Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዋጅ የተመሠረተን ተቋም ገሸሽ አድርጎ ከፎረምና ማኅበር ጋር መሥራት ለምን አስፈለገ?

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ዘርፉ ለአገር ያለውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ለማሳየት ከተፈለገ ያሉበትን ጫናዎች ማቃለልና በትክክል የግሉ ዘርፍ አጋርነት በሚባለው ልክ ሊደገፍ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሰሞኑን በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እንዳመለከቱት፣ የግል ዘርፉ ብዙ ችግሮች ያሉበት ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ሊሻሻሉ ይገባል ያሉትን የመፍትሔ ሐሳቦችም አመላክተዋል፡፡

እንደ አንድ በአዋጅ የተቋቋመ ንግድ ምክር ቤት ተገቢውን ቦታ ሊያገኝ ይገባው እንደነበር የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ አንዳንድ አሠራሮች ግን ይህንን እንደማያመላክቱ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ማስመዝገብ የምንፈልገው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የወጣው በፓርላማ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱን አዋጅ በፓርላማ ማውጣት ያስፈለገው የግል ዘርፉ በተደራጀ መንገድ መምጣት ስላለበትና አንድ ንግድ ምክር ቤት ኖሮ መምጣት ስላለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለእኛ ነጋዴዎች መንግሥት በጀት አይመድብልንም፡፡ እኛ ከአባላት በማሰባሰብ መዋጮ የምንተዳደር እንጂ መንግሥት በጀት መድቦልን አይደለም፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ነገር ግን መንግሥት የንግድ ምክር ቤትን መቋቋም በአዋጅ ማፅደቅ ያስፈለገበት ምክንያት፣ የንግድ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር ለመሥራት በተደራጀ መንገድ መምጣት ስላለበት ቢሆንም፣ የማይታየው ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ‹‹በፓርላማ የወጣን ሕግ ራሱ አለመቀበል የሚያሳየንም ይህንን ነው›› በማለት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይሠራ ነበር ያሉትን ያልተገባ አሠራር ኮንነዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፓርላማ የተቋቋመውን ንግድ ምክር ቤት ትቶ ‹‹የነጋዴዎች ፎረም ህዳሴ ነጋዴዎች ማኅበር›› እየተባለ፣ ኢንፎርማሊ ከተቋቋሙ ማኅበራት ጋር አንዳንዴም የፖለቲካ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡

ይህ ከሆነ ንግድ ምክር ቤቱ በፓርላማ ደረጃ ለምን ተቋቋመ? የሚል ጥያቄ በማንሳትም፣ ከኢንፎርማል ማኅበራት ጋር ሲካሄዱ ነበሩ ያሉትን ግንኙነቶች ተችተዋል፡፡

ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር የሚሠሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ባለማወቅ የሚድረጉ ነገሮች እንዳሉም አብራርተዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤት እንዲህ ባለው አሠራር ላይ ያለውን ሚና አውቀን ትልቅ ሥራ መሥራት እንዳለብን ዕውቅና እንዲሰጥ እፈልጋለሁ፡፡

የግል ዘርፉ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም በማለት እንደ ማሳያ የጠቀሱት ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ ከ20 ዓመታት በላይ እንዲሻሻል ሲጠየቅ የነበረው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እስካሁን ተሻሽሎ ሥራ ላይ ሊውል አለመቻሉን ነው፡፡

የንግድ ምክር ቤት አዋጅ መጀመርያ በ1939 ዓ.ም. ቀጥሎ በ1970 ዓ.ም. ከዚያም በ1995 ዓ.ም. ተሻሽሎ መውጣቱን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በ1995 የወጣው አዋጅ ገና ሲወጣ ጀምሮ የንግዱ ኅብረተሰብ ያልተስማማበትና ያልተቀበለው አዋጅ ነው፡፡

የንግድ ማኅበረሰቡ በዚህ አዋጅ አንደራጅም ብሎ በ1995 የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ መሆን የጀመረው በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት ከዚህ ቀደም የነበሩ ፕሬዚዳንቶችና ቦርዶች አዋጁን አስጠንተው ሊሻሻልልን ይገባል ብለው ለንግድ ሚኒስቴር አቅርበዋል፡፡

