Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከሕግ በላይ ለመሆን የማያመች ለውጥ ያስፈልጋል

ከሕግ በላይ ለመሆን የማያመች ለውጥ ያስፈልጋል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሕገወጥነትን ለመግታት፣ በአጠቃላይ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የሚወሰድ ዕርምጃ እንዴት አድርጎ የገዛ ራስንም የሕግ አክባሪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የውኃ ልክ እንደሚያስገምት ብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ምሳሌዎችና ገጠመኞች በሕይወታችን ውስጥ ሐውልት ሆነው ተቀርፀው፣ ተቋቁመውም የቀሩ ብዙ መታሰቢያዎች እናውቃለን፡፡ ዛሬ እነዚህ ትልልቅ የሚባሉ፣ የራሳቸውን ሐውልት ያቋቋሙ ከሚባሉት መካከል ካልሆነ (አይደለም ሊባል ከሚችል)፣ ከአንድ ትንሽ ተራ ነገር ልነሳና የእሱን ጉዳይ በአጭሩ ልተርክና ነገሬን ላስረዳ፡፡፡ ‹‹ዙሪያ ጥምጥም›› የሚባል ዝርዝር ውስጥ የምገባው የሕግ ማስከበር የአገር ሥራ እንዴት ያለ ለዘመናት የተበላሸ፣ የዘቀጠ፣ እያሳሳቀ እልም ያለ ጉልበተኝነትና ሥርዓተ አልበኝነት ውስጥ እንደወረወረን ለማሳየት (ለመሞከር) እንጂ፣ ጥያቄዬን ወይም ጭብጤን በአጭሩ ማዋቀር እችል ነበር፡፡ ወደኋላ ተመልሼ አነሳዋለሁ፡፡

የምተርክላችሁ ስለታርጋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንደተተረጎመው ታርጋ ማለት፣ ‹‹በተሽከርካሪዎች የፊትና የኋላ አካል ላይ ተጽፎ በግልጽ የሚታይ የመለያ ቁጥር›› ነው፡፡ ታርጋ ጣሊያንኛ ነው፡፡ ከራሱ ከመኪና ጋር እንደ ቦሎ (ቦሌ Bollo ማለት የቀረጥ ቴምበር ነው) ከውጭ/ከጣሊያን የመጣ ቃል ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ‹‹ነምበር ፕሌት›› ወይም ‹‹ላይሰንስ ፕሌት›› ይባላል፡፡ የእንግሊዝኛ መዝገባ ቃላት ይህንን በእንግሊዝኛ ሲፈቱት የባለሞተር ተሽከርካሪ መለያ ይሉና የእኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከዘረዘረው በተጨማሪ የመኪናውን፣ የባለሞተር ተሽከርካሪውን የምዝገባ (Registration) ቁጥር የሚያሳይ ብለው ያሟሉታል፡፡ እንግሊዝኛውን መዝገበ ቃላት ‹‹Registration›› ማለት ራሱ ምንድነው? ብትሉት በተራ ቁጥር ከሚዘረዘሩት ከብዙ ትርጉሞቹ መካከል አንዱ ‹‹legal proof for vehicle: a certificate showing that a motor vehicle has been properly registered with a state’s department of motor vehicles ይላል፡፡ በአጭሩ አግባብ ያለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት መኪናው በሚገባ መመዝገቡን የሚያሳይ የምስክር ወረቀት፣ የሕግ ማስረጃ ነው ማለት ነው፡፡ መኪና ሀብት፣ ንብረት ነው፡፡ ሀብት/ንብረት ሁሉ ግን የመመዝገብ ግዴታ የለበትም፡፡ ሕግ በአጠቃላይ፣ በሁሉም አገር የባለቤትነት ማስረጃ እንደሚኖረው የምዝገባ ግዴታ የሚጥለው በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች (ማለትም ቤቶችን) ነው፡፡ የተለዩ፣ እጅግ ሲበዛ ልዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ፋይዳና አንድምታ ያላቸውን የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችንም ሕግ እንዲመዘገቡ ያዛል፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ሕግ መርከቦችን፣ የሲቪል አቪዬሸን ሕጋችን አውሮፕላኖችን፣ የመንገድ ትራንስፖርት ሕጋችን መኪኖችን እንዲመዘግቡ ያዛሉ፣ ያስገድዳሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ታርጋ›› የሚለውን ቃል ያመጣው ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ በእንግሊዞች አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው መኪናን፣ ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪን የሚገዛው የመጀመሪያው ዘመናዊ ሕግ (ተሽከርካሪ መኪና ያለው ሁሉ ያሳውቅ፣ ያስጽፍ ከሚለው ከ1934 ዓ.ም. አዋጅ በኋላ) በ1935 ዓ.ም. የወጣው የትራንስፖርት/የማመላለሻ አዋጅ ቁጥር 35/1935 ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ማንኛውም ባለሞተር ተሽከርካሪ ‹‹… እመዝገብ ገብቶ እንዲጻፍ›› ታዘዘ፡፡ በዚህ ሕግ እንደተደነገገው/ከዚህም በኋላ በሌሎች የአገር ሕጎች የአገር የኢንዱስትሪው ወይም የዘርፉ ወግና ባህል ሆኖ እንደቀጠለው፣ ‹‹የተሽከርካሪው መኪና ዝርዝር እመዝገብ አግብቶ፣ 12 ብር አስከፍሎ ለመኪናው መለያ ምልክት የሚሆኑ ሁለት ሰሌዳዎች በመኪናው ላይ ይለጠፋሉ፡፡ …ተሽከርካሪው መኪና ለመለያ ምልክት የተሰጡት ሰሌዳዎች ባይገኙበት እመዝገብ ላለመግባቱ በቂ ማስረጃ ሆኖ ይቆጠራልና ምርመራ እስኪደረግ ድረስ ተሽከርካሪው መኪና በፖሊስ ተይዞ ይጠየቃል፡፡ …መኪናው እመዝገብ ለመግባቱ ማስረጃውን ማቅረብ ግዴታ ያለበት የመኪናው ባለቤት ነው፡፡›› እናም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፀንተው በቆዩት ሕጎቻችን መሠረትና ፀንተው በቆዩበት ዘመን ሁሉ፣ አሁንም ጭምር መኪና ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪ ተራ የሚንቀሳቀስ ንብረት አይደለም፡፡ አገር፣ መንግሥት ኦፊሲያል መዝገብ ውስጥ ማለትም ባለንብረትነት የሚታወቅበትና ተረጋግጦ የሚቀመጥበት፣ በየዓመቱም (አስፈላጊ ከሆነም ባጠረ ጊዜ ለማስመዝገብ የሚፈልጉ ዝርዝር ነገሮች ሁሉ ተጽፈው የሚቀመጡበት መዝገብ) እንዲገባ የሚፈልግ የተለየ የንብረት ዓይነት ነው፡፡

ባለንብረትነትን በሚገባ ለማሳወቅና በየዓመቱም ለማስመዝገብ የሚቀርቡ ማመልከቻዎች፣ ደብዳቤዎች፣ ፎርሞችና ሌሎች ጽሑፎች በሙሉ እነዚህን ሁሉ የያዙ ፋይሎች፣ ተደራጅተው በቋሚነት የሚኖሩ ኦፊሲያል ሰነዶች ያሉት የንብረት ዓይነት ነው፡፡ ሰሌዳ የዚህ ሁሉ መታወቂያው፣ ምልክቱ ነው፡፡ ሕግ በሚደነግገው መሠረት ኃላፊነት የሚታሰር ቁጥሩ/ሰሌዳው የመኪናው ቋሚ አካሎች ናቸው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ካለው ሕግ ፊት የነበሩ አቻ ሕጎች እንዲያውም የሰሌዳን ቋሚነት ነዋሪ ይሉት ነበር፡፡ ቋሚ ወይም ነዋሪ የመለያ ቁጥር/ሰሌዳ ፀንቶ የሚቆይበትን ዘመን የሚደነግገው ዛሬም ሥራ ላይ ያለው ሕግ ሰሌዳው በሕግ መሠረት እንዲለወጥ ወይም እንዲተካ ካልተደረገ በቀር፣ ተሽከርካሪው እንዲወላልቅ ወይም ጨርሶ በመንገድ ላይ እንዳይንቀሳቀስ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ይቆያል፡፡ ከወላለቀ ወይም ጨርሶ በመንገድ ላይ እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገ በኋላ፣ ወይም የመኪናው መዝገብ ሲሰረዝ የመኪናው ባለቤት ወይም ባለይዞታ ከባለንብረትና መታወቂያ ደብተር ጋር ሰሌዳውንም ይመልሳል፣ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡

አገራችን ውስጥ ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ በሕግ የተቋቋመው ይህ የአገር ባህል ጭምር የሆነ አሠራር በ1956ቱ አቻ ሕግም ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ የ1956ቱን ሕግ ያሻሻለው የ2003 ዓ.ም. ሕግ (ደንብ ቁጥር 208) በ2009 ዓ.ም. በደንብ ቁጥር 395 ሲሻሻል ይሕ ሕግ በተፈጻሚነት ዘመኑ ውስጥ መመስከር የጀመረው እንግዳና ‹‹ጉዳይ›› ነገር አላምርህ ብለውት ይሁን ወይም ‹ከእጅ አይሻል ዶማ› መፍትሔ ለማበጀት በሕጉ ጠቅላላ የጥንቃቄ መርሆዎች (አንቀጽ 5) ድንጋጌ ተሽከርካሪ ማሽከርከር የሚከለክልበት ሁኔታ በሚለው ንዑስ አንቀጽ (8) ውስጥ ማናቸውም አሽከርካሪ የፊትና በኋላ ሰሌዳ የሌለውን ተሽከርካሪ ማሽከርከር የለበትም የሚል ክልከላ በማሻሻያ ጨመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ደኅንነት ደንብ ቁጥር 27/2002 ታርጋ መንቀልን ቅጣት አድርጎ ያቋቋመ ሕግ አውጥቶ፣ ተፈጻሚነቱም ያለ ሃይ ባይ ደርቶ፣ ዛሬ ይህ አሠራር የአገር ዋና ከተማ ሕግ የማስከበሪያ መሣሪያ፣ የ‹‹ቅጣት›› ዓይነት ሆኖ አርፎታል፡፡ ዛሬ በዚህ ምክንያት ፒንሳ/ጉጠትና ካቻ ቢቴ የትራፊክ ፖሊሶቻችን የሚይዙት ‹‹የሚታጠቁት›› ቋሚ የሥራ መገልገያ መሣሪያ ሆኗል፡፡

ይህንን በወቅቱና በጊዜው፣ በትኩስነቱ የሕግ ባለሙያዎችና ኧረ በሕግ ባዮች ‹‹ብለውት ብለውት የተውትን ነገር›› ዛሬ ያስታወሰኝ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በቅርቡ (በቅርቡ ማለት ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ይርቃል) በ2፡00 ሰዓት የምሽት ዜናው ያቀረበልን ዘገባ ነው፡፡ ‹‹ለረዥም ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ሲፈጸም የቆየው የተሽከርካሪ ሰሌዳ መፍታት ቅጣት ሕግን የጣሰ ቅጣት ነው ተባለ›› ብሎ የሚጀምረው የኢቲቪ ዜና አዲስ አበባ ይህንን የተሽከርካሪ ሰሌዳ የመፍታት ቅጣት እየተገበረ የሚገኘው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣ ሕግ ጥሶ እንደሆነም ይነግረናል፡፡ ሕጎችንም የትራፊክ ደንብ ቁጥር 208/2003 እና ደንብ ቁጥር 395/2009 መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡ የኢቲቪ ዜና ዝርዝሩ ውስጥ ሲገባም፣ ‹‹የአዲስ አበባ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የተሽከርካሪ ሰሌዳ መፍታት የዕለት ሥራቸው አካል መሆኑን፣ ‹‹የፊትም የኋላም ሰሌዳ እንደሚፈቱ ደግሞ ኢቲቪ ለዚህ ባደረገው ቅኝትና ቅጣቱ ከደረሰባቸው ግለሰቦች…›› ማረጋገጡን፣ ‹‹…የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደንብ ቁጥር 27/2002 አንቀጽ 5 አንድ አሽከርካሪ ጥፋት አጥፍቶ በተቆጣጣሪው [የመንጃ] ፈቃድ ሲጠየቅ ከሌለው የፊት ሰሌዳ መፍታት እንዳለበት መደንገጉን፣ ‹‹በተመሳሳይ የትራፊክ ጥፋት አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 3/2002 የፊት ሰሌዳ መፍታት›› ይቻላል ማለቱን፣ ‹‹እነዚህ ሕጎች ግን ከአገር አቀፉ ሕግ በተቃራኒው የቆመ፣ የሌሉና ያልተፈቀደ ቅጣት እንዲፈጽም የሚያደርጉ…›› መሆናቸውን ይዘረዝርና በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲን [ሰዎች] ማነጋገሩን፣ እነሱም ቅጣቱ የተፈቀደና ተገቢ እንደሆነ የነገራቸው መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል መንግሥትን የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎትን ጠይቆ ሥራ ላይ ያሉ የአገር ሕጎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦች ቁጥር 2008/2003 እና ማሻሻያው ቁጥር 395/2009 መሆናቸውን እንደነገሩት ይገልጻል፡፡ ‹‹በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ሰሌዳ የመፍታት ፈቃድ የሰጠ ሕግ እንደሌለ አረጋግጠውልናል›› ይላል፡፡

አለቀለት የሚባል ገና ብዙ ጥረትና ዳርም ማድረስ የሚሻ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ማለፊያ ጥረትና ሙከራ ነው፡፡ ጉዳዩ ደግሞ ዜናው ውስጥ የተጠቀሰው ‹‹…በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ክልሎች ሰሌዳ የመፍታት ፈቃድ የሰጠ ሕግ እንደሌለ…›› መረጋገጡ አይደለም፡፡ ሰሌዳ ወይም ታርጋ መኪና የሚባል የሚንቀሳቀስ ንብረት ቋሚ ወይም ነዋሪ ባህርይ ወይም ‹‹Feature›› ነው፡፡ መኪናው ካልወላለቀና መኪና መሆኑ ካልቀረ፣ አለዚያም ጨርሶ በመንገድ ላይ እንዳይንቀሳቀስ እስካልተደረገ ድረስ ወይም ተሽከርካሪው ምዝገባ ካልተሰረዘ በቀር መኪናው ከሰሌዳው ሊለይ አይችልም፡፡ መኪናውን ከታርጋው መለየት ማለት ሰውየውን ከገዛ ራስ ቆዳ ውስጥ ዘልለህ ውጣ ማለትን ያህል የማይቻል ነው፡፡ ፈርዶበት ያለ ሥልጣኑና ያለ ዕውቀት ሰሌዳ መፍታትን የሕግ ማስፈጸሚያ መሣሪያና ቅጣትም ጭምር ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ደንብ ቁጥር 27/2002 ራሱ በሕጉ መግቢያ እንደሚገልጸው፣ መኪና በተለይም በአራችን በኢትዮጵያ/በአዲስ አበባም ‹‹ገዳይ›› አጥፊ መሣሪያ ነው፡፡ ሕይወት ያጠፋል ንብረት ያወድማል፡፡ ለዚያውም ከድርሻችን በላይ፣ ይህንንና ከድርሻችን በላይ፡፡ የሚያጋጥመንን በመኪና አደጋ የሚደርስ ዕልቂት ብናቃልል፣ ብናስወግድም እንኳን መኪና ከየትኛውም ንብረት በላይና በተለየ በባለቤቱ ላይ የተለየ ኃላፊነት ያስከትላል፡፡ ይህንን ለማስረዳት አሁንም ሥራ ላይ ያለውን የፍትሐ ብሔር ሕግ ሁለት ድንጋጌዎች በምሳሌነት ልጥቀስ፡፡ የመጀመሪያው የዚህ ሕግ አንቀጽ 2081 ነው፡፡

  1. የአንድ መኪና ወይም የአንድ ባለሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት የሆነ ሰው አደጋውን ያደረሰው ይህንን መኪና ወይም ይህንን ባለሞተር ተሽከርካሪ ለማንቀሳቀስ ወይም ለመንዳት ባልተፈቀደለት ሰው ቢሆን እንኳ፣ መኪናው ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪው ባደረሰው ጉዳት ኃላፊ የሚሆነው ባለቤቱ ነው፡፡
  2. ቢሆንም አደጋው በደረሰ ጊዜ መኪናው ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪው የተሰረቀበት ለመሆኑ ማስረዳት የቻለ እንደሆነ ባለሀብቱ ኃላፊነት የለበትም፡፡

ሌላው የፍትሐ ብሔር ቁጥር 2086 ነው፡፡  

  1. በእንስሳት፣ በሕንፃዎች፣ በመኪናዎች ወይም በባለሞተር ተሽከርካሪዎች ወይም በፋብሪካ ተሠርተው የወጡት ነገሮች ምክንያት አደጋ በሚፈጠርበት ወይም በሚደርስበት ጊዜ ሕጉ ኃላፊዎች የሚያደርጋቸው ሰዎች አንዳች ጥፋት ያላደረጉ መሆናቸውን በማስረዳት ወይም የጉዳቱ ምክንያት ሳይታወቅ በመቅረት፣ ወይም ጉዳቱን ለመከላከል አንችልም ነበር፣ ወይም ጉዳቱ የደረሰው በሌላ ሦስተኛ ወገን ጥፋት ነው ብሎ በማስረዳት ጉዳቱ በደረሰበት ሰው በኩል ከኃላፊነት ለማምለጥ አይችሉም፡፡
  2. ጉዳቱ የደረሰው በከፊል ወይም በሙሉ ከተበዳዩ ጥፋት የተነሳ መሆኑ ካልተረጋገጠ በቀር በከፊልም ሆነ በሙሉ ከኃላፊነት ለመዳን አይችሉም፡፡

 

በአጭሩ የመጀመሪያው ድንጋጌ ትርጉም የመኪናው ባለቤት፣ መኪናው ጉዳት ባደረሰበት ጊዜ ተሰርቆበት የነበረ መሆኑን ማስረዳት ካልቻለ በስተቀር፣ ከኃላፊነት አይድንም ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መኪናን፣ ባለሞተር ተሽከርካሪን በመሰለ ነገር ለሚደርስ አደጋ ባለንብረቱ እኔ አላጠፋሁም፣ ጥፋት አላደረስኩም ብሎና ይህንንም በማስረዳትና በማረጋገጥ ከኃላፊነት አያመልጥም፡፡ ባለቤቱ ከኃላፊነት የሚያመልጠው ጉዳቱ የደረሰው በራሱ ጉዳት በደረሰበት በተጎጂው ጥፋት ነው ብሎ ይህንን ካረጋገጠ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

ይህንን የመሰለ ማኅበራዊ ፖሊሲ ላይ የተመሠረተ ፋይዳ ያለው የእነዚህ ንብረቶች (የባለሞተር ተሸከርካሪ) የባለቤትነት ምዝገባ ጉዳይ ያቋቋመውን አሠራር አላዋቂ አስፈጻሚ/አላዋቂ ሳሚም፣ ሕግ ማውጣት ሥልጣን ያልተሰጠው አካልም እንዲያበላሹት መፍቀድ/መፍቀድም ባይሆን ዝም ብሎ እንደተራ ነገር፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ማለፍ ወይም ዝም ማለት ሥርዓት አልባነትን መመረቅ ነው፣ በመኪና በብዙ ጊዜ ልምድ እየተቋቋመ የመጣ የአገር የማኅበራዊ መድን/ኢንሹራንስ ፖሊሲ ድርና ማግ መበጣጠስ ነው፡፡

‹‹ለረዥም ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ሲፈጸም የቆየው [አሁንም ያልተቋረጠው] የተሽከርካሪ ሰሌዳ መፍታት ቅጣት ሕግን የጣሰ ቅጣት ነው ተባለ›› እሚለው የኢቲቪ ዜና ውስጥ የተለያዩ አስተያየቶች/ሐሳቦች ሲነሱ ሰምቼያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ሕግ የለም፡፡ ‹‹ሕግን የጣሰ ብቻ ሳይሆን ወንጀልንም የሚያበረታታ ነው›› መባሉን ሁሉ ዜናው ውስጥ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው፣ መኪና፣ ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪ የሚንቀሳቀስ ንብረት ሆኖ ከሚንቀሳቀሱ ንብረት ዓይነቶች ሁሉ ተለይቶ የመመዝገብ ግዴታ እንዲጣልበት የተደረገበትን መሠረታዊ መርህ አሽቀንጥሮ የሚጥል፣ የማናለብኝነት አድራጎትንና ሳይጠየቁ መቅረትን የሚመርቅ ተግባር ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአንድ ከተማ፣ ለዚያውም በዚያው በፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር በሚወድቅ ጉዳይ ውስጥ የከተማው አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የፌዴራሉ የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ተጠሪዎች/ኃላፊዎች በዚህ ጉዳይ ላይ፣ እዚያ ዜና ላይ እንዳየነው ‹‹ካብ ለካብ›› ሲተያዩ፣ ጭራሽ የተቃራኒ አቋም ሲይዙ ማየታችን ነው፡፡          

ሕግ፣ ሕግ የማውጣቱም፣ ሕግ የማስፈጸምም፣ ሕግ የማስከበርም ሥልጣን እንዴት ሆኖ የፖለቲካ መሣሪያ እንደሚሆን፣ የተቃዋሚ ማጥቂያ ሆኖ እንደሚያገለግል የሚያሳይ ከአዲስ አበባ የበለጠ/የተሻለ ‹የጦርነት አውድማ› የለም፡፡ በምርጫ 97 ውጤት ማግሥት ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን የማሸነፋቸውን የተረጋገጠ መረጃ መሠረት አድርጎ የወጡት ሕጎች የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሕጎች መካከል የአዲስ አበባን አንፃራዊና ራስን የቻለ የትራንስፖርት ዘርፍ ሥልጣን የፌዴራሉ መንግሥት ተራ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ያደረገው ይገኝበታል፡፡ በ1997 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የወጣውና የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ዘርፍ (ለምሳሌ የባለሞተር ተሽከርካሪ ምዝገባን) የፌዴራሉ መንግሥት ያደረገው ሕግ ‹መዘዝ› ዛሬም ድረስ ተወራርዶ ያላለቀ፣ ፀድቆ ያላበቃ መሆኑን የተረዳት አሁን ዛሬ ሥራ ላይ ያለውን የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 1274/2014 ስመለከት ነው፡፡ ይህ ገና አሁን በቅርብ ከሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናውና ያንን የ1997 ሕግ ከእነማሻሻያዎች የተካው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ ነው፣ ገና አሁን ያንን የ97 ጠንቅ በሕግ ‹‹ማስተካከል›› የጀመረው፡፡፡ ስለመብትና ግዴታዎች መተላለፍ የሚደነግገውን የዚህን አዋጅ ድንጋጌ እዩልኝ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስርት ባለሥልጣንና የድሬዳዋ ከተማ የትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ተጠሪነታቸው ለየከተማ መስተዳድሮቻቸው ሆኖ ራሳቸውን ችለው ሥልጣን ባለው አካል ይደራጃሉ››፣ እንዲሁም ‹‹በትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 468/1997 መሠረት ተቋቁመው የነበሩ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ የትራንስፖርት ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መብቶችና ግዴታዎች [ከላይ በተገለጸው መሠረት] ለሚደራጁት የትራንስፖርት ተቋማት ተላልፈዋል›› የተባለው ገና አሁን ነው፡፡

መንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የወጣው፣ ታርጋ መንቀልን የመሰለ ‹‹ሙያ››ን ያስተዋወቀውና የሕግ ማስፈጻሚያና የሕግ መስከበሪያ መሣሪያ  ያደረገው ሕግ 97 ላይ የአራት ኪሎው ፌዴራል መንግሥት በፒያሳው የአዲስ አበባ መንግሥት ላይ ያጠመደው ዓይነት ተንኮል፣ መሠሪነትና ‹‹ፖለቲካ›› አለው ብዬ አላምንም፡፡ ይህ የአሁኑ ዝም ብሎ ‹‹አላዋቂ ሳሚዎች›› የተረባረቡበት የነባይ የጅል ሥራ ነው፡፡ ውጤቱ ግን ሕግ ማስበርና ሕግ ማክበር ላይ ቀውስ ያስከተለ ተግባር ነው፡፡ በተለይም የቅጣት ስም የተሰጠው፣ ቅጣት ተብሎ የሚጠራው ሰሌዳ የመንቀል ተግባር፣ መሠረታዊውን የሕጋዊነት፣ የፍትሕ መርህ የሚቃረን ነው፡፡ ያለሕግ ወንጀል የለም ይላል፣ ዓለም ሥልጣኔ የተቀበለው የተቋቋመ ባህል፡፡ አንድ ሰው አጥፍቷል፣ የወንጀል ድረጊት ሠርቷል ይባል ዘንድ ፈጽመኸዋል የተባለው ድርጊት አስቀድሞ የተከለከለ መሆን አለበት፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የዚህ ቅጣትም አስቀድሞ ይደነግጋል፡፡ የሕጋዊነት መርህ የሚደነግገው ይህንኑ ነው፡፡ ለደንብ መተላለፍም የሚሠራው (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2 እና 734 እና ተከታዮቹ) የሕጋዊነት መርህ በሕግ አስቀድሞ ያልተደነገገ ዕርምጃ ቅጣት አይሆንም፡፡

መልካም ግንኙነታችንና ሰላማችንን የሚያናጋው ዋናው ነገር ልዩ ልዩነታችን፣ የተለያየ ሐሳብ፣ ፈቃድና ፍላጎት ያለን መሆኑ ሳይሆን፣ ይህንን የምገልጽበት፣ የምንፈታበት መድረክ ከሕጋዊውና ከሰላማዊው ምኅዳር ውጪ መውጣቱ ነው፡፡ ሕግ ማውጣትም፣ ሕግ ማስፈጸመምም፣ ሕግ ማስከበርም ራሱ ሕግ ማክበርን ይጠይቃል፡፡ ከሕግ በታች መሆንን ለሕግ መገዛትን ይሻል፡፡ ከሕግ ባላይ ለመሆን በማያመች ለውጥ ውስጥ ገብተናል ማለት የምንችለው፣ እነዚህን ‹‹ጥቃቅን›› ነገሮች ሁሉ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ስንመለከት ነው፡፡ እዚህ ሁሉ ውስጥ ለመግባት ሕዝብን፣ ማፈርንና ማክበር አፍና ተግባርን ማቀራረብንና ማጣጣምን አስተዳደሩ ራሱ ውስጥ ባህል ማድረግ የቻልን፣ ለዚህም የጣርን ከሆነ ነው፡፡            

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...