Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመንበረ ፀባዖት ሙዚየም

የመንበረ ፀባዖት ሙዚየም

ቀን:

ጥቂት የማይባሉ የምዕራባውያን አገሮች ሙዚየሞች በቅኝ ግዛትነት ከያዟቸው አገሮች በተዘረፉ ቅርሶች የታጨቁ ናቸው፡፡ በ19ኛው ምዕት ዓመት በመቅደላ ጦርነት በእንግሊዞች የተዘረፉና በሙዚየሞቻቸው የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችne ለዚህ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ምዕራባውያንና የበለፀጉ አገሮች ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከሌሎችም በቅኝ ግዛት ሲያስተዳድሯቸው ከነበሩ ግዛቶች ዘርፈው በሙዚየሞቻቸው ያኖሯቸውን ልዩ ልዩ ቅርሶች ከተለያዩ የዓለም ክፍል ለሚመጡ ቱሪስቶች በማስጎብኘት ረብጣ በማፈስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ቅርሶች ታላቅ የአገር ሀብቶች ናቸው፡፡ ታሪክን ከመዘከር ትናንትን ከመናገር ባሻገር፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ የራሳቸውን ደማቅ አሻራ እያኖሩ ማንነትን የሚመሰክሩና አገርን አፅንተው የሚያቆሙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ውሰን በሚባሉ ሙዚየሞቿ በያዘቻቸው በርካታ በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ቅርሶቿ የትናንት ታሪኳንና ዛሬ የፀናችበትን መሠረት ለዓለም ትናገራለች፡፡

የመንበረ ፀባዖት ሙዚየም | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በሙዚየሙ ከሚገኙት ክርስቲያናዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ጥቂቱ

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሙዚየሞች አንዱ የሆነው፣ የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሙዚየም ነው፡፡ ሕንፃው በበኩረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ የገንዘብ ድጋፍ ተገንብቶ በ1998 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሙዚየሙ ኃላፊ ቀሲስ ሰሎሞን ማዘንጊያ እንደሚሉት፣ ሙዚየሙ የተቋቋመው በ1883 ዓ.ም. በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከተመሠረተው መካነ ሥላሴ  (ባለወልድ) እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከተገነባው የአሁኑ ካቴድራል በተሰባሰቡ ቅርሶች ነው፡፡

ሙዚየሙ ዕድሜ ጠገብ በርካታ የተለያዩ የብራና መጻሕፍትና ንዋየ ቅዱሳት የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል የብሉይና አዲስ ኪዳን መጻሕፍትን የያዘ በፈረስ ቆዳ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በ15ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የተገለበጠ-ቅዱስ ያሬድ ከደረሳቸው አምስት የዜማ መጽሐፍ መካከል ድጓ የተሰኘው፣ ከአርመንያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ባዝጌን ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1958 ዓ.ም. የተበረከተ የሐዋርያው የቅዱስ ታዴዎስ እጀ አፅም ይገኙበታል፡፡ ቅዱስ ታዴዎስ ከአሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን በሶርያ አገር በመንፈሳዊ አስተምሮ ላይ እንዳለ እጁ የተቆረጠ መሆኑን ቀሲስ ሰሎሞን ይናገራሉ፡፡

ከግብፅ አገር የተበረከተ በዓረብኛ የተጻፈ ፍትሐ ነገሥት፣ የግዕዝና አማርኛ ትርጉም ያለው ፍትሐ ነገሥት፣ አፄ ምኒልክና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ ለጸሎትና ለቅዳሴ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው ዙፋኖች፣ በሙካሽ ብር የተሠራ የአፄ ምኒልክ ለምድና ሱሪ፣ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከወርቅ የተበጀ ለምድ፣ ሱሪና ካባ፣ የእቴጌ መነን ከነጭና ቀይ ከፋይ የተዘጋጀ ካባና የመጀመሪያው የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የሆኑት የሊቀ ሥልጣናት አባ መልዕክቱ አልባሳትም (በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ) በሙዚየሙ የሚገኙ ቅርሶች ናቸው ብለዋል፡፡

