Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነርቭ፣ የወገብ፣ የአጥንት (ዲስክ መንሸራተት) የመሰሉ ሕመሞች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖችን እያሰቃየ ሲሆን የእነዚህ በሽታዎች መንስዔ “እንዲህ ነው” ተብሎ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከጠቀስኳቸው ሕመሞች በሁለቱ ለከፍተኛ ሥቃይ ከተዳረጉት አንዱ ነኝ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ አጎራባች ከተሞች ድረስ በመሄድ “ይፈውሳሉ” የተባሉትን ተዘዋውሬ ለማግኘት ሞክሬያለሁ፡፡

ለዲስክ መንሸራተት ምርመራ ማድረግ ቀዳሚው ጉዳይ ነበር። ቦሌ በሚገኝ አንድ ከፍተኛ ሆስፒታል ለካርድ፣ ለኤክስሬይ ምርመራ በድምሩ አምስት ሺሕ ብር ስከፍል፣ ኤምአርአይ (MRI) ደግሞ 13 ሺሕ ብር ከፈልኩ። የምርመራ ውጤቱን በሲዲ ጭምር ይዤ ሰዎች የሚጠቁሙኝ ቦታ መዞር ጀመርኩ። በተጨማሪ ብዙ አድማጭ ተመልካች አላቸው በሚባሉ አንዳንድ የቲቪ “መዝናኛ” ሚዲያዎች “ታዋቂ የዲስክና የነርቭ ፈዋሽ፣ አዳኝ” ብለው ያቀረቧቸው ግለሰቦች (አንዳንዶቹ ዶክተር ብለው ለራሳቸው ማዕረግ ሰጥተዋል)፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ “ታዋቂ ጸሐፊ” የተባሉ በሚጽፉላቸው “አዳኝ ፈዋሽ ተብዬዎች” ዘንድ መሄድ ቀጠልኩ፡፡

ሰበታ መንገድ፣ የካ አባዶ፣ ሳር ቤት፣ ወለቴ፣ ኮተቤ እግሬ እስኪቀጥን ከተመላለስኩባቸው ይጠቀሳሉ። ቅድሚያ ከ20 እስከ 80 ሺሕ ብር መክፈል ግድ ነው፡፡ ሰበታ መንገድ የሚገኘው ሰው ለሕክምና በየቀኑ የሚጎርፈው ሕዝብ በሺሕ የሚቆጠር ነው። በአንድ ሚዲያ ላይ “ፈዋሽ ናቸው” ተብሎ በመነገሩ የታማሚው ቁጥር በእጥፍ እንዲጨምር አድርጓል። ተበድረውና ያላቸውን ጥሪት አሟጠው ፈውስ ፍለጋ የሚመጡ ሰባና ሰማኒያ ሺሕ ብር ቅድሚያ ከከፈሉ በኋላ “ሐኪም ነኝ” የሚለውን ማግኘት የሚችሉት ሦስት የቀጠሮ ቀናት ብቻ ነው! በቅጥር ግቢው የሚገኙ ወጠምሻ ጋርዶችን አልፎ መግባትና ሰውየውን ማግኘት አይቻልም! “ከገንዘቤም ከሕክምናውም አልሆንኩም” ብለው የሚያማርሩ እጅግ ብዙ ታማሚዎች ሲሆኑ “ፈዋሽ ነኝ” የሚለው ግለሰብ የማግኘት ዕድል ያገኙ ሰውየው የሚሰጣቸው መልስ “የሚያዘኝ አምላክ ላንተ/ላንቺ የፈውስ ኃይሉን ሊሰጠኝ አልቻለም” የሚል ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የተጠቀሰውን ገንዘብ የተበሉ በርካቶችን በአካል አግኝቼ አነጋግሪያለሁ፡፡ ሳግ እየተናነቃቸውና ዕንባ እያፈሰሱ በምሬት ሐዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡ “ፈዋሽ ነኝ” የሚለው ግለሰብ በቀረበበት ሚዲያ ላይ በዩቲዩብ ከሥር የተለጠፋ የበርካታ ታማሚ ተበዳዮች አስተያየት የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ “በእኛ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ፣ ገንዘባችንን ተበልተን መሄጃና መድረሻ አጥተን በሐዘን ቁጭ ብለናል፣ ተጠንቀቁ” የሚሉ ተመሳሰይነት ያላቸው አስተያየቶች ሰፍረው ይገኛሉ፡፡

የከባዱም ሌላው ይገኛል። በስመ ጋዜጠኛነት የሚነግዱ ኮሚሽን ተከፋዮች የሰውየውን የሌለ “ስም፣ ዝና፣ ፈዋሽነት” እየለጠጡ በማኅበራዊ ሚዲያ እየለቀለቁ፣ እንዲሁም ታማሚዎችን አነፍንፈው እያገኙና የተጠቀሰው ቦታ እንዲሄዱ በሹል ምላሳቸው እያሳመኑ ምስኪን ወገኔን ኪስ ያራቁታሉ፡፡ ታማሚው ቅድሚያ እስከ ሃምሳ ሺሕ ብር እንዲከፍል ከተደረገ በኋላ ሳይማር “ዶክተር” ማዕረግ በጮሌ ደላሎቹ የተሰጠው ግለሰብ ዘንድ ይቀርባል። ምላሱ አይጣል ነው። የታዋቂ ሰዎችን ስም እየጠራ፣ “እከሌን የፈወስኩት እኔ ነኝ፣ እነ ማንትስ የተባሉ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ድረስ መጥተው ተፈውሰው ሄደዋል” እያለ የፈጠራ ውሸቱን ይደረድራል። የሚገርመው “አዳንቸው እንኳ” ከሚላቸው ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ሁለቱ በጭራሽ እንደማያውቁት፣ ደላሎቹ “እሱ ዘንድ ሂዱ” ሲሏቸው እንዳልሄዱ ሲናገሩ፣ አንዱ ደግሞ “አንድ ቀን ነው ያገኘሁት፣ ሁኔታው ስላላማረኝ መልሼ ማግኘት አልፈቀድኩም” ይላል። ጮሌ ደላሎቹ ሃምሳ ሺሕ ብር ከከፈለ ታማሚ 7,500 (ሰባት ሺሕ አምስት መቶ) ብር ኮሚሽን ይወስዳሉ። ታማሚው ከከፈለው ገንዘብ በተጨማሪ ለትራንስፖርት የሚያወጣው ከፍተኛ ነው። ርቀቱና መጉላላቱ እንዳለ ሆኖ፡፡ እነዚህ ተደምረው ታማሚው ተስፋ ቆርጦ ይተወዋል።

የወለቴው “ዶክተር” ለየት ይላል። እሱም ሳይማር ለራሱ ያከናነበው ሲሆን ታማሚው “ዶክተር” እያለ ካልጠራው የሚከፋ ዓይነት ነው። “የመፈወስና ማዳን ሥልጣን ከላይ ነው የተሰጠኝ” ይላል። ክብ ቅርፅ ባለው አሎሎ ዓይነት ክብ ድቡልቡል ብረት የታመመውን ቦታ በኃይል እያሽከረከረ ለሦስት ደቂቃ ገደማ ካሸው በኋላ “ተፈውሰሃል” ይላል። የተለየ የሚያደርገው ይህን ያህል ክፈል አይልም። “ከላይ የተሰጠኝ ችሮታ ስለሆነ ደስ ያለህን ክፈል” ይልሃል። ታማሚው ኪሱ የፈቀደውን ይሰጣል። “ተፈወስኩ” የሚል ማግኘት ግን ዘበት ነው፡፡ የቃሊቲው ደግሞ አስደንጋጭ ነው፡፡

የእጅህን መዳፍ ጨብጦ ይዞ “ነርቭና የአጥንት ሕመም አለብህ፣ እጀ ሰብ፣ ሰላቢ፣ አባይ ጠንቋይ፣ መተት ተደርጎብሃል ወይም አልተደረገብህም” ይልሃል። እሱም ሳይማር ዶክተር የሚል ስያሜ ሰጥቷል። “ይፈውስሃል” ብሎ የሚሰጥህ ከቅጠልና ምንነቱ ከማይታወቅ ሥራ ሥር “የተጨመቀ” ተብሎ የሚጠጣ ፈሳሽ ነው። ፈሳሹ በሰውነት ውስጥ ገብቶ የሚያደርሰውን ጉዳትና ሌላ ተጨማሪ በሽታ ሊኖር እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚመለከተው አካል ምርመራ ያላደረገበት፣ ማረጋገጫና ዕውቅና ያልሰጠበት ነው፡፡

ጽሑፌን ሳጠቃልል ለጤና ሚኒስቴርና ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ በማቅረብ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውና ያልተጠቀሱ “ፈዋሽ አዳኝ” ነን ባዮች በሕመም በሚሰቃየው ማኅበረሰብ ላይ የሚፈጽሙትን ማጭበርበር አያውቅም ይሆን!? “ዶክተር” እያሉ ለራሳቸው የውሸት ማዕረግ እየሰጡ በአደባባይ የማጭበርበር ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ማነው ፈቃድ ወይም ዕውቅና የሰጣቸው? አፋጣኝ ዕርምጃ እንደሚወሰድ እገምታለሁ፡፡

(ገላውዲዮስ ነጋ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...