Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሻሁራ እንዴት ናት?

ሻሁራ እንዴት ናት?

ቀን:

በዮሴፍ አትርሳው

ሻሁራ ከተማ የምትገኘው፣ በአማራ ብሔራዊ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከአዲስ አበባ በ517 ኪሎ ሜትር፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ደግሞ በ86 ኪሎ ሜትር ርቀት በስተምዕራብ በኩል ነው።

የስሟ ትርጓሜና የከተማዋ አመሠራረት ከደብረ ጽዮን ሻሁራ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መመሥረት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑ ይወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የክርስትና እምነትን ካስፋፉና በሰሜኑ በኩል ከተነሱ ነገሥታት አንዱና ዋነኛ የነበሩት አፄ ዓምደ ጽዮን ነበሩ፡፡ አፄ ዓምደ ጽዮን መነሻቸው ትግራይ ሲሆን፣ በዘመናቸው ታላቅ ክብርና ዝና የነበራቸው ንጉሠ ነገሥታት እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ የአፄ ዓምደ ጽዮን ስመ መንግሥታቸው ገብረ መስቀል ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡

አፄ ዓምደ ጽዮን ከልጃቸው በኩረ ጽዮን ጋር በመሆን መጀመሪያ እንደመጡ ያረፉበት ቦታ ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ ‹ድኩልኳን› መግቢያ አካባቢ ነበር፡፡ አፄው ከአንድ የዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጠው ተመሳሳይ ከብቶች፣ ቀለማቸው ሻሁር የሆኑ ያያሉ፣ ከዚያም የእነዚህን ሻሁር ከብቶች ባለቤት ጥሩልኝ ብለው አዘዙ፡፡ በዚህም መሠረት ሻሁራ የሚል ስያሜ እንደተገኘ ይተረካል፡፡ እነዚያ የባለሻሁር ከብት ባለቤቶች ወደ ዓምደ ጽዮን በቀረቡበት ጊዜ ንጉሥ እንደሆኑ ወንጌልን እንደሚያስፋፉ፣ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚተክሉ ነገሯቸው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሠራዊታቸው ብዙ ከመሆኑ አንፃር የባለ ሻሁሩ ከብት ባለቤት ለአካባቢው ሕዝብ ምግብ እንዲያዙ ተነገራቸው፡፡ ባለ ሻሁሩም ባለቤትም አካባቢውን ባዘዘበት ጊዜ የሚበላና የሚጠጣውን ጠጅ ብርዝ፣ እርጎውን፣ ወተቱን፣ ዓይቡንና ማሩን ይህ ጎደለ ሳይባል ድግሡ ከመጠን በላይ ለንጉሡ ቀረበላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ አፄ ዓምደ ጽዮን ተገረሙና ‹‹ምን ያለፈለት አገር ነው›› ሲሉ ተሰማ፡፡ ስያሜው ‹‹አለፋ›› ተብሎ ተጠራ ይባላል፡፡

ስለዚህ ሻሁራ፣ አለፋ የሚሉ ሰሞች በአፄ ዓምደ ጽዮን እንደተሰየሙ አፈ ታሪኩ ይገልጻል፡፡

በክልሉ ለወረዳ መቀመጫነት ከሚያገለግሉ ከተሞች አንዷ ሻሁራ ስትሆን፣ የአለፋ ወረዳ ዋና ከተማ ናት። መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧን ስንመለከት አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ሜዳ ሲሆን በዙሪያዋም ወጣ ገባ ያሉ ኮረብቶች ይገኛሉ።

ከተማዋ የተቆረቆረችበት ሥፍራ በደጋና በቆላማ መሃል ነው። የአየር ንብረቷ ወይና ደጋ ነው። ለመኖር ምቹና ለሰው ልጅ የሚስማማ የአየር ሁኔታ አላት። ለዚያም ይመስላል በርኸኞች ብዙ ጊዜ በጋ በጋ ኑሯቸውን ሻሁራ እያደረጉ ክረምት ሲመጣ ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱት።

