Friday, March 1, 2024

የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት የፈጠረው ቀጣናዊ ውጥረት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ ኅብረት ሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት ረቡዕ ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የኅብረቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አየለ ሊሬ (አምባሳደር) እና የሶማሊያ አቻቸው አብዱላሊ ዋርፋ (አምባሳደር) የየአገሮቻቸውን አቋም ማድመጡን ገልጿል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት ምክር ቤቱ ረቡዕ የተደረገውን ስብሰባ በተመለከተ ሐሙስ ባወጣው መግለጫም፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት ውጥረት በእጅጉ እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡ ጉዳዩ ቀጣናውን ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል በሚል ሥጋት በቅርበት እየተከታተለው መሆኑንም አክሏል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ስለጉዳዩ ያወጡት መግለጫን ተገቢነት ያወሳው የፀጥታና ደኅንነት ምክር ቤቱ፣ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሊከበር እንደሚገባው አስምሮበታል፡፡

የኅብረቱ ፀጥታና ደኅንነት ምክር ቤት ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊያ ለኅብረቱ፣    እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ መርሆዎች ተገዥ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡ ሶማሊያም ሆነች ኢትዮጵያ ጠንካራ ጉርብትናቸውንና ወዳጅነታቸውን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ከማድረግ እንዲቆጠቡም አሳስቧል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በቅርቡ የሶማሊያንና የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲከታተሉና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ፣ የአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ልዑክ የሆኑትን ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን በኃላፊነት መመደባቸውንም መግለጫው በመልካም ዕርምጃነት አወድሷል፡፡  

የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት መግለጫ ሲቀጥልም፣ ኦባሳንጆ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ንግግር እንዲጀመር ጥረት እንዲያደርጉ መመደባቸው ወሳኝ ዕርምጃ ነው ይለዋል፡፡ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት አጥብቆ እንደሚቃወም የገለጸው መግለጫው፣ በሰላም ሊፈታ የሚችል የሁለት ወንድማማች አገሮች ጉዳይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህ መግለጫ በወጣበት ዕለት የራሱን መግለጫ ያወጣው የሶማሊያ መንግሥት ግን ሰላማዊ መፍትሔ የሚለውን ሐሳብ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ አጥብቆ ነው የተቃወመው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ግዛት ጋር ስምምነቱን ስትፈራረም ነው የሶማሊያ ሉዓላዊነት የተጣሰው ሲል የሶማሊያ መንግሥት ጠንካራ አቋም አንፀባርቋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነቱን ካልቀደደችና ውድቅ ካላደረገች በስተቀር ከኢትዮጵያ ጋር ሞቃዲሾ አንዳችም ንግግርም ሆነ ድርድር አይኖራትም በማለት መግለጫው አጠንክሮ ይገልጻል፡፡

የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ማድረጋቸው ይታወሳሉ፡፡ ‹‹ሰውየው የሰሜኑን ጦርነት ለቋጨው ስምምነት መፈረም በጎ ሚና ተጫውተዋል›› የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ነገር ግን ‹‹ለኢትዮጵያ መንግሥት ያጋደለ አቋም ያላቸው ናቸው›› በሚል የሚተቿቸው እንዳሉም ይታወቃል፡፡ እኚህ ዲፕሎማት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ለተፈጠረው ችግር ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ መመደባቸው፣ ችግር እየፈጠረ ካለው ቀጣናዊ ቀውስና የደኅንነት ሥጋት አንፃር የሒደቱን ውጤታማነት የተጠራጠሩ ወገኖች ጉዳዩን እየተቃወሙ ነው፡፡

