Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አንድ ዓመት ያህል ዕርዳታ ለተከለከለ ሕዝብ 20 በመቶ ዕርዳታ መጀመር ማለት የሞት ፍርድ ነው›› ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር

የትግራይ ክልል የገጠመው ድርቅና ረሃብ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ችግሩ ከ1977 ዓ.ም. የድርቅና የረሃብ አደጋ ጋር ተነፃፅሮ መቅረቡን ክፉኛ ተቃውሞታል፡፡ ሪፖርተር በትግራይ ክልል የተለያዩ ቀበሌዎች ተገኝቶ ችግሩን በአካል ለመመልከት የሞከረ ሲሆን፣ ይህንንም በተከታታይ ዘገባዎቹ ለሕዝብ ማድረሱ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ ዮናስ አማረ ከአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነሩ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተርበእናንተ በኩል ባለው ግምገማ የድርቁ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር):- መስከረም አካባቢ የነበረው ሁኔታ ከባድ እንደነበር በትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ በተደረገው ግምገማ ታውቋል፡፡ በሦስት ዞኖች በተለይም በደቡብ ዞን፣ በደቡብ ምሥራቅና በምሥራቅ ዞን የዝናብ እጥረት እንደነበር በጥናት ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተራድኦዎችን ጨምሮ የትግራይ ክልል መንግሥትና የክልሉ አመራሮች በተገኙበት የችግሩ ሁኔታ ተገምግሞ ነበር፡፡ በትግራይ ድርቅ መከሰቱ በዚያ ግምገማ ተረጋግጦ ነበር፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ በ141,575 ሔክታር መሬት የሚገኙ 144,384 ቤተሰቦች ለድርቅ መጋለጣቸው የታወቀ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ወደ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ችግር እንደገጠማቸው ታውቆ ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥት ባለበት፣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን ጨምሮ የየክልሎቹ የአደጋ ሥጋትና ግብርና ቢሮዎች በተሳተፉበት በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ምክር ቤትም ሁኔታውን ገምግሞታል፡፡ በፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሪፖርት ቀርቦ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ተገምግሞ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በትግራይ ድርቅ ብቻ አልነበረም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ውርጭና በረዶ፣ አንበጣና ተባይም ማጋጠሙን ዓይተናል፡፡ ካሉን ዞኖች በተለይ የደቡብና የምዕራብ ዞኖች በግጭትና በጦርነት የተነሳ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር አይደሉም፡፡ በተለይ ሽሬን ማዕከል ያደረገውና ሰሜን ምዕራብ የሚባለው፣ እንዲሁም አክሱምን ማዕከል ያደረገውና ማዕከላዊ ዞን የሚባለው ሥርጭቱ ጥሩ የሆነ ዝናብ በመኸር ወቅት አግኝቶ ነበር፡፡ በእነዚህ ዞኖች የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ ሲጠበቅ ግን ውርጭና በረዶ የተቀላቀለበት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አጋጠመ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዛፍና ቅጠላ ቅጠል የሚበላ፣ እንዲሁም ሰብል የሚያወድም አንበጣና ተባይ አጋጠመን፡፡