ሁለት ትይዩ የአስፋልት መንገዶች፣ የተለያዩ ኮብል ስቶንና የጠጠር መንገዶች አሏት። በዋናነት ሁለት መግቢያና መውጫ በሮች ያሏት ሲሆን፣ በተለምዶ ላይኛው መግቢያ፣ ታችኛው መግቢያ ወይም ምሥራቅና ምዕራብ መግቢያ ተብሎ ይጠራል። በሁለቱም መግቢያ በሮች የፍተሻ ኬላዎች አሉ፡፡ ስለሆነም በመኪና ተሳፍረው የሚገቡ ተሳፋሪዎችና የጭነት መኪኖች ፍተሻ ይደርግባቸዋል።

በምዕራቡ መግቢያ በረሃ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚገቡበት ሲሆን፣ በላይኛው መግቢያ በር ደግሞ ደገኞች ይገቡበታል።

ከሁለቱ በሮች በአንዱ ገብተን ከተማዋን ስንመለከት ሰፊ የመኪና መናኸሪያ፣ በርቀት ዳግም ትልልቅ ሆቴሎች፣ ሆስፒታልና ትምህርት ቤቶች ይታያሉ።

ወደ ከተማ መሃል ገባ ብሎ ወደ አንደኛው የአስፋልት መንገድ ዓይኑን ላማተረ ሰው እግረኞች በርከት ብለው መኪና፣ ሞተር፣ ባጃጆችና ጋሪዎች፣ እንዲሁም የተለያየ ቁጥርጥር የተጫኑ አህያዎች፣ ሊሸጡ የመጡ በሬ፣ ላም፣ ፍየልና በጎችን በአንድ ላይ ሞቅ ባለ ድባብ ሲተራመሱና አንዱን መንገድ በጋራ ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደና ምናልባትም በትኩረት ለተመለከተው አግራሞትን የሚጭር ነው።

ከተማዋ በቆላና በደጋ መሃል እንደመገኘቷ የንግድ ማዕከልና የእንግዶች ማረፊያ ናት። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች የመጣች ከተማ ስትሆን በተለይ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ለውጧ አስገራሚ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ሱር የሚባለው ኮንስትራክሽን በሁለት ሺሕ መጀመሪያዎቹ ላይ ደጋውን ከቆላው የሚያገናኝ፣ በከተማዋ መሃል የሚያልፍ ትልቅ የፒስታ መንገድ ሠርቶ ካስረከበ በኋላ ነው።

ከተማዋ በሁለት ቀበሌዎችና በተለያዩ ሠፈሮች የተደራጀች ሲሆን ቴዎድሮስ፣ ድኩልካን፣ ማንዴላ፣ ጨረቃ፣ አዝማሪ የመሳሰሉ የሠፈር ስሞች አሏት። አብዛኛው ነዋሪ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሲሆን፣ ፕሮቴስታንትና ሙስሊሞችም አሉ። አራት በከተማዋ ዙሪያ በተለያየ አቅጣጫ የተሰሩ ቤተ ክርስቲያኖችና አንድ መስጊድ አላት። ከሁሉም ቀዳሚዋና በታሪክ የምትታወቀው የሰባት መቶ ዓመታት ገደማ ዕድሜ ያላት ሻሁራ ጽዮን ማርያም ናት።

 ቅዳሜና ሐሙስ ለሻሁራ የተለዩ የገበያ ቀኖች ሲሆኑ፣ ከሁሉም አቅጣጫ የወረዳው ነዋሪዎችና ከሌሎች ጎረቤት ወረዳ የሚመጡ በረኸኞችና ደገኞች በስፋት ይታያሉ። ከበረሃ አካባቢ የሚመጡት ብዙውን ጊዜ ሰሊጥ፣ ማርና ቅቤ የሚያመጡ ሲሆን፣ ደገኞች ደግሞ ቅመማ ቅመሞችን እንደ በርበሬ፣ ሽንኩርት፣ ባቄላና ገብስ የመሳሰሉትን ይዘው ይመጣሉ። ከተሜዎቹም ደግሞ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ይዘው ይወጣሉ። እነዚህ ቀኖች በጉጉት የሚጠበቁ ሲሆን፣ ኑሮውን ሻሁራ አድርጎ ለከተማው ነዋሪም ሆነ ለገጠሬው የፈለጉትን የሚገዙበት፣ የሚሸጡበት፣ የሚለውጡበትና ሞቅ ያለ የገበያ ውሎ የሚያሳልፉባቸው ቀኖች ናቸው።