ቀጣናዊው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ማኅበር (ኢጋድ) ለዚሁ ጉዳይ መፍትሔ ለማፈላለግ አስቸኳይ ጉባዔ በዑጋንዳ በጠራበት ወቅት፣ የፀጥታ ምክር ቤቱ ኦባሳንጆን መመደቡ አስፈላጊነቱ ያልታያቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ኢጋድ የጠራው ስብሰባም ቢሆን የሱዳንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደማይካፈሉበት በግልጽ ይፋ ባደረጉበት ሁኔታ የሚደረግ መሆኑን የጠቀሱ ተቺዎች፣ ጉዳዩ በቀላሉ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ሊመጣ እንደማይችል ነው ሥጋታቸውን እየገለጹ የሚገኘው፡፡

ያም ቢሆን ግን ‹‹የኢትዮጵያና የሶማሊያ ውጥረት አሳስቦናል›› የሚሉ ወገኖች ለዚሁ አሳሳቢ ላሉት ጉዳይ ሊመክሩ ወኪሎቻቸውን ወደ ኡጋንዳ ካምፓላ ሲልኩ ታይተዋል፡፡ አሜሪካም ከእነዚህ አንዷ ስትሆን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኳን ማይክ ሐመርን (አምባሳደር) ወደ ኢጋድ ስብሰባ ልካለች፡፡ ስምንት አባላት ያሉት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ያሰባሰበው ኢጋድ በኡጋንዳ ካምፓላ ስብሰባው የሱዳንና የኢትዮጵያን ጉዳይ አጀንዳው አድርጓል፡፡ ኢጋድም የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የነፃነት አንድነት እንዲከበር በመጠየቅ፣ ሁለቱ አገሮች ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ብሏል፡፡       

ያም ሆነ ይህ ሶማሊያውያኑ በሰሞኑ ጉዳይ ፍፁም ያመረሩ መሆናቸውን ደጋግመው እያንፀባረቁ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ ወደ ሀርጌሳ ይበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሶማሊያ ባለሥልጣናት አልተፈቀደልህም ተብሎ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ መደረጉ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከሉዓላዊ ግዛታችን ሶማሌላንድ ጋር በልዋጩ ዕውቅና የሚሰጥ የባህር በር ስምምነት ተፈራርማለች ባሏት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስከመክፈት ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ ሲዝቱ ነው የከረሙት፡፡

የኢትዮጵያና የሶማሌላንድን ስምምነትን ተከትሎ የተፈጠረው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ በፍጥነት ተቀያያሪ የሆኑ ለውጦችን እያስተናገደ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ድምፅ እያሰሙ ያሉና አለሁበት የሚሉ ኃይሎች ከሩቅም ከቅርብም እየበዙ ናቸው፡፡

የሶማሊያ ፖለቲከኞች ያልተጠበቀ ባይሆንም እጅግ የተጋነነ ሊባል የሚችል ቁጣና አፀፋ ታክሎበት የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ብዙ ዓይነት ግብረ መልሶችን እያስተናገደ ነው የሚገኘው፡፡ የመግባቢያ ስምምነቱ ሶማሌላንድ በኤደን ባህረ ሰላጤ የ20 ኪሎ ሜትር ጠረፍ ለወደብና ለባህር ኃይል መጠቀሚያነት ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የተስማማችበት ሲሆን፣ በምላሹ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ይፋዊ የሉዓላዊነት ዕውቅና ለመስጠት የተስማማችበት እንደሆነ ሲነገር ሰንብቷል፡፡

ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች አገሮች ዕውቅና ላልተሰጣት ሶማሌላንድ ኢመደበኛ የሆነ ዕውቅና ሲሰጡና ከሀርጌሳ ጋር ግንኙነታቸውን በንግድና በኢኮኖሚ ሲያጠናክሩ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዕውቅና ያልተሰጣትን ሶማሌላንድ ወደቦች ስትጠቀም መቆየቷ የአደባባይ ሚስጥር ሲሆን፣ ብዙ አገሮች ይህንን ዓይነት የወደብ አገልግሎት ጥቅም ሲያገኙ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