ሃያ ዓመት ሙሉ ግን መንግሥት አዋጁን ለማሻሻል በፍጹም አልፈቀደም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት እርሳቸው የሚመሩት ቦርድ አዋጁ እንዲሻሻል ብዙ ጥረቶች ማድረጉንም አስታውሰው ከብዙ ጥረት በኋላ አሁን ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን ይፀድቃል ብለው እንደሚጠብቁ አመልክተዋል፡፡

ይህ የንግድ ምክር ቤት አዋጅን ለማሻሻል ይህንን ያህል ጊዜ መውሰዱ አግባብ እንዳልነበር በማመልከትም፣ ሌሎች አዋጆችን ለማሻሻል ግን ይህንን ያህል ጊዜ አለመወሰዱንም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በሁለት ወር የተሻሻለ አዋጅ አለ፡፡ በሁለት ዓመትና በአንድ ዓመት የተሻሻሉ አዋጆችም እንዳሉ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሃያ ዓመት ሙሉ ንግድ ምክር ቤቱ ይሻሻልልኝ፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ያሉበት አዋጅ ነው ብሎ አስጠንቶና አቅርቦ ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱ ለዘርፉ የተሰጠውን ግምት አመላካች እንደሆነ ጠንከር ባለ መንገድ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የተበጣጠሰ የግል ዘርፍ እንዲኖር መፈለግ የለበትም፡፡ ያሉት መላኩ (ኢንጂነር)፣ ጠንካራ የግል ዘርፍ እንዲኖር መንግሥት ሊሠራ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ከ120 በላይ ማኅበራት አሉ፡፡ እያንዳንዱ ማኅበራት በተቋቋሙበት ዓላማ መሠረት እየሠሩ ነው፡፡ ነገር ግን ጠንካራ ሆነው በተለይ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲሠራ መንግሥት ያወጣውን አዋጅ ራሱ እንዲያከብርም ጠይቀዋል፡፡

ኢንዱስትሪው ላይ ዕውቀትም ልምድም ያላቸው ሰዎች አሉና ዕውቀታቸውና ልምዳቸውን ማካፈል የሚችሉበትና የሚያካፍሉበትን አሠራር መፍጠር ይኖርብናል፡፡

ከቢዝነስ አኳያ ደግሞ ብዙ ጊዜ የግል ቢዝነሶች ከመንግሥት ቢዝነሶች ጋር የመፎካከር ነገር ይታያል፡፡ በዚህ ፉክክር የግል ቢዝነሶች አንዳንዴ የመቀጨጭ፣ የመንግሥት ተቋማት ሥራ የሚወስዱበት ሁኔታም አለ፡፡

የግል ዘርፉ ማደግ አለበት ተብሎ እየተነገረ አብዛኛውን ድርሻ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እየወሰዱ መሆኑንም ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ እንዲህ ያሉት ሁኔታዎችም ሊሻሻሉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ከብድር አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለውን የለውጥ ክፍተት በምሳሌነት የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መመልከት ይቻላል ብለዋል፡፡ ስንት በመቶ ለግል ዘርፉ ብድር እንደተሰጠ፣ ስንት ዘርፉ ለልማት ድርጅቶች እንደተሰጠ መመልከት ይቻላል ብልዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን በመድፈን የግል ዘርፉን ማሳደግና የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲቻል ማበርታታት ይገባል ብለዋል፡፡

የግሉ ዘርፉን ለማሳደግ ሊወሰዱ ይገባቸዋል ብለው የጠቀሱት ሌላው ዕርምጃ ደግሞ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተለይ የግል ዘርፉ እንዲያድግ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መበረታታት እንዳለባቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ኅብረተሰቡም የአገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀም  በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡

‹‹120 ሚሊዮን ሕዝብ ያለን በመሆኑ ይህ ሕዝብ የገበያ ዕድል ነው፤›› ያሉት መላኩ (ኢንጂነር)፣ ነገር ግን 120 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ የውጭ ምርት ጥገኛ ከሆነና የአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀም ካልቻለ፣ የግል ዘርፉ ሊያድግ አይችልም ብለዋል፡፡

‹‹120 ሚሊዮን ሕዝብ የውጭ አገር ምርቶችን የሚያማትር ከሆነ እጆቹ ላይ ያለው ዕድል እያመለጠው ነው›› ያሉት መላኩ (ኢንጂነር)፣ ስለዚህ የኅብረተሰባችንን ግንዛቤ በማዳበር የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀም የሚችልበትን መንገድ ስንፈጥር የሥራ ዕድልን መፍጠር ያስችላል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንም በመተካትም ሆነ በአጠቃላይ ለጥቅል አገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትም ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ስለሚቻል፣ በተቻለ መጠን የአገር ውስጥ ምርትን ለመጠቀም የሚያስችል ፖሊሲ ጭምር ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል፡፡

ለምሳሌ እዚህ አገር መመረት የሚችሉ ምርቶችን ከውጭ የሚያስመጡ ኩባንያዎችን ማገድ አንድ መፍትሔ መሆኑም አስረድተዋል፡፡ የውጭ ኮንትራክቶች አንድ ሥራ በውጭ ምንዛሪ ወስደው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን በንዑስ ተቋራጭነት በብር ከፍለው እያሠሩ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ብዙ ጉዳዮች መስተካከል የሚችሉት በፖሊሲ ስለሆነ፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ጠቀሜታውን በተለያዩ ምሳሌዎች ጭምር የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች እንዳይበረታቱ መሥራት አስፈላጊነትንም አመልክተዋል፡፡

ለምሳሌ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሊያደግና ገበያ ሊያገኝ የሚችለው ከውጭ የሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶችን በማስቀረት እዚህ ያለው ሲበረታታ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ብዙ ሊሠራ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በማጠቃለያቸውም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ የግል ዘርፉ ለዕድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

‹‹መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ከመወቃቀስና እጅ ከመጠቋቆም ወጥተው ለአገር ዕድገት መሠራት እንዳለበት እናምናለን›› ያሉት መላኩ (ኢንጂነር)፣ እንዲህ ያለው አሠራር ከፖለቲካ አመለካከት ወጥቶ ሥራ ላይ ብቻ ካተኮርን ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለው እንደሚያምኑ በመናገር ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የግል ዘርፉ የቴክኒክና ሙያዊ ሥልጠና አስተዳደርን በተመለከተ ውይይት በተደረገበት በዕለቱ ፕሮግራም ላይ፣ የቴክኒክና ሙያዊ ሥልጠናና ከግል ዘርፍ ጋር ያለውን በተመለከተ ያሉ ችግሮች ላይ ምክክር የተደረገባቸው ሲሆን፣ ይህንን ችግር የሚፈታ አዋጅ ግን በዕለቱ መውጣቱ ታውቋል፡፡ ይህ አዋጅ የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኞች በግል ዘርፉ ሥልጠና ሲወሰዱ መሆን ያለበትን አሠራር የሚደነግግ ሲሆን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸውንም ትስስር የሚያመላክት ነው፡፡ አዋጁ በዕለቱ የደረሳቸው መሆኑን የገለጹት መላኩ (ኢንጂነር)፣ አዋጁ መውጣቱ ትልቅ ነገር መሆኑን አስፈላጊነቱንም የሚያምኑበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ምክክር አልተደረገም፡፡ ምክር ብታቸው የታክስ ሕግ ሲወጣ፣ የንግድ ሕግ ሲወጣ፣ የመሬት ሕግ ሲወጣ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ረቂቁ ተልኮልን ዓይተን የግል ዘርፉ ምልከታን ሁሌ ሲያቀርቡ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ስለዚህ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎችም የግል ዘርፉ ተሳትፎ ሊኖርው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በዚህ አዋጅ ማስፈጸሚያ መመርያዎች ላይ ግን ለግል ዘርፉ በሚመች ሁኔታ እንዲወጣ ጥረት መደረግ እንደሚገባውም ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች