮ ጸበሉ ለሕዝቡ ይረጫል፡፡

ሕዝቡ በመጠመቅ ላይ እንዳለ ታቦታቱ ከድንኳኑ ወጥተው በተዘጋጀላቸው ሥፍራ ሲቆሙ ሊቃውንቱ ‹‹ኃዲጎ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባሕር፣ ወወጽኣ በሰላም›› (ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላዕክት ትቶ በባሕር ላይ ቆመ፣ በሰላምም ወጣ) የሚለውን ስብሐተ እግዝአብሔር ያቀርባሉ፡፡ ለዕለቱ የተዘጋጀው ትምህርት ተሰጥቶ፣ ‹‹አቡነ ዘበሰማያት›› ከተጸለየ በኋላ ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት በስተቀር ከላይ የተጠቀሱት ታቦታት በሙሉ በዕለተ በዓሉ ወደ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ዕለት ታቦታቱ ወደ የቤተ መቅደሳቸው ለመሄድ ሲነሱ በካህናትና በምዕመናን ምሥጋና፣ ዝማሬ፣ ዕልልታና ጭፈራ እንዲሁም ሆታ ይታጀባሉ፡፡ ካህናቱ፣ ሊቃውንቱና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ሕዝቡ በዝማሬና በተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ታቦታቱን አጅበው ጉዞ ይጀመራል፡፡ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች በቡድን በቡድን እየሆኑ የተለያዩ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችን፣  ዘፈኖችን እያሰሙ በሆታና በእልልታ ጉዞውን ይቀጥላሉ፡፡ በመቀጠልም ቤተ መቅደሳቸው ሲደርሱ ይቆሙና በዓውደ ምሕረቱ ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› የሚለው ወረብ ይወረባል ይሸበሸባል፡፡ ትምህርትም ይሰጣል፡፡ በመጨረሻም ጸሎት ከተጸለየ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ግን በዚያው ቆይቶ በማግስቱ ጥር 12 ቀን ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል፡፡

አዲስ አበባ የአገሪቱ ዋና ከተማ እንደ መሆኗ የበርካታ ማኅበረሰቦች መኖሪያ ናት፡፡ በመሆኑም በጃንሜዳ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ወቅት የለተያዩ ብሔረሰቦች ያለልዩነት የየአካባቢያቸውን ጨዋታ በዜማና በጭፈራ የሚያሳዩበት መድረክም ነው፡፡ ስለዚህ በዓለ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ዕሴቱ በተጨማሪ ሕዝቦች ማንነታቸውንና ፍላጎታቸውን በነፃነትና በመከባበር፣ በሰላምና በፍቅር የሚያሳዩበት፣ አገራዊ የባህል ልውውጥ፣ የሕዝቦች አብሮ የመኖር ታሪካዊ ልምድ ማሳያም ነው፡፡

አስፈላጊነቱና ጠቀሜታው

አገራችን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ከሚያከብሩ አገሮች አንዷ ናት፡፡ ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ ፋይዳውም ከፍ ያለ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጥምቀት በዓል አከባበር ከፍ ያለ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ክብረ በዓል ነው፡፡

ለሦስት ቀናት ያህል (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተከታታይ በሚከበረው በዚህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ መንፈሳዊ መዝሙሮች፣ የተለያየ ስልት ያላቸው ያሬዳዊ ዜማዎች ይመጣሉ፡፡ በበዓሉ ላይ የየአካባቢው አገረሰባዊ ዘፈኖች፣ ጭፈራዎች፣ ውዝዋዜዎች በስፋት ይከናወናሉ፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ በዓሉም እነዚህን የትውን ጥበባትና የሥነ ቃል ሀብቶች ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ በዓል ሕዝቡን በሰፊው የሚያሳትፍ በመሆኑ ታቦታቱን ለመሸኘት በተሰባሰበው የአካባቢው ነዋሪ መካከል ማኅበራዊ ትስስርን ይፈጥራል፡፡

የጥምቀት በዓል የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ሕይወትና አንድነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክር እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ ለጥምቀት በዓል የቤተሰብ አባላት ከያሉበት ይሰባሰባሉ፡፡ ዘመድ ከዘመዱ ይጠያየቃል፡፡ ስለዚህ ባህልን ከመጠበቅና ከማስቀጠል አንጻርም የጥምቀት በዓል የጎላ ድርሻ  አለው፡፡ በዓለ ጥምቀት ደማቅ ማኅበራዊና ባህላዊ ገጽታዎች (ዕሴቶች) አሉት፡፡ እነዚህ ዕሴቶች በልዩ ልዩ ሁኔታ የሚገለጹ ለሰላምና ለዕርቅ፣ ለአገር የመልካም ገጽታ ግንባታ፣ ለአንድነትና ለመከባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