በአምስት ዞኖች፣ በ36 ወረዳዎችና በ213 ቀበሌዎች ችግር አጋጥሞናል፡፡ በጣም የከፋና የከፋ በሚል ጉዳቱ በየደረጃው ተለይቷል፡፡ በጦርነቱና ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ 2015/16 በሚባለው የመኸር ወቅት 49 በመቶ ብቻ ነው የታረሰው፡፡ በትግራይ በቀደመው ጊዜ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው የሚታረሰው፡፡ ከሚታረሰው መሬት መካከል ደግሞ ለም ተብለው የተለዩት በደቡብና በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህ መሬቶች 60 በመቶ ነው የሚታረሰውን መሬት የሚሸፍኑት፡፡ ሆኖም በጦርነቱ ምክንያት እነዚህ መሬቶች በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር አይገኙም፡፡ ከታረሰው 49 በመቶ መሬት ደግሞ በድርቅ፣ በዝናብና በተባይ ጉዳት የደረሰበት ከፍተኛ ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥት በተለይ ትምህርት፣ ጤና፣ ውኃና ኢነርጂ፣ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከክልላችን የተለያዩ ቢሮዎች ጋር በጋራ በመሆን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች የተገኙበት ዘርፈ ብዙ የሆነ አጠቃላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ በአምስት ዞኖች፣ በ22 ወረዳዎችና በ27 ቀበሌዎች ጥናት ተደረገ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሁልጊዜው የሚደረግ እንጂ የተለየ ነገር አይደለም፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ክፍተት ምንድነው ተብሎ ይጠናል፡፡ በዚህም የመኸር ምርት ምርታማነቱ 38 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተደረሰበት፡፡ ይህ የፌዴራልም፣ የክልሉም መንግሥታት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተግባቡበት ጥናት ነው፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ የተደረገ ጥናትም ነው፡፡ በዚህ መሠረት አጣዳፊ የሰብዓዊ ረድዔት ካልቀረበ በስተቀር በትግራይ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚከፋ የሚያሳይ ነበር፡፡ ወደ 4.5 ሚሊዮን የትግራይ ሕዝብ አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ያረጋገጠ የጥናት ውጤት ነው የቀረበው፡፡ ወደ 46 ሰዎች የተሳተፉበት ለአንድ ወር የተደረገ ጥልቅ ጥናት ውጤት ነው ግኝቱ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ወደ አንድ ሚሊዮን ተፈናቃዮች በጦርነቱ የተነሳ በካምፕ ውስጥ አሉ፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ጦርነት የተፈናቀሉ 1.1 ሚሊዮን ዜጎች በየቤተ ክርስቲያኑና በየካምፑ ተጠልለው ነው የሚኖሩት፡፡ ወደ 1.5 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ደግሞ ወደ መኖሪያቸው ተመልሰዋል፡፡ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ሰላም በመምጣቱ ብዙ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡

ሆኖም ዕርዳታ ተሰረቀ በሚል ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ በማቆማቸው የተነሳ ብዙዎች ችግር ላይ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ቤታቸው የተቃጠለ፣ እንስሶቻቸው ሳይቀሩ የተዘረፉና ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ናቸው፡፡ በተለይ የኤርትራ ሠራዊት በገባባቸው አካባቢዎችና አሁንም ባልወጣባቸው ቦታዎች ችግሩ ይሰፋል፡፡ ይህ ሁሉ አስቸኳይ ዕርዳታ ካልደረሰለት ችግሩ እንደሚሰፋ ቀድሞ የታወቀ ነበር፡፡ አሁን ታኅሳስ [ቃለ መጠይቁ የተደረገበት ጊዜ ነው] መገባደጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች በእነዚህ ወቅቶች ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ የምግብ እጥረት አይታይም፡፡ በተለመደው ወቅት በዚህ ጊዜ ብክነትን ነበር የምንቆጣጠረው፡፡ ሆኖም በዚህ ወቅት ብዙዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የማይበላ ነገር የሚበሉና ክፉውን ቀን ለማለፍ የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ድርቅ እንጂ ረሃብ አልተከሰተም የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ በእናንተ በኩል ደግሞ ከ1977 ዓ.