አዲሱ ስምምነት ነገሩን በይፋ ዕወቁልኝ ከማለት በዘለለ፣ ‹‹ምን የተለየ ነገር ይዞ ስለመጣ ነው እንዲህ የዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበው?›› የሚለው ያነጋግራል፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ (የባህር በር) ለማግኘት ለሶማሌላንድ ዕውቅና እስከ መስጠት ድረስ እንደምትሄድ ከማሳወቋ ውጪ፣ የተለየ ድንገቴ የሆነ ክስተት የመግባቢያ ስምምነቱ ይዞ መምጣቱን የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ በርካታ አገሮች ከሶማሌላንድ ጋር ግንኙነት መፍጠራቸውን ዘርዝሯል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እውነቶች ሕጋዊ ዕውቅናን ለሶማሌላንድ አጎናፅጽፈዋል ባይባልም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት አገሮች ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ያላቸው ሲሆን፣ ኬንያና ግብፅን ጨምሮ ስድስት አገሮች የተወካይ ጽሕፈት ቤቶች ከፍተው በዚህች ራሷን አገር ብላ ባወጀች አገር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አድርጌ መርጪያቸዋለሁ ካለቻቸው ፕሬዚዳንት ጋር እየተነጋገሩና ውል እያሰሩ ግንኙነት ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ በእርግጥ የእነዚህን ጽሕፈት ቤቶች መከፈት ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው ስትል በተደጋጋሚ አምርራ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስታወግዝም ይታያል፤›› በማለት ነው የኢዜማ መግለጫ ያተተው፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ስምምነት መፈረማቸው በእጅጉ ያስቆጣቸው የሶማሊያ ባለሥልጣናት ግን ለኢትዮጵያ አፀፋ ለመስጠት ብዙ ርቀት ሲሄዱ ነው የታየው፡፡ ሶማሊያውያን ኢትዮጵያ ላይ ፊት ለፊት ከመዛትና ከመፎከር አልፈው ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እስከማበር ያሉ ዕርምጃዎችን ሲወስዱ ታይተዋል፡፡ ለጦርነት ዝግጁ ነን ከሚሉ የጦርነት ጉሰማዎች ጀምሮ፣ በሶማሊያ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የጥቃት ዘመቻ እስከ ማፋፋም ያሉ አደጋዎችን ሲፈጥሩ ታይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ሶማሊያውያኑ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ኢትዮጵያ እንድትወገዝ ያላሰለሰ የዲፕሎማሲ ዘመቻ እያካሄዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቀናቃኝ የሆነችው የግብፅ ባለሥልጣናት ጉዳዩን ዓረባዊ ገጽታ እንዲላበስ ከፍተኛ ጥረት ጀምረዋል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት ዓረቦች የተባበረ ዕርምጃ በኢትዮጵያ ላይ እንዲወስዱ መጠየቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ሶማሊያዊያኑ መቆጣታቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ቢሆንም እንኳን፣ እስካሁን እየታየ ባለው ሁኔታ ከኤክስ (ከትዊተር) እና ሌሎች ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻዎች አንስቶ በዚህ ልክ ኢትዮጵያ ላይ ይረባረባሉ ብሎ ያሰቡ ብዙም አልነበሩም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ፖሊሲን ከኢትዮጵያ ዜጎች በማይለይ መንገድ የጠላትነት ዘመቻ በሶማሊያውያኑ ዘንድ መጠናከሩ ከምን የመጣ እንደሆነ ብዙዎች እየጠየቁ ነው፡፡

ሶማሊያውያኑ አገራቸው በእግሯ እንድትቆም ፖሊስና ወታደር ከማሠልጠን ጀምሮ ለተማሪዎቿ የነፃ ትምህርት ዕድል እስከ መስጠት ድረስ ብዙ ዕገዛ ላደረገችው ኢትዮጵያ፣ እያሳዩት ያሉት ከባድ ነቀፌታ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትዝብት የፈጠረ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በሶማሊያ አዝምታ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የደምና አጥንት ዋጋ መክፈሏ፣ በዚህ ፍጥነት በሶማሊያውያኑ ዘንድ መረሳቱ ለኢትዮጵያውያኑ አስገራሚ ነበር፡፡ ሶማሊያ በባህልም፣ በታሪክም ሆነ በሕዝቦች ማንነት ጥብቅ ቁርኝት ካላት ከኢትዮጵያ ይልቅ እንደ ግብፅ ያሉ የኢትዮጵያ ተቀናቃኞችን ስታማትር መታየቷ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከካይሮ እስከ አስመራ በመመላለስና የዓረብ ሊግን ጠንካራ ዕርምጃ በኢትዮጵያ ላይ እንዲወስድ በመጠየቅ፣ ለኢትዮጵያ ጉርብትና ደንታ እንደሌላቸው ስሜታዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሲገቡ መታየታቸው ብዙዎችን ያስገረመ ነበር፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ የሰጠው ግብረ መልስም ቢሆን ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር እየሆነ ነው፡፡ ቻይና ባለፈው ሳምንት ባወጣችው መግለጫ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም አስታውቃለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጉዳዩ አሳስቦኛል የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የዓረብ ሊግና ግብፅ ብቻ ሳይሆኑ ኩዌትን ጨምሮ የተለያዩ ዓረብ አገሮች በተናጠል ኢትዮጵያን የሚቃወም አቋም እያንፀባረቁ ይገኛል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶሃን የአገራቸው ፓርላማ በቀይ ባህርና በአደን ባህረ ሰላጤ ላለፉት 13 ዓመታት ተልዕኮ እየተወጣ ያለውን የቱርክ ባህር ኃይል ቆይታን በአንድ ዓመት እንዲያራዝም የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያፀድቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ የቱርክ ባህር ኃይል በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በኤደን ባህረ ሰላጤ ያለው ቀጣናዊ ሁኔታ የቱርክን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በቀጥታ የሚነካ በመሆኑ፣ ተልዕኮው እንዲራዘምና በቀጣናው ሠፍሮ እንዲቆይ የቱርክ መንግሥት ፍላጎቱን ግልጽ አድርጓል፡፡ ድሮን ለኢትዮጵያ በማስታጠቅ ወዳጅ አገር ስትባል የቆየችው ቱርክ፣ የሶማሊያና የኢትዮጵያ ውዝግብ በከረረ ማግሥት ይህን መወሰኗ አግራሞት ፈጥሯል፡፡ 

የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ከገለጹ የከራረሙ ሲሆን፣ አሜሪካም ቢሆን ሁኔታው ፈታኝና አሥጊ እንደሆነ አሳውቃለች፡፡

ከሰሞኑ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ስትራቴጂካዊ ኮሙዩኒኬሽን አስተባባሪ አድሚራል ጆን ኪርቢ፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ውጥረት ከአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በቀጣናው ማለትም በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ ሰላጤ የየመን ሁቲ አማፂያን ጥቃት በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት፣ እንዲሁም የሶማሊያው ሽብር ቡድን አልሸባብ ሥጋት ገና ባልተቀረፈበት ጊዜ ሶማሊያና ኢትዮጵያ መካረር ውስጥ መግባታቸው አጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድን ብሎም ዓለምን አደጋ ላይ የሚጥል ቀውስ እንደሆነ ሥጋታቸውን በግልጽ ተናግረዋል፡፡

ይህን ሁሉ ዓለም አቀፍ አፀፋ እያስተናገደ የሚገኘው የኢትዮ ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ የተፈጠረው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ፍጥጫ፣ ሐሙስ በኡጋንዳ ካምፓላ በተጠራ የኢጋድ ስብሰባ ላይም ዋና አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ በዚያው ዕለት  ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር)፣ በተለየ ሁኔታ ለዓረብ ሊግና ለግብፆች መግለጫ አፀፋ ሰጥተዋል፡፡