በበዓሉ ላይ ዲያቆናት መስቀል ይዘው ሲጓዙ ሌሎች ሽመል ይዘው በሆታ ያጅባሉ፡፡ አብዛኛው የበዓሉ ታዳሚ ባህላዊ አልባሳትን ስለሚለብስ የኅብረተሰቡን የቆየ ባህላዊ አለባበስ በማስተዋወቅና በማሳደግ ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚባል አባባልም ስላለ ይልቁንም ሴቶች በዚህ ቀን ባህላዊ አልባሶቻቸውን ይለብሳሉ፣ ባህላዊ የፀጉር አሠራራቸውን ይሠራሉ፡፡ በመሆኑም በዚሁ ቀን የአካባቢው ሕዝብ ባህሉን፣ አለባበሱን፣ የፀጉር አሠራሩን፣ አመጋገቡን የሚያሳይበት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የየአካባቢውን ባህል ከማስጠበቅና ከማስተዋወቅ አኳያ ልዩ ጥቅም አለው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዓሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች ከሁሉም ዓለማት ወደ አገራችን ማለትም ወደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ጣና፣ አዲስ አበባ ጃንሜዳና ሌሎች የታሪክና የተፈጥሮ መስህቦችን ያሉባቸው ቦታዎች መጥተው እንዲጎበኙ በማድረግ ለአገሪቱ የመልካም ገጽታ  ግንባታና ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ጠቀሜታ አለው፡፡

በክብረ በዓሉ ቀናት ወጣቶች የትዳር አጋር የሚሆኗቸውን ልጃገረዶች የሚያዩበትና እነርሱም የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በዚህ ቀን የማይጨፍር ወጣት አይኖርም፡፡ የጥምቀት በዓል ከገና በዓል የሚለየውም በዚህ በዓል ሕዝቡ በጉዞና በአደባባይ ተሳታፊ የሚሆንበት፣ ደስታውን የሚገልጽበት የሚዝናናበትና በዓሉን የሚያሳይበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡

የጥምቀት በዓል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም የጎላ ነው፡፡  የመጀመርያው በዓሉ በሚከበርባቸው ዋና ዋና ሥፍራዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ይታደማሉ፡፡ ይህም በአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በተለይም በአገልግሎት ዘርፉ ሰፊ እንቅስቃሴ ይፈጥራል፡፡ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች፣  የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትና የዕደ ጥበብ ውጤቶች አምራቾችና ነጋዴዎች ወዘተ… ሰፊ የሥራና የገቢ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ ሌላው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረገው ወይም ሰፊ ገበያ የሚፈጠረው በባህላዊ አልባሳት ላይ ነው፡፡ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› በሚለው ብሂል አብዛኛው ሰው ለበዓሉ አዳዲስ የአገር ባህል ልብሶችን ይገዛል፡፡ ይህ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎችም ከፍተኛ የገበያ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በዘመናዊ መንገድ የሚዘጋጁ ባህላዊ አልባሳት ለገበያ እስኪቀርቡ ድረስ በሒደቱ ለሚሳተፉ ሁሉ ተጨማሪ የሥራ  ዕድል ይፈጥራል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ስጦታዎች፣ ቁሳቁሶችን በማቅረብና በመሸጥ ላይ ለተሰማሩ ሰዎችም ከፍተኛ የገበያና የሥራ ዕድል ይፈጥራላቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ድንኳኖቻቸውን ጥለው በቀንም ሆነ በማታ አገልግሎት ሲሰጡ የሚቆዩት የሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚያቀርቡት የመጻሕፍት፣ የምግብና መጠጥ፣ የቅዱሳት ሥዕላት፣ የመዝሙር ሕትመቶች፣ የፊልሞች ገበያም ሌላው በዓሉን ሲያደምቁ የሚቆዩና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ የጥምቀት በዓል ወቅት ለፀሐይ መከላከያ ኮፍያዎችና የሰሌን ባርኔጣዎች ለምዕመኑ በስፋት ለሽያጭ ከመቅረባቸውም በላይ የተለያዩ አሳታፊ ባህላዊ ጨዋታዎችና ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles