Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የግብር አሰባሰብን በሚያደናቅፉ ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንወስዳለን›› ከንቲባ አዳነች አቤቤ

‹‹የግብር አሰባሰብን በሚያደናቅፉ ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንወስዳለን›› ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ቀን:

በመንግሥት ቢሮ ውስጥ ሆነው በሌብነት፣ በብልሹ አሠራርና በሕገወጥነት የግብር ገቢ አሰባሰብ ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ሠራተኞች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ ‹‹ግብር ለአገር-ክብር›› በሚል መሪ ቃል እሑድ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአምስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ‹‹የታማኝ ታክስ ከፋዮች›› ዕውቅናና የሽልማት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ መንግሥት ቢሮ ውስጥ ሆነው ከግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ጋር በሕገወጥ መንገድ የሚደራደሩ፣ የተጣለባቸውን የመንግሥት ኃላፊነት ችላ ብለው በሌብነትና በብልሹ አሠራር የሚሳተፉ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ አስተዳደራቸው ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ያላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከታክስ ከፋዩና ከንግ/ ማኅበረሰቡ ጋር በሕገወጥ መንገድ የሚደራደሩ ለሕግ ተገዥ ያልሆኑ ሌቦችንና ሕገወጥ የመንግሥት ሠራተኞችን ከተማ አስተዳደሩ ባገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ በየጊዜው እየተከታተለ ተመጣጣኝ ቅጣት ሲሰጥ መቆየቱን፣ አሁንም አገር በሚጎዳው የሌብነት ድርጊት ተሳታፊ ሆነው በሚገኙት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኝነት እንዳለ ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ጥቂት የማይባሉ ግብር የሚያጭበረብሩና የሚሰውሩ፣ ያለ ደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ፣ ሕገወጥ ደረሰኝ ይዘው በታማኝነት ግብራቸውን ከከፈሉ ግብር ከፋዮች የተሰበሰበን ገቢ በሕገወጥ መንገድ ለመንጠቅ የሚሞክሩ፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራርን በማስፈን የአገር ዕድገትን በሚጎዳ ድርጊት ተሳታፊ ሆነው የሚገኙ በመኖራቸው፣ ሁላችንም እነዚህን በጋራ ልንታገላቸውና ልናወግዛቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከታማኝ ግብር ከፋዮቻችን በሚሰበሰብ ገቢ አገራችንና ከተማችንን በሚመጥን ዕድገትና የብልፅግና ግብ ላይ ለማድረስ ሌት ተቀን እየሠራን እንገኛለን፤›› ያሉት ከንቲባዋ፣ የከተማ አስተዳደሩን የቀየሩ፣ የሥራ ዕድል የፈጠሩ፣ ኢኮኖሚውን ያነቃቁ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እየተተገበሩ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ግብራቸውን በታማኝነት ለከፈሉ አገር ወዳዶች ዕውቅና ሰጥተን በአደባባይ እንዳከበርነው ሁሉ፣ አሠራራችንንና አገልግሎት አሰጣጣችንን በማዘመን ሕገወጦችን በሕግ ተጠያቂ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማን እንደ ስሟ ውብ አበባ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ የአፍሪካ መዲናነቷን ጠብቃ እንድትሄድና የዓለም የዲፕሎማሲ መናኸሪያነቷን ይዛ እንድትቀጥል የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ማሳካት የቻልነው በታማኝ ግብር ከፋዮች አማካይነት ነው፤›› ብለው፣ ትልልቅ ገቢ እያላቸው በዚያው ልክ ከታክስ ስወራና ከሕገወጥ ድርጊት ራሳቸውን ያላራቁ፣ ዛሬም የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት መክፈል ያልቻሉ ጥቂት የማይባሉ በመሆናቸው፣ የገቢዎች ቢሮ በቀጣይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በ2015 በጀት ዓመት ከፍተኛ የሕግ ተገዥነት ካስመዘገቡ ግብር ከፋዮች መካከል 95 በፕላቲንየም፣ 185 በወርቅና 282 በብር ደረጃ ዕውቅና ለመስጠት የምሥጋናና የሽልማት መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱንና ዕውቅና መስጠቱን በአጠቃላይ 562 ታማኝ ግብር ከፋዮች መሸለማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ለእነዚህም ግብር ከፋዮች ዕውቅና ለመስጠት በታክስ ሕግ ተገዥነት በአሥራ ሦስት መሥፈርቶች ተወዳድረው መመረጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

መሠረታዊ የግብር ከፋዩ መረጃዎች፣ ግብርን በወቅቱ ማስታወቅ፣ የግብር ከፋዩ የቅጣት ታሪክ፣ የኦዲት ግኝት ልዩነት፣ የተመላሽ ጥያቄ የልዩነት መጠን፣ ያበረከተው የገቢ አስተዋጽኦ በቅርንጫፍ ከተሰበሰበው ታክስ አማካይ ጋር ያለው ምጣኔ፣ ከታክስ ማጭበርበርና ሥወራ ነፃ መሆን፣ የታክስ ዕዳ አከፋፈል ሁኔታ፣ ያቀረበው ዓመታዊ የሽያጭ መጠን፣ በጉምሩክ በኩል የተመደበበት የሥጋት ደረጃ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያና የደረሰኝ አጠቃቀም፣ እንዲሁም ከፖሊስና ዓቃቤ ሕግ የተገኘ መረጃና የመሳሰሉት ዕውቅናና ሽልማት ለመስጠት እንደ መወዳደሪያ የተቀመጡ መሥፈርቶች መሆናቸውን አቶ አደም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት 140.29 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም. 107.59 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 109.08 ቢሊዮን ብር ከዕቅድ በላይ መሰብሰቡን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...