ም. የባሰ ረሃብ በትግራይ ክልል መከሰቱን ትገልጻላችሁ፡፡ ይህ ልዩነት ከምን የመጣ ነው?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከሁለት ወር በፊት ነው አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተን ሪፖርት ያቀረብነው፡፡ በየቀኑ ለፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሥራ ሪፖርት እናቀርባለን፣ የግንኙነት ችግር የለብንም፡፡ በቅርቡ ወደ ዚህ መጥተው አምስትና ስድስት ወረዳዎች አይተዋል፡፡ ከሁለት ወር በፊት ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለ ማሪያም (አምባሳደር) ትግራይ መጥተው ተወያይተናል፡፡ በተለይ አፅቢ፣ ፀአዳምባ፣ ሰዋ ሰአሳፅብ፣ ደጋ ሐሙስ፣ ፍሬወይኒ፣ እንደርታ፣ አጉላ አካባቢ ራሳቸው መጥተው አይተዋል፡፡ እሳቸውና ሌሎች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሦስት ሰዎች በጋራ መጥተው ሁኔታው ምን እንደሚመስል አይተዋል፡፡ እኛ የምንሰጣቸው ሪፖርት በተጨባጭ መሬት ላይ አለ፣ የለም የሚለውን ወርደው አይተዋል፡፡ ገበሬዎችን አነጋግረዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የሚሠሩትን በተግባር አይተዋል፡፡ በዚያን ጊዜም አስቸጋሪ ሁኔታ መኖሩን ነበር ራሳቸው የገለጹት፡፡ በትግራይ ክልል ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም፣ ረሃብ እንጂ ሞት የለም የሚል መግለጫ የሚሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱ እንግዲህ በተጨባጭ ያለውን ነገር ካዩ አካላት ምስክርነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እናንተም በተጨባጭ ወርዳችሁ ገጠር አይታችኋል፡፡

ያለው ሁኔታ ፖለቲካዊ ድራማ እንዳልሆነ ተረድታችኋል፡፡ ይህ የህሊና ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ እነሱ ይበሉም አይበሉም እኛ ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ ለኢትዮጵያ መንግሥትም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለዓለም ማኅበረሰብም ጥሪ አቅርበናል፡፡ በምግብ ዕጦት መጥፋት የለብንም የሚል ዓለም አቀፍ ጥሪ አቅርበናል፡፡ ራሳቸው መጥተው ያዩትንና በሪፖርት የቀረበውን ሁኔታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር በጦርነት ማግሥት ሁኔታው መፈጠሩን አንስተው ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አቅጣጫ አስቀምጠውበታል፡፡ ይህ ሲሆን ሁሉም ሚኒስትሮች ነበሩ፣ በሚኒስትር ደረጃ የነበሩም ነበሩ፡፡ ይህን መሰል ሪፖርት የቀረበው ደግሞ በትግራይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ክልሎች በተመለከተ ነው፡፡ በጋራ የተደረገና በሁሉም ክልል የተደረገ በመሆኑ በተጨባጭ ቦታው መጥቶ ያየው አካል ነው ጉዳዩን መመስከር ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ አድርጎላችኋል?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- ፌዴራል መንግሥቱ ሦስት ጊዜ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ አንዴ ለተፈናቃይ ዜጎች ሲሆን 31,078 ኩንታል ዕርዳታ ለ362 ሺሕ ሰዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህ ለተፈናቃች ብቻ ተብሎ ሐምሌና ነሐሴ ላይ የተደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው 126,111 ኩንታል ዕርዳታ ሲሆን ለ745 ሺሕ ሰዎች የተላከ ነው፡፡ የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር መጥተው አይተው ከሄዱ በኋላ የተላከልን ግን 77 ሺሕ ኩንታል ሲሆን ለ466,602 ሰዎች የሚሆን ዕርዳታ ነው፡፡ ይህ ለድርቁ ተብሎ የተላከ ዕርዳታ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለአንድ ወር ቢሆንም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአንድ ወር የሚሆን ዕርዳታ በሦስት ዙሮች አግኝተዋል እንደማለት በመሆኑ፣ ለዚህ የፌዴራል መንግሥት መመሥገን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የበጀት አመዳደብ ጉዳይም ሲነሳ ነበር፡፡ ለዕርዳታ ተብሎ የመጣና የመንግሥት ሀብት በአግባቡ የመዋል ጥያቄ ክልሉ ተነስቶበታል፡፡ ለወታደሮች አውላችኋል የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- ዕርዳታው በሙሉ በቀጥታ ወደ ወረዳዎች ነው የሚሄደው፡፡ የሚነገረው ሐሰት ነው፡፡ ወደ ተፈናቃዮች ነው ቀጥታ የሚሄደው፡፡ ለተፈናቃዮች የመጣው 65 የተፈናቃዮች መርጃ ቦታዎች አሉ ወደዚያ ነው የሚሄደው፡፡ ወታደር የሚባል ወዳለበት የሚሄድ ነገር የለም፡፡ ለድርቅ ተብሎ የመጣው 77,466 ኩንታል ወደ ወረዳዎች ነው የሄደው፡፡ መቀሌ የሚራገፍ ነገር የለም፡፡ መጋዘን ውስጥ ከገባ መጫኛና ማውረጃ የሚባል ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ቀጥታ ወደ ወረዳ ነው የሚላከው፡፡ እኔ የወታደር አመራር አይደለሁም፣ የአደጋ ሥጋት አመራር ባለሙያ ነኝ፡፡ ነገር ግን ሕዝብን ለመርዳት የመጣው ሀብት በሙሉ ወደ ሕዝብ ነው የወረደው፡፡ ዕርዳታ ለወታደር ነው የዋለው የሚባለው ፍፁም ሐሰት ነው፡፡ መኪናዎቹ የራሳቸው፣ ሾፌሮቹም የራሳቸው፣ እኛ የምናደርገው ለየት ያለ ወረዳ ዕርዳታ ያስፈልጋል የሚለውን የመለየት ሥራ ብቻ ነው፡፡ ራሳቸው ወረዳ ድረስ ገብተው ነው የሚያራግፉት፡፡ ዕርዳታ ለጦር እያዋሉ ነው የሚለውን ክስ የፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ይናገራል ብለን አንገምትም፡፡ ኮሚሽኑ ሪፖርት አለው፡፡ ሌላ የመንግሥት አካል የሚለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በፕሪቶሪያ ስምምነት የዕርዳታ ኮሪደር ክፍት እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ዕርዳታ የማቅረቢያ ኮሪዶር ችግር አለ?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- የኮሪዶር ችግር የለም፡፡ የሀብት ችግር ነው ያለው፡፡ በቂ ዕርዳታ  የለም፡፡ ወደ 52 የሚሆኑ ቀበሌዎች ኢሮብ፣ ውሎ፣ ማክዳ፣ ጭላ፣ ባድመ ድረስ ያሉ ቀበሌዎች በኤርትራ ጦር ሥር ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች በቀላሉ የሚደረስባቸው አይደሉም፡፡ በምዕራብና በደቡብ ትግራይ ያለውን ሁኔታም የምታውቁት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዕርዳታ ማድረስ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ እጅ ሥር ባልሆኑ ለምሳሌ በኤርትራ ኃይሎች ሥር ወዳሉ እንደ ኢሮብ ያሉ አካባቢዎች ሰብዓዊ ረድዔት ማን ነው የሚያቀርበው ታዲያ? በእነዚህ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- ለዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችም እንኳ እነዚህ ቦታዎች ገና ተደራሽ አልሆኑም፡፡ ጉልበተኞች የያዟቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት መረጃ የለም፣ ዕርዳታ ቢላክም ቦታው የተወረረ ነው፡፡ ከዚያ የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ፡፡ ለእነሱ ዕርዳታ ይደረጋል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን መንቀሳቀስ የማይችሉ እናቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋዊያንና ሌሎች ጭምር ዕርዳታ በነፃነት የሚደርስበት ዕድል የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል መንግሥት በዚህ ጉዳይ ምን ምላሽ አለው?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- እኔ የሰብዓዊ ረድዔት ጉዳይ ነው የሚመለከተኝ፡፡ ነገር ግን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በንግግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ያም ቢሆን ግን ዕርምጃው በቂ አይደለም፡፡ ወደ 52 ቀበሌዎች በትግራይ ሥር አይደሉም፡፡ ለልማት እንቅስቃሴ ክፍት አይደሉም፡፡ ለዕርዳታም ሆነ ለዓለም አቀፍ ረጂዎች ክፍት አይደሉም፡፡ ይህ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱን በቀጥታ የሚመለከት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት የራሱ ዕቅድ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተጨባጭ ግን በመሬት ላይ ሕዝብ ላይ ብዙ መከራ እየደረሰ ነው የሚገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- በባለሀብቶችና በራስ ተነሳሽነት ዕርዳታ ባሰባሰቡ ለጋሾች አማካይነት ዕርዳታ እየተላከ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ወረዳዎች በእኛ ሥር ነው ዕርዳታው ማለፍ ያለበት የሚል ማስገደጃ ያደርጋሉ ይባላል፡፡ ዕርዳታ የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞችና ለጋሾች በቀጥታ ለተጎጂዎች ዕርዳታ ቢያደርሱ ምንድነው ችግሩ?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አንድ የዕርዳታ ምላሽ አሰጣጥ አስተባባሪ ኮሚቴ አዋቅረዋል፡፡ ይህ ከመንግሥት የተለያዩ አካላት የተዋቀረ ግብረ ኃይል ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ባለሀብቶችን፣ መሠረታዊ ማኅበራትን፣ አርቲስቶችንና ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያስተባበረ ጭምር ነው፡፡ ይህ በክልል ደረጃ የተዋቀረ ዓብይ የዕርዳታ አሰባሰብና አቅርቦት ኮሚቴ ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ያሉበት ነው፡፡ ሕዝቡን እንዴት እናድን በሚል በፕሬዚዳንቱ በአቶ ጌታቸው ረዳ የተመሠረተና የሚመራ ሲሆን፣ የእሳቸው መደበኛ ሥራ ግን ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ በውክልና እኔ ነኝ የምመራው፡፡ አንደኛውና ዋናው ጉዳይ ዕርዳታ ማሰባሰቡንም ሆነ ሥርጭቱን ተገቢ በሆነ መንገድ መምራት አለብን የሚለው ነው፡፡ የትግራይ ባለሀብት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአማራም፣ የኦሮሞም ሆነ የሌላው ሕዝብ ባለሀብት መርዳት አለበት፡፡ ጉዳዩ ለሰብዓዊነት እስከሆነና ሰው መዳን እስካለበት ድረስ ዕርዳታ አሰባሰቡ ሁሉንም አሳታፊ መሆን አለበት፡፡ ሁለተኛው ይህን ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት ነው መምራት ያለበት፡፡ እኛ በፌዴራል መንግሥቱ ሥር ያለን አካል እስከሆንን ድረስ በብሔራዊ ደረጃ ይህን ዓይነት የድርቅና ረሃብ አደጋ መምራት የሚኖርበት ፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያለውን አቅም በመጠቀም ሁሉንም ወገን አስተባብሮ ሕዝቡን ማትረፍ አስፈላጊ በመሆኑ ይህን እያደረግን ነው፡፡ በአዲስ አበባም ኮሚቴ ተቋቁሟል፣ በውጭም አስተባባሪ አለ፡፡ ይህ ሰው በመሆን ወይም በሰብዓዊነት የሚሠራ ሥራ በመሆኑ ሁሉም ሰው በግሉ ዕርዳታ ማድረግ በፍፁም አይከለከልም፡፡

ከዚህ አንፃር አንዳንዶች በግል ዕርዳታ ይዘው ተጎጂዎች ዘንድ ይወስዳሉ፡፡ ነገር ግን ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ የመለየት ሥራ እኛ መሥራት አለብን፡፡ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችንና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ለመለየት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጣችን አስፈላጊ በመሆኑ ነው በዚህ ጉዳይ የምንገባው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ዕርዳታ አምጥቶ፣ ገንዘቡን አምጥቶና ልለግስ ብሎ ተመለስ የሚባል አካል የለም፡፡ በንግድ ባንክ፣ በአንበሳም፣ በወጋገንም ሆነ በሌሎች ባንኮች የዕርዳታ ቋት መሥርተናል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን እህል መጥቶም ሆነ ገንዘብ መጥቶ ማደር የለበትም ብለን በአስቸኳይ ዕርዳታ እንዲዳረስ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ዕርዳታ እያለ ሰው መሞት የለበትም፡፡ ዕርዳታ አሰጣጥና አሰባሰብ ላይ ያላግባብ ችግር እንዳይፈጠርም መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ከእነዚህ ውጪ ግን ችግሩ ተለይቷል፡፡ በዞን፣ በወረዳ፣ በቀበሌና በቤተሰብ ደረጃ ችግሩ ያለበት ደረጃ ተለይቷል፡፡ ስለዚህ ዕርዳታው መጥቶ መቆም የለበትም፡፡ አንዳንድ ባልተገባ ሁኔታ ዕርዳታ አሰባሰብና አሰጣጥ ላይ የተፈጠረ ችግር ካለ ግን እሱን አጥርተን እናርማለን፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ አገር አቀፍ ድጋፍና ርብርብ እንዲያገኝ ምን ያህል ሠርታችኋል?

ገብረ ሕወት (ዶ/ር)፡- ገና አሁን ነው ዕቅድ አውጥተን እንቅስቃሴ እያደረግን ያለነው፡፡ ችግሩ ድርቅ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ወደ ረሃብ አድጓል የሚል ነው የእኛ አቋም፡፡ ምርት እየተሰበሰበ ያለበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ገና አሁን ነው ምን ያህል ተሰበሰበ የሚለው ተሰልቶ የችግሩ ዘርፈ ብዙነት የሚታወቀው፡፡ ይህን ደግሞ አድርገናል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባሉበት የተደረገውና 4.5 ሚሊዮን ዜጎች በትግራይ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ይፋ የሆነው ግምገማ መሠረት ነው፡፡ በትግራይ ደረጃ ዕርዳታ ማሰባሰቡን በሰፊው ጀምረናል፡፡ አሁን በአገር ደረጃ ለመንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአዲስ አበባ ዕቅድ ወጥቶ ዕርዳታ ማስተባበሩ ተጀምሯል፡፡ አሁን ደግሞ በፌዴራል ደረጃ እየተጀመረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እስኪደረግ ታች ያለው ሕዝብ መቆያ አለው? ችግሩ ጊዜ የሚሰጥ ነው?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- መቆያ የለውም፡፡ የሚገኘው ምርት 37 በመቶ ነው ካልን፣ ወደ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ነው የተራበው ካልን ችግሩ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ነገሩ በሥርዓት መመራት ስላለበት ነው ዕቅድ፣ ግብረ ኃይል፣ ኮሚቴ ማስተባበር እየተባለ ያለው እንጂ ጉዳዩ ጊዜ የሚሰጥ ሆኖ አይደለም፡፡ የችግሩ አድማስ መታወቅ ስላለበት ነው ጥናት የተደረገው፡፡ መነሻ ስለሚያስፈልግ ነው ሁኔታው የተገመገመው፡፡ እናንተ ጭምር ታች ሕዝቡ ዘንድ ገብታችሁ በአካል ያያችሁት ችግሩ እንዲህ ነው ተብሎ መጀመሪያ ስለተገለጸ ነው፡፡ በተፈለገው ጊዜ ለኅብረተሰቡ እንደርስለታለን የሚል ነው ሐሳባችን፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምን እየተሠራ ነው? ለምሳሌ ሪፖርተር በገባበት አበርገሌ ወረዳ ለተከዜ ግድብ ቅርብ በሆነ ቦታ ያሉ ሰዎች ሳይቀር ውኃም ሆነ ዓሳ እንዳይጠቀሙ እንደሚከለከሉ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ባለው የውኃ ሀብት ልማት አከናውኖ ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው?

ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ የውስጥ አቅም መገንባት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ድርቅ በየአምስት ዓመት ነበር የሚከሰተው፡፡ አሁን አሁን ግን በየአምስት ዓመቱና በየሦስት ዓመቱ እየመጣ ነው፡፡ ከሕዝብ ቁጥር መብዛት ወይም ከአካባቢ መራቆት ጋር በተገናኘ ሊሆን ይችላል፡፡ ድርቁ እየተመላለሰ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ የአደጋ ቅነሳ ስትራቴጂ በሚባለው ዕቅድ መሠረት 70 በመቶ ክልሎች ራሳቸውን ችለው 30 በመቶ ደግሞ የፌዴራል ድጋፍ እንዲጨመርበት ነው የሚታሰበው፡፡ ይህ የሰው ጉልበት፣ መሬትና ውኃ መገናኘትን የሚጠይቅ ነው፡፡ የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ የጀመራቸው የመስኖ ሥራዎች አሉ፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አንዳንድ ድጋፎችን ይፈልጋል፡፡ የዓለም ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም የሚሰጠውን ድጋፍና ዕርዳታ እያቆመ ነው፡፡ ጥቂቶች 20 በመቶ ዕርዳታ መስጠታቸውን መልሰው ጀምረዋል፡፡ አንድ ዓመት ያህል ዕርዳታ ለተከለከለ ሕዝብ በ20 በመቶ ዕርዳታ መጀመር ማለት የሞት ፍርድ ነው፡፡ ሕዝቡ ተፈናቅሏል፡፡ አልምቶ የሚኖርበት መሬትም በወራሪዎች እጅ ነው ያለው፡፡ ተከዜም ይሁን ሌሎች የመስኖ አቅሞችን በመጠቀም ልማት በማካሄድ ሕዝቡን ማትረፍ አለብን ተብሎ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ክልሉ ውስብስብ ችግር ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በዕርዳታ ያለፈለት አገር የለም በጥረት እንጂ፡፡ ከጦርነት በፊት 700 ሺሕ ሕዝብ ብቻ ነበር ሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበረው፡፡ በአብዛኛው ራሳችንን የቻልን ነበርን፡፡ ጦርነት መጣ፣ ሁሉ ነገር ወደመ፡፡ አሁን ደግሞ ከ77 እስከ 91 በመቶ ሕዝባችን የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ለምሳሌ 17/18 ወራት ደመወዝ አልተከፈለውም፡፡ አንዳንድ መምህራን ደመወዝ ስለማይከፈላቸው ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ የፌዴራል መንግሥት አንዱ ትልቁ ኃላፊነቱ መሆን አለበት፡፡ እኛም ሁልጊዜ ስንዴ ስጡን ብሎ መለመን ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ያለው ፀጋ ምንድነው ብለን ማጥናት አለብን፡፡ ተከዜም ሆነ ሌሎች ሀብቶችን ለይቶ ማልማትና መሥራት አለብን፡፡ ለአንድ ዓመት ክልሉ በከበባ ሥር በነበረ ጊዜ በተፈጠረው ችግር የተነሳ፣ ሕዝቡ በራሱ መንገድ ብዙ የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን ነበር፡፡ መሬት የሌለው ጭምር በጣሳ ተክሎ አትክልት ማልማት ጀምሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ዋናው መፍትሔ የውስጥ አቅም መገንባት ነውና ችግሩን ወደ ዕድል መለወጥ አለበት፡፡ ታች ሕዝቡ ዘንድ የመልማትና የመጠቀም ፍላጎት እያለ ሀብቱን እንዳይጠቀም የሚከለከል እንዳይሆን በደንብ መታየት አለበት፡፡ በራሳችን ቢሮክራሲ የአሠራር ችግር የገጠመው ካለ ወርደን እንፈትሻለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...