ከእስራኤል አገር ለአፄ ኃይለ ሥላሴ የተበረከተ ከዝሆን ጥርስና ከዕንቁ የተሠራ የጸሎተ ሐሙስ ምስል፣ ነገሥታቱ ለተለያዩ ክብረ በዓላት ይጠቀሙበት የነበረ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጁራር ጃንጥላዎች፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የአፄ አድያም ሰገድ መስፍን አዛዥ የነበሩ ነጋሲ ክርስቶስ የተባሉ የጻፉትና ለካቴድራሉ የተበረከተ አንጋረ ፈላስፋ/መጽሐፈ ጠቢባን፣ ከብርና ነሐስ የተሠሩ ሰባት ክፍል ያላቸው የሻማ ማብሪያ መቅረዞች፣ ረጅም ዕድሜ ያላቸውና ለቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት የሚሰጡ ዳዊት፣ ድጓና ጾመ ድጓ፣ የዓመት ስንክሳር፣ ተዓምረ ማርያምና ተዓምረ ኢየሱስ የተባሉ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ ብራናዎችም በሙዚየሙ የሚገኙና በቱሪስቶች የሚጎበኙ ቅርሶች መሆናቸውን ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡

ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ (በ1961) የተበረከተና ገበታው በወርቅ የተለበጠ የአራቱ ወንጌሎችና የብራና መጽሐፍ፣ የነሐስ ቃጭል፣ የብር ማኅተም፣ የብር ዕጣን ማቅረቢያ፣ የብር ቋሚ መስቀል ከነ ማስቀመጫው፣ የፔንዱለም ሰዓት፣ ከሸክላ የተቀዳ የዓረብኛ ቅዳሴ፣ ሃይማኖተ አበው በግዕዝ፣ ከበሮና የመሳሰሉት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከሚገኙ በርካታ ቅርሶች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡

የካቴድራሉ ዋነኛ ገቢ ሙዚየሙ መሆኑን የሚናገሩት ቀሲስ ሰሎሞን ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ሙዚየሙ እየተሰነጣጠቀ፣ በክረምት ወቅትም ፍሳሽና ርጥበት እያመጣ በመሆኑ፣ ቅርሶቹ ለረጅም ጊዜ ተጠብቀው ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ ለዚህ ታላቅ ቅርስን ለያዘ ሙዚየም ዕድሳት ሊደረግለትና ሴኩሪቲ ካሜራም ሊገጠምለት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

የካቴድራሉ ዕድሳት

በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ታኅሣሥ 15 ቀን 1924 ዓ.ም. የግንባታ ሥራው ተጀምሮ በጣሊያን ወረራ ወቅት ለአምስት ዓመታት ሥራው የተቋረጠውና እንደገና በድል ማግሥት በሦስት ዓመት ተኩል ተገንብቶ ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም. የተጠናቀቀው የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ላለፉት 80 ዓመታት ከቀለም ቅብና መጠነኛ ዕድሳት ውጪ መሠረታዊ የሚባል ዕድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ ከፍተኛ የመሰነጣጠቅና ሌሎች ችግሮችም ገጥመውት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

ካቴድራሉ የአገር ውድ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን፣ የሚናገረውም አያሌ የታሪክ ሁነትና በውስጡ የያዛቸውም በርካታ የታሪክ ድርሳናት በመኖራቸው ቅርስነቱን ሳይለቅ ከሙሉ ግቢው ጀምሮ ካቴድራሉን ለማደስ ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ የኮንትራት ውል ተገብቶ ዕድሳት እየተደረገለት ይገኛል፡፡

የካቴድራሉን ዕድሳት በተመለከተ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ካቴድራሉና የሥራው ተቋራጭ በጋራ በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ እንደተናገሩት የካቴድራሉ ዕድሳት ቫርኔሮ በተባለ የሕንፃ ሥራ ተቋራጭና ፋሲል ጊዮርጊስ በተባለ አማካሪ ድርጅት በ172.5 ሚሊዮን ብር ዕድሳት እየተደረገለት ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሥራው 50 በመቶ መከናወኑና ዋና ዋና የተባሉ የዕድሳት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የሚገልጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ በየጊዜው እየናረ ከሚሄደው የማቴሪያል ዋጋና ከዶላር እጥረት የተነሳ የሚጠይቀው ገንዘብ ከፍ በማለቱና ከካቴድራሉ አቅም በላይ በመሆኑ መላው አገር ወዳድ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ምዕመናን በዚህ ታሪካዊ የካቴድራሉ ዕድሳት ላይ እጃቸውን እንዲዘረጉና አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማዕከላዊ የታሪክ ቦታ እንደመገኘቱ፣ ከሚሰጠው ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎቶች ባሻገር ታላላቅ የአገሪቱ ቅርሶች የሚገኙበት፣ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በዓለ ሲመት የሚከበርበት፣ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ሊቃውንት፣ አባቶች ካህናት፣ የመንግሥት ሹማምንትና ለአገር ባለውለታ የሆኑ አባት አርበኞች መካነ መቃብር ሆኖ በማገልገል ላይ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...