Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ የመሬት ውሎችን ውድቅ የሚያደርግ ደንብ ተግባራዊ መሆን ጀመረ

በትግራይ በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ የመሬት ውሎችን ውድቅ የሚያደርግ ደንብ ተግባራዊ መሆን ጀመረ

ቀን:

  • የይዞታ ማረጋገጫ የጠፋባቸው በምስክሮች በፍርድ ቤት እንዲረጋገጥ ይደረጋል

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉ ሦስት ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ ማናቸውም የመሬት ግብይት ስምምነቶችን ውድቅ የሚያደርግ ደንብን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ታወቀ። 

የውሎቹን ሕጋዊነት የሚያሳጣው ደንብ የፀደቀው መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሆንም ተፈጻሚ መሆን የጀመረው ሰሞኑን መሆኑን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሬትና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ካልኣዩ ገብረ ሕይወት ለሪፖርተር ተናግረዋል። 

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ተፈርሞ የፀደቀው ደንብ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹የትግራይ ክልል መሬትና የማዕድን ሥራ ማስጀመር›› ተብሎ የሚጠራው ደንብ እስከ ፀደቀበት ጊዜ ድረስ የተፈጸሙ የመሬት ስምምነቶችን ሕጋዊነት ያሳጣል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በደንቡ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ቅቡልነት የሌላቸው የመሬት አገልግሎት ተብለው የተለዩ ሲሆን፣ በመቀሌ ከተማ ሊዝ ቁጥር 68 በልዩ ሁኔታ የተሰጡ መሬቶች አገልግሎት ግን ቅቡልና ሕጋዊ ይሆናል ሲል ተደንግጓል፡፡

የትግራይ ክልል የመሬት ሥራ ማስጀመሪያ ነው የተባለውን ደንብ ማውጣት አስፈላጊ የሆነው፣ ‹‹በጦርነቱ ምክንያት በመሬት ይዞታና ባለቤትነት ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰ በመሆኑና በሕዝብና መንግሥት መሬት ይዞታና ባለቤትነት ላይ ከባድ የማጭበርበር ድርጊት ሙስና እየተፈጸመ ስለሆነ፣ ይህ ድርጊት ወደ መደበኛ አስተዳደርና ተጠያቂነት ለማሸጋገር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ›› መሆኑን ይገልጻል። 

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑ መምህር ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ነው የተካሄደው። ዝርፊያውና ውድመቱ በክልሉ ባሉ ሁሉም ማዘጋጃ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ ከመሬትና ከቤት ይዞታ ጋር የተገናኙ፣ የመጋዘኖች ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶች፣ የፍርድ ቤቶች በተለይም የፍርድ ባለመብትና የፍርድ ባለዕዳ መካከል መሬትን በሚመለከት የተሰጡ ውሳኔዎች፣ የተመዘገቡ ሰነዶችና መረጃዎች (records)ና ማስረጃዎች ወድመዋል። አልፎ አልፎ ደግሞ ሁኔታውን መጠቀሚያ ያደረጉ አንዳንድ ወንጀለኞች ሆን ብለው የተመዘገቡ መረጃዎችን፣ ከላይ የጠቀስኳቸውን የክልሉ አስተዳደር ተቋማት ማኅተሞችንና የግብር ደረሰኞችን ስላጠፉ፣ ከመጥፋትም ባሻገር ወደ ግለሰቦችና ወንጀለኞችም እጅ ስለገቡ፣ እነዚህን በወንጀል የተገኙ የመንግሥት ሰነዶችና ግብይቶች ሕጋዊነት ማረጋገጫዎችን በመጠቀም መሬት ከፍተኛ ዘረፋና ሽያጭ ነው የተካሄደበት፤›› በማለት ገልጸዋል። 

በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የመሬት አገልግሎት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ መደበኛ ሥራ የሚያስጀምረው ይህ ደንብ፣ የትግራይ ክልል መሬትና ማዕድን ቢሮ አገልግሎቱን የሚጀምረው በመሬት ይዞታ የተጠቃሚነት መብት ተረጋግጦላቸው ለቆዩት ብቻ እንደሚሆን ይገልጻል። 

ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት ካሳ የተከፈለበትና ከማንኛውም ክርክር ነፃ የሆነ የከተማ መሬት አዲስ የሊዝ ጨረታ ሊካሄድበት እንደሚችል ሲገለጽ፣ ከተጠቀሰው ጊዜ በፊት ጨረታ አሸንፈው ይፋ የሆኑና ውል ሳያስሩ የቆዩት ብቻ ውል እንዲያስሩ እንደሚደረግም ተመላክቷል፡፡

የትግራይ ክልል መሬትና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ካልኣዩ የማስረጃዎች በየደረጃው ባሉ የክልሉ አስተዳደር ተቋማት በጦርነቱ ወቅት መውደማቸውና መጥፋታቸው በተደጋጋሚ መገለጹንና ቢሮው ሰነዶችን በተመለከተ እንዴት እንደሚሠራ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ሰነዶች ከወረዳ ቢጠፉ ክፍለ ከተማ እንፈልጋለን፡፡ ክፍለ ከተማ ካልተገኙም በከተማ ደረጃ እናያለን፡፡ በዚህ ሁሉ ጥረት ካልተገኙ ግን ከጦርነቱ በፊት ሕጋዊነታቸው ለተረጋገጠ የመሬት ይዞታና ባለቤትነት ምስክሮችን በማቅረብ በፍርድ ቤት እንዲረጋገጡ ይደረጋል፤›› ብለዋል። 

ለክልሉ ነባር የጦር ጉዳተኞች የቤት መሥሪያ ቦታ መስጠትን በተመለከተ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከዚህ ቀደም ስለጉዳዩ በወጣ መመርያ መሠረት ተፈጻሚ እንደሚደረግ አዲሱ ደንብ ይገልጻል። 

የሊዝ ክፍያን፣ የመሬት ኪራይንና ግብርን በተመለከተ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሊከፈሉ የሚገባቸው ክፍያዎችና ግብር በሦስት ዓመታት ተከፋፍሎ እንደሚከፈሉ የተደነገገ ሲሆን፣ ቅጣትና ወለድ ግን ምሕረት መደረጉ ተገልጿል። 

በተገለጸው የጊዜ ገደብ ውስጥ መፈጸም የነበረባቸው የሮያሊቲ፣ የመሬትና የማዕድን ኪራይ ክፍያዎችም በተመሳሳይ መንገድ እንዲስተናገዱ ደንቡ ያዛል። 

ከጦርነቱ መጀመር በፊት ክፍያዎች ያልፈጸሙ ግን ቅጣትና ወለድ ተደምሮ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ደንቡ ያብራራል፡፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክር ቤት በክልሉ ሕገወጥ የመሬት ወረራን የሚቆጣጠርና ወደ ተጠያቂነት የሚያሸጋግር ግብረ ኃይል እንደሚያቋቁም የደነገገ ሲሆን፣ የመሬትና ማዕድን ቢሮ ኃላፊው አቶ ካልኣዩ አሁን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...