ሻሁራ ከተማ የተቆረቆረችበት ሥፍራ የቆላና የደጋ ማዕከል በመሆኑ፣ ነዋሪዎቿም እንዲሁ ከተለያየ ቦታ የመጡ ናቸው። ማኅበረሰቡ እንግዳ ተቀባይ ዘመን የማይሽረው ብዙ ድንቅ ባህልና ወግ ያሉት ነው፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ የገቢ ምንጫቸው ንግድ ሲሆን፣ እርሻና የእንስሳት ዕርባታም የዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሆኑ የከተማ ነዋሪዎችም አሉ።

በእንዲህ ዓይነት መልኩ ኑሮዋን ስትገፋ የኖረችው ሻሁራ ከተማ 2016 ዓ.ም. መልካም ነገርን ይዞ አልመጣላትም፡፡ ዓይታው የማታውቀውን ጭንቅና አስቸጋሪ ዘመን እንጂ።

መስከረም ከተጋመሰበት ጀምሮ ከባድ ፈተናዎች የገጠሟት ሻሁራ፣ አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ፈተናዎችን እንዳልተወጣች ነው የሚነገረው። የዘመን መለወጫና የመስቀል በዓልን እንደቀደመው ሁሉ በሰላም ያከበረችው ከተማዋ፣ ከበዓል ማግሥት በኋላ ያሉት ጊዜያት ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ሊቀጥሉላት አልቻሉም።

በመከላከያና በታጠቁ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭትና ቀጥተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት የአማራ ክልል ቦታዎች የሰላም መደፍረስ እንዳጋጠማቸውና ከመደበኛ እንቅስቃሴያቸው ውጪ ሆነው መቆየታቸው ይወሳል፡፡

ሻሁራ ከተማም እንደሌሎች ሁሉ የብጥብጥና የግጭት ቀጣና በመሆን ገፈት ቀማሽ ሆና ከከረመች ወራት ተቆጥረዋል። በግጭቱ ሳቢያ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ እንደ መብራት፣ ውኃ፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤት የመሳሰሉ ለማኅበረሰቡ ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሠረተ ልማቶች ተዘግተው ከርመዋል።

በተለይ ታጣቂዎችና የመንግሥት ኃይሎች ገጥመው በነበረበት ወቅት፣ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ ተለያየ የገጠሩ ክፍል ሸሽተው እንደቆዩና ከከተማው መውጣት ያልቻሉት ደግሞ ለብዙ ቀናቶች ቤታቸውን ዘግተው መሰንበታቸውን ይናገራሉ፡፡

በሰላም ዕጦት ምክንያት ስትታመስ የከረመችው ሻሁራ መከላከያ ገብቶ በማረጋጋቱ ከሰሞኑ አንፃራዊ ሰላም መታየቱን የከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

መንገዶች በኬላዎች ታጥረውና በብዙ ፍተሻዎች ታጅበው ውስን አገልግሎት እየሰጡ እንዳለ፣ ባጃጆች ከከተማው ውስጥ ብቻ ቢሆንም መሥራት መጀመራቸው፣ መብራት አንድ አንድ ጊዜ አየተለቀቀ እንደሆነና፣ ወደ ገጠር ሸሽተው የነበሩ የከተማው ነዋሪዎች መመለስ መጀመራቸው መልካም ዜና መሆኑን አንድ ነዋሪ ጠቁመው፣ ‹‹ያ አስጨናቂ ጊዜ አልፎ አሁን ላይ ሆነን ስናወራ ደስተኞች ነን፣ ነገር ግን ከእኛ በሞት የተለዩንን ስናስብ ደግሞ እጅግ ሐዘንተኞች ነን፤›› ብለዋል።

‹‹አሁን ላይ ሥጋቱ ብዙ የሆነ ሰላም አለ። መከላከያ ከገባ በኋላ አንፃራዊ ሰላም ታይቷል፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው አሁንም ቢሆን ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ከሥጋት ነፃ እንዳልሆነችና ከአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ውጪ ሁሉም መደበኛ ሥራዎች እንዳልተጀመሩ፣ የድሮ ሰላሟ እንደሚመለስ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...