‹‹የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የደኅንነት ሥጋት ሆናለች ብለው መናገራቸው ቧልት ነው፡፡ የዓረብ ሊግ ሌሎች የዓለም አገሮች በቀይ ባህር ቀጣና ሲስፋፉና በኤደን ባህረ ሰላጤ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ከሩቅ መጥተው ጭምር ሲጠናከሩ አንዲት ነገር ትንፍሽ ብሎ አያውቅም፡፡ ይህ ድርጅት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ተስማማች ብሎ ተቃውሞ ለማሰማት የሞራል ድፍረቱ የለውም፡፡ የዓረብ ሊግ ከተቋቋመበት ዓላማ በተቃራኒ መቆሙንና በማን እየተዘወረ እንዳለም ይታወቃል፤›› በማለት ነበር የውጭ ኃይሎችን በተለይም የግብፅና የዓረብ ሊግን አቋም አጥብቀው የተቹት፡፡

መለስ (አምባሳደር) ከሰጡት መግለጫ በዘለለ፣ በወቅቱ ያለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴና ምላሽ የሚጠይቅ ስለመሆኑ ብዙዎች ሐሳብ እየሰጡ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የገባችባቸውን ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ አጣብቂኞች በዲፕሎማሲው ሜዳ በጠንካራ ሁኔታ ተፋልማ ጥቅሞቿን ማስጠበቅ እንደቻለችው ሁሉ፣ አሁንም ይህንን መድገም እንዳለባት የሚያሳሰቡ በርካቶች ናቸው፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት አገሪቱ የገጠሟትን ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎች ከዳያስፖራው እስከ አገር ቤት ሕዝብ አስተባብራ ስትመክት ቆይታለች፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተለይም በምዕራባዊያኑ ዘንድ የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ግፊት የተቋቋመችው በተመሳሳይ ሁኔታ ሕዝቡን በማስተባበር በተሠሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘመቻዎች እንደሆነም ያወሳሉ፡፡

አሁን በመግባቢያ ስምምነቱ የተነሳ የተፈጠረውን ከባድ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ርብርብም ቢሆን አገሪቱ መቋቋም የምትችለው በዚህ መንገድ መሆኑን ነው እነዚህ ወገኖች የሚመክሩት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ መንግሥት ስለስምምነቱና በባህር በር ጉዳይ ስለሚከተለው ፖሊሲ በግልጽነት ለሕዝቡ በሚገባው ልክ ማብራራትና የጋራ አገራዊ መግባባት በጉዳዩ ላይ መፍጠር ሲቻል እንደሆነ እነዚህ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ስለወደብ ስምምነቱ ውሳኔውን ያሳለፈበትን ሒደትና መነሻ ምክንያት ተዓማኒነት ባለው መንገድ ሀቁን በማስቀመጥ ብዥታውን ማጥራትና የጋራ አገራዊ መተማመን መፍጠር ይጠበቅበታል ሲሉም ያክላሉ፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) በሚዲያ ስለጉዳዩ ከሰጡት ማብራሪያ በዘለለ ከሚዲያ አመራሮች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም ከዲፕሎማቶች ጋር የተለያዩ ዝግ ስብሰባዎችን አድርገዋል፡፡ እስካሁን እንደታየው ከሆነ ግን የወደብ ስምምነቱ ጉዳይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ የጠራ መረዳት እንዲፈጠር በቂ ጥረት አልተደረገም የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያውያን ወደ አንድ መሰባሰብም ሆነ በጋራ መቆም የሚችሉት ጉዳዩ ምን ሒደትን ታልፎ እንደመጣ በግልጽ ሲነገር በመሆኑ፣ መንግሥት ይህንኑ ማድረግ እንዳለበት ነው የሚያሳስቡት፡፡

ባለፈው ሳምንት ከሬድዋን (አምባሳደር) ጋር ውይይት ያደረጉ የፓርቲዎች ተወካዮችም ቢሆኑ ይህንኑ ነበር ለሪፖርተር ያንፀባረቁት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ መንግሥት ወደ መግባቢያ ስምምነቱ የገባበትን ሁኔታ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሰፊው ማብራራቱን አውስተዋል፡፡ ‹‹ውስጣዊ ሰላማችንን እንገንባ፣ ውስጣዊ አንድነታችንን እናጠናክር፣ ከዚህ ውጪ የባህር በር ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነውና አገሪቱ የባህር በር ማግኘቷን እንደግፋለን፤›› የሚል መግባባት በውይይቱ ተፈጥሮ ነው የተለያየነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁንም ቢሆኑ፣ ፓርቲዎቹ በአገር ቤት መቅደም ያለበት ሥራ ብዙ መሆኑንና በሰላም፣ በመረጋጋትና በኢኮኖሚ ረገድ በመንግሥት ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መከናወን እንዳለባቸው ግፊት ከማድረግ በዘለለ የባህር በር ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን መደገፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ፖለቲከኞች ቢሆን በተመሳሳይ መንገድ የባህር በር ማግኘት ጉዳይን እንደሚደግፉ በተደጋጋሚ አንፀባርቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በርካቶች ከዚሁ ጎን ለጎን መንግሥት በተያያዘው መንገድ በጥንቃቄ እንዲራመድ ከማሳሰብ በዘለለ፣ በጉዳዩ ላይ ለኢትዮጵያውያን የበለጠ ግልጽነት እንዲኖር በመወትወት ላይ ናቸው፡፡

ሐሙስ ዕለት  በተናጠል መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር ሐሳብ አንስቷል፡፡ ‹‹ከዓለም አቀፍ ሕግጋትና ከታሪክ አንፃር አገራችን ራሷ ባለቤት ሆና የምታስተዳድረው (Sovereign Ownership) የባህር በርና መተላለፍያ (ኮሪዶር) የማግኘት መብት ሊኖራት እንደሚገባ ኢዜማ ያምናል፤›› የሚለው የኢዜማ መግለጫ ይህንን በሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ መስመር ብቻ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ተነስቶም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፍጥጫ የተመለከቱ ነጥቦችን የሚያነሳው መግለጫው፣ መንግሥት ይህንን መብት ለማረጋገጥ የሄደበትን መንገድ በግልጽ ይፋ እንዲያደርግ ይጠይቃል፡፡

‹‹ለጎረቤት አገሮች ጉዳዩን በበቂ ሁኔታ እንዲያውቁ መደረጉን መንግሥት ቢገልጽም፣ ጉዳዩ ከፍ ያለ የብሔራዊ ጥቅም በመሆኑ ዜጎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስምምነቱን በተመለከተ ከብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የፖለቲካ አንድምታ ካላቸውና ብዥታ ከሚፈጥሩ ዘገባዎች የመንግሥት ሚዲያዎች እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡ በዓለም አቀፍ ቦታዎችም በበቂ ሁኔታ ዕውቀትን፣ ብቃትንና ወጥነትን በተላበሰ መንገድ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሠራ ጥሪ እናቀርባለን።

በተጨማሪም መንግሥት ሌሎች አማራጭ የባህር በሮችን ለመጠቀም ከሌሎች አገሮችም ጋር ውይይት ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም ክልሎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስ የፌዴራል ሥልጣን የሆነውን የውጭ ግንኙነት ጉዳይን በቀጥታ ሲፈጽሙ የሚስተዋል ሲሆን፣ ይህ በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ ይዞ የሚመጣው ችግር የከፋ ሊሆን ስለሚችል በቶሎ ዕርምት እንዲደረግ እንጠይቃለን፤›› በማለት ነው ኢዜማ መግለጫውን ያጠቃለለው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -